Saturday, 21 April 2012 16:42

የዘኬዎስ ጊዜ

Written by  ተሾመ ገ/ሥላሴ
Rate this item
(0 votes)

ዕለቱ የኢያሪኮ የገበያ ቀን ነበር። የከተማው የቀረጥ መሥሪያ ቤት አለቃ እንደመሆኔ ለሠራተኞች የዕለቱን የቀረጥ ተመን አሳውቄ ማሰማራት ይጠበቅብኛል።በሁሉም የከተማዋ በሮች ማንን የት ማሰማራት እንዳለብኝ እያሰብኩ ወትሮ ወደምንገናኝበት አደባባይ አቀናሁ።ጊዜው ረፋድ ቢሆንም ኢያሪኮ በጸጥታ ተውጣለች።ወትሮ በማለዳ ተነስቶ የሚርመሰመሰው የኢያሪኮ ነዋሪ ተጠራርቶ የወጣ ያህል ከተማይቱ ወና ሆናለች።ድንገት ብቅ ብሎ ያየሁት ሰው ዋናውን ጎዳና ተከትሎ ወደ ከተማዋ መውጫ በር ይወናጨፋል።

በዚህ ከተማ በኖርኩባቸው ዓመታት እንደዚህ ያለ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም።ስለሁኔታው የምጠይቀውን አንድም ሰው አላገኘሁም።

የኢያሪኮ ሰዎች መከራና መቅሰፍት እየመጣ መሆኑን ሰምተው፣ ከተማዋን ለቅቀው እንደወጡ ተሰማኝ።ይህ ከሆነ ደግሞ ስለመቅሰፍቱ የሚነግረኝ አንድም ሰው እንደማይኖር አውቃለሁ። እንዲህ ሳስብ ለኢያሪኮ ሕዝብ ያለኝ ጥላቻ በእጥፍ ጨመረ። በዚህ ሰዓት እንኳ ቢያስቡኝ ምናለ?

እንቆቅልሹን ሊፈታልኝ የሚችለው እኔም እንደተቀረው ሕዝብ ወደ በሩ መውጫ ሳመራ እንደሆነ ገባኝ። ጉዞዬንም ወደዚያው አደረግሁ። ሰውነቴ በእልህ፣ በንዴት፣በጥላቻ፣በሐዘን፣...በተደበላለቁ ስሜቶች ይናጥ ጀመር። ቀዝቃዛ ላብ በማጅራቴ ቁልቁል ይንዠረዠራል። ከምኔው በሩ ዘንድ እንደደረስኩ እንኳ አላወቅሁም።

ጎልማሳውና ነጋዴው ጎረቤቴ ጎዳናውን ይዞ ወደ እኔ ሲመጣ አየሁ። በእርግጥ ጠበኞች ነን። ‘ከኛው ተወልዶ ለሮማውያን ይወግናል።’ ብለው ከሚኮንኑኝ በርካታዎች መካከል ነው። በዚህ ግራ በሚያጋባ ረፋድ ከማንም በላይ የከተማዋ ሕዝብ የሔደበትን የሚነግረኝ ያሻኛል። ጎረቤቴ ቀረበኝ።ቆም አልኩና ነዋሪው ወዴት እንደሄደ ጠየቅሁት።ፊቱን አጨፍግጎ፡-

“…መሲሁ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም እየሔደ ነው።በዚህ ማለፉ ስለማይቀር ሕዝቡ ሊቀበለው ወጥቷል። ከትናንት ጀምሮ በከተማዋ ይወራ የነበረው የዚሁ መሲህ መምጣት ነው።ለዚሁም ሲባል ሕዝቡ ትልቅ ግብር አዘጋጅቷል። እኛም ከዲናራችን  አዋጥተናል። በነገራችን ላይ አይነ-ሥውሩ ሄኖን አይኑ በርቶለት እየጨፈረና ከሕዝቡ ጋር ሆታ እያሰማና አታሞውን እየደለቀ ነው። ዘኬዎስ ሆይ! አንተም ብትሆን ከዚህ ኤሊ ካስመሰለህ የተረገመ እጥረትህና ክፋትህ ትፈወስ ይሆናል ሒድ እስኪ ወደ ነብዩ… ” አለና የጥላቻ ፈገግታውን ረጭቶብኝ ካባውን እያወናጨፈ ተፈተለከ።

የኢያሪኮን ሕዝብ ዘለፋና ሽሙጥ የለመድኩት ስለሆነ አልተበሳጨሁም። ይልቁኑ “መሲሁ እየመጣ ነው!” ያለው ንግግር ልቤን በድንጋጤና በጉጉት አናጠረው።ሠራተኞቼ ስለዚህ መሲህ ብዙ ጊዜ ነግረውኛል። እጅግ የምጠላቸው ጸሓፍት ፈሪሳውያን ሊፈትኑት በድንጋይ ትወገር ዘንድ ፊቱ ላቀረቧት ሴት የሰጠውን የፍርድ አርነት ሰምቼ ተደንቄያለሁ። እርሱ ድርጊቶችን ብቻ ሳይሆን የመነሿቸውን ሕመም አድምጦ የሚያክም መሆኑን አውርተውኛል።

“የዚህን አዳኝ የልብስ ጫፍ እንኳ ማየት ለኔ በቂ ነው።” አልኩ ለራሴ። ከዕብራውያን ዘመዶቼ መካከል የተለየ ሆኖ ያገኘሁት ይህ ቅን ፈራጅ  የረገጠውን ትቢያ መርገጥ ለኔ ልዩ ዕድል እንደሆነ ተሰማኝ።

የኢያሪኮን ከተማ ቅጥር መውጫ በር አልፌ ሕዝቡ ወዳቀናበት የገሊላ አቅጣጫ ተፈተለኩ። ብዙም ሳልጓዝ የሕዝቡ የሆታ ድምጽ ከርቀት ተሰማኝ። ለእስራኤል ነገሥታትና ልዑላን የሚቀርበውን ጥንታዊ የውዳሴ ዜማ የሚያቀነቅኑ ልጃገረዶች፤አታሞ የሚደልቁ ጎረምሶች፤ ዘንባባ እያውለበለቡ ‘እልል!’ የሚሉ ባልቴቶችና መጎናፀፊያቸውን ሽቅብ እያጎኑ የሚዘልሉ አረጋውያን የኢያሪኮን መዳረሻ አድምቀዋል።

በዚህ ጠጠር እንኳ ለመጣል በማያፈናፍን የሕዝብ አጀብ መሐል ተጋፍቶ ነቢዩን ለማየት መሞከር ያሰቡትን ሳያሳኩ ተረጋግጦ እንደመሞት ይቆጠራል፤ ቢሆንም  በአንዳች ብልሐት ነቢዩን ሳላይ መቅረት እንደሌለብኝ በድጋሚ ወሰንኩ። የሰው ጎርፍ እኔ ዘንድ ከመድረሱ በፊት ወደ ኋላ ተመልሼ ከከተማይቱ ዋና አደባባይ ደረስኩ።በሰዎች ትከሻ ላይ ቆሜ ነቢዩን ማየት እንዳለብኝ አሰብኩ። ለዚህ ደግሞ ከኢያሪኮ ነዋሪዎች መካከል አንዱ እንኳ ፈቃደኛ እንደማይሆንልኝ የታወቀ ነው።

ከጎዳና ዳርና ዳር ተተክለው ለከተማይቱ ውበት ከሆኑ የአርዘ ሊባኖስና ዋርካ ዛፎች መካከል አንዱ ላይ ብወጣ ነቢዩን ጥሩ አድርጎ ሊያሳየኝ እንደሚችል አሰብኩ። ዛፎቹ  ለኔ እንግዳ አይደሉም። “በዚህ ድንክዬ ቁመትህ እንዴት ልትወጣ?” ብትሉኝ የልጅነቴን የሰቆቃ ጊዜ ታስታውሱኛላችሁ። ወላጆቼ በከተማ ነሪዎች ዘንድ የውርስ ኃጥያት ባለዕዳዎች  እንዳይባሉ እኔን ከጊቢያቸው ቅጥር ውስጥ ባገቱኝ ጊዜ ሰው እየናፈቀኝ ከአጥሩ አምልጬ እወጣ ነበር።ታዲያ አመሻሽ ላይ ተመልሼ ለመምጣት ቅጣትና ዱላቸውን እየፈራሁ በነዚህ ዛፎች ላይ ያደርኩባቸው ሌሊቶች በርካታ ናቸው። ቅርንጫፎቻቸውን ተንጠላጥሎ በአንድ አፍታ ጫፍ ላይ መድረስ ለእኔ ቀላል ነገር ነው። በእያንዳንዷ ዛፍ ላይ ስንት ሌሊት እንዳሳለፍኩና የዛፎቹን ዓይነት ጭምር ለይቼ አውቃለሁ።

መሲሁን ለማየት ቁመት ይሆነኝ ዘንድ በመረጥኩት ዛፍ ላይ  ለመሬት ቅርብ ከሆነው ቅርንጫፍ አግዳሚ ላይ ወጥቼ መጠባበቅ ጀመርኩ።የኢያሪኮ ከተማ የቀረጥ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ዋርካ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ መገኘቱ አስደናቂ ሳይሆን አልቀረም፤ አንዳንዶቹ ቀና ብለው እያዩ ይስቁብኛል። በእርግጥ ይህ ሳቃቸው ለኔ አዲስ አይደለም።

***

“አጭሩ ሰው፤ድንክዬው ፍጡር፤ የቤተሰቡ መርገምት፤…” እየተባልኩ  ነው ያደግሁት።ወላጆቻችን ከወላዷቸው አምስት ልጆች መካከል አጭሩና ድንክዬው ሰው እኔ ብቻ ነኝ።እንዲህ “የምድር ጉድ” ሆኜ መፈጠሬ በእርግጥም እርማን ስለሆንኩ ነውን? እያልኩ ስጠይቅ ነው ያደግሁት።በኛ በዕብራውያን እምነትና ልማድ እንዲህ ያለ እንደኔ ያለ ጉድ የእርግማንና የቤተሰብ ጣጣ ውጤት ነው።በመሆኑም ከቤተሰቦቼ መካከል ማንም ከኔ ጋር በአደባባይ መታየት የሚፈቅድ፤የእርግማን ጣጣ ተቋዳሽ መባልን የሚፈልግ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከቅጥረ-ጊቢው እንዳልወጣና ወላጆቼን እንዳላሰድብ የቤተሰቤ ፍላጎት ነበር።

እኔ ግን በጄ አላልኩም። ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ወደ ከተማ መውጣትና ከሰው መቀላቀል ያስደስተኝ ነበር። በኢያሪኮ ያለው የሌላው ሕዝብ አቀባበል ያው እንደቤተሰቦቼ ጨፍጋጋ ቢሆንም ለኔ ፈጥሮኝ ከሚሳቀቅብኝ ቤተሰቤ የከተማው ስላቅ ይሻለኝ ነበር።

ቢሆንም እኔን የሚያከብር፤ማንነቴን እንደ ዕድል የሚቆጥር ሌላ የኅብረተሰብ ክፍል በኢያሪኮ ነበር- የሮማ ቅኝ ገዢ ወታደሮችና ሹማምንት። ሮማውያን እንደወገኖቼ  ዕብራውያን በመርገምት ዓይን አላዩኝም።ይልቁኑ ንግግሬና ድርጊቴ ሁሉ ለእነርሱ አስገራሚ፣ ብስለትና ብልህነት ያለው ነበር።

“እንደ አንተ ያለው ሰው በኛ በሮማ የቤተ-መንግሥት ባለሟልና የንጉሥ አማካሪ ነው የሚሆነው።” ሲሉ የክብር ሥፍራ ሰጡኝ። እነርሱ በአፈጣጠሬ አልተሳለቁም።እጅግ አቀረቡኝ።ለእነርሱ የተለየ ክብርና ፍቅርም አደረብኝ።ይህን የተረዱት ሮማውያን እንደራሳቸው ቆጠሩኝ። ያለአንዳችም ችግር ተቀላቀልኳቸው። ተወልጄ ያደግሁባት የኢያሪኮ ከተማ ቀረጥ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት አለቃ ሲያደርጉኝም ይህን ሁሉ ገምተው እንደሆነ አስባለሁ።

ከገዛ ወገኖቼ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰጠኝና ስለእርሱ ሳስብ እንድወድደው ያደረገኝ ይህ ዛሬ ላየው የጓጓሁት ነቢይ ብቻ ነው። ከኔ ይልቅ የከፋ የአካል ጉዳት ያለባቸውን እንኳ ሲያድናቸው፡-

“ እንዲህ ሆነው የተፈጠሩት የእግዚአብሔር ክብር በእነርሱ እንዲገለጥ እንጂ ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ እነርሱ ኃጥያት ኖሮባቸው አይደለም።” ሲል በድፍረት ተናገረ።

በሮማውያን የተሾምኩ ጊዜ አጋጣሚውን እንደ ትልቅ ዕድል ነበር የቆጠርኩት። ወዲያውኑ ነበር ይህን ፍቅር የነሳኝ ቤተሰብና ከመቅሰፍት የቆጠረኝን ኅብረተሰብ መበቀል የጀመርከት። ማንስ ቢሆን ከዚህ ውጪ ሌላ ምን ሊያደርግ ይችላል?

በቀረጥ ተመን ማስጨነቅ፤ አስፈላጊና ዋነኛ የሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ከተማዋ ሲገቡ ነጋዴውን በቀረጥ ሥ ም ኪሱን ማራቆት፣ ክፍያ ሳይፈፀምባቸው የሚገቡ ቁሳቁሶችን ያለርህራሔ ‘ውርስ ለቄሳር!’ ማለት፤የማያፈናፍኑ አዳዲስ የቀረጥ ደንቦችን በማውጣት  የተጠቃሚውን ፍዳ ማብዛት፤ ይህ ኅብረተሰብ ለነፈገኝ ጊዜ፤ለከለከለኝ ፍቅር ዋጋ ማስከፈል!

ሕዝበ-ኢያሪኮ በቀረጥ ሲፈጠረቅ፣ በተመን ጣሪያ ሲሰቃይ፣ የእኔ  ከረጢቶች በወርቅ ዲናሮች ይታጨቃሉ። ግምጃ ቤቴ  በውድ ቁሳቁሶች ይሞላል። ኑሮዬ የቅንጦት ደረጃዬም ከታላላቆች ጎራ ይሆናል። ሰው ፍቅርም ነዋይም አጥቶ እንዴት ይኖራል?

መሲሁን ያጀበው ሕዝብ ከተቀመጥኩበት ዛፍ ሥር ማለፍ ከጀመረ ጥቂት ቢቆይም መፈናፈኛ የሌለውና በግፊያ የተሞላ የሰው ጎርፍ ጎዳናውን ማጥለቅለቅ የጀመረው ግን አሁን ነው። ይሔኔ ፈራሁ። አይኖቼ መሲሁን ፍለጋ ተቅበዘበዙ! ከዚህ  አንድ ዓይነት አለባበስ ካለው ሕዝብ መካከል እርሱን እንዴት ልለየው እችላለሁ? ግራ ተጋባሁ። ልቤ ይንፈራገጣል።

ዓይኖቼ አንድ ነገር ላይ አረፉ። እጭቅ ብሎ ከሚተምመው የሕዝብ አጀብ መካከል አንድ ክብና ክፍት ቦታ ይታያል። በዚህ ክፍትና ክብ መሐል ነጭ ቀሚስ ከቀይ መጎናፀፊያ ጋር የለበሰ ወጣት፤ በዝግታ እየተራመደና አንዳች ነገር በኃይለ ቃል እየተናገረ ወደ ፊት ይራመዳል።

“ይሔስ እርሱ ነው!” አልኩ በለሆሳስ። እጅግ የተዋቡቱ ሚስጥራዊ ዓይኖቹ ዛሬም ድረስ ውስጤ አሉ።

የመሲሁ እርምጃ እኔ ካለሁባት ዛፍ ሥር ሊያውም በኔ ትይዩ ሲደርስ ተገታ። ነብዩን በግላጭ ለማየት ዕድሉን አገኘሁ ብዬ በደስታ ስናጥ እኒያ ኃይለኛና መግነጢሳዊ ዓይኖቹ  ቀና አሉና ዓይኔ ላይ አረፉ።ሚዛኔን ስቼ ልወድቅ ነበር። የእርሱን ዓይኖች ተከትለው የኢያሪኮ ከተማ ነዋሪ እልፍ ዓይኖች እላዬ ላይ ሠፈሩ።

የነቢዩ ዓይኖች እላዬ ላይ ጥቂት ጊዜ ቆዩ። ድንጋጤዬ ጨመረ።

“ዘኬዎስ!” አለኝ ነቢዩ። ትንፋሼ ቀጥ ሊል ነበር። እርሱ ለዚህች ከተማ እንግዳ ነው። ታዲያ ሥሜን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? ሰዎች ስለኔ ነግረውታል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ስለኔ አንዳችም በጎ አይነግሩትም። ስለዚህ በነዚህ ወፈ-ሰማይ ‘ጠላቶቼ!’ ፊት ሊያዋርደኝ ነው ማለት ነው። በእርግጥ መዋረዱ ለኔ ያን ያህል አያስፈራኝም፤ ይልቁኑ ከዚህ ቅን ፈራጅ አፍ የሚወጣ ወቀሳ ስለእርሱ የያዝኩትን ተስፋ እንዳይነጥቀኝ ፈራሁ።

ግን ደግሞ ብርሃናቸውን ያጡትን በብርሃን ያጥለቀለቀ፤ እግሮቻቸው የተሰናከሉባቸውን ፈውሶ ያስዘለለ፤ ፍቅር ከውስጣቸው የሞተባቸውን ነፍስ ዘርቶ በእንባ ያጥለቀለቀ  የኔን ሥም ለማወቅ ይቸገራል ማለት ሞኝነት ነው።ይሁና ምን አለ? ግን አሁን የጠራኝ ምን ሊለኝ ነው?

አዕምሮዬ በቅጽበት አያሌ መላምቶችን አፈራረቀ። ነቢዩ ቀጥሎ የሚናገረውን ለማወቅ ጓጓሁ። ዓይኖቼን በእርሱና ባፈጠጠብኝ የኢያሪኮ ሕዝብ ላይ እያፈራረቅሁ የሚሆነውን እጠባበቅ ጀመር።

“ዘኬዎስ ውረድ። ዛሬ ከቤትህ ጣሪያ ሥር እውል ዘንድ ይገባኛል!” አለኝ።

በኖርኩበት ዘመን ሁሉ ከአንዳንድ የሮማ ቅኝ ገዥ አለቆቼ በቀር ከቤቴ ታዛ ሥር በእንግድነት ያረፈና ሊስተናገድም የፈቀደ አንድም ዕብራዊ አልነበረም። በእኛ በዕብራውያን ባህል እንግዳ የፈጣሪ በረከት ምሳሌ ነው። ‘አባታችን አብርሃም ያለ እንግዳ የዕለት መባውን እንኳ አይቆርስም ነበር።’ ሲሉ ሰምቻለሁ።በተቃራኒው እንግዳ የማይጎበኘው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ መረዳት አይከብዳችሁም።

ዛሬ መሲሁ ‘ካንተ ቤት ነኝ!’ አለኝ። የምናገረውን አጣሁ። እኔን በተመለከተ ከነቢዩ አፍ የሚወጣውን የእርግማን መዓት ሊሰማ ያቆበቆበው የኢያሪኮ ሕዝብ  ‘…ከዚህ ቀራጭ ጋር መባ የሚቆርሰው እንዴት ዓይነቱ ኃጥያተኛ ቢሆን ነው?’ እያለ በየአቅጣጫው ተበተነ። ሊያከብረው ከከተማ ወጥቶ የተቀበለው አድናቂ  አፉን በእጆቹ ከድኖ  ሸሸው።

እኔም ከዛፏ ወርጄ ከነቢዩና ደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቤቴ አቀናሁ። ነቢዩ ከቤቴ ታዛ ሥርም ተቀምጦ መባም ቆረሰ፤ ወይንም ጠጣ። አፉም ብሥራትን ተናረች።

“ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል!” አለኝ። እጅግ ደነገጥኩ። በጉልበቴ ተንበርክኬ በደስታ እንባ የቤቴን ወለል አጠብኩ። ‘በሰዎች የተጠላ፤በገዛ ወገኖቹና ቤተሰቦቹ የተገፋ፤ከህጻንነቱ ጀምሮ የተገለለ፤በግፍ የተባረረና በነደደ ብቀላ ሰዎችን በአደባባይ የዘረፈ እንዴት መዳን ይሆንለታል?’ አልኩ ለራሴ።እርሱ ግን ደግሞ ተናገረ፡-

“ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል!”

ላጣሁት ፍቅር ምትክ ብዙ የወርቅ ዲናሮችን፤ ህልቁ መሥፈሪያ የሌላቸውን መልህቆች፤ ውድ ቅርሶች፤የተለያዩ የወርቅና የብር ቁሳቁሶችን ከቤቴ ግምጃ ቤት ሚስጥራዊ ክፍሎች ውስጥ አከማቸሁ። ብዙዎችን ዘረፍኩ። ግን የነፍሴ የጨለማ ጉድጓድ በዚህ ሁሉ ክምችት የሚሞላ አልነበረም። ወይም በጨለማው ላይ አንዳች የብርሃን ብልጭታ የሚፈነጥቅ አልነበረም። የቅጣቱን ቀንበር ባጠበቅሁ ቁጥር ይበልጡኑ የውስጤ የጨለማ ጉድጓዶች ጥልቀት ይጨምር ነበር። ዛሬ ግን ይህ ጉድጓድ ሞላ።

ራሴንም ባስደነቀ ፍጥነት ወደ ምድር ቤት ወረድኩ። ሚስጥራዊውን የሐብቴን ግምጃ ቤት ከፈትሁ። ያከማቸሁትን ሁሉ አውጥቼ ጎዳና ላይ በተንኩ። አሁን ይህ ሁሉ ወርቅ ብርና የከበረ ደንጊያ አያሻኝም። የኢያሪኮ ከተማ ነዋሪዎች ከቅጥረ-ጊቢዬ ፊት ለፊት ቆመው ከሚበተነው ዲናርና ከሚዘረገፈው ወርቅ የቻሉትን ያህል ሲሻሙ አየሁ። ድምጼን ከፍ አድርጌ “የባለቤቱን ለባለቤቱ!” አልኩ።

መሲሁ አመሻሽ ላይ ተሰናብቶኝ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም አቀና።

ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በዓይኔ አልዞረም። ‘ኢያሪኮ የነፈገችኝ ሳይሆን የነፈግኋት  ምንድነው?’ ስል ራሴን ጠየቅሁ። ውስጤ ‘ኢያሪኮ ካንተ ጊዜ ትፈልጋለች።በደንብ ካጤንከው ፍጡር ደግ ነው። እርሱ የነፈገህን አንተ ስትሰጠው ይደነግጣል።ያ! የበጎ፣ የፈውስና የመቀላቀል ጅማሮን ይፈጥራል። ከቂም የጸዳ፤ፍቅርን ያዘለ፤በይቅርታ የተሞላ ጊዜ ለኢያሪኮ!!’ አለኝ።

በማለዳ ተነስቼ ተወልጄ ያደግሁባትን ኢያሪኮን ከዳር እስከዳር ጎበኘሁዋት።በዕውነቱ ለከተማይቱ እንግዳ የሆንኩ ያህል ተሰማኝ። ኢያሪኮ ከሰቀላዎቿ ይልቅ ደሳሳ ጎጆዎቿ ይበዛሉ። የተዋቡ በሮች አሏት ግን ቅጥሮችዋ የፈራረሱ ናቸው።የጠገቡ ሲራራ ነጋዴዎች ብቻ ያሉባት ትመስለኝ የነበረች ኢያሪኮ ዘባተሎ የለበሱ ምስኪናን የዕለት መባቸውን ሊያገኙ ማልደው የሚነሱባት ናት። ጸሐይ ጠልቃ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የልፋታቸውንና የትግላቸውን ያህል አግኝተው የማይመለሱ ድኾች ህልቁ መሥፈሪያ የላቸውም። የምሽት ጉበኞች(ጠባቂዎች) አሏት ግን የብርሃን ዘይት የላቸውም።…ኢያሪኮ አሳዘነችኝ። ምን ላደርግላት እችል እንደሆነ አስብ ጀመር።

ነቢዩ ከቤቴ ጣሪያ ሥር አርፎ ከሔደ በርካታ ወራት ተቆጠሩ። በኢየሩሳሌም ጎልጎታ ተብላ ከምትጠራ ኮረብታ አናት ላይ ለሰዎች ሁሉ መድኅን ይሆን ዘንድ የመሰቀሉ ወሬ ተሰማ። እልፍ አዕላፍትም በስቃዩ ነፃ እንደወጡ ተነገረ።

ይህ ስቅላቱ እኔን ይመለከተኝ ይሆን? ምክንያቱም መሲሁ የኔንና የቤተሰቦቼን መዳን ያበሰረው ከመሰቀሉ  ከብዙ ወራት አስቀድሞ ነው። እኔን ያዳነኝ በደሙ ሳይሆን ሰላሳ ሶስት ዓመት ከሦስት ወር ከቆየባት የምድር ላይ ዕድሜው ላይ ቆርሶ በሰጠኝ የጉብኝት ጊዜ ነው። ይህንንም ሲያረጋግጥልኝም “ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል!” አለኝ። እኔና ቤቴ የዳንነው በተከፈለ ጊዜ እንጂ በፈሰሰ ደም አይደለም ማለቴ ለዚህ ነው።ግን ከጊዜና ከደም የቱ ያይላል?

ከስቅላቱና ሞቱ በኋላ ስለ እርሱ የተባሉትን በጎና በጎ ያልሆኑ ወሬዎች ሁሉ ሰምቻለሁ።

“…ከሞት አልተነሳም። አስከሬኑን ደቀ መዛሙርት ሠርቀውታል። ሞትን ድል ነስቶ አረገ፤ ያለድንግልና ተወለደ የተባለው ሐሰት ነው። በቃላት የሠለጠነ በንግግሩ አፍ የሚያስከፍት፤እነግሳለሁ እያለ የመሪ አልባዎቹን ዕብራውያን የነፃነት  ናፍቆትና ፍላጎት  ለአጀቡ የተጠቀመ፤…እርሱ እንዴት የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል?” ብለውታል።

እናንተዬ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ሆነ አልሆነ እኔ ምን ተዳዬ!

የተባሉት ነገሮች ሁሉ  ለኔ ቁም ነገር  የላቸውም።ድንገት የተባለው ሁሉ ዕውነት ሆኖ ቢገኝ እንኳ ይህ የኔን መዳን ወደ ሞት የሚለውጥ አይደለም።ስድብ ሳያሳፍረው፤ለክብሩ ሳይጨነቅ፤በሕዝብ የተጠላውንና ሕዝቡን የጠላውን የቀራጮች አለቃ እኔ ዘኬዎስን ከሕይወት ጊዜ ላይ ከፍሎ ከጥላቻ እሥራት ነጻ ያወጣ ያ! ወጣት እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ  እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ገንዘብን ከፍሎ ሰዎችን ከእሥራት ማውጣት ይቻል ይሆናል።ደምን ከፍሎ ማዳንም እንዲሁ።እኔ ግን በጊዜ  ዋጋ ክፍያ የዳንኩ የመሲሁ ትሩፋት ነኝ። እኔም ለሌሎች የሚተርፍ ጊዜ ይኖረኝ ዘንድ አድርጎ እንደገና የሠራኝ ይሄው መሲህ ነው።

በፍቅር ውስጥ  የተወለደ የመዳን ጊዜ ለመላው ዘራ-ሰብ ይሁን !

 

 

Read 3512 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:46