Saturday, 13 January 2018 15:25

“የፕሬስ ነጻነት ጨቋኝ መሪዎች ሽልማት”ን ትራምፕና ኤርዶጋን አሸንፈዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የሩሲያው ፑቲንና የግብጹ አልሲሲም ለሽልማት ታጭተው ነበር

   አለማቀፉ የፕሬስ ነጻነት መብቶች ተሟጋች ተቋም ሲፒጄ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ባደረገው “የአለማችን ቀንደኛ የፕሬስ ነጻነት ጨቋኝ መሪዎች”  ልዩ ምጸት አዘል ሽልማት፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የቱርኩ አቻቸው ጠይብ ኤርዶጋን በተለያዩ ዘርፎች አሸናፊዎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ “የአመቱ ምርጥ ውሸታም ሚዲያዎች ሽልማት” የተሰኘና በአይነቱ ልዩ የሆነ ሽልማት በማዘጋጀት በመጪው ሳምንት አሸናፊዎችን ይፋ እንደሚያደርጉ ባለፈው ሰኞ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ያደረገው ሲፒጄ፤ ዶናልድ ትራምፕ ከጋዜጠኞች የሚሰነዘሩባቸውን ትችቶች እየተከታተሉ በማፈንና የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች በመጣስ፣ ከአለማችን መሪዎች ሁሉ አቻ ስለሌላቸው ሸልሜያቸዋለሁ ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2017፣ በተለያዩ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ላይ እከስሳችኋለሁ ወይም የሥራ ፈቃዳችሁን እነጥቃችኋለሁ በሚል በተደጋጋሚ ዝተዋል ያለው ተቋሙ፤ ትራምፕ ባለፉት ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ በትዊተር ባስተላለፏቸው ከ1 ሺህ በላይ መልዕክቶች፣ መገናኛ ብዙሃንን መዝለፋቸውንና ማስፈራራታቸውን አስታውሷል፡፡ ጋዜጠኞችን ከስራ ትባረራላችሁ ሲሉ በይፋ አስፈራርተዋል፤ ተመልካቾች አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃንን እንዳይከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል፤ ለዚህ ሁሉ ድርጊታቸው ሸልሜያቸዋለሁ ብሏል ሲፒጄ፡፡
የጸረ-ሽብር ህጎችን በመጠቀም የፕሬስ ነጻነትን በማፈን ዘርፍ፣ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጠይብ ኤርዶጋን የተሸለሙ ሲሆን በዚሁ ዘርፍ ታጭተው የነበሩት የግብጹ አብዱል ፈታህ አልሲሲ ለጥቂት ተሸንፈዋል ያለው ሲፒጄ፤ በግብጽ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 ብቻ ከ20 በላይ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን አመልክቷል፡፡
በሚዲያ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ሲሸለሙ፣ የሩሲያው ፑቲን ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል፡፡ ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሚገደሉ፣ የሚታሰሩና ጥቃት የሚደርስባቸው የሩሲያ ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ ነው፤ የአገሪቱ ነጻ ሚዲያም እየቀጨጨ መሄዱን ቀጥሏል ያለው ተቋሙ፤በአለማችን ላይ ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ቁጥር በ2017 ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ በአመቱ በአለማችን የተለያዩ አገራት 262 ጋዜጠኞች በእስር ላይ ነበሩ ብሏል - ሲፒጄ፡፡

Read 1546 times