Sunday, 07 January 2018 00:00

ሰሜን ኮርያ በከሸፈ ሚሳኤል ራሷን መደብደቧ ተረጋገጠ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    አገሪቱ በ2016 ካደረገቻቸው 6 የሚሳኤል ሙከራዎች 3ቱ ከሽፈዋል

    ነጋ ጠባ ሚሳኤል እያስወነጨፈች የጎረቤቶቿንና የተቀረውን አለም ቀልብ በመግፈፍ ላይ የምትገኘው ሰሜን ኮርያ ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ለሙከራ ያስወነጨፈቺው ባለስቲክ ሚሳኤል መክሸፉና ከመዲናዋ ፒንግያንግ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ከተማን መደብደቡ መረጋገጡን  ኒውዮርክ ፖስት ዘግቧል፡፡
ሰሜን ኮርያ ባለፈው አመት ካደረገቻቸው ስድስት የሚሳኤል ሙከራዎች ሶስቱ መክሸፋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤በሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ያስወነጨፈቺው ሃዋሶንግ 12 የተሰኘ ባለስቲክ ሚሳኤል ለአንድ ደቂቃ ያህል ከተጓዘ በኋላ በመክሸፍ ተመልሶ ቁልቁል ወርዶ፣ ቶክቹን የተባለቺውን የአገሪቱ ከተማ ማጥቃቱን አመልክቷል፡፡ ይሄው መካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ባለስቲክ ሚሳኤል ፑክቻንግ ከተባለው የአገሪቱ የማስወንጨፊያ ተቋም ከተተኮሰ በኋላ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት ሞተሩ መበላሸቱንና ወደ መሬት ተመልሶ በቶክቹን ከተማ ይገኙ የነበሩ የኢንዱስትሪና የግብርና መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን አንድ የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣን በምርመራ አረጋግጠናል ማለታቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
የከሸፈው ሚሳኤል ያደረሰውን ሰብዓዊ ጉዳትና ዝርዝር ጥፋት ለማወቅ ባይቻልም በሳተላይት የተነሱ ምስሎች ግን ከፍተኛ ጥፋት ማድረሱን እንደሚያመልክቱ የጠቆመው ዘገባው፤ የሚሳኤሉ መክሸፍ ከዚህ ቀደም በወሬ ደረጃ ቢነገርም በተጨባጭ ተረጋግጧል የሚል ዘገባ ሲወጣ ግን ይህ የመጀመሪያው መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 4023 times