Saturday, 13 January 2018 15:05

የታሰሩ ፖለቲከኞች የሚፈቱበትን ቀን በተስፋ እየተጠባበቁ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  በፍቺያቸው ጉዳይ ፍንጭ አለመገኘቱን ጠበቆች ተናግረዋል

    የታሰሩ ፖለቲከኞች  ለተሻለ ሀገራዊ መግባባት ሲባል በምህረት ወይም በይቅርታ ከእስር ይፈታሉ መባሉን ተከትሎ፣ ታሳሪዎች በተስፋ እየተጠባበቁ ቢሆንም እስከ ትናንት አመሻሽ ድረስ አንድም በምህረት ወይም በይቅርታ የተፈታ ፖለቲከኛ አለመኖሩን ከጠበቆችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም የአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ የፖለቲካ አመራሮችና ግለሰቦች ከእስር ይለቀቃሉ ቢሉም እስካሁን የተፈታ የፖለቲካ አመራር አለመኖሩን ጠበቆች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ከ600 በላይ ለሚደርሱ የሽብር ተከሳሾች እንዲሁም ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎች በነፃ የህግ ድጋፍና ምክር በመስጠት በጥብቅና እያገለገሉ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ወንድሙ ኢብሳ፤ ጉዳያቸውን ከሚከታተሉላቸው ፖለቲከኞች መካከል የተፈታ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ተጨማሪ በቀረበባቸው የአቃቤ ህግ ማስረጃ መሰረት ለጥር 24 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ያስታወሱት አቶ ወንድሙ፤ የመንግስት አመራሮች የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ፣ ዶክተሩ ከእስር እፈታለሁ የሚል ተስፋ አድርገው እንደነበር ጠቁመው ሆኖም እስከ ትናንት አመሻሽ ድረስ የደረሳቸው ምንም መልዕክት እንደሌለ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙ ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባም ክሳቸው የሚቋረጥ ስለመሆኑ ፍንጭ አለመገኘቱን የጠቆሙት አቶ ወንድሙ፤ ይፈታሉ ተብሎ ሲጠበቅ በፍ/ቤት መዳፈር የ6 ወር ቅጣት እንደተጣለባቸውም አስታውቀዋል፡፡
ለሽብር ተከሳሽ ጋዜጠኞች፣ ለፖለቲካ ሰዎችና ግለሰቦች የህግ ማማከርና ጥብቅና አገልግሎት በመስጠት የሚታወቁት ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ አመሃ መኮንንም እስከ ትናንት ድረስ መንግስት ቃሉን ጠብቆ ከእስር የፈታቸው ፖለቲከኞች አለመኖራቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
አመራሮቻችን ታስረውብናል በማለት ተደጋጋሚ መግለጫ ከሚሰጡ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ፤ የቀድሞ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረን ጨምሮ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ አመራሮቹና አባላቱ በእስር ላይ እንደሚገኙ ነገር ግን በሳምንቱ ውስጥ የተፈታ እንደሌለ ገልጿል፡፡
የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ የታሰሩት አመራሮቻችን ይፈታሉ ብለን ስንጠብቅ በጎን ሌሎች አመራሮቻችን እየታሰሩብን ነው ሲሉ በደቡብ ክልል በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀናት የታሰሩባቸውን አመራሮች ጠቅሰዋል፡፡
የፓርቲው የቀድሞ ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ መኮንንና የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት አባል የነበሩት መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ቀደም ሲል በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በነፃ ተሰናብተው ከእስር ቤት ወጥተው የነበረ ቢሆንም ከ6 ወራት ቆይታ በኋላ ሰሞኑን አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆባቸው፣ ለጥር 16 ቀን 2010 ጉዳያቸው መቀጠሩን ያስታወቁት አቶ ሙሉጌታ እስሩና ወከባው ይበልጥ በርትቷል ብለዋል፡፡
ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው፤ ታሳሪዎች ይፈታሉ ተብሎ የሚጠበቀው በይቅርታ፣ በምህረትና በአመክሮ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ አንድ ሰው በይቅርታ የሚፈታ ከሆነ ስሙ ከወንጀል መዝገብ ላይ አይነሳም፣ በምህረት ከሆነ ግን ሙሉ ለሙሉ ከክሱ ነፃ ይሆናል ብለዋል፡፡ እሳቸው በፍ/ቤት የሚከራከሩላቸው ዶ/ር መረራ፣ አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች የኦፌኮ አመራሮች ይህን ምህረት በተስፋ ሲጠባበቁ መሰንበታቸውን አቶ ወንድሙ አስታውቀዋል፡፡   

Read 3875 times