Saturday, 06 January 2018 12:02

ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የባቡር መስመር እንደምትዘረጋ አስታወቀች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በባቡር መስመር የመገናኘት እቅድ እንዳላትና ከካርቱም ኢትዮጵያ ድንበር የሚደርስ የባቡር መስመር በቅርቡ መገንባት እንደምትጀምር የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከትናንት በስቲያ ከካርቱም ወደ ሌላኛዋ የሱዳን ከተማ ኤልገዚራ የተገነባውን የባቡር መስመር መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ሱዳንን የሚያገናኝ ረጅም የባቡር መስመር ሃገራቸው እንደምትገነባ ተናግረዋል፡፡  
ወደ ኢትዮጵያ የሚገነባው የባቡር መስመር የራሷ ወደብ ለሌላት ኢትዮጵያ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑንና ወደ ደቡብ ሱዳን የሚዘረጋው መስመርም በተለይ ከኬንያና ከኡጋንዳ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰቦች መካከል መቀራረብና የንግድ ቅልጥፍናን ይፈጥራል ብለዋል- ፕሬዚዳንቱ፡፡
አሜሪካ በሱዳን ላይ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ ካነሳች በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ መነቃቃት መጀመሩን የዘገበው ሱዳን ትሪቡን፤ አዳዲስ የባቡር መስመሮችን እየገነባች ከመሆኑ በተጨማሪ አሮጌዎቹንም እየጠገነች ስራ እያስጀመረች መሆኑን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር መስመር ከታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም አንስቶ የመንገደኞች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በ4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የባቡር መስመሩ፣ የመንገደኞችና የጭነት ትራንስፖርት ዋጋም ወጥቶለታል፡፡    
ለእቃ ማመላለሻ ባቡር ለአንድ ቶን በኪሎ ሜትር 1 ብር ከ75 ሳንቲም ሲሆን ለመንገደኞች ማጓጓዣ ከለቡ ተነስቶ ጅቡቲ ለመድረስ በወንበር ተቀምጠው ለሚሄዱ 503 ብር፣ በመኝታ ክፍሎች ተጠቅመው ለሚጓጓዙ እንደየ ደረጃው 671፣922 እና 1,006ብር ዋጋ ተተምኗል፡፡
ከለቡ ወደ ድሬደዋ ለመሄድ በወንበር 308 ብር እንዲሁም በአልጋ ለሚጓዙ እንደ አልጋው ደረጃ 410፣ 564 እና 616 ብር ተተምኗል፡፡ በልዩ መኝታ ክፍሎች ከለቡ ተነስተው ጅቡቲ ለሚጓዙ 1,258 ብር እና 1,341 ብር ዋጋ እንደወጣለት ታውቋል፡፡   

Read 2381 times