Print this page
Saturday, 06 January 2018 13:28

‹‹…ሐኪም የታካሚውን መብት…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(0 votes)

 በሕክምና ስነምግባር ውስጥ አንድ ከጠቅላላው ስነምግባር ጋር በተያያዘ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ እሱም የህክምና ባለሙያው ለአንድ ሰው ሕክምና ሲያደርግ ምን ማድረግ ይገባዋል የሚል ነው፡፡ በእርግጥ የህክምና ሙያ ስነምግባር ከሌላው ስነምግባር ይለያል ለማለት ሳይሆን ነገር ግን በስራ ባህርይው ይዋል ይደር የማይባል እንዲሁም በሚሰጠው አገልግሎት መዛባት ከተከሰተ ሕይወትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያሳልፍ በተቃራኒው ደግሞ ከሞት አፋፍ ላይ የደረሰን ሕይወት እንዲቀጥል ማድረግ የሚያስችል ሙያ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል ይላል ዶ/ር አዳሙ አዲሴ የሰጡን ዶክመንት ፡፡ዶ/ር አዳሙ በዚህ እትምም ቀሪውን ቁምነገር ለአንባቢ ያጋራሉ፡፡
በሕክምናው ስነምግባር አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር …ይላል ጽሁፉ ፡፡ልዩ ትኩረትን ይሻል ቢባልም ነገር ግን ህይወትን በሚመለከት መጀመሪያና መጨረሻ ተደርጎ መታሰብ እንደሌለበትና ይልቁንም የሐኪሙና ታካሚው መቀራረብ ፣ሰዎች በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ምን ውሳኔ አላቸው? የአካል ንቅለ ተከላ ፣የጤና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች ስርጭት ፣ስለጤና አጠባበቅ ያለው አቅም ፣አለምአቀፉ የጤና አጠባበቅ ወይንም አገልግሎት ጉዳይ ምን እንደሚ መስል መመልከት እና ሐኪሙ በግል ወይንም በአዛዥነት ሰሜት በታካሚው መብት መወሰን እና ከታካሚው ጋር በመቀራረብ የታካሚውን መብት በማክበር መመራት መካከል ያለ ውን ልዩነት የሙያ ስነምግባሩ የሚያወጣቸው የአሰራር ስልቶች ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡ ይህም በሐኪሙና በሕመምተኛው መካከል የሚኖረው ቅርበት ወይንም ግንኙነትን በሚመ ለከት በሐ ኪሙ አዛዥነት ብቻ የህክምናው አገልግሎት መሰጠቱ ትክክል እንዳልሆነ ለማሳየትና ፍላጎቱ ንም ለመገደብ ያገለግላል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት የነበረው አሰራር ሐኪሞች ሁሉን ነገር ይወ ስናሉ፡፡ታካሚዎች ደግሞ ይቀበላሉ… የሚል አይነት ነበር፡፡ አሁን ግን ያ አካሄድ ተለውጦ ሐኪም የታካሚውን መብት ያከብራል፡፡ በተፈጠረው የጤና መዛባት ላይ ሁለቱም በግልጽ መወያያት አለባቸው፡፡

ዶ/ር አዳሙ እንደሚያብራሩት የህክምና ስነምግባር አለም አቀፍ ነው፡፡ መርሆዎቹም በየትኛውም አገር ያሉ የህክምና ባለሙያዎች የሚሰሩበት ወይንም የሚከተሉት ነው፡፡ እነዚህ መርሆዎችም በደረጃ የተከፋፈሉ ናቸው፡፡
የታካሚዎችን መብት ማክበር (ለታካሚዎች አስፈላጊውን አክብሮት …መረጃ መስጠት እና መወሰን በሚገባቸው ቦታ ላይ በበቂ ሁኔታ መረጃው ገብቶአቸው የራሳቸውን ውሳኔ እንዲሰጡ የማስቻል መብታቸውን ማክበር የሚለውን ያጠቃልላል፡፡ስለዚህም ከሕክምናው ጋር በተያያዘ የሚሰጠው መድሀኒት ምንድነው? የቀዶ ሕክምና ያስፈልጋል ወይ? ለምን? የሚለውን ሐኪሙ ለታካሚው እንዲያስረዳ ሙያው ያስገድደዋል፡፡
የሕክምና ሙያ ስነምግባር ሌላው የሚመለከተው ነገር የህክምናው ጠቀሜታ ምንድነው? የሚለውን ነው፡፡ ሐኪሙ ከታካሚው ፊት ሲሆን ሁልግዜ እንዲያስብ የሚፈለገው የምሰጠው ሕክምና ለዚህ ታካሚ ምን ይጠቅማል? የሚለውን መሆን አለበት፡፡ በእርግጥ ይህ ምንም አጠያያቂ ሆኖ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ወደሕክምና ትምህርት ቤት ገብቶ ሙያውን የሚማረው ሕመምተኛን አድናለሁ ብሎ ነው፡፡ ነገር ግን እንደሰው አንዳንድ ጊዜ የጥቅም ግጭት የሚባል ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡ ለምሳሌም አንድ ሕመምተኛ ኦፕራሲዮን መደረግ አለብህ ሲባል ከታካ ሚው ፍላጎትና የጤና ሁኔታ በመነሳት ነው? ወይንስ ሐኪሙ ያንን በመስራቱ የሚጠቀ መው ነገር ስላለ ነው? የሚለውን ለመለየት እንዲያስችል ነው፡፡
ዶ/ር አዳሙ አክለውም ወታደሮች ሀገር ለማስከበር የህይወት መስዋእትነት እንደሚከፍሉት ሁሉ የህክምና ሙያም መስዋእትነትን የሚያስከፍል ነው ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ይህ ኃላፊነት ቢዘነጋም በመመሪያ ደረጃ ግን አገልግሎቱ እስከመስዋእትነት ድረስ ከፍ ያለ መሆኑን መቀበል ግድ ይሆናል፡፡ የሙያ ስነምግባሩም ሊያሳይ የሚገባው ይህንኑ ነው፡፡ የታካሚዎችን ጥቅም እንደማሰብ ሁሉ ታካሚን ሊጎዳ የሚችል ነገር መኖር አለመኖሩንም አስቀድሞ ማገናዘብ ይገባል፡፡ ለምሳሌም መድሀኒት ለበሽተኛ ሲታዘዝ መድሀኒት ጥቅም እንደሚኖረው ሁሉ የጎን ዮሽ ጉዳትም አለው፡፡ ስለዚህ ሐኪሙ ወይንም የመድሀኒት ባለሙያው መድሀኒቱን ለታካሚው ሲሰጡ መድሀኒቱ ጠቃሚ እንደሆነና ነገር ግን የጎንዮሽ ጉዳት እንዳያመጣ ሊወሰዱ የሚገባ ቸውን ጥንቃቄዎች፣ አመጋገቦች ሁሉ በዝርዝር ማስረዳት ከባለሙያዎቹ ይጠበቃል፡፡ ይህ ቸል ከተባለ ከህመሙ ሊያገግም ያሰበው ሕመምተኛ በሌላ በሽታ ተይዞ የማይጎዳበት ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህም ታካሚው ሐኪሙን የሰጠኸኝ መድሀኒት ሌላ በሽታ አመጣብኝ ብሎ ቢጠይቅ እንደስህተት የማይቆጠርበት መንግድ አለ፡፡  የህክምና ሙያ ስነምግባሩ እንደነዚህ አይነት ኃላፊነቶ ችንም ሊያመላክት ይችላል፡፡
ለምንድነው ታካሚዎች ሐኪሞች ላይ ክስ የሚመሰርቱት ተብሎ ሲጠየቅ አንዳንድ ጊዜ ታካሚዎች በትክክል የተፈጠረውን ችግር እና ሐኪሙ ሕመምተኛውን ለመርዳት ሲል ስራውን በመስራት ላይ እንዳለ የተፈጠረ ስህተት መሆኑን ካለመረዳት የሚመጣ ነው እንደ ዶ/ር አዳሙ አባባል፡፡ በእርግጥ ታካሚውም ሆን ብሎ ችግር ለመፍጠር ሲል የሚያነሳው ጥያቄ ነው ለማት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡- ድንገተኛ ወይንም አስቸኩዋይ ነገር ተፈጥሮ ቶሎ ወደቀዶ ሕክምና የገባ ሐኪም አስቀድሞ መረጃ ላይሰጥ ይችላል፡፡ ስራው ከተጠናቀቀ በሁዋላ ግን መረጃውን ለሚመ ለከተው ወይንም ለታካሚው ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ይህ እንግዲህ ከሕይወት የሚ በልጥ ነገር ስለሌለ በድንገት የሚኬድበት አሰራር ነው፡፡ በዚህ መካከል ሕይወት ከተረፈ በሁዋላ ግን በታካሚው ዘንድ ሊነሱ የሚችሉ ትናንሽ ጥያቄዎች ወደተጠያቂነት ሊያመሩ የሚችሉበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ እንደዚህ ያሉት ነገሮች በሙያ ስነምግባሩ ላይ በግልጽ ሲሰፍሩ ለታካሚውም ሆነ ለሐኪሙ በጋራ የሚጠቅም ነገር ይኖራል፡፡
ሌላው እምነትን ማሳደር ነው፡፡ ታካሚዎች በሐኪሙ ላይ …ሐኪሙም በታካሚዎች ላይ እምነትን ማሳደር የሚገባ ሲሆን በእርግጥ እምነት ሲባል ተጠያቂነት የሌለበት እምነት ሳይሆን ሐኪሙ ጥፋት ካለበት ሊጠየቅ እንደሚገባ በማመን ነው፡፡ ስለዚህም ሐኪሙ በታካሚው እምነት እንዲያድርበት አድርጎ መስራት እንደሚ ገባው የሚያሳይ ነው፡፡
የህክምናው ዘርፍ የተለያየ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ከሌሎች የህክምና ዘርፎች ውስጥ ብዙ ክስ የሚነሳበት ፍርድ ቤት ድረስ የሚቀረብበት ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ይህ ለምንድነው?
ዶ/ር አዳሙ እንደሚሉት የማህጸንና ጽንስ ሕክምና አብዛኛውን ጊዜ ከቀዶ ሕክምና ጋር የሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አንዲት እርጉዝ ሴት በተለያየ ምክንያት ልጅዋን ከቀዶ ሕክምና አገልግሎት ውጭ ልትገላገለው ካልቻለች እና ያ ደግሞ ለእስዋም ሕይወት አስጊ ከሆነ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ምን አይነት ይሁን የሚለውን የሚወስነው ሐኪሙ ነው፡፡ በእርግጥ እናትየው ቀዶ ሕክምና ሊደረግላት መሆኑን ቢነገራትም ያ ባይሆን ግን በልጅዋ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ምን እንደሆነ ለማስረዳት ሊከብድና እስዋም በቀላሉ ልትረዳው የማትችለው ሆናል፡፡ ስለዚህም ሐኪሙ በአስቸኳይ ቀዶ ሕክምናውን ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ሕክምናው ካለፈ በሁዋላ የእናትየውም ሆነ የልጁ ሕይወት በጤና ከቀጠለ በሁዋላ ታካሚዋ ቀላል በሆነው ጉዳይ ጥያቄ ልታነሳ ትችላለች፡፡ለምሳሌ….ቀዶ ሕክምናው ሲደረግ የተከሰተው ጠባሳ  በዚህ መልክ መሆን አልነበረበትም የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ የሐኪሙ እሩጫ ህይወት ለማዳን የነበረ ሲሆን የታካሚዎቹ ጥያቄ ደግሞ ከውበት ጋር የተያያዘ ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚበልጠው ጥቅሙ ነው ወይንስ ጉዳቱ? የሚለውን መመዘን ያስፈልጋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለታካሚ ሲሰጥ ያልታሰቡ ነገሮች ሊገጥሙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌም ሐኪሙ ሕጻኑን ለማትረፍ ሲል እናትየውን ኦፕራሲዮን ቢያደርግ እና ህጻኑ በአጋ ጣሚ ባይተርፍ በቀጥታ ምክንያት የሆነው ሐኪሙ ነው ወይንም ሐኪሙ ጥፋተኛ ነው ማለት አይደለም፡፡ ባለጉዳዮች እንደዚህ ያለውን ጥያቄ ማንሳት የለባቸውም ለማለት ሳይሆን ግን ምክንያቱን በትክክል መረዳት እና የትጋ ችግር እንደተፈጠረ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ጥያቄ እንኩዋን ቢነሳ መጀመሪያ የት ሊታይ ይገባል? ፖሊስ? በመስ ሪያ ቤቱ የስነምግባር ኮሚቴ? በመገናኛ ብዙሀን? የት ድረስ መሄድ ይገባል? የሚለውንም ማገና ዘብ ይጠበቃል፡፡ እንደአካሄድ ግን መጀመሪያ መታየት ያለበት በሙያው ነው፡፡ ብለዋል ዶ/ር አዳሙ፡፡  
በኢትዮያጵያ የህክምና ማህበሩ ያወጣው (Code of Practice) አለ፡፡ ስለዚህም ሕክምና በየጊዜው እያደገ ሳይንሱ እየተሻሻለ የሚሄድ በመሆኑ በእርግጥ አንድ ጊዜ መመሪያ ወጥቶአል ተብሎ የሚተው ባለመሆኑ በየጊዜው እየታደሰ ነጥቦች እየተካተቱበት ይገኛል፡፡ስለዚህም የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች የሙያ ስነምግባርም ከዚህ በመነሳት በሙያው ያሉ የተለዩ ነጥቦችን በማካተት ለመስራት የተጀመረ በመሆኑ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ዶ/ር አዳሙ አዲሴ ገልጸዋል፡፡

Read 2220 times