Saturday, 06 January 2018 12:31

ኢህአዴግ ዋናዎቹን ችግሮች ባይፈታም፣ የስልጣን ሽኩቻዎቹን አጠናቀቀ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

 .ይመስላል - ለጥፋት የሚዳርግ ሌላ የሽኩቻ ዙር፣ መቼ እንደሚያመጣ ባይታወቅም።
   .ለጊዜው ግን ጥሩ ነው - ፋታ የለሽ አጥፊ ቀውስ ረግቦ ትንሽ እፎይታ ብናገኝበት!
   .ከህይወት ጥፋት፣ ከአካል ጉዳትና ከኑሮ ጉስቁልና፣ ከእስርና ከመጠፋፋትም ትንሽ ፋታ!  
   .ነገር ግን፣ ዋና ዋናዎቹ የቀውስ ስረ መንስኤዎች በቅጡ ታይተው መፍትሄ አላገኙም።
   .መሰረታዊ የስልጣኔ ሃሳቦችና ዋናዎቹ የፖለቲካ ነፃነት (የግል ነፃነት) ጥያቄዎች አልተነሱም።
   .እየተባባሰ የሚሄደውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመፍታት፣ የነፃ ገበያ ስርዓትን ማስፋፋትም አልታሰበም።
   .ሰው፣ እንደየአቅሙ በራሱ ጥረት የራሱን ሕይወት የሚያሻሽልበት ነው - የነፃ ገበያ (የካፒታሊዝም) ስርዓት።
   .ይሄ ፍትሃዊ ካልሆነ የትኛው ይሆን ፍትሃዊ? ሙስናና የሃብት ብክነት የበረከተው መንግስት ቢዝነስ ሲገባ አይደለም?
   .በዚያ ላይ፣ አስፈሪውንና አጥፊውን የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ የሚያስተካክል መፍትሄስ የታለ?

    “የጠበበውን የዲሞክራሲ ሜዳ ማስፋት”፣… “የውይይት ሃሳቦችን ማንሸራሸርና መገማገም” እና “ሃሳቦችን በማፋጨት መከራከርና መተጋገል”… በእንደዚህ አይነት አባባሎች፣… ወይም በሌጣው፣ “ዲሞክራሲ፣ ውይይት፣”… እያልን በቁንፅል ብናራግብ፣ በቂ አይደለም። የሚዘልቅ መልካም ለውጥን እንጂ፣ ለጊዜው እያጨበጨብን የምናራግበው፣ ከዚያም እያወዛገበ የሚያቃውስ፣ እንደገና እንደአዲስ እያጨበጨቡ ማራገብማ ምን ዋጋ አለው? ካሁን በፊት በተደጋጋሚ ሲሞከር አይተነው የለ? “ዲሞክራሲ፣ ውይይት፣”… እያልን በቁንፅል ብናራግብ፣… ብዙም አያሞቅም። ብዙም ሳይቆይ እያቃጠለ ያንገበግብ እንደሆነ እንጂ። እድሜ አይኖረውም።
እድሜ ያለውና እያደገ እየበለፀገ የሚሄድ የስልጣኔ ጉዞ እንዲሆን ማድረግ አንፈልግም? አንችልም? የአዙሪት ድራማውማ፣ እየደጋገምን ያየነው አድክም ድራማ ነው። እየተከፈተ እየተዘጋ እንደሚፈራረቀው የኢንተርኔት ግንኙነት እንደማለት ነው። እንዲዘልቅ ለማድረግ ያልተቻለው ለምን ይሆን? እየተከፈተ እየተቀወጠ እየተዘጋ መደበኛ አዙሪት ሲሆን እንዳየነው የፌስቡክ ግንኙነት ማለት ነው። ወይም እንደ ሃይማኖታዊ ክርክር ቁጠሩት። የአገራችን የፖለቲካ ውይይት፣ ከጭፍን ሃይማኖታዊ ክርክር ብዙም አይለይም።
አዎ፣ በሃይማኖት ዙሪያ፣ በተጨባጭ መረጃና በሳይንሳዊ ትንታኔ ላይ የተመሰረተ ስልጡን ውይይት ማካሄድ ይቻላል - ለእውነተኛ መረጃና ለትክክለኛ የሃሳብ ትንታኔ ፅኑ ዋጋ በሚሰጥ የስልጣኔ ጎዳና ውስጥ። ይሄ የሳይንስ ጉዳይ ስለሆነ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻሻለ፣ በምርምር ተጨማሪ እውቀት እየተገኘበትና እየበለፀገ ሊቀጥል ይችላል። በፊዚክስ ወይም በኬሚስትሪ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚካሄድ ውይይት፣… አዳዲስ የግኝት መረጃዎችን ለመለዋወጥና ግንዛቤን የሚያዳብሩ ትንታኔዎችን ለማየት እድል ይሰጥ እንደሆነ እንጂ፤ ለውዝግብ፣ ለግጭትና ለቀውስ እንዳያጋልጥ ያሰጋል እንዴ? ሃይማኖታዊ ክርክር ግን ከዚህ ይለያል።
የተጨባጭ መረጃ ወይም የትክክለኛ ሃሳብ አይሆንም - ጭፍን ሃይማኖታዊ ክርክር። እናም አይበጅም። አዎ፣ ለአንድ ስብሰባ፣ ለአንድ ወር… የተሟሟቀና የሚስብ ውይይት መስሎ ሊታየን ይችላል። ግን፣ መጨረሻው እንደማያምር እናውቀዋለን - ብዙዎቻችን። ሃይማኖታዊ ክርክር በየቴሌቪዥኑና በየሬድዮው ቢጧጧፍ፣ በአንዳች ተዓምር፣ አንዳች የመፍትሄ ሃሳብ፣ አንዳች መልካም ለውጥ ይመጣል ብለን እናስባለን? ብዙዎች፣ እንዲህ የሚያስቡ አይመስለኝም። ይልቅስ አደጋው ነው የሚታያቸው። እውነተኛ መረጃና ትክክለኛ የሃሳብ ትንታኔ የማቅረብ ጉዳይ ስላልሆነ፣ በጭፍን የሚናቆሩ፣ በስድብና በውግዘት ጥላሸት እያዘነቡ የሚጨቀዩ፣ መወነጃጀልና መጠፋፋት… መጨረሻው ከዚህ ውጭ ሊሆን እንደማይችል ብዙ ሰዎች አያውቁም? በቅጡ አልያም እንደነገሩ፣ የሚያውቁ ይመስለኛል።
እንዲያም ሆኖ፣… ሃይማኖታዊ ክርክር ከንቱና ጎጂ ቢሆንም፣… ማገድና መከልከል፣… ከቀውጢ የአደጋ ጊዜ ለማምለጥ ፋታ ይሰጥ እንደሆነ እንጂ፣ የሚያዛልቅ ሁነኛ መፍትሄ አይደለም። ነፃነትን በአፈና ማጥበብ፣ ለጊዜው መፍትሄ ይመስል እንደሆነ እንጂ፣ አያዋጣም። ይልቅስ፣ ሁነኛውና ዘላቂው መፍትሄ፣… ሃይማኖታዊም ሆኑ ሌሎች ጭፍን ክርክሮች፣ ከንቱና ጎጂ እንደሆኑ፣ በተጨባጭ እውነተኛ መረጃና በትክክለኛ የሃሳብ ትንታኔ ማሳየት ነው። ይህንን ለማድረግ፣ ማለትም… “እውነተኛ መረጃና ትክክለኛ ሃሳብ ለማቅረብ”፣… ነፃነት ያስፈልጋል። ማለትም፣… የግል ነፃነት! የጋራ፣ የቡድን፣ የአገር፣ የብሄር ብሄረሰብ፣ የሰፈርና የቀዬ፣… የጋራ አንጎልና አእምሮ የለም። የግል አእምሮ ነው ያው። የሰፈርና የቀዬ ሰዎች ቢሰበሰቡ እንኳ፣ የየግል አእምሮ ይዘው ነው የሚሰበሰቡት። ከግል ነፃነት ውጭና ከግል መብት የተለየ፣ “የቡድን ነፃነት፣ የቡድን መብት”… እየተባለ የሚወራው፤ አንድም አሳዛኝ ስህተትና የአላዋቂነት ውጤት ነው፤ አልያም ለምዕተዓመታት የክፋት መሸፋፈኛና ማመካኛ እየሆነ፣ የግል ነፃነትን ለመፃረርና ለማፍረስ የሚያገለግል የጥፋትና የአምባገነንነት መሳሪያ ነው።
ነፃነትን፣… ማለትም የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ለመጣስ ሲያሰኛቸው፤ “እኔ፣… እኔ አይደለሁም፣ የህዝብ ነኝ። ሃሳቤ፣… የኔ ሃሳብ አይደለም፣ የህዝብ ሃሳብ ነው። ስለዚህ፣ እኔን መቃወም፣ ህዝብን መቃወም ነው። እኔን አለመታዘዝ፣ አገርን መድፈር ነው። እኔን መተቸት፣ የኦሮሞ የሶማሌ ህዝብን መተቸት፣ የአማራ የትግራይ ህዝብን ማንቋሸሽ ነው።” ይላሉ። በዚህ ማመካኛ ዘዴ፣… የሁሉንም ሰው የግል ነፃነት መጣስ! “የብሔር ብሄረሰብ የቋንቋ መብት፣ የአገር ነፃነት”፣ ብለው ሲናገሩ፣… “ሰዎች፣ ለኑሮ በሚያስፈልጋቸውና በሚችሉት ቋንቋ አይነት ሁሉ እንደአመቺነቱ የመናገርና የመጠቀም የግል ነፃነት አላቸው” ማለታቸው አይደለም። “በእንግሊዝኛ አታስተምር”፣ “እዚህኛው ከተማ ከዚህኛው ቋንቋ ውጭ ማስታወቂ መለጠፍ አትችልም”፣ “ያንን ቋንቋ ብቻ ተጠቀም”፣ “በዚያኛው ቋንቋ ብቻ ፃፍ” ብለው የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት በመጣስ ለማዘዝ ነው የሚፈልጉት።
በሌላ አነጋገር፤ ከእያንዳንዱ ሰው የግል ነፃነት ውጭ የሆነና ከግል መብት የተለየ፣ “የቡድን መብት”፣ “የጋራ ነጻነት” ብሎ ነገር የለም። ነፃነትና መብት ማለት፣ የእያንዳንዱ ሰው የግል ነፃነት፣ የሁሉም ሰው የግል መብት ማለት እንደሆነ በቅጡ መገነዘብና በፅናት መያዝ ይገባል። ምክንያቱም፣ በጣም ድንቅና ውድ ነው። ለምሳሌም…     
ሁነኛና የሚያዛልቁ ከእውነተኛ መረጃዎች የፈለቁ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማበጀትና ለማቅረብ፣ የግል ነፃነት ያስፈልጋል ብለናል። መረጃ የማፈላለግና እውነተኛነቱን የማረጋገጥ፣ መረጃ የመለዋወጥና የማሰራጨት፣ ሃሳብን የመግለፅና የመወያየት የግል ነጻነት ያስፈልጋል።
በአጭሩ፤ የማሰብና የመናገር ነፃነት ያስፈልጋል - ለዘላቂና ለሁነኛ መፍትሄዎች።
በዚያው ልክ፣… ነፃነትም ሁነኛ አለኝታ ያስፈልገዋል። በየጊዜው ብቅ ብቅ የሚለው ነፃነት በተለመደው አዙሪት በእንጭጩ እንዳይቀጭ ከፈልግን፣… ነፃነት ከምር እንዲዘልቅ ከፈለግን፣ ሁነኛው መላ፣… “እውነተኛ መረጃንና ትክክለኛ ሃሳብን የመሻት፣ የመውደድና የማክበር ስልጡን ባህል እንዲስፋፋ መጣር” ነው። በዚህ የስልጣኔ  መንገድ ነው፤ ከአዙሪት ድራማ መገላገል የምንችለው። የሚያዛልቅና አስተማማኝ፣ የፖለቲካ ነፃነትን መገንባት የምንችለው፤ የሃሳብና ሃሳብን የመግለፅ ነጻነትን ማስፋፋት የምንችለው። አለበለዚያ፣ እንዳለፉት አመታት፣ በአሳዛኝ ሁኔታ በተደጋጋሚ የቀውስ አዙሪት እየተሸከረከርን ለባሰ ጥፋት እንዳረጋለን። በኢኮኖሚ መስክም እንዲሁ፣ መንግስት ቢዝነስ ውስጥ እየገባ የሚያባክነውን የቢሊዮን ብሮች ሃብት በማስቆም፣ ሰዎች የአቅማቸውን ያህል በራሳቸው ጥረት ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚችሉበት የነፃ ገበያ ስርዓትን ለማስፋፋት ስንጥር ነው፣ ከኢኮኖሚ ቀውስ አዙሪት መላቀቅ የምንችለው።

Read 1596 times Last modified on Saturday, 06 January 2018 12:34