Tuesday, 02 January 2018 10:04

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)


    “--ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ በደልን እንሸከማለን፣ ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ ኢ-ፍትሃዊነት አናታችን ላይ ይናጥጣል፡፡ …
ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ አለማወቃችን አሸንፎን፣ ከኔ በላይ አዋቂ ላሳር በማለት እንገበዛለን፡፡ ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ በማያስቀው እየሳቅን፣ በማያሳዝነው እናለቅሳለን፡፡ ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ---”
 
    “ከመስታወት ፊት ቆምሁ፣
ወደ ውስጥ አየሁ፣
ራሴን አጣሁ!”
ገጣሚው ወዳጄ እንደሚነግረን፣ መስታወቱ ውስጥ የተመለከተው መልኩን፣ ቁመናውንና አለባበሱን ነው፡፡ …. እሱነቱ አብሮት አይደለም፡፡ … ተደብቋል፣ … ጠፍቷል ወይ ተሰርቋል፡፡
ወዳጄ፤ ራስን በመስታወት እያዩ ‹ራሴን› … አጣሁ ማለት ምን ማለት ይመስልሃል? … ምናልባት በደንብ አልፈለገው ይሆን? … ወይስ መጀመሪያውኑ አልነበረም? … እንደዛ ከሆነ ደግሞ ያልነበረን ነገር መፈለግ ቅዠት ይሆናል። በርግጥ ራስን ማጣት፣ ራስን ፈልጎ አለማግኘት ሲባል -- የባዶነት ስሜት ይመስለኛል፡፡ … ስሜት ደግሞ መንፈስ ነው። … መንፈስ ደግሞ እንኳን በመስተዋት በx-ray አይታይም፡፡
በየደቂቃው፣ በየሰዓቱ፣ በየቀኑ … ማንነታችን ቢቀያየርም … የማይለወጥ እኛነት ደግሞ አለ!! … Real self, … invariant self, … essential self … አንዳንዶች ነፍስ ብለው የሚጠሩት ህላዌ ነገር!! … እያንዳንዱ ፍጡር ውስጥ በነፍስ ወከፍ ይገኛል የሚባል እኔነት! … ምናልባት ገጣሚው ያጣው ይህንን እውነተኛ ማንነት ይመስለኛል። … የሆኖ ሆኖ ወዳጄ፤ ያንተስ “አንተነት” … አብሮህ አለ? … ወይስ ሌሎች ሰዎች ችግርህን፣ ጥቃትህን፣ ዕድለ ቢስነትህን፣ በግል አመለካከትህና በተለያዩ ምክንያቶች የሚደርስብህን የጭቆና ጫና አስታከው፣ ራሳቸው ባመቻቹት ‹ደካማ ጎንህ› … ተጠቅመው፣ ውስጥህን ቆልፈውበታል? … መልሱ አንተው ጋ ነው ያለው!!
መጠጥ ቤት፣ ስብሰባ አዳራሽ፣ ኳስ ሜዳና በመሳሰሉት ቦታዎች ስትገኝ … በአጋጣሚ ወይም ሆን ተብለው በሚነሱ ሃሳቦችና ጭውውቶች ላይ የሌሎችን ጥቅሻ (facial expression)፣ እንቅስቃሴዎችና ምልክቶች (gestures) ችላ ብለህ፣ ያለ ምንም ፍራቻ፣ ነገ ምን ይደርስብኛል በማለት ሳትሰጋ፣ በሙሉ ነፃነት፣ ውስጥህ የሚነግርህን ዕውነት … ‹ልክ ነው!› … ያልመሰለህን ደግሞ ‹ልክ አይደለም!› … በማለት ተከራክረህ ማንነትህን ታሳውቃለህ? … መልሱ አንተ ጋ ነው ያለው!!
ወዳጄ፤ ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ስለምንሆን ‹ለምን?› … ብለን አንጠይቅም። … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ በህዝባዊነት ስሜት፣ ህዝባችንን የሚጎዱ መመሪያዎች አስፈፃሚ እንሆናለን፡፡ horses of instruction … እንደሚባለው፡፡ ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ በደልን እንሸከማለን፣ ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ ኢ-ፍትሃዊነት አናታችን ላይ ይናጥጣል። … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ አለማወቃችን አሸንፎን፣ ከኔ በላይ አዋቂ ላሳር በማለት እንገበዛለን፡፡ ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ በማያስቀው እየሳቅን፣ በማያሳዝነው እናለቅሳለን። … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ ፈሪና ተጠራጣሪ የሚያደርገው ፀበል ተረጭቶብናል ማለት ነው። … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ በሚደብር ዘፈን ያዙን ልቀቁን እያልን እንወራጫለን፣ … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ ራሳችንን ከፍ ከፍ፣ ታላላቆቻችንን ዝቅ፣ ዝቅ ለማድረግ ይዳዳናል፡፡ … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ ለልጆቻችን ውሸት እናወራለን፡፡ … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ ያላየነውን እንዳየን፣ ያልሰማነውን እንደሰማን መስለን እንተረተራለን። … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ ሳይጠሩን አቤት፣ ሳይልኩን ወዴት የምንል ወዶ ገባ ተላላኪ እንሆናለን፡፡ … ውስጣችን ላይ ከተቆለፈ፣ በጥቅም ስለምንገዛ … ከጳጳሱ ቄሱ፣ ከመምህሩ ደቀ-መዝሙሩ እንደሚባለው ዓይነት፣ “የተሰራ” … ሰው እንሆናለን፡፡ … አንተስ ወዳጄ፤ ውስጥህ አልተቆለፈበትም? … መልሱ አንተው ጋ ነው ያለው!!
ሊቃውንት፤ “ፍልስፍና ለጥያቄዎቻችን መልስ አይሰጠንም፡፡ መንገዳችንን ይመራናል እንጂ።” ይላሉ፡፡ … ራሳችን ከራሳችን ጋር መኖራችንን ለማረጋገጥ ወይም የማንኛውንም ጉዳይ ውስጠ ነገር ለመመርመር የሚጠቅመን አንዱ የዕውቀት መንገድ ጥበብ (Art) መሆኑን በአፅንኦት ይናገራሉ።
“የጥበብ አላማው የነገሮችን ውጫዊ አካል ማጉላት ሳይሆን ውስጣዊ ባህሪያቸውን ሸልቅቆ በማውጣት እውነተኛውን ስዕል ማሳየት ነው።” (…The aim of art is to represent not the outward appearance of things, but their inward significance…) በማለት አርስቶትል ጽፎልናል፡፡
ወዳጄ፤ ጠቢብን ጠቢብ የሚያሰኘው… ሌሎች ከማያዩት፣ ልብ ከማይሉት፣ ሰምተው ካልገባቸው ነገር ውስጥ… የሚታይ፣ የሚስተዋል፣ የሚደመጥ፤ ሊፈቀር ወይ ቸል ሊባል የሚገባው ፍሬ ሊኖር እንደሚችል ማሳየቱ ነው፡፡… የጥበብ ሰዎች የተደበቀውን ቆፍሮ የማውጣት አቅም አላቸው።… የራሳቸው ስራ ወይም ፈጠራ ከሆነም፣ ሌሎች ሰዎች ጥረውና መርምረው የመረዳትን ፀጋ… (The Joy of understanding) እንዲታደሉ ያደርጓቸዋል። ‹መኖር› የሚባለውን ነገር በቀላሉ በመተርጎም፣ ዘወትር የሚሹት ደስታ ቅርባቸው የተደበቀ መሆኑን የሚያሳይ የብርሃን ፍንጣቂ ይልኩላቸዋል፡፡
ወዳጄ፤ ብዙዎቻችን ጨለማን እንደ እርግማን ነው የምናስበው፡፡ …ከጨለማ ውጭ መኖር የማይችሉ ብዙ ፍጥረታት እንዳሉ እንዘነጋለን፡፡ ጨለማ ከሌለ ከዋክብቶችን ማየት እንደማንችል፣ የምንበላቸውና የምንጠጣቸው ነገሮች ከጨለማ ውስጥ እንደሚበቅሉና እንደሚመነጩ እንረሳለን።…እኛም እንደ ወፍ ጫጩት፤ ጨለማ ውስጥ ተቀፍቅፈን፣ ጉዞአችን ሲጠናቀቅ፣ ወደዛው እንደምንመለስ እንኳን  ማመን ይተናነቀናል፡፡  
ጨለማና ብርሃን አእምሯችን ውስጥ በሃሳባችን ቀለማት የምንስላቸው፣ አንዱ ከሌላው የማይነጠል ክስተቶች ናቸው፡፡… እንደ ክፋትና ደግነት!!...ጥቁሯ ነጥብ የምትታየው በነጭ ወረቀት ላይ በመስፈሯ እንደሆነ ሁሉ፣ ነጯኑም ነጥብ ማየት የምንችለው፣ በጥቁር ወረቀት ላይ ስትስፍር ብቻ ነው፡.. አንዱ ያለ ሌላው ምንም ይሆናል፡፡… የተማርንበትን ሰሌዳና ጠመኔ ነጣጥሎ ማሰብ እንዴት ይቻላል?
“We often forgot that not only is therc a soul of goodness in things evil, but in general, there is also a soul of truth in things erroneous” በማለት ይህንን ዕውነት የሚያረጋግጥልን ደግሞ ኸርበርት ስፔንሰር ነው፡፡
ወዳጄ፤ የተነሳንበትን እናስታውስና… አንተ፤ “ከንቱ”፣ “መናጢ”፣ ምስኪን ልትሆን ትችላለህ፣ ወይም ገንዘብ፣ ዝናና ስልጣን የሞቀህ ባለ ጊዜ!... ጥያቄው እንደ ገጣሚው፣ ከመስታወትህ ፊት ቆመህ ራስህን ከራስህ ውስጥ ስታጣው ምን ትላለህ?... የሚል ነው፡፡… መልሱ አንተው ራስህ ጋ ነው!!
ከአብዱል ተረቶች ልቀንጭብልህ፡-
የአንድ ሃገር ንጉሥ ነበር፡፡… ከዕለታት አንድ ቀን በዕውቅ ልብስ ሰፊ የተዘጋጀ ልብስ ለብሶ፣ ለህዝቡ እንደሚታይ በዐዋጅ ተነገረለት፡፡… ይህንን ልዩ ልብሱን፣ ዐዋቂና ብልህ ያልሆነ ሰው (wisdom የሌለው እንደማለት) … ሊያየው እንደማይችልም ከዳር እስከ ዳር ተወራ፡፡
…ቀኑ ደረሰና ንጉሱ  በመኳንንቱ ታጅቦ ወደ አደባባይ ወጣ፡፡… ሰው ሁሉ… “እንዴት የሚያምር ልብስ ነው!?”… እያለ አጨበጨበ… አደነቀ፡፡… ከአባቱ ጋር ወደ አደባባይ የወጣ አንድ ህፃን ልጅ ግን ንጉሡን እንደተመለከተው፡-
“ንጉሡ ራቁቱን ነው”... (The King is naked!!)… በማለት ዕውነቱን ተናገረ፡፡…
አንተስ ወዳጄ፤… ተቆልፎብሃል? ወይስ … መልሱ አንተው ጋ ነው ያለው!!
ሠላም!!

Read 711 times