Saturday, 06 January 2018 12:12

የገና በዓል ገበያ እንዴት ነው?

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 የበሬ ዋጋ ከዓምናው በእጅጉ አሻቅቧል

   በዘንድሮው የገና በዓል ገበያ የተለያዩ አካባቢዎችን የዳሰስን ሲሆን በተለምዶ ሾላ የሚባለውና ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አጠገብ በሚገኘው ገበያ ዶሮዎች እንደየ መጠናቸው ከ210 ብር እስከ 350 ብር እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡ አይብ በኪሎ 120 ብር፣ ቅቤ ከ180 እስከ 250 ብር የሚሸጥ ሲሆን የሀበሻም የፈረጅም እንቁላል አንዱ በ4 ብር ሂሳብ  ይገኛል፡፡
ከዚሁ ገበያ ከፍ ብሎ በሚገኘው ሰሜን ማዘጋጃ፣በግ ከ2000 እስከ 4200 ብር ባለው ዋጋ  እየተሸጠ ነው፡፡ በሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ በሚገኙ ወፍጮ ቤቶች ያነጋገርናቸው የእህል ነጋዴዎች፣ 1ኛ ደረጃ ማኛ ጤፍ በኪሎ 29 ብር፣ ሰርገኛ 23 ብር እንደሚሸጥና ክክ ምስር በኪሎ 53 ብር፣ ድፍን ምስር 28 ብር እንደሚሸጥ ገልጸውልናል፡፡    ፒያሳ አትክልት ተራ ባደረግነው ቅኝት፣ ሰሞኑን 9 እና 10 ብር ይሸጥ የነበረው ሽንኩርት ለበዓሉ እንደየ ደረጃው ከ12 እስከ 16 ብር እየተሸጠ ሲሆን ነጭ ሽንኩርት በኪሎ ከ45-50 ብር፣ ዝንጅብል 80 ብር፣ ቲማቲም ከ8-10 ብር፣ ቃሪያ በኪሎ 28 ብር ይሸጣል፡፡ በተለያዩ ባልትና ቤቶች ተዘዋውረን እንዳየነው፤ የተፈጨ በርበሬ በኪሎ  140 ብር፣ ኮሮሪማ 120 ብር፣ ዝንጅብል 80 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በመገናኛ ሾላ ገበያ፣ በሬ ከ14ሺ- 20ሺ ብር በሚደርስ ዋጋ የሚገኝ ሲሆን ዶሮ ከ180 ብር እስከ 400 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በዚሁ ገበያ ቀይ ሽንኩርት 16 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 55 ብር፣ ድንች በኪሎ 8 ብር የሚሸጥ ሲሆን የሀበሻ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 25 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
በአቃቂ ቄራ ገበያ የበሬ ዋጋ ከባለፈው ዓመት በእጅጉ ማሻቀቡን ነጋዴዎች የገለጹልን ሲሆን የበግና የፍየል ዋጋ እምብዛም ጭማሪ አላሳየም፡፡ ባለፈው ዓመት ለገና በዓል የበሬ ዋጋ ከ7 ሺህ እስከ 22 ሺህ ብር እንደነበር ያስታወሱት ነጋዴዎች፤ በዘንድሮ በዓል ትንሹ 12 ሺ ብር፣ መካከለኛው 25 ሺ እንዲሁም ትልቁ 38 ሺ ብር ዋጋ ማውጣቱን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የበግ ዋጋ ላይ እምብዛም ለውጥ አለመኖሩን ለማወቅ የቻልን ሲሆን ከ1700 ብር እስከ 3500 ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ የበግም ሆነ የበሬ ዋጋ በበአሉ ዋዜማ (ዛሬ ማለት ነው) ሊያሻቅብ እንደሚችል ነጋዴዎች ነግረውናል፡፡ የበሬ ዋጋ ከወትሮው ለምን አሻቀበ ስንል የጠየቅናቸው ነጋዴዎች፤ በስፋት ከብቶች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ወደ ማደለቢያ በረቶች እየገቡ ተቀልበው ወደ ውጪ ኤክስፖርት እየተደረጉ በመሆኑ በቀላሉ ከገጠር ወደ ከተማ አምጥቶ መሸጥ ባለመቻሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ መጪው ጊዜ የሰርግ ወራት መሆኑም በበሬ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማስከተሉን ነጋዴዎቹ  ጠቁመዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከገና በዓል ጋር የተያያዙ እንደ ገና ዛፍ ያሉትን ዋጋም በተለያዩ መደብሮች የቃኘን ሲሆን ፒያሳ፣ ቦሌ፣ አዲሱ ገበያ እና ሜክሲኮ አካባቢ የገና ዛፍ በ180 ብር የሚገኘውን ያህል 200 ሺ ብር የሚሸጥም አይተናል፡፡ ቀይ የገና የወንዶች ኮፍያ 200 ብር፣ ጫፉ ላይ እና ዙሪያው ነጭ  የገና የሴት ኮፍያ ከ40 እስከ 60 ብር፣ ፖስት ካርዶች ደግሞ እንደ ዓይነታቸው ከ10 እስከ 35 ብር እንደሚሸጡ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
 መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ!!  

Read 5170 times