Saturday, 06 January 2018 12:14

ዶ/ር መረራ ጉዲና የ67 ሺ ብር ካሳ እንዲከፈላቸው ተወሰነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   በአቃቤ ህግ ማስረጃ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጥቷል

    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌን በመተላለፍ የወንጀል ክስ በቀረበባቸው የኦፌኮ ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ አቃቤ ህግ የሰውና ሰነድ እንዲሁም ተጨማሪ የድምፅ ማስረጃዎችን አቅርቦ ያጠናቀቀ ሲሆን በማስረጃው ላይ ብይን ለመስጠት ፍ/ቤቱ ለጥር  24 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባላቸው ክስ ምክንያት ጠበቃቸው ጉዳያቸውን በጊዜ ወደ ፍ/ቤት ባለመውሰዳቸው በጠበቃቸው ላይ ክስ የመሰረቱት ዶ/ር መረራ፤ የ67 ሺህ ብር የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው በፍ/ቤት እንደተወሰነላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡  
አቃቤ ህግ በዶ/ር መረራ ላይ ከቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ በተጨማሪ በሲዲ የተቀረፀ የድምፅ ማስረጃ ማቅረቡን የጠቆሙት ጠበቃቸው አቶ ወንድሙ ኢብሳ፤ የሲዲ ማስረጃው አስቀድሞ ማስረጃ ዝርዝር ውስጥ ያልነበረና በመሃል የመጣ መሆኑን በመግለጽ፣ ማስረጃው እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ጠቅሰው፣ አቃቤ ህግ ቢቃወምም፣ ፍ/ቤቱ የተከሳሹ ጠበቆች ማስረጃውን ተመልክተው ምላሽ መስጠት አለባቸው የሚል ብይን ማስተላለፉን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ጥር 19 ቀን 2010 ዓ.ም ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፤ “ከአፄ ኃይለ ሥላሴ አንስቶ እስካሁን ያለው መንግስት ድረስ ፍትህ ሊገኝ አልቻለም፡፡ እኔ የተከሰስኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለተፈፀመው ስህተት ጥፋቱ የመንግስት ነው ብለው ይቅርታ በጠየቁበት ጉዳይ ነው፤ አሁን በእስር ላይ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዳይ መከሰሳችን “የእምዬን ወደ አብዬ” አይነት ካልሆነ በቀር መከሰሳችን ተገቢ አይደለም፤ መለቀቅ አለብን” ሲሉ መናገራቸውን ከጠበቃቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡  
 ይህ በእንዲህ እንዳለ  ዶ/ር መረራ ጉዲና፤”የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከልክሎኛል፣ የ6 ወር ደሞዝ አልከፈለኝም” ያሉትን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለመክሰስ ያዘጋጁትን ክስ እንዲመሰርቱላቸው የቀጠሯቸው ጠበቃ ደርበው ተመስገን፣ በውሉ መሰረት በጊዜ ክሱን ሳይመሰርቱ ቀርተው ጉዳዩ በይርጋ መታገዱን ተከትሎ በጠበቃው ላይ አቤቱታ ያቀረቡት ዶ/ር መረራ፣ ካሣ እንዲከፈላቸው በፍ/ቤት ተወስኗል፡፡
የጉዳት ካሣውን 67ሺ ብርም  ጠበቃው እንዲከፍሉ መወሰኑን የጠቆሙት አቶ ወንድሙ፤ ጠበቃው 30 ሺ ብር መክፈላቸውንና 37 ሺ ብር እንደሚቀርባቸው ጠቁመዋል፡፡   

Read 6953 times