Saturday, 06 January 2018 12:19

‹‹ይመጣል እያሉኝ--የት ደርሷል ስላቸው?!››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

 “--የአመራር ቀውስ ም ን ዓይነት ችግር ሊ ያመጣ እንደሚችል በከፋ መልኩ ተምረናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመሪዎቹ የበለጠ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት እንዳለው ለመመስከር የሚያስችል ተጨባጭ ምሣሌ አግኝተናል፡፡ ሆኖም በኢህአዴግ አመራር፣ ተቃዋሚዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ወዳጆቹም አመኔታ አጥተዋል፡፡--”
 
   ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ስነሳ፤ በጭንቅላቴ ደጋግሞ እየተመላለሰ ያስቸግረኝ የነበረ አንድ ሐረግ ነበረ፡፡ የመምህሬ የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ አንድ ግጥም አንድ ሐረግ ነው፡፡ ‹‹ይመጣል እያሉኝ የደስታ ዘመን…›› የሚል ስንኝ ችክ ብሎ ያዘኝ፡፡ ግጥሙን ለማንበብ ከመደርደሪያዬ ያገኘሁትን አንድ የዶ/ር ፈቃደ የግጥም መድበል አነሳሁ፡፡ አስቸጋሪውን ግጥም ፈልጌ አጣሁት፡፡ እንዲያም ሆኖ ጭንቅላቴ፤ ‹‹ይመጣል እያሉኝ….›› ከማለት አላረፈም፡፡
ከአነሳሁት የግጥም መድበል የፈለግሁትን ግጥም ሳጣው፤ ምናልባት ግጥሙን ከጓደኞቼ ጋር ወደ እርሱ ቢሮ በሄድንበት አንድ አጋጣሚ አንብቦልን ይሆናል ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ዶ/ር ፈቃደ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ቢሮው ስንሄድ፤ (በወቅቱ ገና ያልታተሙ) ግጥሞቹን ያነብልን ነበር፡፡ በነገራችን ላይ፣ ዶ/ር ፈቃደ ጥሩ መምህር ነበር፡፡ እኔ ግን በአደባባይ አመስግኜው አላውቅም፡፡ ደበበ ሰይፉም ሆነ እርሱ ባልተለመደ ሁኔታ ሐሳባችንን በነጻነት እንድንገልጽ መንገድ ይሰጡን ነበር፡፡ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ዶ/ር ፈቃደ በአስተማሪነቱ ዘመን ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ ወዲህ አንድ - ሦስት በሚሆኑ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች እንዳጋጣሚ በተገናኘን ጊዜ፤ ስለ ራሴ በጎ ነገር እንዳስብ የሚያደርጉ እና እንድተጋ የሚያደርግ አስተያየቶችን እንደዋዛ ጣል ያደርግልኝ ነበር፡፡ ‹‹ጥሩ ሄደሃል›› ዓይነት አስተያየት ወርወር አድርጎልኛል፡፡ በጊዜው ከቁም ነገር ባልቆጥረውም፤ አሁን ‹‹ይመጣል እያሉኝ›› በሚለው ሐረግ ሰበብ ስለ እርሱ ሳስብ፤ ቁም ነገር ሆኖ ታየኝ፡፡ ይህን ጉዳይ በዚሁ ትቼ ወደ መነሻ ነገሬ ልመለስ፡፡
እንዳልኩት ‹‹ይመጣል እያሉኝ›› የሚለውን ግጥም ማስታወስ አልቻልኩም፡፡ ሆኖም የዚህ ጽሑፌ ጭብጥ ከእርሱ ግጥም ጋር ተጣበቀ፡፡ ሓሳቤ በእርሱ የግጥም ሐሳብ ላይ እንደ ‹‹ተገድራ›› በቅሎ ዝም አለ፡፡ ተገድራ፤ እንደ ዋርካ እና ወይራ በመሳሰሉ ዛፎች ላይ በጥገኝነት እጅብ ብሎ የሚበቅል የዕፀዋት ዓይነት ነው፡፡ የእኔም ሐሳብ እንዲያ ሆነ፡፡ ለፍለጋ ሰነፍኩ፡፡ ለመጻፍ ቸኮልኩ፡፡ ስለዚህ የተዛባም ቢሆን የእርሱን ግጥም እጠቅሳለሁ፡፡ ግጥሙን በጣም አዛብቸው ከሆነ፤ መምህሬን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ግን እንዲህ የሚል መሰለኝ፤
ይመጣል እያሉኝ፣ የደስታ ጊዜ፣ የሰላም ዘመን፤
የት ደርሷል ስላቸው፤
ይኸው ድርሷል ሲሉኝ፤
ናፍቆቱ፣ ናፍቆቱ፣ ናፍቆቱ ገደለኝ፡፡
ይመጣል እያሉኝ፣ አስቸጋሪ ጊዜ፣ የከፋ ዘመን፤
የት ደርሷል ስላቸው፤
ይኸው ደርሷል ሲሉኝ፤
ሥጋቱ፣ ሥጋቱ፣ ሥጋቱ ገደለኝ፡፡
ግጥሙ ናፍቆት እና ሥጋትን ትይዩ አድርጎ የሚጫወት ግጥም ነው፡፡ የሐገራችን ወቅታዊ ሁኔታም በዚሁ ግጥም ሊተረጎም የሚችል ነገር አለው፡፡ ብዙ ጊዜ በልምድና ንባብ የደረጀ አስተያየታቸው የሚያሸንፈኝ ሦስት ጓደኞቼን ስለ ሐገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ስጠይቃቸው ሦስት ተቃራኒ አስተያየቶችን ሰጡኝ፡፡
ሥራ ብዙ ለሆነው ለአንደኛው ጓደኛዬ፣ በሞባይል የአጭር ጽሑፍ መልዕክት ላኩለት -በእንግሊዝኛ፡፡ ‹‹Is it 1966 or 1997›› አልኩት። ጽሑፉ በእንግሊዝኛ ሆኖ፤ ዘመኑ ‹‹በአማርኛ›› በመሆኑ፤ ለማለት የፈለግኩት ነገር ግራ ሊያጋባው ይችላል የሚል ሥጋት ነበረኝ፡፡ ሆኖም ከዚያ የረዘመ ነገር በማብራራት ለመጻፍ ሰነፍኩ፡፡ መልዕክቱን ከላኩለት ምናልባት ከሦስት ወይም ከአራት ሰዓት በኋላ ደወለልኝ፡፡ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ገባ፡፡ እንዲህ አለኝ፤ ‹‹1966 አይደለም፡፡ 1997ም አይደለም፡፡ ይህ 2010 ነው›› አለኝ፡፡ እውነቱን ነው የምንገኝበት ዘመን 2010 ነው፡፡ እርሱም አሁን የምንገኘው የራሱ የሆነ ባህርይ ባለው ፖለቲካ ንቅናቄ ውስጥ እንጂ ከ66 እና ከ97 ጋር የሚመሳሰል አይደለም ማለቱ ነው፡፡ እርሱ ሁኔታችን አሳሳቢ መሆኑን ቢቀበልም፤ መውጫ የሌለው ሐገር የሚያፈርስ ችግር ሆኖ አልታየውም፡፡ በእተያየቱ መጨረሻ፤ ‹‹ህዝቡ ለኢህአዴግ ብዙ ትንፋሽ መውሰጃ ጊዜ ቢሰጠውም እርሱ አልተጠቀመበትም፡፡ ሆኖም አሁንም ሊመለስ ይችላል፡፡ ነገሩ በጣም ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም አንተ ባሰብከው መጠን ግን ተስፋ አስቆራጭ አይደለም›› አለኝ፡፡  
ደግሞ በሌላ ቀን ለሁለተኛው ጓደኛዬ ደወልኩለት፡፡ ለዚህኛው ጓደኛዬ ስደውልለት ሥጋትና ሽብር የገነነበት ስሜት ውስጥ ነበርኩ። ይኸኛው ጓደኛዬ በአጠቃላይ በሚታየው ነገር ከመጨነቅ ራቅ ብሎ ተስፋ የማጣትና የመሰላቸት ሁኔታ ውስጥ ነበር፡፡ በአጭሩ እንዲህ አለኝ፤ ‹‹አሁን የምንሰማቸውን መጥፎ ዜናዎች እየሰማን አንድ ሁለት ዓመት ልንገፋ እንችላለን፡፡ እንጂ እንደምትሰጋው የየመንና የሶርያን ከመሰለ ሁኔታ ውስጥ በቶሎ አንደርስም›› አለኝ፡፡
የሐገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ግጭቶችን ወደ ክልል ደረጃ ያወረዳቸው በመሆኑ ለረጅም ጊዜ በአሁኑ ሁኔታ የመንገታት ዕድል አለን ያለኝ ጓደኛዬ፤ የሰላምና የደህንነት ሥጋቱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እየተጠናከረና እየተራዘመ ሲመጣ፣ ችግሮቹ በድምር ሊባባሱ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ያንን አያሳየኝ አለኝ፡፡
የሦስተኛው ጓደኛዬ አስተያየት ከሁለቱ ይለያል፡፡ የእርሱ አስተያየት ከእኔ ሥጋት የቀረበ ቅኝት እና ይዘት ያለው ነው፡፡ ግን አስተያየቱ በጣም ከረር ያለ ነው፡፡ እኔ በእርሱ መጠን ድርስ አደጋ ላይ መሆናችንን ከመቀበል አልደረስኩም። የእርሱ አስተያየት፤ ‹‹ነገሩ የ1966ቱን አብዮት ጎዳና የተከተለ ነው፡፡ ችግሩ ብዙ መልክ እያወጣ ለመረዳትና ለማስተካከል አስቸጋሪ እየሆነ እንዲሁም ፍፁም እየተበታተነ መጥቷል፡፡ ብዙዎቹ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ወደ ማይቀር ምዕራፍ ሲያመሩ፤ አሁን የምናየውን ዓይነት መልክ ይይዛሉ፡፡ በኔ አስተያየት አሁን የቀረን ጊዜ የታሪክን የመጨረሻ ገቢር ለመመልከትና መጋረጃውን ለመዝጋት የሚሆን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በምንሰራው ሥራ የታሪክን ጉዞ መቀየር ከምንችልበት ምዕራፍ አልፈን ሄደናል። አሁን የሚሆነውን ነገር ዝም ብሎ ከመመልከትና ፍዝ የታሪክ ታዛቢ ከመሆን በቀር ሌላ ድርሻ የለንም›› አለኝ፡፡
ደስ አይልም፡፡ ግን ከዓመት በፊት ስናወጋ፤ የሐገራችን ሁኔታ የአርማጌዶን ትዕይንት መስሎ ሲታየኝ፤ ተስፋ ሲርቀኝ ተስፋ የሚያበድረኝ ሰው ነበር፡፡ ታሪክ እና ተጨባጭ የህዝባችንን ትስስር እያነሳ ተስፋ የሚለግሰኝ፤ በጠፍ ጨረቃ አቅጣጫና ብርሃን የሚታየው ሰው ነበር፡፡ ብርድ ብርድ በሚል ሁኔታ ውስጥ ሙቀት ለመፍጠር የሚችሉ አስተያየቶች ያሉት ሰው ነበር፡፡ አሁን ተቀየረ፡፡
እኔ ቀደም ሲል፤ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ የሽፍትነት ወይም ለጥ ብሎ የመገዛት ሐሳብ እንጂ የ‹ማግናካርታ› መንፈስ የለውም፡፡ የለውጥ ማዕበል ሲመታው፤ ለውጡን በሚያግዝ ስሜት ውስጥ ሆኖ በዝምታ ፍጻሜውን ይከታተላል እንጂ፤ ለውጡ እርሱ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እንዲሄድ ግልጽና ስውር ተጽእኖ በማሳደር ታሪክን ማረቅ አይችልም። ስለዚህ የለውጥ ዕድሎች አስተዋይና በሳል የሆነ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች ሳይሆን፤ ደፋርና ጨካኝ በሆኑ ሰዎች እጅ የሚገቡበት ሁኔታ የተመቻቸ ሆኖ ይታየኛል›› ስለው  ይሞግተኝ ነበር፡፡
እርሱ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እምነት አለው። የአሁኑ አስተያየቱ የተለየ ሆነብኝ፡፡ ለሰዎች አስተያየት ደንታ የሌለው ታሪክ፤ ዝቋላን እሚያክል ጫማ አድርጎ ሲረመርመን ታየኝ፡፡ በኃይል የታጀበ ህዝባዊ ተቃውሞ በተካሄደበት ጎዳና ታየኝ፡፡ ነገሩን እንደ ቀደመው ለማድረግ ባይቻልም፤ እንዲያው ብቻ በአመጹ የተመሳቀሉ ነገሮችን ለመሰብሰብና የተጎዱ ንብረቶችን ለመጠገን የሚሞክር ህዝብ ታየኝ፡፡
ይህን አስተያየቱን አልወደድኩትም፡፡ ‹‹እኔ በሰው ልጅ ዘላለማዊነት ወይም ህያውነት አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹ አማራጮች ሁሉ ደስ አይሉኝም›› ካለው ሰውዬ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ፤ ለወትሮው በተስፋ የሚሞላኝን የዚህን ጓደኛዬን አስተያየት ላለመቀበል በውስጤ ታገልኩ።   
በዚህ ሁሉ መካከል፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ‹‹የጥልቅ ተሐድሶ ንቅናቄው ባስቀመጥነው አቅጣጫ እየተጓዘ ነው›› እያለ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ኢህአዴግ ‹‹የጥልቅ ተሐድሶ ዘመን ይመጣል›› እያለ በናፍቆት ሲገድለን ከረመ፡፡ በሌላ በኩል፤ በሐገሪቱ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ፤ የእኔም ሆነ የጓደኞቼ ልምድና ትንታኔ ‹‹የከፋ ዘመን ይመጣል›› እያለ በሥጋት አከረመን፡፡
‹‹ነቢይ ሁለት ጊዜ ይሞታል›› ይላሉ -(አንድም አስቀድሞ የሚመጣውን አይቶ በሐሳቡ፤ አንድም የቁርጡ ቀን ሲመጣ በእውኑ)፡፡ አንደኛውን ሞት በበቂ መጠን የሞትን ይመስለኛል፡፡ እኔም እንደ መጀመሪያው ጓደኛዬ የስጋት ጉም የለበሰ ተስፋ ማየት እንኳን ተስኖኝ፤ እንደ ሁለተኛው ወዳጄ አሁን በሚታየው ሁኔታ ለረጅም ጊዜ የመቆየት አቅም አንሶኝ፤ እንደ ሦስተኛው ወንድሜ ‹‹ጀንትልማን ሱሳይድ›› የሚባል ሁኔታ ውስጥ መሆናችንን መቀበል አቅቶኝ፤ የታሪክን ጨካኝና ደንታ ቢስ ፍርድ ዝም ብሎ ለመመልከት የሚያስችል ጠንካራ መንፈስ ለመያዝ ስታገል ቆየሁ፡፡
እንግዲህ በዚህ መሐል ነበር፤ የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ‹‹ታሪካዊ ውሳኔ ለመወሰን›› የሚያስችል ጉባዔ የማድረጉ ዜና የታወጀው፡፡ ‹‹ሥጋት›› እና ‹‹ናፍቆት›› ኃይላቸውን አሰባስበው እንደ ሐገር ጨምድደው - አጨማደው ይዘውን ስለቆዩ፤ ሁላችንም ዜናውን በልዩ ስሜት ተቀበልነው፡፡
ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለ17 ቀናት ውይይት ካደረገ በኋላ፤ በመጨረሻ ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት የቆዩት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ ውሳኔ ይፋ ሆነ፡፡ በመቀጠል የአራቱ እህትማማች ድርጅቶች ሊቃነመናብርት በአንድነት መግለጫ ሰጡ፡፡ በመግለጫው ይፋ ካደረጉት የመንግስት ውሳኔዎች መካከል አንዱ፤ ከደርግ ዘመን ጀምሮ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት የያዙ ሰዎችና ሌሎች ዜጎች ማጎሪያና የግፍ ምርመራ ይደረግበት የነበረው እና ‹‹ማዕከላዊ›› በሚል የሚታወቀው እስር ቤት እንዲዘጋ የመወሰኑ ጉዳይ ነበር፡፡ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት የታሰሩ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች፣ አባላትና ሌሎች ሰዎች ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሠረት በምህረት ከእስር እንደሚፈቱ አስታወቁን፡፡ ይህ የተስፋ ድምጽ ነው፡፡  
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፉት አስራ ሰባት ቀናት ባደረገው ግምገማ፣ በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች በተለይ ደግሞ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር እየሰደደ እንደመጣ፤ ….ዴሞክራሲ እየጠበበ አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙነትና አካሄድ የተለመደ ስልት ወደ መሆን እንደተሸጋገረ፤… ይህን የመሰለው በጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መርህ አልባ ግንኙነት ኢህአዴግና አባል ድርጀቶቹን የማዳከም ውጤት እንዳስከተለ፤ … ከዚያም አልፎ ዴሞክራሲው መስፋትና መጠናከር ሲገባው በተለያዩ መንገዶች እየጠበበ የመጣበት አዝማሚያም እንደተስተዋለ፤ …ህገ መንግስታዊ ስርአቱ ልዩነቶች በዴሞክራሲያዊ፣ ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲስተናገዱ በቂና አስተማማኝ እድል ከፍቶ እያለ፣ አመራሩ ዴሞክራሲውን የማስፋት ግዴታውን ባለመወጣቱ ችግሮችና ልዩነቶች በግጭት መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ እንደተፈጠረ፤ …ይህም የሀገሪቱን ለሰላም እንዳወከ በመግለጽ፤ ሥራ አስፈጻሚው የሐሳብ እና የድርጊት አንድነት ፈጥሮ መውጣቱንና ችግሩን በፍጥነት ለማስተካከል የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
በአሁኑ ወቅት ናፍቆትና ሥጋት ቦታቸውን እንደያዙ ቢሆንም የሆነ ተስፋ የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ የዜጎች ሞት፣ የአካል ጉዳትና መፈናቀል ይወገድ ይሆናል የሚል ተስፋ አሳድረናል፡፡ የአመራር ቀውስ ምን ዓይነት ችግር ሊያመጣ እንደሚችል በከፋ መልኩ ተምረናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመሪዎቹ የበለጠ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት እንዳለው ለመመስከር የሚያስችል ተጨባጭ ምሣሌ አግኝተናል፡፡ ሆኖም በኢህአዴግ አመራር፣ ተቃዋሚዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ወዳጆቹም አመኔታ አጥተዋል፡፡ ስለዚህ ‹‹ደጉ ዘመን ይመጣል›› እየተባለ በናፍቆትና በሥጋት ሲንገላታ የቆየው ህዝብ፤ በሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ተግባራዊነት ላይ ጥርጣሬ መያዙ የሚጠረጠር አይደለም፡፡ እንኳን ህዝቡ ከግንባሩ አባል ድርጅት ሊቃነመናብርትም መካከል አንዳንዶቹ ‹‹ካላየሁ አላምንም›› በሚል የጥርጣሬ መንፈስ ሲናገሩ አዳምጠናል፡፡ ይህ ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አመራሮቹ የመጨረሻ ምሽግ ውስጥ ሆነው እየተናገሩ መሆናቸውን አውቀውታል። ይህን መሠረት አድርገን በውሳኔአቸው ቁርጠኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመገመት እንችላለን፡፡      
ግን ነገሩ በዚህ አያበቃም፡፡ በሥራ አስፈጻሚው ደረጃ የሚታየው ቁርጠኝነት ፍሬ እንዲያፈራ፤ የአራቱ የግንባሩ አባላት ድርጅቶች አባላት ተመሳሳይ እምነት ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ወደ ብሔራዊ ድርጅቶቻቸው ሄደው፤ ከአባላት ጋር ተነጋግረው የሐሳብ አንድነት የመፍጠር ከባድ ሥራ አለባቸው፡፡ በእስካሁኑ ሂደት በነበረው የመጠራጠር ስሜት የተነሳ፤ በየብሔራዊ ድርጅቶቹ የሚገኙት በርካታ አባላት የጎሸ ስሜት ይዘው ቆይተዋል። በግልጽ በአደባባይ ሲቃሩኑና አንዳንዴም ሲዘላለፉ አይተናል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው ‹‹መርህ የለሽ›› ሲል በገለጸው ጉድኝት ሳቢያ ጠንክሮ የወጣ የአሰላለፍ ተቃርኖ አለ፡፡ ተቃርኖው ገኖ እና ገንግኖ ለመውጣት የሚያስችል የመጎልመሻ ጊዜ አግኝቶ ነበር፡፡ በመሆኑም፤ ከሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች ፊት የተደቀነው ከባድ ሥራ በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ አባላት ጋር ውይይት አድርጎ፣ በአንድ ሣንባ ለመተንፈስ የሚያበቃ ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ ነው፡፡
አሁን ከአባላት ጋር የሚደረጉት ውይይቶች፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ከሚደረግ ውይይት በላይ ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም መፈራቀቅ፣ መጠራጠርና አለመተማመን ሰፍነው በቆዩባቸው ጊዜያት የተለያየ አመለካከት ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ ይህን አመለካከት ሽሮ፣ ፍሬ ያለው የዓላማ እና የድርጊት አንድነት ለመፍጠር የሚቻለው፤ በአባላት ደረጃ የሐሳብና የድርጊት አንድነት መፍጠር ሲቻል ነው፡፡  ስለዚህ ፈተናው ገና ነው፡፡
በጥቅሉ፤ የሐሳብና የድርጊት አንድነት ከመፍጠር አኳያ ድርጅቱ ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው የሚያመለክት ጉዳይ አይቻለሁ፡፡ ይህን ያየሁት ከብሔራዊ ድርጅቶቹ ሊቃነመናብርት መግለጫው ነው፡፡ አመራሮቹ ‹‹በድርጅት አጥር ሳንገደብ ችግሩን ለማየት ሞክረናል፡፡ በነጻነት እና ያለ ገደብ መሠረታዊ ለውጥ እናምጣ ብለን ተግተናል። ለየብቻችን የምናመጣው ለውጥ የለም›› ሲሉ ሰምተናል፡፡ እንደኔ አስተያየት፤ ኢህአዴግ በዚህ ረገድ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከቆረጠ፣ ራሱን ወደ ህብረ ብሔራዊ ድርጀት መቀየር ይኖርበታል፡፡
ቀደም ሲል፤ የትግል ስልት ሆኖ በመታየቱ፣ ድርጅቶቹ ብሔራዊ አደረጃጀት ይዘው ከመጡ በኋላ ትግሉ ወደ ሌላ ምዕራፍ ሲሸጋገር፣ በ1982 ዓ.ም ብሔራዊ ድርጅቶች ኢህአዴግ በሚል ግንባር ተደራጅተዋል፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ህብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ፕሮግራም ይዞ ሳለ የቀደመውን ብሔራዊ አደረጃጀት እንደያዘ አስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡ ብሔራዊ ድርጅቶቹ የተለየ ፕሮግራም ሳይኖራቸው፤ ‹‹የድርጅት አጥር›› በሚፈጥር  ግንባር ታቅፈው ጉዞ ቀጥለዋል፡፡
ለምሣሌ፤ አዋጪ የትግል ስልት በመሆኑ በብሔር ተደራጅቶ ሲታገል የቆየው ህወሓት፤ ህብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ፕሮግራም ሲይዝ፤ ትግሉን በክልል የተወሰነ አድርገው ይመለከቱ የነበሩ በርካታ አባላቶቹ  ከድርጅቱ መለየታቸውን ታሪካቸው ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ህወሓት የትግል ስልት አድርጎ ይዞት የነበረውን ብሔራዊ አደረጃጀት እንደያዘ፤ የፖለቲካ ፕሮግራሙን ህብረ ብሔራዊ በማድረግ ግንባር ፈጥሮ መጓዙን ቀጠለ፡፡ በተቃራኒው ኢህዴን ወደ ብአዴን ስያሜውን ለወጠ፡፡ አሁን ይህ አደረጃጀት ‹‹የድርጅት አጥር›› ገንብቶ፣ ችግር ሲፈጥር ተመለከትን፡፡
ሆኖም ከትናንት ወዲያ መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች፤ ኢህአዴግ እንደ ግንባር መቀጠሉ ‹‹የድርጅት አጥር›› ከመፍጠር በቀር ትርጉም የለሽ መሆኑን ለመናገር አልደፈሩም፡፡ በዚህ ሁኔታ የሐሳብ፣ የዓላማ እና የድርጊት አንድነት ለመፍጠር አስቸጋሪ ይሆናል። ኢህአዴግ አደረጃጀቱን ለመፈተሽ አሁን የታየው ሁኔታ በቂ ነው፡፡ ሌላ የጥልቅ ተሐድሶ ዕድል እንደ ሌለው እና ‹‹ተሐድሶ›› ቢልም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነገሩን የአሰፋ እናት ታሪክ የተለየ ነገር እንደማይገጥመው የተረዳ ይመስለኛል፡፡ የኢህአዴግም ‹‹ይመጣል እያሉኝ›› የሚለው ግጥም ከዚህ በላይ ሊነበብ የሚችል አይደለም፡፡

Read 1267 times