Saturday, 13 January 2018 15:23

ዘርዓያዕቆብና የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ፅንሰት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(5 votes)

  ክፍል ፩ - የዘርዓያዕቆብ ትንሳኤ

    (ይህ ፅሁፍ በምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን አዘጋጅነት “ዋኖቻችንን እናስብ” በሚል ዓላማ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር፣ ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብን ለመዘከር በተዘጋጀው መድረክ ላይ የቀረበ ነው፣ ከተወሰነ ጭማሪ ጋር)
           
   ታላቁ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዓያዕቆብ በእንደዚህ ዓይነት ከፍ ባለ የኪነ ጥበብ ምሽት ሲዘከር ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡
በዚህ ታላቅ የኪነ ጥበብ ምሽትም የምንዘክረው፣ ከዛሬ 350 ዓመታት በፊት አክሱም ላይ ተወልዶ፣ እንፍራንዝ (ጎንደር) ላይ ስለከተመው እንግዳ ሰው ነው፡፡
ዛሬ፣ አክሱም አባርራው እንፍራንዝ ሸሸጋ ስላቆየችልን፣ የእንፍራንዝን ውለታ እናወራለን።
ዛሬ፣ የንጉሱን ዘርዓያዕቆብ ሳይሆን፣ የፈላስፋው ዘርዓያዕቆብን ርዕይ እንናገራለን።
ዛሬ፣ ከዛሬ 350 ዓመታት በፊት በአንዲት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ሆነው እየተብሰለሰሉ፣ “የሀገሬ ሰዎች፣ የኢትዮጵያ ልጆች!!” እያሉ ስለፃፉት ሀገር ወዳዶቹ ዘርዓያዕቆብና ተማሪው ወልደ ሕይወት እናወራለን፡፡
ከዛሬ 350 ዓመታት በፊት በድብቅ ስለተፃፈው የኢትዮጵያ ራዕይ፣ ዛሬ በአደባባይ እንናገራለን።
ዛሬ፣ በኢትዮጵያ የሥነ ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ “ግለ ታሪክ” (Autobiography) የአፃፃፍ ዘውግን ስላስተዋወቀው ዘርዓያዕቆብ እናወራለን፡፡
ዛሬ፣ ለሺ ዓመታት ከቆየው የገዳማቱ ሥርዓተ ትምህርት አፈንግጦና የስነ ሰብዕ ይዘት ያለው የራሱን አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ለመፍጠር ይተጋ ስለነበረው አፈንጋጩና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው Humanist ዘርዓያዕቆብ እናወራለን፡፡
ዛሬ፣ አፄ ሱስንዮስ  ስለ ሊቅነቱ ምስክርነታቸውን ስለሰጡለት፣ አውሮፓውያን ግን “እንዴት አንድ ኢትዮጵያዊ እንደዚህ ሊያስብ ይችላል?” እያሉ ስለተወዛገቡበት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዓያዕቆብ እንደሰኩራለን፡፡
ምንም እንኳ ሀገራችን በጣም የቆየ ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት የነበራት ቢሆንም፣ ከዚህ ሥርዓተ ትምህርት የወጡ ሊቃውንት ግን የህዝቡን ባህሉንና የርስበርስ ግንኙነቱን ሲፈትሹ፣ አፈ ታሪካዊና ልማዳዊ አስተሳሰቦቹን ሲተቹ፣ ቁሳዊ ህይወቱንም የሚያሻሽሉ ሐሳቦችን ሲያመነጩ አልታዩም። ዛሬ፣ በኢትዮጵያ የምሁራን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ስለሆነው አይምሬው የባህል ሐያሲ እናወራለን፡፡
ዛሬ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሴት መብት ተሟጋች ስለሆነው፣ የሃይማኖትና የግለሰብ ነፃነትም እንዲኖር አብዝቶ ስለተሟገተው ዘርዓያዕቆብና ተማሪው ወልደ ሕይወት እንናገራለን፡፡
ዛሬ፣ “የኢትዮጵያውያን ድህነትና ኋላቀርነት መንስኤው በመንፈሳዊ ህይወትና በዓለማዊ ህይወት መካከል የተፈጠረው የተካረረ ቅራኔ ነው” በማለት መንፈሳዊውንና ዓለማዊውን ህይወት በማስታረቅ፣ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ድህነትና ኋላቀርነት የሚወጡበትን አዲስ የህይወት ፕሮጀክት ይዞ ስለመጣው ዘርዓያዕቆብ እናወራለን፡፡
ዛሬ፣ 17ኛው ክ/ዘ ላይ ሆኖ ወደ ኋላ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ (ከእነ ማስተካከያው)፣ ወደ ፊት ደግሞ በአፄ ቴዎድሮስ የሚጀመረውን የነገስታቱን የዘመናዊነት ፕሮጀክት በመንፈስ የሚያስተሳስረውን ዘርዓያዕቆብን እንዘክራለን።
ይህ ዓመት (2010 ዓ.ም) ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ የሚዘከርበት ዓመት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓመት ብቻ ዘርዓያዕቆብ ላይ የተለያዩ መፃህፍትና መጣጥፎች የተፃፉ ሲሆን፣ በፍልስፍናው ላይም የተለያዩ የግምገማ መድረኮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ በዘርዓያዕቆብ ላይ የሬድዮ ውይይቶችና እንደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደግሞ ህዝባዊ ዲስኩሮች (Public Lectures) ተደርገዋል፡፡ አሁን ደግሞ ታዋቂ ገጣሚያንና ምሁራን በተገኙበት መድረክ ፈላስፋው የሚዘከርበት ታላቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተዘጋጅቶለታል፡፡ የቀረ ነገር ቢኖር የዘርዓያዕቆብ ህይወትና ፍልስፍና ላይ የሚያጠነጥን ፊልምና የስዕል ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት ነው፡፡ እናም 2010 ዓ.ም የዘርዓያዕቆብ ትንሳኤ ነው ማለት እንችላለን።
ዘርዓያዕቆብን ለትንሳኤ ያበቃው ሁለት ገፊ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ከ2004 ዓ.ም ወዲህ በዘርዓያዕቆብ ላይ የተለያዩ የውይይት መድረኮች መዘጋጀታቸው እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የቤ/ክ ሊቃውንት ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ላይ ትኩረት ማድረግ መጀመራቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሊሆኑ የሚችሉት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፣
በ2004 ዓ.ም በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የቀረበ ዲስኩር፣
በ2006 ዓ.ም በፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ የቀረበ የትርጉም ሥራ፣
በ2008 ዓ.ም በአለቃ ያሬድ ፈንታ የቀረበ የትርጉም ሥራ፣
በነሐሴ 2009 ዓ.ም በብሩህ ዓለምነህ የቀረበ የትንታኔ ሥራ፣
ከሐምሌ 2009 እስከ ጥቅምት 2010 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ የወጡ ፅሁፎች፣
በጥቅምትና ህዳር 2010 ዓ.ም በብስራት FM ሬዲዮ ጣቢያ ላይ ለተከታታይ ስምንት ሳምንታት የተዘጋጀው የሬዲዮ ፕሮግራም፣
በ2010 ዓ.ም በዳንኤል ወርቁ የቀረበው የትርጉም ሥራ፣
እንግዲህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘርዓያዕቆብ ላይ በዚህ መልኩ የቀረቡ ስራዎች ተጠራቅመው 2010ን የዘርዓያዕቆብ ትንሳኤ አድርጎታል፡፡
በተለይ በ2004 ዓ.ም በሚዩዚክ ሜይዴይ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ዶ/ር ዳኛቸው፣ ዘርዓያዕቆብ ላይ ያቀረቡት ዲስኩር የበርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ የታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ባቀረቡት የትርጉም ስራ ውስጥም “ዘርዓያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ነው? ወይስ አይደለም?” በሚለው ውዝግብ  ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ያልተሰሙ አዳዲስ ምልከታዎችን በማምጣት የዘርዓያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የቅኔና የአቡሻህር (የባህረ ሐሳብ) ሊቁ የአለቃ ያሬድ ፈንታ ስጦታ ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ የማናቀውን ወልደ ሕይወትን ከዘርዓያዕቆብ ጋር አጣምረው ማምጣታቸው ነው፡፡ የእኔም የትንታኔ መፅሐፍ የዶ/ር ዳኛቸውን፣ የፕ/ር ጌታቸውንና የፕ/ር ክላውድ ሰምነርን ሐሳቦች አጣምሮ የያዘ ነው። በመሆኑም ከ2004 ዓ.ም ወዲህ በሀገራችን ህዝባዊ አደባባይ ላይ ዘርዓያዕቆብ እየነገሰ መጥቷል።
የዘርዓያዕቆብ እየነገሰ መሄድ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የኢህአዴግ የዘመናዊነት ፕሮጀክት መክሸፉን ተከትሎ፣ አዲሱ ትውልድ ለመጪዋ ኢትዮጵያ ትንሳኤ የሚሆን፣ ሁሉንም የሚያስማማ አርዓያ (Role Model) ፍለጋ ላይ ዘርዓያዕቆብ ዕጩ ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡
እንደሚታወቀው 20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ የተነሳው አዲሱ የተማረ ትውልድ ሀገሩን ለማዘመን ሮል ሞዴል አድርጎ የወሰደው ከሀገር ጃፓንን ሲሆን፣ ከንጉስ ደግሞ አፄ ቴዎድሮስን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህ ምኞታቸው ሳይሳካ ተራማጆቹ ምሁራን በአብዮተኞቹ ተማሪዎች ተተኩ፡፡ ተማሪዎቹም በተራቸው ሀገራቸውን ለማዘመን ከሀገር ሩሲያንና ቻይናን፣ ከርዕዮተ ዓለም ደግሞ ማርክሲዝምን እንደ ሮል ሞዴል ወሰዱ፡፡
ሙሉ በሙሉ የባዕዳን ሐሳብ ላይ የተንጠለጠለው የተማሪዎች ርዕይ ግን በሁለት ትውልድ (በደርግና በኢህአዴግ) የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተሞክሮ አልሰራም፡፡ እናም ከኢህአዴግ በኋላ የምትመጣው ኢትዮጵያ ህዝቦቿን ወደፊት የምታራምድበት አዲስ ሀገር በቀል የሆነ ሮል ሞዴል ፍለጋ ላይ ነች፡፡ እኔና አዲሱ ትውልድ፣ ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብን ዕጩ አድርገን አቅርበናል፡፡
ኢህአዴግ በታሪክ ንትርክ ላይ ባበቀለው የብሄር ፖለቲካ የተነሳ ካለፉ ነገስታት መካከል ሮል ሞዴል መፍጠር አንችልም፡፡ ሮል ሞዴል ከውጭ መዋሱም እንደማያዋጣን ከደርግና ከኢህአዴግ ተሞክሮ አይተነዋል፡፡ በመሆኑም ለመጪው የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ነዳጅ የሚሰጠንን ሮል ሞዴል ከሀገራችን ባህልና ታሪክ ውስጥ ማፈላለግ አለብን፡፡
ዘርዓያዕቆብ የአዲሱ የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ውስጥ ሮል ሞዴል ሆኖ ሊቀርብ የሚችልበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ አሁን በተዘፈቅንበት የሃይማኖት፣ የታሪክና የብሄር ንትርክ ውስጥ ገለልተኛ ሆኖ ሁላችንንም ሊያስማማ የሚችለው ዘርዓያዕቆብ ብቻ ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብ በገለልተኛነት ለእውነትና ለዕውቀት በመቆሙ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሮል ሞዴል ሆኖ ቢነሳ ከክርስትያኖችም ሆነ ከሙስሊሞች ድጋፍ ያሰጠዋል፡፡
ሁለተኛ፣ ዘርዓያዕቆብ በያሬዳዊው ሥልጣኔና በአዲሱ ዘመን መካከል አገናኝ መንፈስ ነው። ይሄም የድሮው መንፈስ ተቆርጦ እንዳይጣል ለሚፈልጉ ሰዎች ዘርዓያዕቆብን ቅቡል ያደርገዋል። ምንም እንኳ ዘርዓያዕቆብ ባህልን፣ ልማድን፣ አፈ ታሪክንና ሃይማኖትን የሚተች ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ከፅንሰቷ ጀምሮ ስትቀባበለው ከነበረው መንፈስ የተገነጠለ ሰው አለመሆኑን ግን ማወቅ ያስፈልጋል። ዘርዓያዕቆብ 17ኛው ክ/ዘ ላይ ሆኖ፣ በ6ኛውና በ20ኛው ክ/ዘ ተራማጅ ምሁራን መካከል ንግግር የፈጠረ አገናኝ ድልድይ ነው፡፡ የ20ኛው ክ/ዘ ተራማጅ ምሁራን ያነሷቸው አብዛኞቹ ሐሳቦች (ለምሳሌ - ባርነት እንዲቀር፣ የመሬት ሥሪቱ እንዲሻሻል፣ የሴቶች መብት፣ የሃይማኖት ነፃነት፣ የሐሳብ ብዝሃነትን የሚመለከቱ ሐሳቦች) አስቀድሞ በ17ኛው ክ/ዘ ላይ በዘርዓያዕቆብና በወልደ ሕይወት ተነስተዋል።
ሦስተኛ፣ ጥንታዊዋን ኢትዮጵያ ወደ አዲሱ ዘመን ለማሻገር የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና ምርጥ ሞዴል ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስም ሆኑ አፄ ምኒሊክ ሀገር የማዘመኑን ፕሮጀክት ከላይ (ከፖለቲካው) ነበር የጀመሩት፡፡ እንደዚህ ዓይነት አካሄድ ግን ስህተት እንደነበረ በስተመጨረሻ ነበር የተረዱት። ኢህአዴግም ግለሰብን ትቶ በብሄር በኩል ያመጣው ፕሮጀክት የሚያስኬድ እንዳልሆነ የዚህ ዘመን ሰዎች በተጨባጭ አይተነዋል። የዘመናዊነት ፕሮጀክት በመጀመሪያ መሰራት ያለበት የህዝቡ ባህልና የግለሰብ አእምሮ ላይ ነው፡፡ ይሄ ነው የዘርዓያዕቆብ አቀራረብ፡፡
አራተኛ፣ በአሁኑ ወቅት ዓለም እየተመራበት ያለው የዘመናዊነት ፕሮጀክት ሦስት መርሆዎች አሉት - ዓለማዊነት (Secularization)፣ የግለሰብ ነፃነትና ብዝሃነት፡፡ እነዚህን የዘመናዊነት መርሆዎች የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና ውስጥ በግልፅ እናገኛቸዋለን፡፡ እናም በመጪው የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ውስጥ ዘርዓያዕቆብ ሮል ሞዴል ሆኖ ቢወጣ ሀገራችንን በአሁኑ ወቅት ዓለም ከሚመራበት መንፈስ ጋር ለማስተካከልና ለማዋኻድ ጥሩ አማራጭ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
በክፍል ሁለት ፅሁፌ ዘርዓያዕቆብ እንዴት የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ጠንሳሽ እንደሆነ ከ3ቱ የዘመናዊነት መርሆዎች ጋር በማስተሳሰር፣ የኪነ ጥበበብ ምሽቱ ላይ ያቀረብኩትን ፅሁፍ ዋቢ አድርጌ አቀርባለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡

Read 5064 times