Saturday, 13 January 2018 15:22

ለሰማዕቶቻችን አንድ ቀን!!

Written by  አያሌው አሰረስ
Rate this item
(0 votes)

 መጋቢት 28 ቀን 1928 ዓ.ም ጀኔራል ቦዶሊዮ አዲስ አበባን ያዘ፡፡ ለዚህ ዘመቻ 13 ሺህ ወታደር አሰልፎ ነበር፡፡ በዚሁ ቀን በነበረ ተቃውሞ፣ 1500 የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተገድለዋል። ጣሊያኖች  ‹‹የመጣነው ኢትዮጵያን ለማሠልጠን ነው›› በማለት አስቀድመውም የሰበኩ ቢሆንም፣ ከባንዳዎች በስተቀር አዎ ብሎ እጁን ዘርግቶ የተቀበላቸው  ኢትዮጵያዊ  አላገኙም፡፡ ወጣት ምሁራንና ካህናት፣ ውስጥ ለውስጥ  ጸረ ኢጣሊያ ቅስቀሳቸውን በማፋፋማቸው፣ ከተማዋ አንድ ቀን በአርበኞች እጅ ልትወድቅ ትችላለች የሚል ሥጋት ገና በጥዋቱ  እያደረባቸው መጣ፡፡
አዲስ አበባ በተያዘች በአራተኛ ወር፣ በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ አርበኞች በአራቱም አቅጣጫ ጥቃት በመሰንዘር፣ የአዲስ አበባ ከተማን ለመያዝና ጠላትን ለማስወጣት ለሐምሌ 28 ቀን 1928 ዓ.ም ቀጠሮ ያዙ፡፡ በመገናኛ ችግር እቅዱ እንደታሰበው ባይሄድም፣ የደጃዝማች ፍቅረ ማርያም ጦር እስከ ቤተ መንግሥቱ ፣ የደጃዝማች ባልቻ እስከ አሮጌው አይሮፕላን ማረፊያ (የአሁኑ ጦር ኃይሎች) ድረስ አጠቃ፡፡ ለዚህ ዘመቻ ከጦሩ ጋር ወደ አዲስ አበባ የመጡት አቡነ ጴጥሮስ በጠላት እጅ ወደቁ፡፡
ጣሊያኖች የአቡኑ መያዝ ትልቅ ድል ሆኖ ታያቸው፡፡ የኢጣሊያን መንግሥት ይቀበሉ ዘንድ በወቅቱ ለጣሊያን ባደሩ መኳንንትም ጭምር  አስለመኗቸው፡፡ አቡኑ ግን የሚታጠፍ እምነትም አቋምም አልነበራቸውምና ለፍርድ ቀረቡ። እንዲገደሉ ተፈረደ፡፡ ሕዝብ በተሰበሰበበት  በአምስት አልሞ ተኳሾች ፊት ቆመው፣ ሕዝቡም መሬቱም ለኢጣሊያ እንዳይገዛ ገዘቱ፡፡ ወዲያው የአልሞ ተኳሾች ጥይት እላያቸው ላይ ፈሰሰ። በወደቁበት በሶስት ጥይት የምርመራ ተኩስ ሕይወታቸው አለፈ፡፡ ሕዝቡ ይበልጥ  ተከፋ፡፡
ጣሊያኖች የከተማዋን ጥበቃ ያጠናከሩት በዚህ ጊዜ ይመስላል፤ 3ሺ ሊቢያዊያን፣ 5ሺ ኤርትራዊያን፣ 35ሺ ሜትሮ ፖሊታንት እና 40ሺ የፋሺዝም ታማኝ ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ወታደሮች፣ በድምሩ 83ሺ የጦር ኃይል አዲስ አበባ ውስጥ እንዲኖራቸው አደረጉ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝብ መከፋት እየባሰ በመሄዱ፣ ግራዚያኒ ተቃውሞውን የሚያለዝብበት መንገድ እየፈለገ በነበረበት ወቅት  አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። በኢጣሊያ የሲሲሊ ግዛት ልዕልት ወለደች። የልጁን ልደት ምክንያት በማድረግ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም  ለድሆች ምጽዋት ለመስጠት ታሰበ፤ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ (ባሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) እንዲገኙ ተጠሩ፡፡ የከተማዋ ነዋሪ  አለባበሱን አሳምሮ እንዲወጣ፣ ባይወጣ ግን እንደሚቀጣ ተለፈፈ፡፡
የኢጣሊያን ጦር በእነሱ ክንድ ከሀገር ማስወጣት ባይችሉ እንኳ ጨካኙን ግራዚያኒን በመግደል የኢትዮጵያን ሕዝብ አፎይ ለማሰኘት፤ አልፎም በዓለም ፊት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን  በሰላም እየገዛች፣ ሕዝቡም ለጥ ሰጥ ብሎ እየተገዛ  አለመሆኑን ለማሳየት የፈለጉት አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስጎደም እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው ይህን ቀን እየጠበቁት ነበር፡፡
ጀኔራል ግራዚያኒ፤ ‹‹አርበኞች ነን ባዮች በየሸለቆው እየተሽሎከለኩ ያልቃሉ፡፡ ከታላቁ ገዥ ሞሶሎኒ የመጣላቸውን ምህረት ቢቀበሉ ይድናሉ። ታላቋ ኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካን በቁጥጥሯ ሥር ሳታደርግ አታርፍም ›› በማለት  ለተሰበሰበው ሕዝብ እየተናገረ እያለ፣  እነ አብርሃም አከታትለው ሰባት ቦምቦች ወረወሩ፡፡ ሰላሳ የኢጣሊያ ባለሥልጣናት ቆሰሉ፡፡ የመርዝ ጋዝ በሕዝብ ላይ የሚያዘንበው የአየር ኃይሉ አዛዥ ተገደለ፡፡ ከድንጋጤያቸው እንደ ወጡ ካራሚኔሮች (ባንዳ ወታደሮች ) ተኩስ ከፈቱ። ጄኔራል ግራዚያኒና  በአዲስ አበባ የፋሺስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጉይዳ ክርስቲ፤  ‹‹በዚህ ሶስት ቀን ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን አጥፉ›› ሲሉ የግድያ ትእዛዝ ሰጡ፡፡ እጅግ የከፈው የብቀላ ተግባር  ተጀመረ፡፡ ጭፍጨፋውን በምስል ማስቀረት እንዳይቻል ፎቶ ግራፍ ማንሳት ተከለከለ፡፡ ፎቶ ግራፍ ማንሻ  የያዙ ሰዎች ተነጠቁ፡፡
በጥቂት ሰዓታት ውስጥ 300 ሰዎች ቤተ መንግሥቱ ግቢ ውስጥ ተገደሉ፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ የሚወስዱ መንገዶች በሬሳ ተሞሉ። ሰዎች በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ፣ በምንገድ የተገኙት ወደ ቤት እንዲገቡ እየተደረገ  እየተዘጋባቸው፣ ቤቱ ላይ ቤንዚን እየተርከፈከፈ እንደ ጧፍ ነደዱ፡፡ ነፍስያ ይዟቸው ከእሳቱ ለመውጣት የሚሞክሩት በመትረየስ ጥይት ተለቀሙ፡፡ ጣሊያኖች ክርስቲያኖች ናቸው፤ ያዝኑልናል  ብለው  ጊዮርጊስ የተጠለሉትም ከእነ ቤተ ክርስቲያኑ እሳት እንዲበላቸው ሆነ፡፡ የፋሺስት ባለሥልጣናት ሚስቶችም፣ ይህን እልቂት እንደ አንድ ልዩ ትርኢት ተመለከቱት፡፡ ግራዚያኒም ከተኛበት ሆስፒታል ሆኖ አዲስ አበባ እየነደደች እንዳለች ተመለከተ፡፡
የኢጣሊያ ወታደሮች ከሚገሏቸው ሰዎች የሚያገኙትን ገንዘብና ጌጣ ጌጥ እንዲሁም ከሚበረብሩት ቤት የሚያገኙትን ገንዘብ፣ ባንክ ቤቶች ሌሊቱን ሁሉ ከፍት ሆነው እንዲጠብቋቸው ተደርጎ፣ የዘረፉትን ሃብት ያለ ገደብ  እንዲያከማቹ ተደረገ፡፡ ደህና ደህና ቤቶች ላይም ‹‹የእኔ ነው›› እያሉ የባለቤትነት ማስታወቂያ ለጠፉ፡፡ አንዱ መቶ ሌላው ሰማኒያ እንደገደለ፣ አንዱ ባንድ ትንሽ ጣሳ በያዘው ቤንዚን አስር ቤት እንዳቃጠለ፣አንዱ ብቻ ሁለት ሰው እንደገደለ-- (ስለ አነሰበት እየተጸጸተ ይመስላል) በወቅቱ መናገራቸውን ታሪክ መዝግቦታል፡፡
መሣሪያ በእጃቸው ጨብጠው  የማያውቁ ተኳሽና ገዳይ በሆኑባቸው በነዚያ ሶስት ቀናት፣ የጦር ሠፈር ለመጠበቅ ከቀረው የኢጣሊያ ሠራዊትና ‹‹ምንም መሣሪያ ባልያዘ ሕዝብ ላይ አንተኩስም›› ብለው ከአመጹና ከታሰሩ አንዳንድ ኤርትራዊያን በስተቀር ኢትየጵያዊያንን ለመግደል ያልተሰለፈ የጠላት ኃይል አልነበረም፡፡ በወቅቱ  አንድ መቶ ሺህ በሚገመተው የአዲስ አበባ ኗሪ ላይ፣ በግምት ከስልሳ ሺህ በላይ ገዳይ ሠራዊት ዘምቶበት፣ አንዱ እስከ መቶ እንደገደለ  እየተናገረ በዚህ ጊዜ ያለቀውን የአዲስ አበባን  ሕዝብ ከሰላሳ ሺህ በላይ ይሆናል ብለው የገመቱ አሉ፡፡ ይህን ግምት መቀበል የከበደው አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የካቲት 12 ቀን 1954 ዓ.ም ባወጣው እትሙ፣ የካቲት 12ን ‹‹ አረመኔው ፋሺስት ሴትና ልጅ ሳይል ቁጥራቸው ከሰማኒያ ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያንን በገፍ የፈጀበት ቀን ነው›› በማለት ገልጾታል፡፡  ግድያው በአዲስ አበባ ተወስኖ አለመቅረቱና የደብረ ሊባኖስ መነኮሳትም መገደላቸው መታወስ  ይኖርበታል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› በተባለው መጽሐፉ፤ (ለዚህ ጽሑፍ ዋና የመረጃ ምንጭ) በዚያን ጊዜ ታፍሰው ኢጣሊያ ሶማሊ ላንድ ተወስደው ታስረው የነበሩት አቶ ሚካኤል ተሰማ፤  ‹‹በምግብ ችግር በቀን ከአስር እስከ ሰላሳ ሰው ይሞት ነበር›› በማለት ምስክርነታቸውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስጠታቸውን ገልጧል፡፡
ከተፈጸመው ጥቃት በላይ በብዙ እጥፍ በሆነ በቀል ኢትዮጵያዊያን ያለቁበትን ቀን፣ ታሪክ ጸሐፊው ተድላ ዘዮሐንስ፤ “በኢትዮጵያ የነጻነት ትግል ውስጥ  አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት እለት” በማለት ገልጸውታል፡፡ ለዚህ ቀን  መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የካቲት 12 ሆስፒታል ፊት ለፊት የሚገኘው የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ቀኑም ‹‹የሰማዕታት ቀን›› ተብሎ በየዓመቱ የካቲት 12 ቀን በብሔራዊ በአልነት  እስከ ንጉሠ ነገሥቱ የመንግሥት ዘመን  ፍጻሜ ድረስ ሲከበር ቆይቷል፡፡
ደርግ በ1967 ዓ.ም የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ጊዜ ሶስት የእስልምና ሐይማኖታዊ ቀኖችን ብሔራዊ በአል በማድረግ ጥሩ ሥራ መሥራቱ ይጠቀሳል፡፡ በአንጻሩ በሚከተለው ርእዮተ ዓለም የተነሳ የዓለም ሠራተኞችን ቀን (May Day) ብሔራዊ በአል አድርጎ ሲያውጅ፣ የካቲት 12 ማለትም የሰማዕታትን ቀንን ግን ታስቦ የሚውል ቀን በማድረግ፣ ኢትዮጵያዊያን ሰማዕታታቸውን የሚያከብሩበት ቀን አሳጣቸው፡፡ ኢሕአዴግም የቀጠለው በዚያው ነው፡፡ መጋቢት 27ን ሰርዞ ሚያዝያ 27ን ሲያጸድቅ፣ የሰማዕታትን ቀን ግን ባለበት ተወው፡፡
ከ1928 እስከ 1933 ድረስ ለአምስት ዓመታት በቆየው የኢጣሊያ ወረራ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። አነዚህ ወገኖቻችን የሚከበሩበት  የሚዘከሩበት ቀን ያስፈልጋቸዋል፡፡
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር”፤ “አንድ ጣት አንድ ነው አምስቱ ቡጢ ነው” የሚሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉን፡፡ ሁሉም የአንድነትን አስፈላጊነት የሚያስረዱ ናቸው፡፡ አንድነት እንኳን በአንድ አገር ሕዝብ መካከል ቀርቶ በአገራትም መካከል አስፈላጊ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወይም ሌሎች መሰል ተቋማት የቆሙት አንድነት አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡
ኤርትራዊያን ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት አሸናፊ ሆና  እንድትወጣ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ከጣሊያን ጋር፣ በኋላም ለአስር አመት ‹‹ኢትዮጵያ ወይም ሞት›› ብለው ከእንግሊዝ የሞግዚት አስተደደር ጋር የተፋለሙት ለነጻነትና ለኢትዮጵያዊነት ነበር፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ የፌደሬሽን ግንኙነት መፍረስ ምክንያት በኤርትራ ምድር በተቀሰቀሰቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ለሰላሳ ዓመታት ከጀበሐና ከሻዕቢያ ጋር ሲፋለሙ አካላቸውንና ሕይወታቸውን የገበሩ ወገኖቻችን (የእኔን ታላቅ ወንድም  መቶ አለቃ ዳኛቸው አስረስን ጨምሮ) ቀደም ሲል የተከፈለውን መስዋእትነት፣ የእነ ራስ አሉላን ተጋድሎ  ለመጠበቅ የተደረገ እንጂ የወረራ አልነበረም፡፡ የፈዴሬሽን ግንኙነቱን መልሶ በማቋቋም ችግሩን ማስወገድ ሲቻል፣ በወታደራዊ ኃይል እንፈታለን ብለው በተነሱ መሪዎች ስህተት፣  የእነ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ የእነ ብላቴን ጌታ ሌሬንሶ ትዕዛዝ፣ የእነ ብላታ ኤፍሬም ተወልደ መድህን  ዲፕሎማሲያዊ ድካም  ሁሉ ከንቱ ሆነ እንጂ አንድ ለሀገሩ ዘብ የሚቆም ዜጋ የሚያደርገውን የፈጸሙ ሰማዕታት ናቸው- በኤርትራ ምድር የተሰዉ፡፡
ሁለት ጊዜ ከሞቃዲሾ መንግሥት፣ አንድ ጊዜ ከኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ወረራ መክተው የሀገራችንን ዳር ድንበር ያስከበሩ፣  ‹‹ከአዲስ ቅኝ ገዥዎች›› መዳፍ እንዳንወድቅ የታደጉን ወገኖቻችን መከበርና መዘከር አይኖርባቸውም? ለእነሱ ክብር ያልሰጠን ለማንስ ልንሰጥ እንችላለን?
ከኮሪያ ጀምሮ አገራችን በተሳተፈችባቸው ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያን  መልካም ስም የተከሉና የጠበቁ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ልፋታቸው ዋጋ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህን በማድረግ የቀደሙትን የማያከብር  ትውልድ፣ እሱን የሚያከብረው ትውልድ በእግሩ እንዴት መተካት ይችላል?
ኢሕአዴግ ግንቦት ሃያን የሚያከብረው ስለአሸነፈ እንጂ የተነሳበት አላማና የተጓዘበት መንገድ የተለየ ሆኖ አይደለም፡፡ የንጉሡን መንግሥት ለመጣል እነ ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ፣ እነ ደጃዝማች ታከለ ወልደ ሐዋርያት ሞክረው ሕይወታቸውን ገብረዋል፡፡ ደርግን ለመጣል ኢዲዩ፣ ኢሕአፓ፣ ኢጭአት ወዘተ ሥር የተሰበሰቡ ወጣቶች ታግለዋል፡፡ በ1981 ግንቦት ኩዴታ የተሳተፉት እነ ጀኔራል ደምሴ ቡልቶም  የሞቱት በዚሁ መንገድ ተጉዘው ነው፡፡ ሁሉም ለሞት የተዳረጉት በግል ጉዳያቸው ሳይሆን ለሀገርና ለሕዝብ በጎ ብለው ያሰቡትን በተግባር ለማየት  ነው፡፡ ኢሕዴግ የራሱን ተጋድሎ እንደሚያከብረው ሁሉ የሌሎችንም መስዋዕትነት ማክበር  የለበትም?
ዛሬ በመንግሥት ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የሚገኙት ሰዎች ከሃያ ሰባት አመታት በፊት ተቃዋሚና በመንግሥት ላይ ያመጹ ነበሩ፡፡ እነሱንም ጨምሮ ትናንት የንጉሡን መንግሥትና የደርግን መንግሥት ትክክለኛ ባልሆነ አመራራቸው ይቃወሙ፣ ትክክለኛው መንገድ ይህ ነው እያሉ ይጮሁ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ ሁሉ  ዛሬም አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ከአንድም ሁለት ጊዜ ተሐድሶ እያለ ወደ ግምገማ የገባው ከብር ለእነሱ ይሁንና ተቀናቃኞቹ፣ በጠራ አማርኛ ተቃዋሚዎቹ በቀሰቀሱትና  ሕዝብ ተቀብሎ በልዩ ልዩ መንገድ ድጋፉን ባሳየበት  ጥያቄ ነው፡፡ ገሞራው (ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ) ‹‹የበሰለው ያራል ጥሬው እሰኪበስል›› ያለውም እንደነዚህ ያሉ ወገኖችን  አስቦ አይደል፡፡
ለአንድ አገርና ሕዝብ የሚከፈል መሰዋዕትነት በጦር ሜዳና በፖለቲካ መስክ ብቻ የተወሰነ  አይደለም፡፡ እንዲህ ሥልጣኔ በእያንዳንዳችን እጅ መዳፍ ላይ ሳይጥለው ዳገት ወጥተው፣ ቁልቁለት ወርደው፣ የበረሃውን ንዳድ ተሸክመው በእባብ እየተነደፉ  በመላ አገሪቱ  የስልክ መስመር የዘረጉ የቴሌ ሰዎች፣ ለዚህች አገር እድገት ሰማዕት አይደሉም? በመንገድ፣ በመብራት፣ በወባ መከላከል ወዘተ በግንባታ፣ በጤና ጥበቃ  ሥራ ላይ ለተሳተፉ ሁሉ፣ አሁን ለአለንበት ቀን ለመድረሳችን ሰማዕት ናቸው፡፡
ድሮ ከዘመነ ኢሕአዴግ በፊት ከአንዱ ጠቅላይ ግዛት ወደ ሌላው የሚደረግ  የመምህራን ዝውውር የሚፈጸመው አዲስ አበባ ላይ ነበር። አንድ ጊዜ ኤሉአባቦር ሞቻ  አውራጃ አምስት አመት የአስተማረ መምህር፤ ‹‹ሞቻ ስንት አመት እንዳስተምር ትፈልጋላችሁ?›› ሲል ይጮኻል። ሹሙ የመለሱለት፤ “የእኔ ጸጉር የተመለጠው ምን ስሰራ ይመስልሃል”  በማለት ነው፡፡ በሲዳሞ አቶ ቦጋለ ዋለሉ፣ በጎጃም አቶ በትረ ጽድቅ ካሳ ለትምህርት መስፋፋት ከፍተኛ መሰዋዕትነት የከፈሉ፣ ትውልድ ሊዘክራቸው የሚገባ ሰዎች ናችው፡፡  በግብርናው፣ በሕከምናው፣ በአስተዳደሩ ወዘተ--- የሥራ መስኮች መጠቀስና በትውልድ ፊት መታወስ ያለበቸው ብዙዎች  አሉ፡፡ እድሉ ከተሰጠ በሩ ከተከፈተ ሕዝቡ በየመስኩ የየራሱን  ፋና ወጊዎች ያወጣቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያ  በየሥራ ዘርፉ ያሉ ውድ ልጆቿን  በብሔራዊ ደረጃ  የምታከብርበት የሰማዕታት ቀን ያስፈልጋታል የምለው፡፡ ሁሉንም የሚያሰባስብና የሚያገናኝ፣ ነባሩን  ከዘመኑ ጋር የሚያዛምድና የሚያስተሳስር አንድ ቀን  ለሰማዕታቶቻችን ያስፈልጋል፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት ሆይ!! ይህን ጉዳይ በቀኝ እጅህ ያዝልን፤ የተረሳን ታሪክ በማክበር ለራስህም ታሪክ ሥራ፡፡ እስቲ 81ኛ ዓመቱን ከነሙሉ ክብሩ ለማክበር አብቃን፡፡

Read 900 times