Saturday, 06 January 2018 12:16

የህዝቡን ነፃነት የሚያረጋግጡ ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ዓለማቀፍ የመብት ተሟጋቾች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት አርቆ አሳቢነት ነው-አፍሪካ ህብረት

    ገዥው ፓርቲ ማዕከላዊ  እስር ቤትን ለመዝጋትና የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት መወሰኑ ሃገሪቱ ለረጅም ዓመታት ስሟ በመጥፎ የሚነሳበትን የሰብአዊ መብት አያያዟን ለማስተካከል መንገድ እንደሚከፍትላት የገለጹት ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት፤የህዝብን ነፃነት የሚያረጋግጡ ተጨማሪ የመብት እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡  
አራቱ የኢህአዴግ መሪ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ በምርመራ ሰበብ ማሰቃያ የሚፈፀምበትን ማዕከላዊ እስር ቤትን ለመዝጋት እንዲሁም የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚል ፖለቲከኞችን ከእስር ለመፍታት መወሰኑን ያደነቁት ሂውማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ በተባለው መሰረትም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
ምን ያህል ፖለቲከኞች እንደሚለቀቁ፣ እነማን እንደሚለቀቁና መቼ እንደሚለቀቁ በግልጽ አለመነገሩን የጠቆመው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ይህም በአፋጣኝ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
“የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ቡድን ለረጅም ዓመታት ማዕከላዊን፣ ታዋቂ ፖለቲከኞችን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾችንና ጋዜጠኞችን ለማሰቃያነት ሲጠቀምበት ነበር” ያለው የመብት ተሟጋች ቡድኑ፤ “እስር ቤቱ ቶርቸርና ኢ-ሰብአዊ የምርመራ ተግባራት ሲፈፀምበት እንደቆየም  ማስረጃ አለኝ” ብሏል፡፡
“ማዕከላዊን ለመዝጋት መወሰኑ መልካም ዜና ነው” ያለው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ “ነገር ግን እስረኞችን ወደ ሌላ አዲስ እስር ቤት አዘዋውሮ፣ ተመሳሳይ የመብት ጥሰት የሚፈፀም ከሆነ ለውጥ የለውም” ብሏል፡፡ መንግስት ለደህንነት አካላት፣ ቶርቸርና የተለያየ የስቃይ ምርመራ መቅረት እንዳለበትና በህግ እንደሚያስጠይቅ በግልፅ ማወጅ አለበት ያለው ተቋሙ፤ በማዕከላዊ እስር ቤት የስቃይ ምርመራ ሲፈፅሙ የነበሩትንም አጣርቶ በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በ10ሺዎች የሚቆጠሩትን ማሰራቸውንና ከ1 ሺ በላይ ተቃዋሚዎችን መግደላቸውን በመግለጫው ያስታወሰው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ይህም ጉዳይ በአውሮፓ ህብረት፣ በአሜሪካ መንግስትና በሌሎች ሃገራት መንግስታት መወገዙን  ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አሁን እወስደዋለሁ ካለው በጎ እርምጃ በተጨማሪ የህዝብን ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማረጋገጥ ሌሎች የሰብአዊ መብት አያያዞችን የሚያሻሽሉ አዎንታዊ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባ ተቋሙ አስታውቋል፡፡
ሰላማዊ ተቃውሞዎችን መፍቀድ፣ አፋኝ ህጎችን ማስወገድ ሊወሰዱ ይገባል ከተባሉ እርምጃዎች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን የዜጎች መረጃ የማግኘት፣ የመናገር፣ የመፃፍ መብት መረጋገጥ እንዲሁም የኢንተርኔትና የማህበራዊ ሚዲያ አፈናዎች መቆም በተጨማሪነት ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎች መሆናቸውን ተቋሙ ጠቁሟል፡፡  
የማሰቃያ ማዕከሉን ለመዝጋት መወሰኑ ለሰብአዊ መብት መረጋገጥ መልካም ምልክት ነው ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ፖለቲከኞችን ከእስር ከመልቀቅ ባሻገር እ.ኤ.አ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ደብዛቸው ስለጠፋ ሰዎች ምርመራ እንዲካሄድና ያሉበት ሁኔታ እንዲገለፅ ጠይቋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ፤ በወቅቱ ሊቀ መንበር ሙሣ ፋኪ መሃመት በኩል ባስተላለፈው መልዕክቱ፤ የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት ገዥው ፓርቲ መወሠኑ ጠቃሚና አዎንታዊ እርምጃ ነው ብሏል፡፡
“የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት አርቆ አሣቢነት ነው” ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ ውሣኔው ሃገሪቱን በማረጋጋትና ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር፣ ዲሞክራሲን ለማስፋት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ህብረቱም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሣኔ እንደሚደግፍ ሙሣ ፋኪ አስታውቀዋል፡፡

Read 3524 times