Saturday, 06 January 2018 13:17

ታጅ ማሃል በቀን ከ40 ሺህ በላይ ቱሪስቶች እንዳይጎበኙት ሊከለከል ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የህንዱ ታጅ ማሃል በእረፍት ቀናት እስከ 70 ሺህ ቱሪስቶች ይጎበኙታል

    የህንድ መንግስት በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለትንና ከአለማችን ጥንታዊ የቱሪዝም መስህቦች አንዱ የሆነውን ታጅ መሃልን፣ በአንድ ቀን ውስጥ መጎብኘት የሚችሉ የአገሪቱ ቱሪስቶች ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ እንዳያልፍ የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ ሊያደርግ ማቀዱ ተዘግቧል፡፡
ታጅ ማሃል በተለይ በእረፍት ቀናት እስከ 70 ሺህ በሚደርሱ ህንዳውያን እንደሚጎበኝ ያስታወሰው ቢቢሲ፤፣ ከቱሪስቶች መብዛት ጋር በተያያዘ በጥንታዊው የቱሪስት መስህብ ላይ ጥፋቶች እየደረሱ በመሆኑ ይህንን ጥፋት ለመቀነስ በማሰብ መንግስት በአንድ ቀን ውስጥ ከ40 ሺህ በላይ የአገር ውስጥ ቱሪስት እንዳይጎበኘው ለማገድ ማቀዱን ዘግቧል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ህግ፣ ህንዳውያን ቱሪስቶች በዩኔስኮ የአለም ቅርስነት በተመዘገበው ታጅ ማሃል የሚኖራቸውን የጉብኝት ቆይታ ጊዜ 3 ሰዓታት ብቻ እንደሚያደርገውም ዘገባው አመልክቷል፡፡
አዲሱ የታጅ መሃል ህግ በህንዳውያን ቱሪስቶች ላይ እንጂ በሌሎች አገራት ጎብኝዎች ላይ እንደማይሰራ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ታጅ ማሃል በ2016 የፈረንጆች አመት ብቻ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት ጎብኝዎች 8.8 ሚሊዮን ፓውንድ ያህል ገቢ ማስገኘቱን አስታውሷል፡፡

--------------------------


               ሙጋቤ ቤትና 3 ዘመናዊ መኪኖችን ጨምሮ ጠቀም ያለ ጡረታ ይሰጣቸዋል

   አዲሱ የዚምባበዌ መንግስት ለቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ዳጎስ ያለ ደመወዝ፣ ምቹ የመኖሪያ ቤትና ሶስት ዘመናዊ መኪኖችን ጨምሮ ተገቢውን የጡረታ ጥቅማጥቅም እንዲከበርላቸው ውሳኔ ማሳለፉን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
አገሪቱን ለ37 አመታት ያህል የገዙትና በቅርቡ ስልጣናቸውን የለቀቁት ሙጋቤ፣ ጠባቂዎችን ጨምሮ በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው “አቤት ወዴት” ብለው የሚታዘዟቸው 20 ሰራተኞች ይመደቡላቸዋል ያለው ዘገባው፤ በአመት አራት ነጻ የአንደኛ ደረጃ የአውሮፕላን በረራ አገልግሎትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችንም እንደሚያገኙ አመልክቷል፡፡
ሙጋቤ የጡረታ ህይወታቸውን በምቾት ያሳልፉ ዘንድ ከአዲሱ መንግስት ዘመናዊ መርሴድስ ቤንዝን ጨምሮ ሶስት መኪኖች እንደሚሰጧቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ዕድሜ ይስጣቸው እንጂ በህይወት እስካሉ ድረስ የሶስቱንም መኪኖች የነዳጅ ወጪ የሚሸፍንላቸውም የአገሪቱ መንግስት ነው መባሉን ገልጧል፡፡
ሙጋቤ ከአዲሱ መንግስት የገንዘብ ድጎማ ይደረግላቸው አይደረግላቸው የታወቀ ነገር የለም ያለው ዘገባው፣ ይህም ሆኖ ግን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ሙጋቤ ስልጣናቸውን የለቀቁት 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር ሲሉ መዘገባቸውን አስረድቷል፡፡
መገናኛ ብዙሃኑ ከዚህ በተጨማሪም ሙጋቤ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው የሚለቁ ከሆነ በራሳቸው መሬት ላይ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት እንደሚገነባላቸውና ጥበቃዎችን ጨምሮ ሙሉ ሰራተኞች እንደሚቀጠሩላቸው ተነግሯቸው ነበር ማለታቸውንም ዘገባው አስታውሷል።

Read 2066 times