Tuesday, 02 January 2018 10:09

“ኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

(ምናባዊ ወግ)
    እንደተለመደው፣ ዓርብ ከሰዓት በኋላ በሙዚቀኛው ስቱዲዮ ውስጥ ተገናኙ፡፡ የሙዚቀኛው ስቱዲዮ ከመሃል ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኝ ቢሆንም፣ ከሚሊኒየሙ በፊት መስፋት የጀመረው ከተማ፣ ወጣ ያለ የሚባለውን ስፍራ አልፎት ኼዶ፣ ውጪውን ውስጥ አድርጎታል። ስቱዲዮው የሚገኘው የፎቁ ምድር ቤት ውስጥ ነው፡፡ የፎቁ ባለቤት የእራሱ የሙዚቀኛው አባት በመኾናቸው፣ ስቱዲዮው ለልጃቸው ቤቱ ነው፡፡ ፎቁ ለባለቤትየውና ለልጆቻቸው መኖሪያም፣ የሥራ ገበታም ሆኖ ያገለግላል፡፡
በተለምዶ፣ ዓርብ ከሰዓት በኋላ የሚሰባሰቡት ሙዚቀኛውና ሁለት ጓደኞቹ መላክ እና ሥዩም ቢሆኑም፣ ዛሬ ግን አንድ እንግዳ ጨምረው አራት ሆነዋል፡፡ እንግዳውን ይዞ የመጣው መላክ ነው። መላክ፣ ጥበብን ከመስራት ይልቅ፣ ተሰጥኦውና ዝንባሌው፣ የጥበብ ቤተሰቦችን በማቀራረብ ላይ ያተኩራል፡፡ እንግድየው ደራሲ እንደሆነ በደፈናው ነገራቸው፡፡ የስቱዲዮው ባለቤት፣ ጓደኞቹ ‹ማንም ሰው› ዝም ብለው እንደማያመጡ ስለሚያምን፣ አክብሮ መጤውን ተቀበለው፡፡ እንግዳ ሲመጣ እንደሚያደርገው፣ የሰራቸውን ሙዚቃዎች እየከፈተ አስተያየት ለመስማት ተዘጋጀ፡፡ በቂ ሙዚቃዎች በደኅና እና ጥርት ባለ  ድምፅ ከክፍሉ ከተንቆረቆሩ በኋላ፣ እንግድየው አስተያየቱን ሰጠ፡፡
“እንደዚህ ዐይነት ሙዚቃ በዚህ ሀገር ውስጥ ሲሰራ የመጀመሪያው ጊዜ ነው፣ አይደል?”
“ለማለት ይቻላል፣” ብሎ ሙዚቀኛው በውጪአዊ ትህትና፣ በውስጣዊ እርካታ መለሰ፡፡
“የሙዚቃው ዘውግ ምን ተብሎ ይጠራል?”
“ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ፡፡ ግን ወደ ሀገርኛ ቋንቋ ስሙን በአግባቡ መመለስ ያስፈልጋል፡፡”
“ኤሌክትሮን የዐማርኛ አቻ ሳይኖረው፣ “ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ” እንዴት ይተረጎማል?” ብሎ ስዩም ሁሉንም አሳቃቸው፡፡ ሙዚቃ የሚለው ቃል እራሱ መች ሀገርኛ ፍቺ አለው፤ አርመኖቹና ጣሊያኖቹ በነገሩን ነው የቀጠልነው፡፡ ‹ዘፈነ› ማለት “ሞዘቀ” ማለት አይደለም!” አለ መላከ፡፡ ወደ ሳቅ አጋድሎ የነበረውን የውይይት አዝማሚያ ኮስተር አደረገው፡፡
ደራሲ ተብሎ የተዋወቀው እንግዳ፣ ሐሳብ እንዲሰጥ የሚጠበቅ ስለመሰለው፣ ጉሮሮውን እያጠራ፣ የሚለውን ነገር በፍጥነት አደረጀ፡፡ ከዚህ በፊት የሙዚቃ ማቀናበሪያ ክፍል ገብቶ አያውቅም፤ ሙዚቀኛም ገጥሞት አያውቅም፡፡ ክፍሉ በትልልቅ ድምፅ-ማጉያዎች ተከብቦአል፡፡ እንደ የኮምፒውተር የመሰለ ስክሪን ከተገጠመለት በጣም ዘመናዊ ኪ-ቦርድ ፊት ለፊት፣ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ የተቀመጠው ወጣት ለጥበቡ ሲል ብዙ የተጎሳቆለ ይመስላል፡፡ አራት ኤሌክትሪክ ጊታሮች በሁለት ማዕዘን በተዘረጉ ሶፋዎች ላይ አፈ-ሙዛቸውን ወደ ኮርኒሱ ደግነው ተቀምጠዋል። በአፉ የተደፋው ትራምፔት ወርቃማና ብራማ ቀለማቱን እያንፀባረቀ ቀጥሎ ስለሚነፋበት ትንፋሽ የሚያሰላስል ይመስላል፡፡ የ‹ባንጎ› ከበሮው ላይ አንዳች ኤሌክትሮኒክ ስራ የሚሰራ ሰሌዳ መሰል ነገር ተቀምጦበታል፡፡ የክፍሉ ግርግዳ፣ ድምፅ ከውጪ እንዳይገባ በሚከለከል፣ ስፖንጅ መሰል ሽፋን ተለብጧል፡፡
“ስለዚህ፣” አለ ደራሲው፤ “ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ወደ ኢትዮጵያ በአንተ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገባ፣ በየትኛው የመግቢያ ዐቅል ላይ ነው የሚቀመጠው? የሚል ይኾናል መሠረታዊ ጥያቄ፡፡”
የውይይቱ የስበት እምብርት የሚመስለው የተነሣው ሐሳብ ሳይኾን ውይይቱ የሚካኼድበት የዘመናዊ ስቱዲዮ ባለቤት የኾነው ልጅ ነበር፡፡ ልጁና የእርሱ ሙዚቃ በስቱዲዮ ውስጥ ባይገኙ፣ ስቱዲዮውም የልጁ አባት ፎቅ ውስጥ ባይቀመጥ፣ ጥያቄዎቹ አሁን በአቀኑበት አቅጣጫ ላይቀጥሉ በቻሉ ነበር፡፡
ደራሲው የጠየቀውን ጥያቄ፣ ሙዚቀኛው ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ሰማ’ና፡-
“ስምህን ማነው ያልከኝ?” አለው ደራሲውን፡፡
“ስለሺ፣” አለለት - መላክ፤ ደራሲውን ያመጣው እርሱ ስለሆነ ተሸቀዳድሞ፡፡
“ስለሺ፤ የኔን ስም ይዘኸዋል አይደል? ሚክፓፕስ እባላለሁ፡፡ ሚክፓፕስ ስለሺ… ስለሺ ሚክፕስ… ዮ፣ ዮ….fell me, bro.  የኛ “ፒፓ” መቼም ወደ ፊት አይራመድም፡፡ ስለዚህ dude, የሚራመደው ቴክኖው ነው… ቴክሎጂውን ታ-ስ-ጨ-መ-ድደ-ዋለ-ኽ፡፡ It’s all about the future, It’s bro about keeping up with your hair… keeping up with the time, and the time is for this shit right here, bro. ዲጅታል ቴክኖሎጂን ፒፓው እ-የ-አ-ጨ ማለቀው አይደል እንዴ፡፡ እኛ’ኮ የሰጠነው ከሚያጨልማቀው ነገር ጋር የሚኼድ ሙዚቃ ነው፡፡  It’s the shoes that fits the age; you can’t wear the shoe and leave the style…or the mode. It’s all about style and this here style will be the mannerism of the new age. You feel me, bro? it’s all about change”
ሙዚቀኛው ሲያወራ እንደ የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ አርቲስት ሳይኾን እንደ Hip-Hop አርቲስት መምሰሉ የታወቀው አይመስልም፡፡ ደራሲው ጭንቅላቱን ነቀነቀ፣ ተስማምቼአለሁ ለማለት ሳይሆን ገብቶኛል ለማለት፡፡
“መጀመሪያ” አለ ደራሲው፣ “ሰው በትንፋሹ ይዘፍን ነበር- “ይዘፍን” ወይም “ያመሰግን” የሚለው አያጣላንም፡፡ ከዚያ ቀጠለና፣ወይንም ሲቀጥል፣ ትንፋሹን በዋሽንቱ ውስጥ አንቆረቆረው - በጊታር ውስጥ ወይም በቫየሊን፣ መሳሪያ አያጣሉንም፡፡ ዋሽንቱ ላይ የኤሌክትሪክ አምፕሊፋየር ገጠመበት ወይም ጊታሩን በኤሌክትሪክ እንዲሠራ አደረገው። ይሄ የቅርጽ ለውጥ እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አይደለም፡፡ አኹን እናንተ ይዛችሁ የመጣችሁት ግን ኮምፕዩተር የፈጠረውን ድምፅ፣ ኮምፕዩተር አቀናብሮ ለሰው ማስደመጥ ነው፡፡ ተሳስቼ ከሆነ አስረዱኝ፡፡”
“እና ቢኾንስ?” ሥዩም የተባለው ተበሳጨ፣ “የ-ሰው ልጅ ድምፅ ከሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ካልመጣ በስተቀር አይለወጥም፣ እና ዝንጀሮ ሰው እስኪኾን ኤቬሉሽንን እንጠብቅ እንዴ? የሰው ልጅ የራሱን ለውጥ ፋሲሊቴት የሚያደርገው በሚፈጥረው ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው፡፡ የሰውን ልጅ ድምፅ ከመግራት ቴክኖሎጂን መግራት ይቀልልአል፡፡ (በእጁ እየጠቆመ) የሰው መጠን እዚህ ነው (ከመሬት ትንሽ ከፍ አድርጎ)፣ የአበሻ መጠን እዚህ ነው (መሬቱን አስነክቶ)፣ ቴክኖሎጂ ግን ይሄ ነው (ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ ተነሥቶ እየዘለለ፣ ጣራውን ለመንካት እየሞከረ)፡፡”
በሙዚቃ አቀናባሪው መሪነት፣ በተናጋሪው አማካኝነት፣ ከደራሲ በቀር፣ ኹሉም ሳቁ፡፡ የደራሲው ፊት ቀላ፡፡ “Where there is ego I go!” በሚለው መርሑ፣ ጸንቶ ዝም ማለት ወይም ተሰናብቶ መኼድ ቢያምረውም እልኽ ያዘው፡፡ በክርክሩ ገፋበት፡፡
“እኔ ቃላትን ከድምፅ በበለጠ መጠቀም የምሻው ለዚህ ነው፡፡ ድምፅ በሒሳባዊ ስሌት በከፍልፋይና በብዜት የተዋቀረ ነገር ነው፡፡ ቅርጽ ነው፡፡ ይዘት የለውም፡፡ የሙዚቃ ዓለም ከዲጅታሉ ጋር ሲዋሐድ፣ ስሜት ቁስን ትመስላለች፣ መንፈስን ልታመጥቅ አይቻላትም፡፡ ነፍስን ቃላት እንጂ ኤሌክትሪክ ሊነዝራት አይችልም፡፡ ኤሌክትሪክ ፊዚክስ ነው፣ ለአካል ወይም ለቁስ የተፈጠረ ነው። በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቁስ አካሉን አምላክና የእሱን እስረኞች ነው የምታገለግሉት፡፡ ኢትዮጵያ መንፈሳዊት ሀገር ናት፤ መንፈሳዊ ዕውቀትዋም ከምዕራባውያን የቁስ ዕውቀት ጋር ዝንተዓለም ሊታረቅ አይችልም፡፡ መንፈሳዊቷና ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የናንተን ሙዚቃ አታደምጥም፡፡”
“Watch and see, bro! Dude, መንፈሳዊቷ ኢትዮጵያ አውሮፓ ነው ያለው ቀልብዋ። መንፈሳዊቷን ኢትዮጵያ እያነቃነቀ ያለው‘ኮ ኤሌክትሪክ ነው፡፡ እንዲያውም፣ ለኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ኢትዮጵያዊ ስም አገኘሁለት my goodness, I’m about to be enligtened, am about to become a genious … ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን “መንፈሳዊቷ ኢትዮጵያ” ብዬ ሰይሜዋለሁ፡፡”
ነገሩ መካረሩን መላከ ዐይቶ፣ ወሬውን ወደ ሌላ አቅጣጫ አስቀየረ፡፡ ከተቀየረው ወሬ ጋር ሙዚቀኛው ከቀጠለ፣ ወሬው ይደራል፤ ግድ አልሰጠው ከአለ፣ በሌላ ቅያስ አቋርጦ፣ እንደሚገኙበት ስቱዲዮ እና ፎቅ ፍላጎት ይቀለበሳል፡፡
የደራሲውና የሙዚቀኛው ልጅ ኮከብ ጥርሱ ለምን እንደአልገጠመ ሳይገባቸው ቀርቶ፣ መላከ በስተመጨረሻ፣ “ሁለታችሁም “ሊዮ” ስለሆናችሁ ነው፣” ብሎ አሳቃቸው፡፡
ደራሲው፣ የእንግድነቱን ዘመን ወደ አባልነት ወይም ወደ ጓደኝነት ሳይቀይር፣ ተሰናብቶአቸው ሄደ፡፡ “ግሩፑ”፣ በተለይ፣ ሙዚቀኛው፣ ከዚያች ቀን በኋላ አንድ ‹ተራማጅ› ያልሆነ ሰው ሲገጥመው፣ “እንደ ‹ፍሬንድ›፣ እንደ ባህላዊው ደራሲ!” እያለ ማጣቀሻ አድርጎት ቆየ፡፡

Read 1881 times