Monday, 15 January 2018 00:00

የመኪና አደጋ በአመት 1.25 ሚ. ሞት እና 50 ሚ. የከፋ መቁሰል ያስከትላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአለማችን የተለያዩ አገራት የሚከሰቱ የመኪና አደጋዎች በየአመቱ 1.25 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት፣ 50 ሚሊዮን ሰዎችን ደግሞ ለከፋ የመቁሰል አደጋ አየዳረጉ እንደሚገኙ የአለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአለማችን በመኪና አደጋዎች ሳቢያ ከሚከሰቱ የመቁሰል አደጋዎች መካከል 90 በመቶ ያህሉ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚከሰቱ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤የመኪና አደጋ በአገራቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
የአለም ባንክ ከ135 የአለማችን አገራት ለ24 አመታት ያህል የሰበሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ ያወጣው ሪፖርት እንደሚገልጸው፣ የመኪና አደጋ ከ15 እስከ 29 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አምራች ሃይል የሆኑ ዜጎችን ለሞትና ለአካል ጉዳተኝነት በመዳረግ ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ ይገኛል፡፡ ይህም የመኪና አደጋ በአገራት ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳያል ተብሏል፡፡
አገራት በመኪና አደጋ ሳቢያ የሚከሰቱ የሞትና የመቁሰል አደጋዎችን በግማሽ ያህል መቀነስ ከቻሉና ችግሩን በዘላቂነት ማቃለል ከቻሉ፣ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርታቸውን እስከ 24 አመታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ከ7 እስከ 22 በመቶ ማሳደግ ይችላሉ ብሏል ሪፖርቱ፡፡

Read 3302 times