Saturday, 06 January 2018 12:59

“የአመፃ መንገድ” ድፍረቶች

Written by  በቅድመ - አለም በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

   እንደሚታወቀው ያለማቋረጥ ለአገራችን አንባቢያን በርከትከት ያሉ መጽሐፍትን ለንባብ እየበቁ ነው፡፡ መጽሐፍቱ ታዲያ ቅርጽና ይዘታቸው ተገማች ይሆን ይዟል፡፡ ያለፈውን ዘመን ዞር ብለው ታሪክን የሚመረምሩቱን ከግምት እናውጣ ካልን፥ መጽሐፍት በገጽ ብዛታቸው እጥር ምጥን እያሉ፥ በአቀራራባቸው እየቀለሉ፣ በርዕሰ ጉዳይ ምርጫቸው ወደ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ስላቅ እያዘነበሉ መጥተዋል፡፡ ዘመነ ትዊተርና ቴክስት ሜሴጅ የአትኩሮት እድሜውን ክፉኛ ያሳጠሩበትን አንባቢ ላለመወናበድ አጫጭር ትርክቶችን ማሰባሰብ ዓይነተኛ መላ የሆነም ይመስላል፡፡ ብዙ ጊዜም ቁም ነገር ማስጨበጥ፣ ጠናን እውነት መመሥረትና የእውቀትን ብርሃን ማፍካት፣ በማዝናናት ድል ተመትተው ሲዘረሩ ይስተዋላል፡፡
ከሰሞኑ እጄ ገብቶ ያነበብኩት የተክሉ አስኳሉ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ግን ከዚህ የዘመን ግርፍ ተለይቶብኛል፡፡ ላቅ ያለ ፋይዳ ያለው በመሆኑም  በቀላሉ ላለፈው አልቻልኩም፡፡ “የአመፃ መንገድ” ይሰኛል ርዕሱ፡፡ ከጀማው ለመነጠሉ የመጀመሪያው ምስክር ግዝፈቱ ነው፡፡ የገፆቹ ብዛት 342 ሲሆን፥ ጥቅጥቅ ያለ የውስጥ ቅንብሩ ከዚህ ይበልጥ ሊዳጉስ ይችል እንደነበር ይጠቁማል፡፡ አቀራረቡም ቢሆን ኮስተርተር ያለ፣ ማጣቀሻዎችና የሕዳግ ማስታወሻዎች የበረከቱበት ነው፡፡ የገበያውን ነፋስ በሚገባ ስናጤን፣ ይህ በራሱ አንድ ድፍረት እንደሆነ መረዳት አያዳግተንም፡፡ ነገር ግን በውስጡ የያዛቸው ፍሬ ነገሮች የፀሐፊውን ከወጀቡ በተቃራኒ የመዋኘት ተነሳሽነት ጠቋሚ  ናቸው፡፡
“አንድ ሕዝብ አሊያም የህብረተሰብ ክፍል ስሙር የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሐብታዊ ጉዞ ሊኖረው የሚችለው ለዘመናት ፀድቀውና ተጠብቀው የኖሩትን ባሕላዊ እሴቶቹን በተቻለ መጠን መጠበቅ ሲችል ነው፡፡” ሲል ያስታውሰናል ጸሐፊው በመቅድሙ ላይ፡፡ “የአመፃ መንገድ” ታዲያ እነዚህን እሴቶች መቀመቅ ይከታሉ ያላቸውን የአስተሳሰብ አዝማሚያዎች፣ የአኗኗር ፈሊጦችና የሕይወት ብያኔዎች ሥረ መሰረት ለማመላከት የጣረበት መጽሐፍ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በውስጡ ያቀፋቸው ሦሰት አብይ ርዕሰ ጉዳዮች በራሳቸው መጽሐፍ ሊሆኑ ይችሉ ነበር። ይህም የመታከትን ስሜት በአንባቢ ላይ ቢፈጥር አይደንቀኝም፡፡ ምናልባት በመካከላቸው ያለውን የእርስ በርስ መሰናሰልና መጠላለፍ ጸሐፊውን በአንድ እንዲያጭቃቸው ገፋፍቶት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በመጀመሪያው የመጽሐፉ ክፍል (125 ገፆች ያህል ይረዝማል) ከነገረ ፆታና ከሥነ ወሲብ ጋር በተያያዘ አሁን በምንኖርበት ዓለም አመለካከት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረዋል ያላቸውን ሦስት የሥነ ልቦና ሊቃውንት ያስተዋውቃል፤ የሥራዎቻቸውን እንከኖች ያመላክታል፤ እንደምን ወደ አረንቋ እንደዘፈቁን ያሳያል፡፡
የፍካሬ ልቦና አባት እየተባለ ተገቢ ሙገሳ ዘወትር የሚዘንብለት ሲግመንድ ፍሮይድ ከሦስቱ ጎልቶ የሚታየው ነው፡፡ የፍሮይድን ሥራዎችና እሳቤዎች በጠሊቁ ካስተዋወቀን በኋላ፥ የእርሱ ኅልዮቶች እንደምን የኋላ ኋላ ለተቀጣጠለው “የወሲብ አብዮት” የመነሻ እርሾ እንደሆኑ ያስረዳናል፡፡ በሥነ ወሲብ ዙርያ ላይ ሰፊ ጥናት ያደረገውን ሐቭሎክ ኤልስን እና ግብረ ሰዶማዊነትን አስመልክቶ ባቀረባቸው መላ ምቶች ስሙ የገነነውን አልፍሬድ ኬንሴይን አሻራዎች ለጥቆ ይጠቁመናል፡፡ በተለይ ብዙ ግብረ ሰዶማዊነትን አስመልክቶ የሚሰበኩና መነሻቸውን ከኬንሲይ የሚመዝዙ “ሳይንሳዊ እውነታዎች”፥ ትክክለኛ ሳይንሳዊ መንገዶችን ተከትለው መሰራታቸው ስለማጠራጠሩ፣ ሌሎች በርካታ ሳይንቲስቶችን እያጣቀሰ ይገልጽልናል፡፡
የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ይሄው ነገረ ሰዶም ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አንባቢን ማስደንገጥና “ወይ ጉድ!” ማስባል ዓይነተኛ መገለጫቸው፣ ግባቸው ብሎም የገበያ ማራኪነታቸው ያደረጉ ድርሳናትና የጋዜጣ ላይ መጣጥፎች በግብረ ሰዶማዊነት ዙርያ እንደተፃፉ እናውቃለን፡፡ ተክሉ የሚያደርገው ግን ያንን አይደለም፡፡ ልማዱን አንድም አፈንጋጭነት ነው፣ አንድም አደገኛ ነው፣ በዚያውም ኢ-ተገቢ ነው ሲል የሚከራከረው ሳይንሳዊ፣ ምሁራዊና አመክንዮአዊ ድጋፎችን ይዞ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የግብረ ሰዶማዊነት “ባህል” እየተሰራጨና በ‘እኔ ምናገባኝ’ ሙግት ቅቡልነት እያገኘ ካለባቸው መንገዶች አንዱ ማደንዘዝ (desensitization) ነው ይለናል፡፡ ይህም ግብሩ እንዳይቀፍፈን ፣ እንዳያስፀይፈንና እንዳያስደነግጠን ደንታ ቢስ ማድረግ ወይንም በአጭሩ ማላመድ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ሌላኛው መንገድ ደግሞ መወሸቅ (jamming)  ነው፡፡ የግብረ ሰዶማዊነትን ጉዳይ በታሪክ ከተጨቆኑ አካላት (ለምሳሌ ጥቁር አሜሪካዊያን) እና ከሴቶች ጉዳይ ጋር ቀላቅሎ የመብት ጥያቄ አስመስሎ ማቅረብ፡፡
ሦስተኛውና በእኔ እይታ አውራው የመጽሐፉ ክፍል፣ የሴቶች መብት ጥያቄ አንግቦ የተነሳው የእንስታዊነትን እንቅስቃሴ “ውዥንብሮች” ከተለያየ  አንፃር እንድንመለከተው እድል የፈጠረበት ነው። ገና ከመነሻው “አስተውሉልኝ በአንድ ፆታ አሊያም የህብረተሰብ ክፍል ላይ የመነሳት ዓላማ የለኝም። የ’ኔ መሻት ሥራተ ኅላዌና ማህበራዊ ኑሮን የሚያቃውሱ ኢ-ፍትሐዊ እሳቤዎችን የሚያሰራጩ  ኃይሎችን ማሳየት ነው” ሲል የሚማፀነን ጸሐፊው፥ በሴቶች እኩልነት ስም የሚደለቁ አታሞዎችን በጥንቃቄ እንድናጤን ይመክረናል፡፡
ነገረ ወሲብን በፍካሬ ልቦና እና በሥነ ልቦና ሳይንስ ጥናት መነጽሮች ያሳየንን ያህል፣ ሥነ ፆታ ደግሞ የማርክሲስት ኤንግሊስት ማኅበራዊ አወቃቀር ፍልስፍና ተራዛሚ ጥላ ነው ይለናል፡፡ በእርግጥ የካርል ማርክስ ህልፈተ ሕይወት ወዲያ ትቷቸው ያለፋቸውን የማስታወሻ ላይ ጽሑፎች መነሻው በማድረግ፣ ወዳጁ ፍሬድሪክ ኤንግልስ ባሳተመው “The Origin of the Family, Private Property and the State” የተባለ የ1883 መጽሐፍ ላይ “የታሪክ የመጀመሪያው የመደብ ትግል የተከሰተው በአንድ ለአንድ ጋብቻ ውስጥ እያደገ በመጣው የወንድና ሴት ቅራኔ ውስጥ ነው” ሲል ማተቱን ያስታውሰንና  በተለይ  ጀንደር  ፌሚኒስቶች የሚባሉትና በአክራሪነታቸው የሚታወቁት እንስታዊያን፣ ቤተሰብ የሚባለውን መዋቅር የማፈራረስ ተቀዳሚ ኤንግልሳዊ ግብ ይዘዋል ሲል ይሟገታል፡፡ እንደ ግሎሪያ ስተይነም፣ ሹላሚትዝ ፋየርስቶንና ኢርሻድ ማንጅ የመሳሰሉ ዝነኛና ተጽዕኖ አድራሽ እንስታዊያን ለተከታዮቻቸው የሚያቀርቡትን “ፍትፍት” አመክንዮአዊ ሕፀፆች፣ ሥነ ተፈጥሯዊ እንከኖች መዝዞ ያወጣና የኃሳብ ምክክቶሽ ይገጥማቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሴቶች ጋብቻ ለመፈፀም እንዳይጣደፉ ይመክራሉ፤ በተቃራኒው ደግሞ ወሲብ የሚጀመርበት ዕድሜ ዝቅ ይል ዘንድ ይሽታሉ ይላል፡፡ ወይንም ደግሞ ሴቶች የየራሳቸው ፍላጎትና ምርጫ እንዲከበርላቸው በርተትን እየሰራን ነው ይላሉ፤ ነገር ግን አንዲት ሴት ውጭ ውጭ ማለት የማይማርካት ቢሆንና የቤት እመቤትነት ምርጫዋ ቢሆን መላው የሴት ዘር ላይ በደል የፈፀመች ያህል ያብጠለጥሏታል ሲል ግርምታውን ያጋራናል፡፡ በአንድ በኩል ወንዶችንና እነርሱን ያገንናል የሚሉትን ሥርዓት ያጥላሉ፤ ወዲያውም ግን ሴቶች እንደ ወንዶች እንዲሰሩ፣ እንዲኖሩ፣ እንዲለብሱና በአጠቃላይ እንዲሆኑ ያበረታታሉ፡፡
መጽሐፉ ለህትመት ከበቃ በኋላ ካነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮች የዓለምን የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ ስበዋል፡፡ ለዛሬ ሁለት ክስተቶች ብቻ ልጥቀስ፡፡ አንደኛው የአሜሪካ ላዕላይ ምክር ቤት፣ ግብረ ሰዶማዊያን የመጋባት መብት እንዳላቸው በድምጽ ብልጫ ወስኗል። ይህ ጸሐፊው ሊሆን እንደሚችል የገመተውና ጋብቻ የሚባለውን መሠረታዊ ማህበራዊ ተቋም የማፈራርስ አንድ አካል ነው ያለው ነው፡፡ በመቀጠል በመጽሐፉ ውስጥ በስም ጠቅሶ በእኩይ ተግባራት ተጠምዷል ሲል የወነጀለው የአሜሪካዊ ውርጃ አስፈጸሚ ተቋም Planned Parenthood ሴቶች የሚያስወርዷቸውን ጽንሶች አካላት እየቆራረጠ እንደሚቸበችብ የሚያሳብቁ ቪዲዮዎች በተከታታይ መለቀቃቸው ነው፡፡ (በአንደኛው ቪዲዮ ላይ የተቋሙ ሹም የሆኑ እንስት፣ ሽያጩ የሚያስፈልግበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ውድ የመኪና ዓይነት ጠቅሰው “እርሱ ያስፈልገኛል” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡)
ለማሳያነት ያቀረብኳቸውን ሁለቱም ክስተቶች የተከናወኑት ከአትላንቲክ ማዶ ነውና “እኛን ምን ያገባናል?” የሚል የዋህ አንባቢ ካለ፣ ጸሐፊው አስቀድሞ ምላሽ አሰናድቷል፡፡ “ተወደደም ተጠላም ያለንበት ዘመን በየትኛውም ዓለም የሚከሰት አስተሳሰብ አይመለከተኝም እንድንል ዕድል የሚሰጥ አይመስለኝም” ሲል ይደመድማል። አያይዞም፤ “በ1960ዎቹ በያ ትውልድ ይቀነቀን የነበረው ርዕዮት ከአምሳ ዓመት በፊት በራሺያ ውስጥ ቦልሸቪኮች ሲያራምዱት የነበረው ዓይነት ነው፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ ላይ ፌሚኒስቶች ስለ ሴቶች እኩልነት እያሰሙት ያለው ጫጫታ፣ የዛሬ አርባ ዓመት በምድረ አሜሪካ አክራሪ ፌሚኒስቶች ሲያሰሙት የነበረው ነው” ይልና የጎምቱ እንስታዊያኑን እሳቤዎች እያነሱ መወያየቱ ያለውን ፋይዳ ይነግረናል፡፡
በአገራችንም ምስጋናው ለዓለም አቀፍ ተቋማት ረጅም እጅ፣ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና ለ“አጥፊ ልሂቃን” ይሁንና፣ እነዚህ የአስተሳሰብ ቅንብሮች በአደባባዩ መናኘታቸው አይቀሬ ነው ሲል ያረዳናል፡፡ “ስቴሪዮታይፕ”፣ “ዳይቨርሲቲ”፣ “ኢንቶለራንስ”፣ “ሆሞፎቢያ”፣ “ሴክሲስት” የመሳሰሉ የመጫወቻ ቃላት በሥነ ልቦናችን መደላደል መያዛቸው፣ ከአንደበታችንም መበራከታቸው የመጪው ዝናብ ምልክት ደመናው ነው ይላል፡፡
“የዓመፃ መንገድ” ከኃሳብ እጭቅታውምና ከአንዳንድ የኃሳብ ድግግሞሹ በተጨማሪ እንዳሻው ሰርጎ የሚገባው የጸሐፊው ብያኔ፤ የመከራከሪያዎቹ ስሜት ንክርነትና የአንባቢው አጭር ፍላጎት እንቅፋት እንዳይሆንበት መስጋት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ድፍረትን ትጥቁ፣ በቂ ዝግጅትን ስንቁ ባደረገ ጸሐፊ እጅግ በርካታ ቢያብሰለስሏቸው የሚበጁ ላቅ ያሉ ኃሳቦችን ያዘለ መጽሐፍ እንደሆነ መመሥከር ይገባል፡፡ ከእርሱ መከራከሪያዎች ወይንም ድምዳሜዎች ጋር ባይስማሙም እንኳ ገናን የዘመናችን መንፈሶች መነሻቸው ክየት፣ ሥረ ነገራቸው ደግሞ ከምን እንደሆነ ለመመርመር በቂ ግብዓት ማግኘት ይቻላል፡፡
የመጽሐፉ ዋና የትኩረት አቅጣጫ “የሰው ልጅ ስልጣኔ የማዕዘን ድንጋይ በመሆን ለዘመናት የዘለቁት ሄትሮሴክሹላዊ ባህሎች፣ ልማዶችና መርሆዎች በመናቃቸው የተነሳ በምዕራቡ ዓለም ማህበራዊ ኑሮ [ላይ] ያስከተሉትን መጥፎና የተበላሹ ድርጊቶች በስልጣኔ ሽሚያና ባልሰለጠነ ሩጫ አማካይነት በማደግ ላይ ባሉት አገራት እንዳይደገም ማሳየት” እንደመሆኑ፣ ግቡን ከሞላ ጎደል አሳክቷል ቢባልም አይበዛበትም፡፡

Read 1975 times