Tuesday, 02 January 2018 10:25

ETHICS …የሙያ ስነ ምግባር…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(2 votes)

በማንኛውም የሙያ ዘርፍ ከሚስተናገድበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተገልጋዩ ሕብረተሰብ የሚያነሳው እሮሮ ይኖራል፡፡ በተለይም ወደ ሕክምናው ዘርፍ ሲዘለቅ ለሚነሱ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ወይንም ለሚፈለገው አገልግሎት የሚሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም ከሚል የሚታየው ቅሬታ አየል ይላል፡፡የዚህም ምክንያት ነው ተብሎ የሚገመተው አንድም ጥያቄው ከሕይወት ጋር የተያያዘ ነው ወይንም የህክምና ባለሙያዎቹም ያው እንደሌላው ሰው ስለሆኑ የባህርይ ችግር ሊታይባቸው ይችላል የሚል ነው፡፡ ስለዚህም ግልጽና ወጥ የሆነ የስነ ምግባር መመሪያ አስፈላጊ ነው። ተገልጋዩ ክፍልም መብቱን ሊጠይቅ የሚችልበት… አገልግሎት ሰጪውም እስከምን ድረስ አገልግሎት መስጠት እችላለሁ የሚለውን የሚወስንበት ግልጽ የሆነ የሙያ ስነምግባር መመሪያ ያስፈልጋል፡፡
ህዳር 25-26/ የማህጸንና የጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ያቀናጀው የስነምግባር መመሪያ ስልጠና በአዲስ አበባ ተካሂዶአል፡፡ የማህጸንና የጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች በተለይ አገልግሎት ለመስጠት ሊያጣቅሱት የሚችሉት የሙያ ስነምግባር እየተሰራ መሆኑ በስልጠናው ላይ ተነስቶአል፡፡ ስልጠናውን ከተለያዩ ክፍሎች የተሳተፉ ባለሙያዎች የሰጡ ሲሆን ለዚህ እትም አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጋበዙት ዶ/ር አዳሙ አዲሴ ናቸው፡፡ ዶ/ር አዳሙ አዲሴ የህክምና ባለሙያ እና በተጨማሪም የህክምና ስነምግባር ባለሙያ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ስልጠናውን ለማድረግ ከውጭ የመጡ ፕሮፌሰር ሸዋርዝ የሚባሉ እንግዳም ነበሩ፡፡
ፕሮፌሰር ሸዋርዝ  እንደገለጹት ‹‹…ETHICS… ወይንም የሙያ ስነምግባር ማለት አንድን ሰው ወይንም ባለሙያ በትክክለኛው ወይንም በታወቀ መንገድ እንዲመራ ወይንም ስራውን እንዲሰራ የሚያስችል እምነት እንዲኖረው እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃም ሁሉም ባለሙያ ወጥ በሆነ አሰራር እንዲሰራ የሚያስችል አስተሳሰብን እንዲሁም እምነትን በተቀናጀ ሁኔታ ለመምራት የሚረዳ የአሰራር መመሪያ ነው፡፡ በተለይም በሴቶች ጤና ዙሪያ ሲታሰብ እጅግ በጣም ጠቃሚ አካሄድ ነው፡፡ የሙያ ስነምግባር ጎደለ ሲባል አልፎ አልፎ ለስራው የተዘረጋው መረብ ችግር ስለአለበት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው አስቀድሞውኑ በባህሪያቸው ችግር ያለባቸው ሰዎች እንደምክንያት ሲጠቀሙበት ስለሚታይ እንጂ በቅንነት ሙያውን ለሚያከብር እና ተገልጋዩን በትክክል ችግሩን ለመፍታት… ሕይወትን ለማዳን ለሚፈልጉ አያገለግልም፡፡ በእርግጥ ደረጃው ቢለያይም ስነምግባሩን ለሚያከብሩም ሰዎች አቅጣጫ ባለማመላከቱ ችግር አይደለም ተብሎ ሊደመደም አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ታካሚ በግብረስጋ ግንኙነት ሳቢያ የሚተላለፍ በሽታ ቢይዘውና ለሚስቱ ወይንም ለፍቅረኛው እንዲነገርበት ካልፈለገ ሐኪሙ ይህ የበሽተኛው የራሱ ጉዳይ ነው ብሎ መተው ሳይሆን በምክር አገልግሎት እንዲሁም እንደ ቅርብ ቤተሰብ ወይንም ጉዋደኛ በመቅረብ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለእንደዚህ ያለው አጋጣሚ የአሰራር ወይንም የተዘጋጀ የስነምግባር መመሪያ ሲኖር መደረግ ያለበትንና መደረግ የሌለበትን ነገር አስቀድሞውኑ ለማወቅ ያስችላል፡፡ ስለዚህም የስነምግባር መመሪያ መኖሩ አስፈላጊ ነው፡፡›› ብለዋል ፕሮፌሰር ሸዋርዝ፡፡
ዶ/ር አዳሙ አዲሴ እንደሚሉት በሕክምናው የሙያ ስነምግባር ተጠቃሽ የሆኑ አራት መሰረታው ነጥቦች አሉ፡፡
1) Beneficence,
ጥሩ መስራት በጎ መሆን በቅንነት ማገልገል
2) Non-Maleficence,
ጎጂ አለመሆን ጥቃት አለማድረስ ከጥፋት እራስን ማግለል
3) Respect for Autonomy, and
በራስ የመተማመን ብቃት እና ስለስራው ጥሩ ግምት ወይንም ክብር ማሰብ
4) Justice.
ፍትሀዊነት፡- የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
መሰረታዊ የሆኑት የህክምና ሙያ ስነምግባሮች ሲተነተኑ ቀዳሚው ለተገልጋዩ ጥቅም መቆም የሚለው ይገኝበታል፡፡ ታካሚዎችን በመጥቀም ረገድ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ዶ/ር አዳሙ ካነሱዋቸው ምሳሌዎች አንዱን እናስነብባችሁ፡፡
አንዲት ከጠቅላላ ሐኪምነት ወደ ማህጸንና ጽንስ ሐኪምነት ለመሸጋገር የሙያ ተማሪ የሆነች ሐኪም አንድ ታካሚ ትገጥማታለች፡፡ ታካሚዋ የ28 አመት የማህጸንና ጽንስ ታካሚ የሆነች እርጉዝ ሴት ናት፡፡ እርግዝናው 13 ሳምንት ሆኖታል፡፡ በእርግጥ ሴትየዋ ከአሁን በፊት ሌሎች 3 ጤነኛ ልጆችን ወልዳለች፡፡ የማህጸን ካንሰር ሐኪሙ በምርመራው የካንሰር ሕመምዋ 2ኛ ደረጃ ላይ ስለደረሰ ኬሞቴራፒ የተሰኘው የህክምና ዘዴ ወይንም መድሀኒት መጀመር እንዳለባት እና በቅድሚያ ግን እርግዝናዋ መቋረጥ አለበት የሚል ነበር ውሳኔው፡፡ ሐኪምዋ ግን ይህ እርግዝናን ማቋረጥ ህጋዊ ነው ወይንስ አይደለም በሚል ተጨነቀች፡፡
እንግዲህ ከላይ እንዳነበባችሁት አይነት ሌሎችም ሐኪሞችን  ለውሳኔ  የሚፈታተናቸው  ብዙ አይነት ጉዳዮች አሉ፡፡ ስለዚህም በሕክምና ዘርፍ የሙያ ስነምግባር ግድ ሲሆን በተለይም የማህጸንና ጽንስ  ሕክምና እራሱን የቻለ ውስብስብ ችግሮች ስለሚገጥሙት የሙያ ስነምግባር መመሪያው ያስፈልጋል እንደ ባለሙያዎቹ እምነት፡፡ በሙያ ስነምግባሩ የመጀመሪያው ነጥብ ጥሩ መሆን በጎ መስራት እና በቅንነት ማገልገል ነው፡፡ ይህም ሲባል፣
የህክምና ባለያዎች የራሳቸው ስሜት ሳይሆን የታካሚዎቻቸው ስሜት ተገዢ መሆን አለባቸው። ታካሚዎች ከጉዳት እንዳይወድቁ መከላከል አለባቸው፡፡ ጉዳትን ማስወገድ አለባቸው። ታካሚዎች ጥሩ አገልግሎት እንደሚያገኙ ማስተዋወቅ ወይንም ለታካሚዎች መግለጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በጤና አገልግሎት መስጫ ተቋሙ ውስጥ ታካሚዎችን ከጉዳት መጠበቅ ሲባል በተከሰተው ህመም ምክንያት የሚደርስ የህመም ስቃይ በሽታውን… የአካል መጎዳቱንና ሞትን ጭምር እንዳይደርስ መከላከልን የሚመለከት ነው፡፡
በተመሳሳይም ጥሩ ከሚባሉት ነገሮች ውስጥ ከሕመም መፈወስ… ጤንነት ማግኘት እና ሕይወትን ለክፉ የሚሰጥ ነገር እንደሌለ የሚያሳይ ትክክለኛ አገልግሎት መሆኑን ማሳየት ይጠበቃል፡፡
ይህ መመሪያ ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ አንድ ነገር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ በስራ ላይ እንዲውል የተዘጋጀው የህክምና እርዳታ በታካሚዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለማስወገድ ያስችላል? ለታካሚው ጥሩ ሁኔታን… ደህንነትን ይፈጥራል? የሚለውን ማሰብ ይጠቅማል፡፡
ለምሳሌም፡-
ሞት ምንጊዜም ሊከላከሉት ወይንም እንደይደርስ የሚመኙት… ሕይወት ግን ምንጊዜም እንዲቀጥል የሚመኙት ነገር ሲሆን አንዳንድ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ግን ነገሩን ከጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ቤተሰብ ወይንም የቅርብ ዘመዶች ሕመምተኛው በትክክለኛው መንገድ እንኩዋን ባይሆን በአርተፊሻል አተነፋፈስም ይሁን በተመሳሳይ መንገድ ሳይሞት እንዲኖር ሊመኙ ይችላሉ፡፡ በሌላው አቅጣጫ ደግሞ ታካሚው ከሕመሙ በትክክለኛው መንገድ ሳያገግም እንዲያውም መኖር በማይባል ሁኔታ በአርተፊሻል እስተንፋሶች እየተረዳ የሁዋላ ሁዋላ መሞቱ የማይቀረው ሰው በተፈጥሮአዊው መንገድ ታምሞ ቢሞት የተሻለ ነው ሊባል ይችላል፡፡
ስለዚህ በየትኛውም አቅጣጫ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ጠቃሚ እንዲሆንና ጉዳትን ማስወገድ እንዲችል ሊያግዝ የሚችል የስነምግባር መመሪያ መኖሩ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ የሙያ ስነምግባሩ ለሐኪሞቹ ብቻም ሳይሆን ለሕክምና ተቋማቱም በሀገር ደረጃ በተመሳሳይ መንገድ አሰራራቸውን ለመቅረጽ የሚያግዛቸው ነው፡፡
ይቀጥላል  

Read 2366 times