Saturday, 06 January 2018 12:56

“የፖለቲካ ጅዝብትና”!?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “--ኦክሲሞሮን…ግን ቃሉ እንደሚገልፀው የማይመጣጠኑ… አንድ ላይ ሊሰባሰቡ በማይችሉ ነገሮች መሀል የሚደረግ ጋብቻ ነው፡፡… የእብድና የጤነኛ ጋብቻ እንደማለት፡፡… እብድ መንግስት፣ ጤነኛ ህዝብን ቢያስተዳድር እንደማለት፡፡ ወይንም ባል ሞቶ ሳለ፣ ሚስቱ በመቅበር ፋንታ አብራው ስትኖር… አይነት፡፡--”

   አርዕስቱ ራሱ ፓራዶክስ ነው አይደል? ፓራዶክስ እንኳን አይደለም፤ ኦክሲሞሮን ነው። “oxymoron” ከሁለት ሃሳቦች ጥምረት የተሰራ ነው፡፡ Oxy (sharp), moron (foolish) “አያዋ” (Pardoxe) ከሁለት የሚመጣጠኑ የሃሳብ ተፎካካሪዎች ጥምረት የሚገኝ የአቻ ጋብቻ ውጤት ነው፡፡ የተመጣጣኞች ጋብቻ እንቆቅልሽ ይባላል። እንቆቅልሽ እድገት ነው፡፡ አዎንታዊ ድምር ነው፡፡ ማንኛውም አይነት የሰው ልጅ መረዳት፣ የተለያዩ የሚመስሉ የሀሳብ አቻዎችን አቻችሎ ከማስማማት ይወለዳል፡፡ እንቆቅልሹን መጀመሪያ አቀራርቦ ለማጋጠም ሲሞክር ግጭት ይፈጠራል፡፡ ግጭቱ ያስደነግጠዋል፡፡ ደንግጦ በአንዱና በሌላው መሀል እየለዋወጠ ያያል፡፡ ያመነታል፡፡ “ማመንታት” የሚለው ቃል ራሱ… መንታ መንገድ ላይ ቆሞ የመመዘንን ሂደት የሚያሳይ ነው፡፡ እንቆቅልሽ የማመንታትን ጥበብ የማስተማሪያ ዘዴ ነው፡፡
ይሄ ከላይ ለማሳየት የጣርኩት ሁሉ ጤነኛውን የሁለት ተመጣጣኝ ነገሮችን የጋብቻ ሂደት ነው። ፖለቲካ ህዝብን የማስተዳደሪያ ዘዴ ነው። የማስተዳደሪያ አቅም ወይንም ጥበብ ያለው… መተዳደር የሚፈልገውን የሚመራበት መንገድ ነው። ይኼ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ተመጣጣኝ አስተዳዳሪና ተመጣጣኝ ህዝብ ሲገናኙ እንቆቅልሽ ይሰምራል፡፡ ዘመንና ታሪክ ከዚህ ተመጣጣኝ እንቆቅልሽ ውስጥ ይወለዳል፡፡ አስተዳዳሪው ህዝብን ይመስላል… የህዝብን ችግር እንደ ራሱ ችግር አድርጎ ይፈታል፡፡ ህዝብም አስተዳዳሪውን እንደኔ ሆነህልኛልና…በዙፋኑ ላይ ቆይልኝ ይለዋል። ህዝብን ግለሰብ (አስተዳዳሪ)፣ ግለሰብን ህዝብ ማድረጉ ነው እንቆቅልሹ፡፡ እንቆቅልሹ፤ ተግባቦቱ ከሰመረ “አያዋ” መሆኑ ይቀራል፡፡ “አዎ-አዎ” ሆኖ አንድና ያው መስሎ ይደመራል፡፡
ኦክሲሞሮን…ግን ቃሉ እንደሚገልፀው የማይመጣጠኑ… አንድ ላይ ሊሰባሰቡ በማይችሉ ነገሮች መሀል የሚደረግ ጋብቻ ነው፡፡… የእብድና የጤነኛ ጋብቻ እንደማለት፡፡… እብድ መንግስት፣ ጤነኛ ህዝብን ቢያስተዳድር እንደማለት፡፡ ወይንም ባል ሞቶ ሳለ፣ ሚስቱ በመቅበር ፋንታ አብራው ስትኖር… አይነት፡፡
ከዚህ በፊት እንዳልኩት፣ ለጥበብ ወይንም ለመለኮታዊ ውበት ባለሟልነት ሲል፣ ከተራው ሰው አመለካከቱና አኗኗሩ የሚለይን ሰው እኔ ጀዝባ ብዬ ነው የምጠራው፡፡ የብትህውና ህይወት በጥበብ ምክኒያት የመረጠ ማለት ነው፡፡ በሀይማኖታዊ ወይንም በሳይንሳዊ አንፃር ሳይሆን በጥበብ ውስጥ እውነት የሚፈልግ ሰው ነው ጀዝባ ለኔ፡፡ ሌሎች ደግሞ በሱስ ምክኒያት… ወይንም ለመረጠው ሱስ ሲል መደበኛ ህይወቱን የጣለ ሰውን ጀዝባ ብለው ይጠሩታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለጥበብ ብሎ የሚኖር ሰውም ከጥበብ ህይወቱ ጋር ስለሚመሳሰል ለሰስ ብሎ የሚኖረውን ሰው ባህሪ፣ ከጥበብ ግቡ ጋር አብሮ ሲያራምድ ይታያል፡፡ ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ጥበቡን እንደሆነ በስራው ይገልፀዋል፡፡
አስቡት፤ ይኼ ጥበበኛ ጥበብን የሚፈጥረው ወይንም ለመፍጠር የሚሞክረው የፖለቲካ ስልጣን ላይ ተቀምጦ ቢሆንና የፈጠራው ውጤቶች ህዝቦቹ ቢሆኑ፡፡ …ዛሬ አንዱን ገፀ ባህርይ ይፈጥረዋል፡፡…ሲፈልግ የፈጠረውን ገፀ ባህርይ ከእነ ወረቀቱ ጨማዶ ሊጥለው ይችላል፡፡ ወይ መፃፍ የጀመረውን ነገር በደንብ ሳያጠና ሊሆን ይችላል መፃፍ የሚጀምረው፡፡ ጀምሮ ሊተወው ይችላል፡፡ ዛሬ የጀመረውን ትቶ  ነገም ከነገ ወዲያም ሊጀምር ይችላል፡፡… እንደ ጀዝባ ጥበበኛነቱ፣ ይሄንን ሁሉ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ግን ችግሩ ገፀባህሪዎቹና ድርሰቶቹ በተጨባጭ ህይወት የሚኖሩ…ህልውና ያላችሁ መሆናቸው ነው፡፡…
… ምናልባት ፖለቲከኛው የሙሉ ጊዜ ጀዝባና የጥበብ ሰው ለመሆን ይሆናል የተፈጠረው። ምናልባት የተፈጠረበትን ምክኒያት ሳያውቅ ሊሆን ይችላል ፖለቲካ ውስጥ የገባው፡፡… ወይንም በፖለቲካ (ተጨባጭ) እና ጥበብ (ምናባዊው) መሀል ብዙ ልዩነት አይታየው ይሆናል፡፡… መድረክ ላይ አሻንጉሊቶችን በክር አማካኝነት የሚያስደንሱ አርቲስቶች አሉ፡፡…. በክር አንጠልጥሎ የሚያስደንሳቸው ስጋ ለባሽ ሰዎች ከሆኑ ግን  sharp…ይሆን የነበረው ጥበብ… ወደ አሰቃቂ ክፋት ተለውጧል፡፡ ኦክሲሞሮን ተፈጥሯል… የጭካኔ ፈጠራ ሆኗል፡፡ “Kind cruelness”…
በአሻንጉሊቶቹ ላይ በክር እንጠልጥሎ እየጣለና እያነሳ ሲቀልድባቸው…ተመልካች ስለ ሰዎች እየመሰለ እንደሆነ ይገባቸዋል፡፡… በምሳሌው ግን ያስተምራቸዋል እንጂ ምሳሌውን እነሱ አድርጎ አይጫወትባቸውም፡፡
ጀዝባው በራሱ ህይወት ሊጫወት ይችላል። ስለሚሰራው ጥበብ ለማጥናት ሲል የራሱን ህይወት የመጫወቻ ሜዳ አድርጎ፣ ራሱን ከጥበቡ አሳንሶ ችላ ሊል ይችላል፡፡ ፖለቲከኛውም እንደ ትክክለኛ አስተዳዳሪ ራሱን ዝቅ አድርጎ፣ የህዝቡን አገልግሎቶች ከፍ ለማድረግ ሲሞክር ትክክለኛ የህዝብ መሪ ነው፡፡ ፖለቲከኛው ጀዝባ የሚሆነው ራሱን ከፍ አድርጎ ህዝቡን ሲንቅ ነው። “ፐርፐዙን” ሲተው ጀዘበ ይባላል፡፡… ህዝቡን በማስተዳደር ፈንታ ራሱን በህዝቡ ፈንታ ወይንም ጫንቃ የሚያስተዳድር ከሆነ… ለፖለቲከኛነት ሚናው ጀዝቧል፡፡ … ዓላማውን ክዷል፡፡ ሰይጣን ጀዝባ ነው፡፡ የመልአክነት ስራውን ወደ መልዕክት አዛቢነት ስለቀየረ፡፡
ዋናው ነገርዬው የሚመዘነው ከሚናው (Purpose) አንፃር ነው፡፡ የመጠቀ ወይም የዘቀጠ የሚለው መለኪያ የሚመጣው ለመጫወት ከመረጠው ሚናው አንፃር ነው፡፡ ፖለቲከኛነት ህዝብን ማስተዳደር ነው፡፡ ህዝብን ማስተዳደር ካልቻለ ለምን እንዳልቻለ መታወቅ ይኖርበታል።… አቅም አንሶት ከሆነ አቅም ላለው ሚናውን አሳልፎ መስጠት አለበት፡፡ ስራዬን የመሥራት አቅም የለኝም፤ መስራት ለሚችልም ግን አሳልፌ መስጠት አልፈልግም ካለ…ይኼኔ የፖለቲካ ጀዝባ ሆኗል። …መስራትም ሆነ ሌሎች እንዲሰሩ መፍቀድ ያልቻለውን ሚና፤ “ሥልጣን” ብሎ ይጠራዋል፡፡ ሥልጣኑ ያለው ስራውን መስራት ላይ አይደለም፡፡ ስራውን  ለመስራት አቅም የለውም፡፡ ግን ስራውን አላሰራ ያለው አቅም ማነስ፣ ሌሎች እንዳይሰሩ ወይም ለወደፊትም መስራት እንዳይሞክሩ አድርጎ የመሰባበር ታላቅ አቅም አለው፡፡ ስንፍናውን በዘላቂነት ለማስቀጠል ጎበዝ ነው፡፡ ጉብዝናው ያለው ግን ያለ ቦታው ነው፡፡ ጀዝባ ማለት ይኼ ነው… በፖለቲካ አንፃር ሳየው “Sharp loser” አይነት ነው፡፡ “ብቆጣም እመታሻለሁ….ብትቆጭም እመታሻለሁ” የሚለውን የአሰራር ዘዴ ተጠቅሞ ጀዝባነቱን ብቃት አስመስሎ ማቅረብ፡፡ ግን ይኼ ጅዝብትና ስልጣን ላይ ያለው ሰው ዘንድ ወይም አጋሮቹ ጋር ብቻ ተወስኖ አይቀርም፡፡
የሚንቀውን ሰው አስተዳዳሪ አድርጎ በተደጋጋሚ የሚመርጥ ህዝብም የዛው በሽታ ተጠቂ ነው፡፡ የጅዝብትና፡፡ ህዝቡ “የዝንብ ጠንጋራን የሚያውቅ” ሆኖ ግን የሚያዋጣውን ፖለቲካ የማያውቅ ከሆነ ጀዝባ ነው፡፡ እውቀቱ ያለው የማይመለከተው ነገር ላይ በመሆኑ፡፡ ህልውናውን በቀጥታ የሚመለከተውን ነገር ትቶ፣ “የዝንብ ጠንጋራን” በመለየት ከተጠመደ፣ ህዝብም ጀዝባ ፖለቲከኛ ነው፡፡… ማን የማን የሥራ ውጤት እንደሆነም ለማወቅ አዳጋች ይሆናል፡፡
ባለፈው “ENN” ተብሎ በሚጠራው ቴሌቪዥን ላይ  አንድ ማስታወቂያ ሲነገር  ጆሮዬ ጥልቅ አለ። “በ…ወዘተ… ወዘተ.. ስልክ ቁጥር መሪዎቻችሁን በቀጥታ ስልክ አግኝታችሁ ማነጋገር የምትችሉበት ፕሮግራም….” ምናምን ይላል ጥቅል መልዕክቱ፡፡ ይኼ ራሱ ኦክሲሞሮን ነው፡፡…. መንግስትና ህዝብ…. በቀጥታ መስመር ስላልተገናኙ ነው ያልተዋወቁት ለማለት ነው፡፡ …በአካል ላይ ጭንቅላትንና አካልን በስልክ  ለማወያየት እንደመሞከር ነው፡፡ ደም ስር…ስጋ አጥንት…እና በሚጫወቱት ሚና መግባባት ያልቻሉ ነገሮችን በቀጭኑ ሽቦ… “አንድ አድማጭ መስመር ላይ ገብቷል” እየተባባሉ ሊነጋገሩ። ግን አልሳቅሁም፡፡ ሳቅ የእንቆቅልሽን አዲስነት የሚያበስር የማወቅ ሂደት ነው፡፡… የማይመስል ሀሳብ ሲደጋገም…ያበሽቃል፡፡ መበሻሸቅ ነው የያዙት። …ጥሩ የአስማት በትረ ስልጣን የያዘ መሪ እንደ ሙሴ የችግርን ባህር ከፍሎ ህዝቡን ያሻግራል። …የፖለቲካ ጀዝባ እጅ ላይ ግን አስማታዊው ህዝብን የማስተዳደሪያ ስልጣን ጓሮን እንኳን አፅድቶ ወደማይጠርግ ያለቀ መጥረጊያ ይለወጥበታል፡፡ ስልጣኑም በእጁ ውስጥ የእሱን ባህሪ ተላብሶ ይጀዝባል፡፡ ሁለት “trivial planes” በሚያደርጉት ሰበቃ “The absolute” ፕሌን ላይ የሚደረስ ይመስላቸዋል፡፡ የሚደርሱት ግን “tragic plane” ላይ ነው፡፡
ዮናስ፤ እግዚአብሔር የሰጠውን መልእክት ወደ ነነዌ ሰዎች ሄዶ የማስተላለፍ ተልዕኮ ይቅርብኝ … ተራው ህይወቴ ይሻለኛል ብሎ አልሰማም አለ። … አልሰማ ያለው ችግር ገፍቶ መጣና ዓሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ጨመረው፡፡ በዓሳ ነባሪው ሆድ ውስጥ ቀናትን ቆይቶ ሲተፋ ግን እንደ ቀድሞው ችላ ባይ አልሆነም፡፡ …  የዓሳ ነባሪው የሆድ እቃ ጨለማ፣ የእግዚአብሔር ነብይ አድርጎ ነው ያወጣው። ተራው ህይወት (Trivial plane) በፈተና መስዋዕትነት (Tragic plane) ውስጥ ሲያልፍ … አልፎ በህይወት ከተረፈ፣ ከተራነት ጅዝብትናው ወጥቶ ተልዕኮውን ወደ መገንዘብ … ከሰውነት በላይ ከፍ ብሎ ወደተቀመጠው ማዕረግ ከፍ ወደ ማለት ይጠጋ ይሆናል፡፡
ይሄ ህዝባችን በብዙ ጨለማ ውስጥ አልፏል ይላሉ የታሪክ ዘገባዎች፡፡ … ታዲያ ከዛ ሁሉ የዓሳ ነባሪ ሆድ የተተፋ ህዝብ፣ እንዴ መልሶ እዛው ተራነት ውስጥ እየተመላለሰ ይታሻል፡፡ … ምናልባት ህዝቡ እንደ ዮናስ በተለያዩ የፖለቲካ ጀዝቦች ብልጠት ለአሳ ነባሪ ሲሰጥ ኖረ እንጂ አስተዳዳሪዎቹ ይሄ እጣ ፈንታ ገጥሟቸው አያውቅ ይሆናል፡፡ … የህዝብ አካል ያልሆነ ፖለቲከኛ ወይንም አስተዳዳሪ … አሊያም ብልጣብልጥ የሚባል ዝርያ አለ እንዴ? ..
...ተዉት በቃ! ...መልሱ ተከሰተልኝ፡፡ ህዝቡ ከድሮም እስከ አሁን በአስተዳዳሪዎቹ ሆድ እቃ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የፖለቲካ ጀዝባዎቹ ናቸው ዓሳ ነባሪዎቹ፡፡ እየተቀባበሉ ይዋዋጡታል እንጂ ተፍተውት አያውቅም፡፡ ታዲያ ይሄ ህዝብ ከጨለማው ተሞክሮው (Tragic plane) ትምህርት ወስዶ ወደተሻለ የፍፁማዊነት ጎዳና  እንዴት ያምራ? …አንድ ጨለማ ሲመሽ ሌላ ጨለማ እየነጋበት፣ አፍሪካን የምታክል የዓሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ እስረኛ ሆኖ ቀርቷል፡፡
…አልፎ አልፎ ዓሳ ነባሪው አፉን ገርበብ አድርጎ ሲከፍት፣ ሊተፋው ይመስለውና የተስፋ ህልም ያያል፡፡ “I see light at the end of tunnel, I think this time around we are  going to emerge into the light, into the clear--” ብሎ ይመኛል፡፡ … በዓሳ ነባሪው አፍ ግን የተስፈ ህልምና ወደ ጨለማው ተውጦ የሚቀላቀል አባል ብቻ ነው የሚጨመረው፡፡
…ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ መፍረድም ይከብዳል። …በጨለማ ውስጥ ሆነው ጀዝቦቹ እርስ በራስ ይወነጃጀላሉ፡፡ “በቀጥታ የስልክ መስመር” ተነጋግረን ችግራችንን እንቅረፍ ይባባላሉ፡፡ … ችግራቸውን እንዲህ በቀላል እንደማይፈቱ እያወቁ፣ እንዳላወቁ ---- ገልባጭ መኪና ሙሉ መፈክርና ፕሮፓጋንዳ፣ አንዱ የጨለማ ፍጡር በሌላኛው ጀርባ ላይ ወስዶ ይደፋል፡፡ … “ገላጋይ መስሎ አጥቂ” ይሆናል፡፡ መአት አይነት “ኦክሲሞሮን” እያዳቀለ ያራባል፡፡ የጅዝብትና እና የመደንዘዝ ውጤት ነው፡፡

Read 880 times