Tuesday, 02 January 2018 10:28

ዓለም ባለፉት 12 ወራት- በወፍ በረር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዓለማችን ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ በቀረው የፈረንጆች ዓመት 2017፣ እጅግ በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳለች፡፡ ባለፉት 12 ወራት ዓለማችን ያስተናገደቻቸውን ዋና ዋና ክስተቶች በተመለከተ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከሰሞኑ ለንባብ ካበቋቸው አበይት መረጃዎች መካከል ጥቂቶቹን መርጠን እነሆ ብለናል!
የትራምፕ መምጣት
የፈረንጆች አመት 2017 አሃዱ ብሎ ሲጀምር፣ አለማችን ካስተናገደቻቸው ዋነኛ መነጋገሪያ ጉዳዮች መካከል የዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት አንዱ ነበር፡፡ ለወራት በዘለቀው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የቅስቀሳ ዘመቻ ላይ “ሙስሊሞችን ከአገሬ አባርራለሁ” የሚለውን ጨምሮ በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮችን በአደባባይ ሲያስተጋቡ የከረሙት ትራምፕ፤ ዲሞክራቷን ተፎካካሪያቸው ሄላሪ ክሊንተንን አሸንፈው መንበረ ስልጣኑን ይረከባሉ ብሎ የጠበቃቸው ብዙ ሰው ባይኖርም፣ ድል ቀንቷቸው አለምን አስገርመዋል፡፡
በአመቱ የመጀመሪያ ወር ላይ በደማቅ በዓለ ሲመት፣ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ትራምፕ፤ አመቱን ሙሉ አለምን የሚያስገርሙና በአነጋጋሪነታቸው ጎልተው የወጡ እርምጃዎችን በመውሰድ ነበር ያሳለፉት፡፡
ሰብዓዊ ቀውሶች
በዓለማችን የከፋው የሰብዓዊ ቀውስ ሰለባ እንደሆነች አመቱን አገባድዳለች - በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰዋ የመን፡፡ ከ17 ሚሊዮን በላይ የመናውያን የሚልሱ የሚቀምሱት አጥተው አመቱን በርሃብ አልፈውታል፡፡ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው የኮሎራ ወረርሽኝም 1 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን ሲያጠቃ፣ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለሞት ዳርጓል፡፡
የዓለም ባንክ ባወጣው አመታዊ ሪፖርት እንዳለው፤ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በ45 የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ 83 ሚሊዮን ያህል ዜጎች የርሃብ አደጋ ተጠቂና የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ነበሩ፡፡ ይህ ቁጥር ከሁለት አመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር፣ በ70 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
የተፈጥሮ አደጋ
የፈረንጆች አመት 2017 ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ ደቡብ አሜሪካ፣ በተለያዩ የአለማችን አገራት በርካታ ቁጥር ያላቸው የተፈጥሮ አደጋዎች የተከሰቱበትና ከፍተኛ ጥፋት ያደረሱበት ነበር፡፡ 2017 የካሊፎርኒያና የፖርቹጋልን ጨምሮ በርካታ የሰደድ እሳቶች የተከሰቱበት ዓመት ነበር፡፡ ከአሜሪካዎቹ ሃሪኬኖች እስከ አየርላንድ አውሎንፋሶች ድረስ እጅግ ከፍተኛ ጥፋት አስከትለዋል፡፡
ሰሜን ኮርያ
ሰሜን ኮርያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዘንድሮ በሚሳኤል ሙከራና በኒውክሌር ማስፋፋት የተጠመደችበት ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀብም ሆነ የአሜሪካና የሌሎች አገራት ዛቻና ማስፈራሪያ ያልበገራት ሰሜን ኮርያ፤ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ከ12 ጊዜያት በላይ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡ ሰሜን ኮርያ ወሩ በገባ በሁለተኛው ሳምንት ወደ ጃፓን ባህር ባስወነጨፉት ሚሳኤል የተጀመረው የሚሳኤል ሙከራ፤ የአካባቢውን አገራት ብቻ ሳይሆን የተቀረውን አለምም ያስደነገጠና ስጋት ውስጥ ከትቶ ያለፈ ነበር፡፡
ሰሜን ኮርያና አሜሪካ፤ በቃላት ጦርነትና በፍጥጫ ነበር አመቱን ያገባደዱት፡፡ ትራምፕ እና ኪም ጁንግ ኡን አንዳቸው ሌላኛቸውን በቃላት ሲያዋርዱና ሲዘልፉ፣ ከአሁን አሁን ተታኮሱ በሚል አለምን ሲያስጨንቁ፣ አመቱን በቃላት ጦርነት አገባድደውታል፡፡
የሮሂንጋ ሙስሊሞች መከራ
የፈረንጆች 2017 በማይንማር ለሚኖሩ የሮሂንጋ ሙስሊሞች፣ ከመቼው ጊዜ የከፋ የመከራና የስቃይ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡ የማይንማር ወታደሮች በወራት ጊዜ ውስጥ ከ6 ሺህ 700 በላይ የሮሂንጋ ሙስሊሞችን መግደላቸው ተነግሯል፡፡ ቤታቸው በእሳት ሲጋይባቸው፣ ወገኖቻቸው አይናቸው እያየ ሲታረዱባቸው፣ ነፍሳቸውን ለማዳን በየጫካው የተበተኑና አገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ባንግላዴሽ የተሰደዱ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ከ600 ሺህ በላይ እንደሚደርሱም የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡  የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ አለማቀፉ ማህበረሰብ የሚገባውን ያህል ትኩረት አልሰጠውም የተባለው የሮሂንጋ ሙስሊሞች ቀውስ፤ ለመጪው 2018 የፈረንጆች አመትም ባለበት ሁኔታ ይቀጥላል ተብሎ እየተነገረ ነው፡፡
የሽብር ጥቃቶች
ግንቦት 22 ቀን ምሽት ላይ…
በእንግሊዟ ማንችስተር የተዘጋጀውን የአርያና ግራንዴ የሙዚቃ ኮንሰርት ለመታደም በአዳራሽ ውስጥ የተገኙ የሙዚቃ አፍቃሪያን ራሳቸውን ያላሰቡት መከራ ውስጥ አገኙ፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የተሰማው ድንገተኛ ፍንዳታ፣ ተደጋግሞ ቀጠለ፡፡ ሁሉም ነፍሱን ለማዳን በየአቅጣጫው ተራወጠ። 22 ያህል ሰዎችን ለሞት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎችም ለመቁሰል አደጋ ተዳረጉ፡፡
ልክ እንደ ማንችስተር ሁሉ፣ ከስቶክሆልም እስከ ባርሴሎና፣ ከበርሊን እስከ ፓሪስ በርካታ የአውሮፓ አገራት ከተሞች በሽብር ጥቃቶች እየተናወጡ ነበር አመቱን የገፉት፡፡ የሽብር ጥቃቱ አውሮፓ ላይ አያበቃም፡፡ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራት በአይሲስ እንዲሁም በተለያዩ ጽንፈኛ ቡድኖችና ወፈፌ ገዳዮች ሲሸበሩ ነው የከረሙት፡፡
የሙጋቤ መውረድ
አፍሪካ በአመቱ ካስተናገደቻቸው አነጋጋሪና ጉልህ ክስተቶች መካከል፣ ላለፉት 37 አመታት አገራቸውን የገዙት የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ስልጣን መልቀቅ አንዱ ነበር፡፡ ወታደሩ በሙጋቤ ላይ መፈንቅለ መንግስት አደረገ በሚል አስደንጋጭ ዜና የጀመረው የዚምባቡዌ ጉዳይ፤ አገሪቱን ወደ ከፋ የእርስ በእርስ ግጭት ይከታታል ተብሎ ሲገመት፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ፣ ሙጋቤ በሰላማዊ መንገድ ስልጣናቸውን ለተፎካካሪያቸው ምናንጋዋ አስረክበዋል፡፡
ዛሬም የባሪያ ፍንገላ
ሲኤንኤን አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ከወደ ሊቢያ ያሰማው ወሬም ሌላኛው አለምን ያስደነገጠ ጉዳይ ነበር፡፡ የባርነት ዘመን አበቃ ተብሎ ከታወጀ ከረጅም አመታት በኋላ፣ አፍሪካውያን በሊቢያ እንደ ሸቀጥ እየተሸጡና ለባርነት እየተፈነገሉ መሆኑን  የሚያትተው ይህ ዘገባ፤ ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ከሞት ጋር እየታገሉ አሰቃቂውን የውቅያኖስ ጉዞ ለመጋፈጥ አገራቸውን ጥለው ወደ አውሮፓ የስደት ጉዞ የጀመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን፤ ሊቢያ ላይ በጨካኞች መዳፍ ላይ ወድቀው ለባርነት መሸጣቸው አለምን እያነጋገረ አመቱ ተገባድዷል፡፡
ኢየሩሳሌም
አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት፣ አለምን ያስደነገጠ ነገር ከወደ ዋይት ሃውስ ተሰማ…
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ የኢየሩሳሌምን የእስራኤል መዲናነት እውቅና እንደሚሰጡ አስታወቁ፡፡ ይህን ተከትሎ እስራኤል በደስታ ስትፈነድቅ፣ ፍልስጤምና ፍልስጤማውያን ደግሞ በቁጣ ነድደው፣ አደባባይ በመውጣት፣ ትራምፕንና አሜሪካን አወገዙ፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የአለማችን አገራት፣ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ያለውን ለዘመናት የዘለቀ የይገባኛል ውዝግብ፣ ወደ ከፋ ምዕራፍ ያሸጋገረና ተገቢነት የሌለው ነው በማለት በይፋ የትራምፕን ውሳኔ አወገዙት፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የትራምፕን ውሳኔ ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ ለማስተላለፍ አባል አገራቱ ድምጽ እንዲሰጡ አደረገ፡፡ 128 ያህል የአለማችን አገራት ሃሳቡን ደግፈው ድምጻቸውን በመስጠታቸውም፣ የትራምፕ ውሳኔ ውድቅ ተደረገ፡፡


Read 814 times