Print this page
Saturday, 06 January 2018 12:18

የፖለቲከኞች መፈታት፣ የማዕከላዊ መዘጋት የሚበረታታ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

   የፖለቲከኞች መፈታት፣ የማዕከላዊ መዘጋት የሚበረታታ ነው

 “ማዕከላዊ ፈርሶ ሌላ ተመሳሳይ የምርመራ ቢሮ የሚገነባ ከሆነ ለውጥ አያመጣም”      - ተቃዋሚ ፓርቲዎች

    ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታትና ማዕከላዊን ለመዝጋት መወሰኑን በበጎ ዓይን እንደሚመለከቱት የገለፁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮች ለዘለቄታው ለመፍታት ግን መንግስት ተጨማሪ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡  
ኢህአዴግ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች እንደሚፈቱና የማሰቃያ ምርመራ ይካሄድበታል የተባለው ማዕከላዊ እስር ቤት ተዘግቶ ሙዚየም እንደሚሆን መወሰኑን ተከትሎ  መድረክ፣ ኦፌኮ፣ መኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ፤ ጅምሩ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን አፋጣኝና አስተማማኝ ተግባራዊ እርምጃ ያስፈልጋል  ብለዋል፡፡
የኦፌኮ እና የመድረክ ም/ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ፓርቲያቸው ከግማሽ በላይ አመራሮችን በእስር ማጣቱንና ፖለቲካዊ ተግባሩን በአግባቡ ማከናወን ተስኖት መቆየቱን ጠቁመው፣ ”ውሳኔውን በጥርጣሬ ነው የምንመለከተው፤ ተግባራዊ እርምጃውን እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡
“የፖለቲካ አመራሮችና አባላት ብቻ ሳይሆኑ ሽብርተኛ ተብለው የታሰሩ ሁሉ እንዲፈቱ እንፈልጋለን” ያሉት አቶ ሙላቱ፤”ይሄ እርምጃ ሳይወሰድ የተወሰኑ ብቻ ተፈተው፣ ሌሎች በእስር የሚቀሩ ከሆኑ ሙሉ ውጤት አያመጣም” ብለዋል፡፡
ማዕከላዊ መፍረሱን ፓርቲያችን እንደ በጎ እርምጃ ይቀበለዋል ያሉት ም/ሊቀመንበሩ፤”ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ተመሳሳይ የስቃይ ምርመራ ቢሮዎችም ሊዘጉ ይገባል፤ በሀገሪቱም የስቃይ ምርመራ ፈፅሞ መወገድ አለበት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህን ሰቆቃ የሚፈፅሙ አካላትም በህግ እንደሚጠየቁ በአዋጅ መነገር አለበት የሚል አቋም ፓርቲያቸው እንዳለው የጠቆሙት አቶ ሙላቱ፤ ማዕከላዊ ፈርሶ በጎን ሌላ ተመሳሳይ የምርመራ ቢሮ የሚገነባ ከሆነ ግን ለውጥ የለውም ብለዋል፡፡
መድረክ እና ኦፌኮ አሁንም ያለ አግባብ የተገደሉ ዜጎች ቤተሰቦች፣ ተገቢውን ካሣ ማግኘት አለባቸው፣ ሰው የገደሉና ያስገደሉ አካላትም በግልፅ ለፍትህ መቅረብ ይገባቸዋል የሚል ጥብቅ አቋም እንዳላቸው የጠቆሙት ም/ሊቀመንበሩ፤ ቀጣዩ የመንግስት እርምጃም ይህንን ማድረግ ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በግጭት ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ 7መቶ ሺ ያህል ዜጎችም ወደ ቀዬአቸው ተመልሰውና ድጋፍ ተደርጎላቸው ኑሯቸውን እንዲጀምሩ፣ሙሉ ዋስትና ማግኘት አለባቸው ብለዋል - ም/ሊቀመንበሩ።
21 ያህል አመራሮቹና አባላቱ እንደታሰሩበት የገለጸው መኢአድ በበኩሉ፤ በገዥው ፓርቲ ውሳኔ ደስተኛ መሆኑን ነገር ግን ተግባራዊነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳለው አስታውቋል፡፡
“ወደ ድርድሩ የገባነው በዋናነት የፖለቲካ እስረኞችን ለማስፈታት ነው” ያሉት የመኢአድ አመራሮች፤ ጉዳዩ በሂደት ላይ እያለ ገዥው ፓርቲ ውሳኔውን ማሳለፉ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ታሳሪዎችን  መፍታት ብቻውን ግን በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ ለውጥ አያመጣም ይላል - መኢአድ፡፡
የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን፤ መንግስት ሀገራዊ መግባባት መፍጠር የሚችለው እስረኞችን ከመፍታት ባሻገር በሀገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ፓርቲዎች ጋር ግልፅ ውይይት ሲያደርግ ነው፤ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት አለበት ብለዋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ መመለስና የሀገሪቱን ህልውና ማስጠበቅ ያዳግታል  ያሉት አቶ አዳነ፤ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል፣ የህግ የበላይነት፣ የዳኝነት ነፃነትና የሲቪክ ተቋማት ነፃነት መረጋገጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ መኢአድ፤ ገዥው ፓርቲ ስልጣንን ማጋራት አለበት የሚል አቋም እንዳለውም ዋና ጸሃፊው ተናግረዋል፡፡  
በርካታ አባሎቹን በእስር ማጣቱን ያወሳው ሰማያዊ ፓርቲም፤ እስረኞች ይፈታሉ መባሉ ተስፋ ሰጪ ነው ብሏል፡፡ “እርምጃው ጥሩ ጅምር ነው” ያሉት የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፤ “ተግባራዊነቱን እንከተላለን” ብለዋል፡፡
“ፖለቲከኞች መፈታታቸው የሃገሪቱ ችግሮች ማብቂያ አይሆንም” ያሉት የፓርቲው ሊቀ መንበር፤ በቀጣይም በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ማስተካከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እውነተኛ ውይይትና ድርድር መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ፣ የፍ/ቤቶች አሰራር፣ የሚዲያ ምህዳሩ --- ተስተካክሎ ነፃ፣ ተዓማኒና ተቀባይነት ያለው ምርጫ የሚደረግበት ሁኔታን ለመፍጠር ገዥው ፓርቲ ቁርጠኛ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባም አቶ የሸዋስ ተናግረዋል፡፡   
ማዕከላዊ የምርመራ ማዕከልን በታሰሩበት አጋጣሚ መመልከታቸውን የጠቆሙት የፓርቲው ሊቀ መንበር፤ ቦታው እጅግ አሰቃቂ ከመሆኑ አንፃር መዝጋቱ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በዚያው ልክ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ተመሳሳይ የምርመራ ማዕከላት ተዘግተው፣ የህግ ምርመራዎች ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ መካሄድ እንዳለባቸውና የስቃይ ምርመራ ከሃገሪቱ መወገድ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ (ኦብኮ) በበኩሉ፤ የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ውሳኔዎችን በበጎ ጅምርነት እንደሚመለከተው ጠቁሞ፣ በተለይ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መወሰኑ ድርጅቱ ለለውጥ ቁርጠኝነት እንዳለው የሚያስገነዝብ ነው  ብሏል፡፡
የፖለቲካ እስረኞች የመፈታት ጉዳይ በተግባር እንዲተረጎም የጠየቀው ኦብኮ፤በቀጣይም የሀገሪቱን የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚያሻሽሉ እንዲሁም የምርጫ ስርአቱን ፍትሃዊ ሊያደርጉ የሚችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቋል፡፡
የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፤የፖለቲካ መፍትሄ ጉዳይ በህዝቡ ሲጠየቅ የነበረ በመሆኑ ውሳኔው በበጎ የሚታይ ነው፣ ነገር ግን ፖለቲከኞችን ብቻ ፈትቶ፣ ሌሎች የለውጥ እርምጃዎች ካልተወሰዱ የተለየ ውጤት አያመጣም ብለዋል፡፡ “በአሸባሪነት ከተፈረጁ ድርጅቶችም ጋርም ቢሆን ፖለቲካዊ ድርድር ማካሄድ ያስፈልጋል” ሲሉም አክለዋል - አቶ ግርማ፡፡
ማዕከላዊ መዘጋቱ ቢያንስ የስቃይ ምርመራ የሚካሄድባቸው ቦታዎች እንዲቀንሱ ያደርጋል ያሉት አቶ ግርማ፤ ይህም ቢሆን ሊደገፍ የሚገባው እርምጃ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ገዥው ፓርቲ የወሰደው እርምጃ ለለውጥ የመዘጋጀት ምልክት ነው እንጂ በራሱ ለውጥ አይደለም ያሉት አቶ ግርማ፤ በቀጣይ ደረጃ በደረጃ ፖለቲካዊ ለውጦች መምጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
“የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች በርካታና ውስብስብ ናቸው” ያሉት የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶ/ር ንጋት አስፋው በበኩላቸው፤ “እስረኞች ይፈታሉ፣ ማዕከላዊ ይዘጋል፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ማሻሻያ ይደረጋል መባሉ የለውጥ ምልክት ነው” ብለዋል፡፡
በህዝቡ በተደረገው ግፊትና በግንባሩ ውስጠ ግምገማ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ መወሰኑ መልካም ነው ያሉት ዶ/ር ንጋት፤ በቀጣይም ብሄራዊ እርቀ ሠላም መካሄድ አለበት፣ ይሄም ተቃዋሚዎች ላለፉት 25 ዓመታት ሲጠይቁ የኖሩት ነው ብለዋል፡፡ የፀረ ሽብር ህጉም መሰረዝ አለበት ያሉት ዶ/ር ንጋት፤ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሃገሩ የሚገፋበት ሳይሆን ዘብ መቆም የሚችልበት መግባባት መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡
የተለያዩ አካላት የፖለቲካ ሰዎችን ከእስር መፈታት ሲጠይቁ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ ክቡር ገና ደግሞ “እርምጃው ተስፋ ሰጪ ነው፣ በቀጣይም ሰዎቹ የታሰሩበት ምክንያት ዜጎችን ለእስር የማይዳርግበት ሁኔታ መፈጠር አለበት” ብለዋል፡፡
በሃገሪቱ ጉዳይ ከኢህአዴግ ውጪ ሌሎች የሃገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች እንዳሉ መታሰብ አለበት ያሉት አቶ ክቡር፤ በዚህ በኩል ሁሉን አሣታፊ የሆነ ውይይት መካሄድ አለበት፤ወጣቶችም የኢኮኖሚና የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት ዕድል ሊፈጠር ይገባል ብለዋል፡፡
የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት በሀገሪቱ ለሚጠበቀው የፖለቲካ ለውጥና መሻሻል አጋዥ ይሆናል ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ የፖለቲካ እስረኞች ሲባል ግን ታዋቂ የሆኑትን ብቻ ሳይሆን በመቃወማቸው የታሰሩ ሁሉ መፈታት አለባቸው ብለዋል፡፡ በወልቃይት ጉዳይ፣ በኢሬቻ በአል ላይ ካጋጠመ ችግር ጋር ተያይዞ የታሰሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያስታወሱት ዶ/ር በድሉ፤ ከእስር የመፈታቱ ጉዳይ እነዚህንም ማካተት አለበት ብለዋል፡፡
ዛሬም በየፍርድ ቤቱ በምርመራ መሰቃየታቸውን የሚናገሩ እስረኞች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር በድሉ፤ “ማዕከላዊ በደርግ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዘመንም የማሰቃያ ማዕከል ነበር፣ ያ ባይሆን ኖሮ በ1983 ዓ.ም ይዘጋ ነበር” ብለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ መንግስት በትክክል የተፈፀመውን ገልፆ፣ በድጋሚ እንዳያጋጥም የእርምት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል ያሉት ምሁሩ፤ “ትልቁ ቁምነገር ማዕከላዊን መዝጋት ወይም ቦታ መቀየር ሳይሆን የስቃይ ምርመራን ማስቆም ነው” ብለዋል፡፡

Read 5526 times