Saturday, 06 January 2018 12:47

የገና ስጦታዎች በበዓሉ ዋዜማ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የዘንድሮውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ለማህበረሰቡና ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተለያዩ
ሥጦታዎችን እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ የገና በዓል ስጦታ ሰጪ ተቋማት ውስጥ ጥቂቶቹን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣
ቃኝታ እንደሚከተለው አጠናቅራለች፡፡

    አዲስ አበባ ሜዲካል
ቢዝነስ ኮሌጅ - ነጻ የትምህርት ዕድል
በ1996 ዓ.ም በ80 ተማሪዎች ስራ የጀመረው አዲስ አበባ ሜዲካልና ቢዝነስ ኮሌጅ፣ እስከ ዛሬ 50 ሺ ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን በየዓመቱ ከፍለው መማር ለማይችሉ ወገኖች በተለይም ለሴቶች ቅድሚያ በመስጠት ከ10ሺ በላይ ለሆኑ ሰልጣኞች ነፃ የትምህርት እድል በመስጠት አስመርቋል፡፡በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም የተለመደውን መደበኛ ነፃ የትምህርት ዕድል የሰጠ ሲሆን የገና በዓልንና ለሁለተኛ ድግሪ ከትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ፈቃድ ማግኘቱን ምክንያት በማድረግ፣ አዲስ አበባ፣ ዝዋይ፣ ድሬደዋ፣ መተሀራና ሀርጌሳ በሚገኙ ካምፓሶች ለ50 ከፍለው መማር ለማይችሉ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በስጦታ መልክ አበርክቷል፡፡
የኮሌጁ ባለቤትና ፕሬዚዳንት አቶ ሀብታሙ ጋቢሳ ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ ሰሜን ሆቴል አካባቢ በሚገኘው ሶርአምባ ሆቴል ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከተለያዩ ሆስፒታሎች ተወክለው ከመጡ ሃላፊዎች ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ተመዝጋቢዎች የትምህርት ሚኒስቴርን የመግቢያ መስፈርት ካሟሉና ከየሚኖሩበት አካባቢ ከፍለው መማር እንደማይችሉ ካስመሰከሩ፣ ከጥር 1-10 ቀን 2010 ዓ.ም በየሚቀርቧቸው የኮሌጅ ካምፓሶች መወዳደር እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡
ነፃ የትምህርት እድሉ ከሌቨል 1 እስከ ሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪ ድረስ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አቶ ሀብታሙ ገቢሳ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

መሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት - ዶሮና እንቁላል
ከአራት ዓመት በፊት በበጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ እውቅና ያገኘውና በኤጀንሲውም ሆነ በሌሎች ተቋማት በስራው ውጤታማነት የተለያዩ ሽልማቶችን የተቀዳጀው መሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት፤ ያለ ዕድሜያቸው ተደፍረው ወይም ተታለው የልጅ እናት የሆኑና ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች ተስፋ በመሆን ላለፉት አምስት አመታት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
“የእናቶችና የህፃናት ተስፋ” እየተባለ የሚጠራው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ፤ ዛሬ በገና ዋዜማ 700 ለሚሆኑ የድርጅቱ ተረጅዎች በቋሚነት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ሁሉም ቤተሰብ እንደየ እምነቱና እንደየ ፍላጎቱ፣ በዓሉን በደስታ እንዲያከብር ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ዶሮና ስድስት እንቁላል እንደሚለግስ የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት አዛገ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ይህ በገንዘብ ሲተመን ከ300 ሺህ ብር በላይ እንደሚሆን የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ ስጦታው በመደበኛ ወጪ ውስጥ ያልተካተተና በየበዓሉ ገንዘብ እያሰባሰቡና እርዳታ እየጠየቁ ለድርጅቱ ተረጂዎች የሚደጉሙት እንደሆነ ጠቁመው፣ ለዚህ በጎ ተግባር ድጋፍ ያደረጉላቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች በማመስገን ለእምነቱ ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

2ሺ ካ.ሜ ቦታ - ለኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ማዕከል
ከ400 በላይ የኩላሊት ህሙማንን በአባልነት ለያዘውና ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ለህሙማኑ ለሚያደርገው የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ማዕከል፤ ከመንግስት የ2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንደ የገና ስጦታ ተበርክቶለታል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የሚገነባው ህንፃም የኩላሊት እጥበት ማዕከል (ዲያሊስስ ሴንተር)፣ ከክልል የሚመጡ የኩላሊት ህሙማን ማረፊያ፣ የአስተዳደር ቢሮ እና ሌሎችንም አገልግሎቶች የሚሰጥ ሲሆን የሚከራዩ በርካታ ሱቆች እንደሚኖሩትና ከዚህም ቋሚ ገቢ በማግኘት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከልመና ወጥቶ፣ ስፋትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለህሙማን ለመስጠት እንደሚያስችል የድርጅቱ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋና የሥራ ባልደረባቸው ከትላንት በስቲያ በማሪዮት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡
 መሬቱ ለህሙማኑም ለስራም ምቹ በሆነ ቦታ እንዲፈቀድላቸውና ቦታዎቹም በልደታ፣ በቦሌና በቂርቆስ ክ/ከተማ እንዲሆንላቸው መጠየቃቸውን የገለፁት ሀላፊዎቹ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የጉዳዩን ሂደት መጀመሩንና ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ቦታውን እንረከባለን ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በጎ አድራጎት ድርጅቱ፣ ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በሚለመን ገንዘብ የህሙማኑን የዲያሊስስ ወጪ በመጋራትና በማገዝ የሚችለውን እያደረገ እንደሆነ የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፤ ህንፃው ሲገነባ የዲያሊስስን ወጪ ሙሉ በሙሉ እስከ ንቅለ ተከላ የማገዝ፣ ከአዲስ አበባ አልፎ ከክልል የሚመጡ ህሙማንን ማገዝና የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም፣ አስከፊውን የኩላሊት ህመም ለመከላከል ግንዛቤ የመፍጠር ህልም እንዳላቸው የጠቆሙ ሲሆን  ቦታውን በመፍቀድ ረገድ  ምላሽ የሰጠውን መንግስት አመስግነዋል፡፡ ሀላፊዎቹ አክለውም፤ አሁንም ለኩላሊት እጥበቱ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ ማህበረሰቡ በ8846 አጭር የፅሁፍ መልዕክት እንዲልክና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍልውሃ ቅርንጫፍ በተከፈተ 1000091822559 ድጋፍ በማድረግ፣ ህሙማኑን እንዲታደጉ ሀላፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ራይድ” የታክሲ ቴክኖሎጂ - የዋጋ ቅናሽ
“ራይድ” ታክሲ ቴክኖሎጂ፤ ከ3 ዓመት በፊት ኮንትራት ታክሲንና ተጠቃሚውን በቴክኖሎጂ የማገናኘት ህልምን ይዞ የተመሰረተ ኩባንያ ነው፡፡ 8294 ላይ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት አገልግሎት ፈላጊንና አገልግሎት ሰጪን ማገናኘት የጀመረው የቴክኖሎጂ ኩባንያው፤ በአሁኑ ወቅት የ2016 ዓ.ም ስሪት ከሆኑት 751 ያህል “ዘሉሲ ሜትር ታክሲዎች” ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት ማዕከል ከፍቶና ለእያንዳንዱ አሽከርካሪ በስድስት ወር የሚከፈል ታብሌት ስልክ ሰጥቶ፣ ለተጠቃሚው ደህንነቱ ዩተጠበቀ፣ በዋጋ ንትርክ የማይገባበት፣ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ “የራይድ ቴክኖሎጂ ኩባንያ” ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት ሳምራዊት ፍቅሩ ትናገራለች፡፡
ታዲያ ሰሞኑን ኩባንያው የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ መኪና ላላቸውም ሆነ መኪና ለሌላቸው የታክሲ ተጠቃሚዎች፣ በበዓሉ ግርግር መንገድ እንዳይጨናነቅባቸው ታክሲዎቹ ላይ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ በሪቫን የታሰረ ኩፖን በየኮንደሚኒየሙ በር ላይ በማስቀመጥ፣ ማህበረሰቡን ለማገዝ የበኩላቸውን እያደረጉ እንደሆነ ሥራ አስኪያጇ ገልፃለች፡፡ ለምሳሌ በእድሉ ለሚጠቀም የታክሲዎቹ ደንበኛ፣ የ150 ብር መንገድ ከሄደ 100 ብር ብቻ እንዲከፍልና የ50 ብር ቅናሽ እንደሚደረግለት ሥራ አስኪያጁ አስታውቃለች፡፡ ወደፊት አገልግሎቱን በማስፋፋትም፣በበዓል ጠጥቶ በማሽከርከር ከሚደርሰው አደጋ እግረኞችንም ሆነ አሽከርካሪዎችን ለማዳን ተመሳሳይ ቅናሾችን በማድረግ እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመስራት የማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፎ ለማድረግ ኩባንያው እቅድ መያዙን ስራ አስኪያጇ ጨምራ ጠቁማለች፡፡
 ላለፉት ሦስት ዓመታት ከለጋሾች በተገኘ 8 ሚሊዮን ብር ሲሰሩና ቴክኖሎጂውን ሲያጠናክሩ እንደቆዩ የገለጸችው ወ/ሪት ሳምራዊት፤ እስካሁን ምንም አይነት ገቢ ከአሽከርካሪዎቹ እንዳላገኙ ጠቁማ፣ በቅርቡ ኩባንያውን ማግኘት የሚገባውን ጥቅም መግኘት እንደሚጀምር አስታውቃለች፡፡ የራይድ ታክሲ ቴክኖሎጂ ሥራ አስኪያጅ ጨምራ እንደገለጸችውም፤ “በበዓሉ መኪና ይዛችሁ ወጥታችሁ ከምትጨናነቁ፣ ባደረግነው ቅናሽ ተጠቅማችሁ፣ ጉዳያችሁን  አቀላጥፉ” ስትል ጥሪ አቅርባለች፡፡  

Read 1851 times