Saturday, 13 January 2018 15:44

“እስኪ ልየው”ን ---- አየሁት

Written by  ፊያሜታ
Rate this item
(1 Vote)

  (ሄለንን እያነበብን ወደ ጉማይሌ ስንጓዝ)
          
   መንገደኛ ነኝ…
“እንጀራ” ከቤቶቼ ነጥሎ፣ ከሸገር ወደ ደቡብ የሸኘኝ የማክሰኞ ማለዳ ባለ ጉዳይ!...
ከሻሸመኔ እስከ ሃላባ የተዘረጋውን… የብላቴን ወንዝ አሻግሮ፣ ወደ አጄ የሚያቀናውን… መስኩን መሃል ለመሃል ሰንጥቆ፣ ወደ ሾኔ የሚያዘልቀውን… ግራ ቀኝ እየተጠማዘዘ፣ ወደ ሶዶ የሚያመራውን… ረጅሙን መንገድ ተከትላ ወደፊት በምትወረወር፣ ሙሌ በሚዘውራት ባለ አራት ክንፍ ላንድ ክሩዘር ውስጥ ነኝ፡፡
ሶዶን የሚሻገረውን፣ አባያ እና ጫሞን አልፎ ወደ ኮንሶ የሚዘልቀውን፣ ዳገት ቁልቁለት አቆራርጦ ደራሼዎች መንደር የሚደርሰውን፣ ጉማይሌ ላይ የሚቋጨውን፣ ከ580 ኪ.ሜ በላይ የሚሸፍነውን ረጅሙን ጉዞ ማልደን ነው የጀመርነው፡፡
ወደ ሶዶ ስንቃረብ ግን… ሁለት ሆነን የጀመርነውን ጉዞ፣ ሶስት ሆነን ስንቀጥለው ተገኘን!...
አሁን ሶስት ነን… እኔ፣ ሙሌ እና እሷ - ባለጉዳዩዋ! ስንነሳ አብራን አልነበረቺም… አብራን ጉዞ አልጀመረቺም… አብራን እዚህ አልደረሰቺም… በምንጃር ምት አንኳኩታ፣ ድንገት ከመኪናችን የሙዚቃ ማጫወቻ ብቅ ያለች፣ ሶስተኛዋ መንገደኛ መካከላችን ተገኘች፡፡
“ባለ ጉዳይ ነኝ!...” አለቺኝ፡፡
ምን እሚሉት ጉዳይ ብዬ እስክጠይቃት አልጠበቀችኝም፡፡ ባለጉዳይነቷንና ጉዳዩዋን እያዜመችልኝ፣  እንዳመጣጧ ሁሉ፣ ድንገት ከመኪናችን ወረደች፡፡
ከበስተቀኝ የተገጠገጠውን አዘርዝሮ የሸጎጠ መስክ ሙሉ የበቆሎ ማሳ መሃል ለመሃል እየሰነጠቀች… የሰማይን ጥግ ታክኮ በሞገስ ወደቆመው፣ ባሻገር ወደሚታየኝ ወደ ዳሞታ ተራራ ሽቅብ ትገሰግሳለች -  “ባለ ጉዳይ ነኝ!...” እያለች፡፡
ያቻት ባለጉዳዩዋ! ወደ ጉዳዩዋ ስትከንፍ፣ ወደ ከፍታው ስትገሰግስ በሩቅ አያታለሁ…
“ባለ ጉዳይ ነኝ ባለ ጉዳይ
ይጠብቀኛል ሺ ጉዳይ…” እያለች ወደ ላይ ትወጣለች - ወደ ከፍታው፡፡
የተጠራሁት ከካጣሁት ወዳጄ በላይ ግርማ ላለው፣ ከዳሞታ ተራራ በላይ ለገዘፈ አላማ ነው ብላ ያመነች፣ ከእጇ ካመለጣት ወዳጅ ይልቅ ከፊቷ የሚጠብቃት ኣላማ እንደሚበልጥ የገባት፣ ወደ ኋላ ዞሮ ከመብከንከን ይልቅ ወደፊት መግፋት እንደሚያተርፋት የተረዳች፣ በህይወት ውስጥ ከሚከሰት ቅንጣት ውድቀት ይልቅ የህይወት አላማ በእጅጉ እንደሚልቅ የገባት ብርቱ ነፍስ፣ በጽናት ወደ ዳሞታ ከፍታ ሽቅብ ስትወጣ ትታየኛለች፡፡
እሷ ትወድድ ነበር… ተስፋ ታደርግ ነበር… ትጠብቅ ነበር… በኋላ ግን ሁሉም እንዳይሆን ሆነባት… እንዲህ ሲሆንባት ታዲያ፣ አለም አበቃ… ህይወት ተደመደመ ብላ አልተንበረከከቺም፡፡ ለሰቀቀን እጅ አልሰጠቺም፡፡ አልተሸነፈቺም፡፡
እሷ… የተጠራቺው ከዚህ ለበለጠ ነገር ነው… የበለጠው ነገር ከፊቷ ይጠብቃታል!
“የወደድኩት ጠላኝ ተውኝ ብዬ
ከህይወት አልፋታም
ገና ስንት አለ ከፊቴ ብርቱ ጉዳይ
የኔ ያልኩትን ባጣም…
ሰው ሄደ ብዬም አልሸበር
ቀድሞም ሲጀመር የኔ አልነበር
ህይወት ከፊቴ ስትጠብቀኝ
ሳይመሽ በጊዜ ቤቷ ልገኝ…” እያለች የህይወትን አላማ ከፍታ፣ የመኖርን ዋጋ ክብረት ታዜማለች - እጅ ባለመስጠት ወደ ነገ በትጋት መግፋትን ትሰብካለች፡፡
ይህን የጽናትና ያልሸነፍ ባይነት ድምጽ፣ “አንዳንዴ” በሚለው ሌላኛው ዜማዋ ላይም ትደግመዋለች፡፡
“ያለምኩትን ቀን ናፋቂ
ቀን ጠባቂ
አዎ
አንዳንዴ ቅርብ ያልኩት ይርቃል
ከጄ ላይ የያዝኩት ይወድቃል
ሳር ቅጠል ተነስቶብኝ ያውቃል
ልቤ ግን ህልሙን ይጠብቃል
የምመኘውን እስከማገኝ
ድካም የማያውቀኝ
የኔ ያልኩትን ቀን ጠባቂ
ቀን ናፋቂ” እያለች በጽናት ወደ ነገ እያማተረች ትገሰግሳለች፡፡
“እስኪ ልየው” በተሰኘው አዲሱ የሄለን በርሄ የሙዚቃ አልበም ውስጥ ከተካተቱት 14 ዘፈኖች አንዱ የሆነውን “ባለጉዳይ” መላልሼ እያደመጥኩ ነው፣ ሶዶን ወደ ኋላዬ ትቼ፣ ወደ አርባዎቹ ምንጮች የገሰገስኩት፡፡
ደስ ይላል!...
አበቃልኝ!... ተደመደምኩ!... ተፈጸምኩ!... በሚል የሽንፈት ዜማ ከተቃኘው የአገሬ ሰቀቀናም ዘፈን ውስጥ፣ ተስፋንና ብርታትን የሚሰብክ… ህይወትንና አላማን የሚያስተሳስር… ህይወት የሚያስቀጥል የመነሳት ዜማ መስማት ደስ ይላል!
ይህ በምንጃር ምት የተቃኘ ነፍስና ደም የሚያሞቅ ዜማ፣ የህንዳዊውን ባለቅኔ የራቢንድራናት ታጎርን እውነት ከፍ አድርጎ ደገመልኝ - “ወደ ህይወት የተጠራኸው፣ ከዚህ ከፍ ላለ ነገር ነው!”
አሁንም ከሄለን ጋር ነኝ…
እርስ በእርሱ በማይያያዝ፣ በተበጣጠሰ የስንኝ ክር የተሸመነ የዘመኔ “ባለ አንካሳ ሃሳብ” ውሽልሽል ሙዚቃ ያሰለቸው ጆሮዬ፣  ጥልቅ ሃሳብን በውብ ቃላት እያጠለለች የምታንቆረቁር ሄለንን እያደመጠ ፈነደቀ፡፡ “የኔ ቆንጆ” በሚል ዜማዋ፣  በወረቀት ግጥምና በዘፈን ግጥም መካከል የተሰመረውን ድንበር እንደ ዋዛ ስትደመስሰው እያየሁ ተገረምኩ፡፡
“ላላ እያረጉ መኖር ይከብዳል
ፍቅር ቅኔ ነው ጠበቅ ይወዳል
ወደው እንደሰም መቅለጥ ከፈሩ
በምን ይለያል ወርቅና አፈሩ…” እያለች፡፡
ዘፈን ዜማ ነው ወይስ ግጥም የሚል፣ የኖረ ሙግት ውስጥ አልገባም፡፡ ጥሩ ዜማም፣ ጥሩ ግጥምም ነፍሴን ጮቤ ያስረግጧታል፡፡ ከሰሞኑ እንደመጣው እሱባለው ይታየው ሁሉ፣ ጠብሰቅ ያለ ግጥም ይዘው መጥተው ያስፈነደቁኝ  ብዙ ድምጻውያን አሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ ከአበበ ተካ በኋላ ከጫፍ እስከ ጫፍ በረቀቀ ግጥም ተሸልሞ፣ ነፍሴን ያጠፋው የመጀመሪያው አልበም የሄለን “እስኪ ልየው” ሆነ፡፡
አብዛኞቹ ዘፋኞቻችን ጠንከር ያለ ሃሳብ ሸሽተው ላላ ያሉ ቃላት በሚመርጡበት፣ “ይሄማ የወረቀት ግጥም ነው፤ ቃላቶቹ አፍ ላይ ይከብዳሉ” እያሉ ኮስታራ ስንኞችን ወደ ገጣሚው በሚገፉበት በዚህ ዘመን፣ ሄለን በርሄ፣ አለማየሁ ደነቀ የከተበውን የአንዲት ምስኪን ሴት የዕለት ውሎ መዝገብ እየገለጠች አዜመቺው - እና አስደነገጠችኝ፡፡
የአንዲትን ምስኪን ሴት የአንድ አመት ሰቆቃ በአምስት ደቂቃ ይተርካል - “365” የሚል ርዕስ ያለው የሄለን ዜማ፡፡
“60 እንቅልፍ አልባ ቀናት
70 ከባድ የራስ ምታት
ባንተ ምክንያት ነው ባንድ አመት
ካይኔ ሃይቅ ያህል እንባ
አንዲት የፍቅር አበባ
የሆነው ሁሉ አንድ አይረባ…” ትለናለች አንጀት በሚበላ ዜማ፡፡
የዚያች ምስኪን ሚስት የዕለት ውሎ መዝገብ ሲገለጥ፣ ሃዘንና ጭንቀት ባረበበበት፣ ንዝንዝና ጭንቀት በተሞላ፣ ንትርክና ቅናት በገነገነበት ጥቁር ጎጆ ውስጥ ያለፈ ከንቱ አንድ አመት ተጣጥፎ ቁጭ እንዳለ ይገኛል፡፡
“የኔን የውሎ ማስታወሻ
ባየው አስከመጨረሻ
ሙሉ የራስ ምታት ማስታገሻ
ፍቅር ያልነውም ለስሙ
የኛስ ጭጋግ ነው ቀለሙ
ከዚስ ብቸኝነት በስንት ጣዕሙ…”
ትዳር ህመም የሆነባትን፣ ዓለም ከል የለበሰባትን፣ ባል ስቃይ የሆነባትን ያልታደለችን ሴት እያሰብን አቀርቅረን ስንብሰከሰክ ቆይተን ታዲያ፣ ሌላ የሆነላት ሴት ትመጣና ቀና ታደርገናለች - “ፊታውራሪ” ትለናለች።
“አንተ ፊት አዉራሪ
ከፊት የሌለብህ አይኔን ልቤን አብሪ
ስምህ ፊት አውራሪ
ጨዋታዬን ቀዳሽ የቃላቴ መሪ
አንተ ፊት አውራሪ
እጄን በጅህ ይዘህ መንገድ አሻጋሪ
ስምህ ፊት አውራሪ
በጨለማ መሃል ንጋትን አብሳሪ…” እያለች ታቀነቅናለች፡፡
ህይወት እንዲህ ናት፤ ላንዱ መራር ላንዱ ጣፋጭ ጣዕም ትለግሳለች፡፡ እዚያ አመት ሙሉ ስቃይ፣ አመት ሙሉ ጭንቀት የሆነ ትዳር፣ እዚህ የዘለለት ደስታ የዕድሜ ልክ ፍንደቃ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የዚያችን ፊት ማዲያት ያለበሰ ትዳር፣ እዚህች ቤት ግርማ ሞገስና የውበት ምንጭ ሆኖ ይመጣል፡፡ ያቺ ከባሏ ያተረፈቺውን መከራ ስታንጎራጉር፣ ይህቺ በባሏ የተጎናጸፈቺውን ሰላምና ደስታ ትዘምራለች፡፡
“አንተ ፊት አውራሪ
ከፊት የምትገኝ ዋስ ሆነህ ተጠሪ
ስምህ ፊት አውራሪ
ስምህን ለብሼ ተባልኩኝ ስታምሪ
አንተ ፊት አውራሪ
ግርማ ሞገሴ ነህ ውበቴን ቀማሪ
ስምህ ፊት አውራሪ
አንተን ስለሰጠኝ ይመስገን ፈጣሪ…” እያለች፡፡
በሄለን በርሄ አልበም ውስጥ ከጥልቅ ሃዘንና ብስጭት፣ ስር ከሰደደ መገፋትና መበደል የሚመዘዙ ኮስተር ያሉ ሃሳቦች ብቻ ሳይሆን፣ ተራ ኩርፊያ የሚመስሉ - ግን በቅጡ ሲያጤኗቸው ግርምትን የሚያጭሩ ርዕሰ ጉዳዮችም ተዳስሰዋል፤ አላቆላመጥከኝም ብላ እንዳኮረፈቺው ሴት አይነት፡፡
ማን አስለምደኝ አለው የሚለው ዜማ፣ በፍቅርና በትዳር ህይወታችን ውስጥ የአጋራችንን ስሜት ላለመጉዳት ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንዳለብን ያሳያል። እንደዋዛ ያስለመድነው ነገር፣ ውሎ ሲያድር ምን ያህል ዋጋ እንደሚኖረው ይጠቁመናል፡፡
“የኔማር የኔማር ቆንጂዬ ልጅ እያለ
ሁልግዜ በቁልምጫ ሲያወራኝ እንዳልዋለ
በስሜ ሲጠራኝ ዛሬ
ቀረሁኝ አቀርቅሬ
ለመዝለቅ ካላስቻለው
ማን አስለምደኝ አለው….
ያ ጣፋጭ አንደበቱ እንደማር የሚጥመኝ
በድንገት ሳላስብ ነው ያስከፋኝ ያሳመመኝ
ለወረት ላንድ ሰሞን ለመዝለቅ ካላደለው
ይህንን አጉል
ነገር ማን አስለምደኝ አለው…” ትላለች - በቁልምጫ ሲጠራት፣ ነፍሷ በደስታ ስትሰክር ኖራ፣ ያስለመዳትን ቁልምጫ ትቶ በአዘቦት  ስሟ ሲጠራት፣ የገዛ ስሟ ያስጠላት ተፈቃሪ፡፡
ብራቮ ሄለንና ገጣሚዎቿ!

Read 1823 times