Saturday, 13 January 2018 15:03

አሜሪካ በኢትዮጵያ ለሚጓዙ ዜጎቿ ማስጠንቀቂያ ሰጠች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፤ የዓለም ሃገራትን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው የደረጃ ሰንጠረዥ፤ ኢትዮጵያን በጉዞ ወቅት የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ከሚያስፈልግባቸው ሃገራት ተርታ መድቧታል፡፡
በደረጃ አንድ የተመደቡ ሀገራት የተለመደው ጥንቃቄ ተደርጎ ጉዞ ሊደረግባቸው የሚችሉ ሲሆን ኢትዮጵያ የተመደበችበት ደግሞ የፀጥታ ሁኔታቸው የሚያሰጋና በጣም ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ከሚገቡ ሀገራት ተርታ ነው ብሏል- የአሜሪካ ድምፅ ባቀረበው ዘገባ፡፡
የግጭቶች የመከሰት እድሉ ከፍተኛ መሆኑንና  መንግስት ኢንተርኔት በተደጋጋሚ መዝጋቱ ሀገሪቱን በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ከሚያስፈልጋቸው ሀገራት እንድትመደብ ዋና ምክንያት ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲም በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ዜጎቹን በመረጃ መድረስ እንደማይችል ተጠቅሷል፡፡
አሜሪካውያን በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንዲከታተሉና ለመረጃዎች ንቁ እንዲሆኑ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የጉብኝትና የጉዞ አካባቢዎችንም በ4 ደረጃዎች መድቦ፣ ዜጎቹ ጉዟቸውን በጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰበው መግለጫው፤ በአንደኛ ደረጃ የተመደቡት የተለመደ ጉዞ ማድረግ የሚቻልባቸው ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌና አፋር ክልል የደናክል አካባቢ በ3ኛ ደረጃ የተመደቡ መሆኑ ታውቋል፡፡ በ3ኛ ደረጃ የተመደቡ አካባቢዎች የሚደረጉ ጉዞዎችን ደጋግሞ በማሰብ፣ እስከመሰረዝ የሚገቡ ናቸው ይላል ሪፖርቱ፡፡
ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት ያለባቸው የምስራቅ ሃረርጌ አካባቢ ግጭቶች ሊያገረሹ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ተጠቁሟል፡፡
ደህንነታቸው ፍፁም የተጠበቀ አይደለም ተብለው በ4ኛ ደረጃ ከተመደቡት መካከል ደግሞ የሶማሌ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡ የጉዞ ማስጠንቀቂያው በ4ኛ ደረጃ ወደተመደቡ አካባቢዎች የሚደረግን ጉዞ ይከለክላል፡፡
ሁኔታዎች በተሻሻሉ ቁጥር በሪፖርቱ ላይ ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡

Read 5714 times