Saturday, 13 January 2018 15:39

“ኢትዮጵያዊነት ይለምልም” የጉዞ አድዋ የኪነጥበብ ምሽት ሰኞ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 122ኛውን የአድዋ በዓልና የጉዞ አድዋን 5ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ “ኢትዮጵያዊነት ይለምልም” የተሰኘ የኪነጥበብ ምሽት ከነገ ወዲያ ሰኞ፣ ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ ቦሌ በሚገኘው ሞዛይክ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ የኪነጥበብ ምሽቱ፣ የዘንድሮ የአድዋ ተጓዦች መሸኚያ መሆኑንም አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡ በምሽቱ ግጥሞች፣ በ“ዜማ ነጋሪት” ባንድ የሚታጀቡ የጀግንነትና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያላቸው ሙዚቃዎች የሚቀርቡ ሲሆን የታሪክ ምሁሩ ብርሀኑ ደቦጭ ስለ አድዋ ምልከታቸውን የሚያንጸባርቁበት ጽሁፍ እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡ በሌሎች ታሪክ አዋቂዎችም የሚቀርቡ ፅሁፎች አሉ ተብሏል፡፡
 በዚህ ምሽት ከዚህ በፊት ጉዞ አድዋ ላይ የተሳተፉ የእውቅና የምስክር ወረቀት የሚያገኙ ሲሆን የዘንድሮው ተጓዦች ቃል የሚገቡበት ነው ተብሏል፡፡ በኪነጥበብ የታጀበው የሽኝት ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ ተጓዦች አዳራቸውን በጣይቱ ሆቴል በማድረግ፣ ማክሰኞ በሌሊት ከምኒልክ አደባባይ ጉዞ እንደሚጀምሩ፣ከጉዞ አድዋ መሥራቾች አንዱ የሆነው የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ ጨምሮ ገልጿል፡፡
ለዘንድሮው የአድዋ ጉዞ 391 ሰዎች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከልም ቀድመው የተመዘገቡና የጤና ምርመራ ያቀረቡ 25 ሰዎች ማለፋቸውን የገለፀው ከጉዞ አድዋ መሥራቾች አንዱ የሆነው የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ፤ ከ25ቱ ውስጥ አምስቱ  ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡ ጉዞ አድዋ፣ የ2009 ዓ.ም “የበጎ ሰው ሽልማት” አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል፡፡

Read 2789 times