Tuesday, 02 January 2018 10:27

ቻይና በ3 አመታት ከ13 ሺህ በላይ ድረ-ገጾችን ዘግታለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ስለ ጉዳዩ አስተያየት ከሰጡ ቻይናውያን፣ 90 በመቶው እርምጃውን ደግፈውታል

   የኢንተርኔት ነጻነትን በመጣስና ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የሚታወቀው የቻይና መንግስት፤ ባለፉት 3 አመታት ብቻ ህግና መመሪያዎችን ጥሰዋል በሚል ከ13 ሺህ በላይ የተለያዩ ድረ-ገጾችን በመዝጋት ከአገልግሎት ውጭ ማድረጉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቻይና በተለይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ዢ ፒንግ ስልጣን ከያዙ በኋላ፣በነበሩት ያለፉት አምስት አመታት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በሚጥስ መልኩ በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ የምታደርገው ጥብቅ ቁጥጥርና ቅጣት በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል ያለው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት የሚሰነዘሩበትን ትችቶች ለማፈን፣ ብዙ ድረገጾችን እየዘጋ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
አለማቀፍ ተቋማት የቻይናን ጥብቅ የኢንተርኔት ቁጥጥር በተደጋጋሚ ቢተቹትም፣ የአገሪቱ መንግስት ግን “ሁሉም አገራት የሚያደርጉትን ነው እያደረግሁ ያለሁት፤ በኢንተርኔት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የማደርገው ብሄራዊ ደህንነቴን ለመጠበቅና ማህበራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር በማሰብ ነው” ሲል ምላሽ መስጠቱ ተነግሯል፡፡
የመብት ተሟጋች ተቋማት፤ የቻይና መንግስት የዜጎቹን መብት እየጣሰ ነው ሲሉ ቢወነጅሉትም፣ የድረገጾቹን መዘጋት በተመለከተ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ከተጠየቁት ቻይናውያን መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአንጻሩ እርምጃውን እንደሚደግፉ መናገራቸውንም የሮይተርስ ዘገባ አስረድቷል፡፡
ቻይና 13 ሺህ ድረገጾችን በመዝጋቷ ሳቢያ 10 ሚሊዮን ያህል አካውንቶች ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል ያለው ዘገባው፤ “የአገሪቱ መንግስትም የተባለው ነገር እውነት መሆኑን አምኖ፣ ልቅ ወሲብና ብጥብጥ የሚያጭሩ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን አደገኛ ድርጊት ለማስቆም ስል ህገወጥ ድርጊቱን ሲፈጽሙ ያገኘኋቸውን ድረገጾች ዘግቻለሁ” ብሏል፡፡

Read 1107 times