Saturday, 13 January 2018 15:47

የበቀለ መኮንን “ባሩድና ብርጉድ”

Written by  ሚፍታ ዘለቀ (የሥነጥበብ አጋፋሪ)
Rate this item
(2 votes)

 ቆይ ለማን ነው እንዲህ አይነቱን ሃሳብ አንገፍጦ የሚሰደው? ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው ብሎ ነው? … ወይስ ሠዓሊው ይህን ያህል የተጠበበው ሥነ-ጥበብ በዚህች ሃገርና በማህበረሰቦቿ ምን ለውጥ ያመጣል ብሎ ነው? ያመጣል ካለስ ትርዒቱ ሊከስት ከሚችለው የንቃተ ህሊናና የሃሳባዊ ደርዝ አንፃር እንዲሁም ሙዚየምም ሆነ የሥነ-ጥበብ ቦታዎችን ያለመጎብኘት ጥልቅ ዝንጋኤ ውስጥ ከተዘፈቀው የሰፊው ማህበረሰብ ልምድ አንፃር እንዲህ አይነቱ ትርዒት ለምን በሙዚየም ውስጥ እንዲወሰን ሆነ? ይህ ትርዒት በዚህ ዘመን፣ አሁን ባለንበት ጊዜ፣ ሃገራችን ባለችበት ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ መታየቱ ምን ዓይነት አንድምታዎችን ያመላክተናል? በዘመናዊውና በዘመንኛው የሃገራችን የሥነ-ጥበብ ሂደት ምን አይነት አሻራ ይኖረዋል? ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ቤተ-መዘክር ገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል በሠዓሊ፣ ቀራፂ፣ ገጣሚና የሥነ-ጥበብ መምህር በቀለ መኮንን (ረዳት ፕሮፌሰር) የቀረበው ‘ባሩድና ብርጉድ’ የሥነ-ጥበብ ትርዒት ከፈጠረብኝ በርካታ ጥያቄዎች  መሃል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ታላቁ ደራሲና አሰላሳይ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር፣ በሕይወቱ የመጨረሻ ሳምንታት “እሴት ያለው ሕይወት ኑር” በሚል ርዕስ በፃፈው ማስታወሻ/ደብዳቤ ውስጥ “እሴት ያለው ሕይወት መኖር ባጋጣሚ አይመጣም። ሁኔታዎች የሚወስኑት ጉዳይ ሳይሆን፣ አንተ ራስህ መርጠህ የምትፈፅመው ነው፡፡”  የሚል የምንጊዜም እውነት አስቀምጧል፡፡ እሴት ያለው ትርዒትስ? እንደውም! እሴት ያለው ትርዒት ማሳየት ባጋጣሚ እንደማይመጣ፣ ሁኔታዎች እንደማይወስኑት ይልቅስ እንደሚያጋግሉት፤ ሠዓሊው መርጦ የሚፈጽመው እንደሆነ በትርዒቱ በከፊልም ቢሆን የሚንጸባረቅ ሲሆን ትርዒቱን በታደምኩበት የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓትም ሆነ ይህን ፅሁፍ ለማዘጋጀት ሳስብ ትርዒቱን  ደጋግሜ ባየሁባቸው ጊዜያት ትኩረቴን የሳቡ ወሽመጥ መሳይ ሃሳቦች ውል ብለውብኛል። እነዚህን ሃሳቦች ላነሳቸውና ልወያይባቸው በመሻቴም ይህ ፅሁፍ ተዘጋጅቷል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ነበሩ ትርዒቱን የከፈቱት፡፡ ምንም አይነት ንግግር ሳያደርጉ ትርዒቱን መክፈታቸው ትንሽ የሚያስገርም ቢሆንም በሚኒስትር የሥነ-ጥበብ ትርዒት መከፈቱ ብቻ ‘ለሥነ-ጥበባችን ሕዳሴ’ አበረታች  ጅማሬ ይመስለኛል፡፡ የሙዚየሙ ሃላፊ ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ ከማለት ውጪ እንደ ሥነ-ጥበብ አጋፋሪ፣ ስለ ትርዒቱ በቃል እንኳን ባይሆን በጽሑፍ ሃሳባቸውን ማቀበል አለመቻላቸው ሌሎች በዚህ ጽሁፍ መባቻ ከማነሳቸው ነጥቦች ጋር ተዳምሮ ትርዒቱን አጋፋሪ የሌለው ያስመሰለው ሲሆን ምናልባትም በጥቂት ቀናት ውስጥ ታትሞ ለውይይቱ እንደሚደርስ ቃል የተገባው ካታሎግ ላይ የአጋፋሪነት ሃሳባቸውን እንደሚያሰፍሩ ተስፋ በማድረግ ሊታለፍ ይችላል፡፡
በትርዒቱ የቀረቡ ስራዎች በቁጥር ስምንት ናቸው። ከእነዚህ ውስጥም አራቱ በኩልኮላ (Installation) ማለትም ለማስተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት የሚወክሉ የተለያዩ ቁሶችን በመደርደርና በመኮልኮል የሥነ-ጥበብ ውጤት በማቅረብ የተከወኑ ሲሆኑ ከቀሪዎቹ አራቱ መሃከል ሁለቱ በቀለም ቅብና በድብልቅ ቁስ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ የባለ ሁለት አውታር መጠን ቅርጽ ባህሪ ያላቸው ሥራዎች ናቸው፡፡
ትርዒቱ ዘመናዊ (Modern) እና ዘመንኛ (Contemporary) የሥነ-ጥበብ የአሰራር መንገዶችን እየመላለስ ጥቅም ላይ በማዋል፣ የዘመናዊና የዘመንኛ አስተሳስብ መሰረቶችን መለስ ብለን እንድንቃኝ እድል ይከፍትልናል፡፡ ሆኖም ይህ እድል በተለያዩ የዓለም ሃገራት ተጉዞ ስራዎቹን ማሳየት ብቻ ሳይሆን አንቱታን ያተረፈ፤ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በሃገራችን ሥነ-ጥበብ ልዩ ገጽ ያሳየው የዳይሜንሽን ግሩፕ መስራች ከሆኑት አንዱና ቡድኑን ካንቀሳቀሱት መሃል ሰፊ ድርሻ የነበረው፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ውስጥ ለሶስት አስርት ዓመታት ገደማ በመምህርነትና ሁለት ጊዜያት ት/ቤቱን በዳይሬክተርነት ሲመራ በቆየባቸው አመታትና ከዚያም በቀጠሉት ጊዜያት በተለይ በሥነ-ጥበብ አሰራር የአስተሳሰብ መንገዶች ት/ቤቱ ካዳበረውና ካቆየው ባህል ያፈነገጡና ዘመናዊና ዘመንኛ የሥነ-ጥበብ አሰራሮችን ከማስተዋወቅ በዘለለ የሚታይ ተጽዕኖ ከፈጠረና የፈጠረውም ተጽዕኖ የት/ቤቱ የትምህርት አሰጣጥና አቀባበል ባሕል በተለይ ባለፉት ጥቂት አመታት መንታ መንገድ ላይ እንዲገኝ ካደረገ ተጽዕኖ ፈጣሪ፤ ት/ቤቱ በዘመኑ እውን ካደረጋቸው እመርታዎች መሃል አንዱ የሆነው የሥነ-ጥበብና የፊልም ድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን በመፍጠር ሂደት ጉልህ ሚና ከተጫወተ ባለሙያ፤ እንዲሁም ከአስር ዓመታት በኋላ የግል ትርዒቱን ለዕይታ ካበቃ ታላቅ ሰዓሊ ልምድ አንፃር፣ የትርዒቱን ዳራዎች ለማመላከት የተሞከረው ሠዓሊው በፃፈው መደንግግ ላይ ብቻ መሆኑ፤ በመደንግጉም ላይ በዕይታ የቀረቡት ስራዎች ከሚሰነዝሩት ቡጢ አንፃር በማዋዛትና በማለሳለስ፣ እንደውም ዲፕሎማሲያዊ በሚመስል አቀራረብ የተነተናቸው ‘እፍኝ  ሀሳቦች’ በትርዒቱ የቀረቡትን ግዘፍ የሚነሱና ክርር ያሉ ሀሳቦችን የማለዘብ ውጥን ያላቸው መስለው ታይተውኛል፡፡
በነገራችን ላይ ትርዒቱ በዋነኝነት የፌደራል ፖሊሶችንና የጳጳሳትን አልባሳት እንደ ‘እይታዊ ሆሄ’ ተጠቅሟል፡፡ ሠዓሊው በመደንግጉ እንደገለፀውና እኔም ከዚህ በመቀጠል አሳጥሬ እንደማቀርበው በሰው ልጅና በሚለብሰው ልብስ መካከል ያለው አስገራሚ ግንኙነት … የሰው ገላ በሚሸፍነው ጨርቅ የተነሳ በተመልካቹም በለባሹም አስተሳሰብ ላይ ብርቱ ተፅዕኖ ስለመፍጠሩ … በየዘመኑ እየተራቀቀ የመጣው የሰው ልጅ ገላን የመሸፈን ባህል በራሱ ትልቅ የጥናትና የማስላሰያ ርዕስ ጉዳይ መሆኑ … ጨርቆቹን ከስቱዲዮው በማኖር ሲወጣ ሲገባ እያነጋገራቸው … የፈጠሩበት ምስልና የኮረኮሩትን ሀሳብ በሚታይ ድርሰት ለማደራጀት ባለፈበት ሂደት፤ “በጨርቆቹ መስኮትነት የህይወታችንን መዛግብት ከትውስታችን ሰማያት፤ ከምኞታችን ኮሮጆ፣ ከድርጊታችን አደባባይ የሚቀዳ አንዳች የመስል ቁዋት እንደማላጣ እርግጠኛ ሆንኩ። ታዲያ እነዚህ ምስሎች ተገኙም አልተገኙም፣ የማብራራትና የመተረክ ተልዕኮ የላቸውም፤ የትኛውንም አስተያየትና አመለካከት ለመሞገት ወይም ለመስበክ የታለሙም አይደሉም፡ … እንደ እድል ሆኖ የሚኮረኩሩት ጥያቄ ወይም ግርታ ካለ ውይይት አለ፤ ትችትና አቃቂር አለ ማለት ነው። በደረስንበት ዘመን ከዚህ በላይ ምን ትርፍ አለ!” ይላል፡፡
እኔ ግን ይህ ትርዒት እንደ ስያሜው ያመቀው ‘ባሩድና ብርጉድ’ በተወለወለ መነፅር እንዲተኮርና በተኮረኮረ ጆሮ እንዲሰማ፣ በተገራ ጽንሰ ሃሳባዊ መሰረት መቃኘት አለበት እላለሁ [የትርዒቱ ካታሎግ ይህን አሟልቶ ሊሆን ይችል ይሆናል]። ለተመልካችና ለአንባቢ የተሸፈነውን የመግለፅ፣ ፀሐይ የማሞቅና ይበልጥ የማብሰል፣ የበሰለውን ተመግበን ህዋሳችን እንዲጎለብት፣ ህሊናችን እንዲነቃ ማድረግን ታሳቢ በማድረግ የሚከተለው ጽንሰ ሃሳባዊ ደጀን የትርዒቱ አካል ሆኖ ቢታሰብ እንደሚበጅ በማመን  እቀጥላለሁ፡፡
ዘመናዊነት
አንድ ዘመን የሚያስተናግዳቸው አንኳር ክስተቶችና አስተሳሰቦች በጊዜው የሚካሄዱ የማህበራዊ፣ የባህላዊ፣ የኢኮኖሚያዊ፣ የፖለቲካዊ… ወዘተ ጉዳዮች የውይይት ትኩረት ከመሆናቸው ባሻገር ስለ አንድ ማህበረሰብ፣ ሃገርና በጠቅላላው የሰው ልጅ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥን ለመቃኘት ያስችለናል፡፡ ዘመን የሚያስተናግዳቸው ክስተቶችና የምክንያታዊ ሚዛንን የሚደፋ አስተሳሰቦችን መሰረት በማድረግ የሚነሱ የአኗኗር፣ የአስተሳሰብና የለውጥ ክዋኔዎችን እውን ማድረግ መቻል ወይም እውን ለማድረግ መሞከር ዘመናዊነት ይባላል፡፡
በዘመናዊነት ላይ ጥናቶችን ማድረግና መፈላሰፍ ብቻ ሳይሆን ዘመናዊነትን በተብላሉና ጠንካራ መሰረት ባላቸውና ዓለም-አቀፋዊ እንዲሁም ታሪካዊ ፍልስፍናዎች ጋር አቆራኝተው በመተንተን የሚታወቁት ጎምቱው ምሁር ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፤ Modernity: Its Uniqueness and Its Advent in Ethiopia  በተሰኘው ጽሑፋቸው ያካተቷቸው ዋና ዋና የዘመናዊነት ልዩ ባህሪያትን በማውሳት፣ ‹ባሩድና ብርጉድ› እንዴት ከዚህ የዘመናዊነት ግዘፍ-ሚነሳ ትረካ(Grand Narrative) ጥላ ውስጥ በምን አይነት አቋቋም የቆመ ትርዒት እንደሆነ ለማመላከት እሞክራለሁ፡፡
ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ በፅሑፋቸው፣ የሄግልያን ፍልስፍናን በመጥቀስ፣ ዘመናዊነት በየታሪክ ምዕራፎቹ ጫፍ ሊያሳካ የሚሻው የመጨረሻ ግብ፣ የሰው ልጅን ነፃነት እውን ማድረግ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በዚህም ረገድ የአብራሄ-ጥበብ (Enlightment) እሴቶች እንዲሁም ይበልጥ ቅርብና ቀጥታ በሆነ መንገድ የፈረንሳይ አብዮት ሶስቱ እሴቶች ማለትም፡- ነፃነትን እኩልነትንና ወንድማማችነትን - ዘመናዊነት እውን ያደርጋል ማለት ነው፡፡ በዚህም የሀይማኖታዊና የትውፊታዊ የበላይነቶች እንዲሁም ያለፈባቸው ወይም እያለፈባቸው ያሉ የበላይነት መገለጫዎች እንዲያሽቆለቁሉ ወይም እንዲያከትሙ በማገዝ፣ ዘመናዊነት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ በውጤቱም፣ ዘመናዊ የመንግስት አገዛዝም ሆነ ስልጣንን በጉልበት የሚያስቀጥል አገዛዝ፣ አግባብና ተቀባይነት ባለው ሂደት እንዲመራ፣ ዘመናዊነት ይሞግተዋል፡፡
ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰቦች ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ፍልስፍናዊና ሞራላዊ መመሪያዎች፣ በአንድ ዘመን ተነስተው ወዲያውኑ የሚጠፉ ታሪካዊ ሁኔታዎች ሳይሆኑ ይልቅስ የዲሞክራሲ ህዝባዊ ባህል ቋሚ መገለጫ እንደሆኑ ዶን ራውልስን በመጥቅስ፣ ፕሮፌሰር አንድሪያስ ያብራራሉ፡፡ ዘመናዊ አኗኗር በሂደቱም ምክንያታዊ ንግግሮችንና መግባባቶችን ያካትታል፡፡ በዚህም ለማህበረሰቡ ‹ልክ› እና ‹ፍትሃዊ› የሆነውን አካሄድ መቀየስም፣ ዘመናዊነት የሚያሳካው ተቀዳሚና ብቸኛ ግብ ነው፡፡ ከላይ የተገለፁት ነጥቦች ሲጠቃለሉም፣ የዘመናዊነት ልዩ ባህሪያት አንድም ነፃነትን ምሉዕነት በተላበሰ መልኩ ክሱት ማድረግ አልያም ነፃነት ሊገኝ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ነው፡፡  
አንድ ዘመናዊ ለመሆን የሚያስብ ማህበረሰብና ሀገር፣ ዲሞክራሲን ለማስፈን በመረባረቢያ የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የተለያዩ ግጭቶች ሊነሱ እንደሚችሉም ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም ዲሞክራሲ ማለት ዜግነትና ሉአላዊነት የሚጣመሩበት ሂደት በመሆኑ፣ የተለያዩ ልማዳዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ትውፊታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ …ወዘተ መስተጋብሮች ዜጎችን እኩል ባይሆንም ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ ሲገባቸው፣ አንደኛው ወይም የተወሰኑ የማህበረሰቡ ወይም የሀገሪቱ ዜጎች የበላይ እንዲሆኑ በማድረግ ግጭቶችና ወንጀሎች እንዲበራከቱ እድል ሊፈጥር መቻሉ፣ የዘመናዊነት አሉታዊ ጥላ እንደሆነ ምሳሌዎችን በማንሳት ፕሮፌሰር ያትታሉ፡፡ ከዚህ አይነት አሉታዊ ጥላዎች ባሻገር የአንድ ሃገር ህዝቦች ወይም የሰው ልጆች ሊጋሯቸው የሚችሏቸው እሴቶች፣ ዓላማዎችና ትስስሮችን በመከሰት የአንድነት ዘመናዊ መገለጫ የሆነው ወንድማማችነትን እውን ማድረግ መቻል፣ የዘመናዊነት የማይካድ ትሩፋት ነው፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብና ዜጋ ባለቤትነት የሚኖረውና የሚጋራው የጋራ መዳረሻ ብቻ ሳይሆን የጋራ እጣ ፈንታና የጋራ ህዝባዊ ባህል መፍጠር፣ የዘመናዊነት ስኬት እንደሆነ ፕሮፌሰር አንድሪያስ ያመላክታሉ፡፡
የዘመናዊ ህይወት ጥልቅ የሞራል መርህ፣ የሰው ልጆች ህይወት፣ እኩልነትና ክብር ነው። ተጠቃሚነታቸው በማይመጣጠን መልኩ አብዛኛውን ጥቅም የሚያጋብሱ የማህበረሰብ አባላትና ዜጎች፣ በሀገራቸው ከእነሱ ቀጥሎ ለሚመጡት ትውልዶች የማይመች ሁኔታ ከመፍጠራቸው ባሻገር በማህበረሰባቸው ውስጥ እና በዙሪያቸው ባለው ዓለም የሚገኙ ድሆች፣ ትርጉም ያለው ህይወት እንዳይመሩ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ሁኔታዎች እየተባባሱ፣ አንድ ሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ ቀውሶች እየተወሳሰቡ ሊቀለበስ የማይችል አዘቅት ውስጥ ሲገባ፤ ሁኔታዎች ከአቅም በላይ ሆኖባቸው በዝምታ የተቀመጡ የነበሩት ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ ዜጎችና የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ዘላቂ መፍትሔ መሻት ይጀምራሉ፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች እንዴት በ‹ባሩድና ብርጉድ› እንደተንፀባረቁና ትርዒቱ በምን አይነት መልኩ የዘመናዊነት ጥላ ውስጥ የሚገኝ ስለመሆኑ ተዛምዶችን ከማሳየቴ በፊት ከዘመናዊነት ስለሚወለደው ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ (Modern Art) እንዲሁም የልጅ ልጁ ስለሆነው ዘመንኛ ሥነ-ጥበብ(Contemporary Art) በማተት፣ የ’ባሩድና ብርጉድ’ን ዘመናዊነትና ዘመንኛነትን አመላክታለሁ፡፡
ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ፤ የሥነ-ጥበብ እሴትና ሚና አዲስ በሆኑ መንገዶች እንዲታይ የቁሶችን ተፈጥሮና ግልጋሎት በተለየ ሁኔታ ጥቅም ላይ የሚያውል፤ ትኩረቱም የዘመናዊ ማህበረሰብን ወይም የማህበረሰቡን አኗኗርና የአስተሳሰብ ሂደቶች ለመግለፅ ሲሆን ከቀደምት የሥነ-ጥበብ አሰራሮች ይልቅ አዳዲስ ፈጠራዎች፣ ሙከራዎችና ቅርፆች መገለጫዎቹ ናቸው። ይህን የሚያደርግበት ምክንያት የሚዛመደውም የሰው ልጅን አይነተኛ ራዕይና ማህበረሰብ በለውጥ ሂደት የሚያጋጥመውን ሁኔታዎች በማሄስ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዘመንኛ ሥነ-ጥበብ፤ ወቅታዊ በሆኑ ክስተቶችና የህዝብ አመለካከት አዝማሚያዎች ላይ ተመስርቶ ሥር-ነቀል፣ አዲስና አሁን እንዲያውም ዘመኑን የሚቀድሙ ሀሳቦችን በተለያዩ የሥነ-ጥበብ አሰራር ዘይቤዎች የሚያቀርብ ነው፡፡ የዘመንኛ ሥነ-ጥበብ ትርጓሜዎች በሚተርኩት ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ሀሳቦቹ በሚዛመዷቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያም ያጠነጥናሉ፡፡ ዘመንኛ ሥነ-ጥበብን ይበልጥ ከሚገልፁ ሶስት የጊዜ መረዳቶችን ብንመለከት፡- አንደኛው የነበሩ ነገሮች እንደሚወድሙ፣ ሁለተኛው የነበሩ ነገሮች እንደሚቀየሩ፣ ሦስተኛ የነበሩ ነገሮች ሲጠፉና ሲቀያየሩ የሚቀረው ብዥታ ላይ ዘመንኛ ሥነ-ጥበብ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ እንረዳለን፡፡
በመቀጠል ‹ባሩድና ብርጉድ› የዘመናዊነት ጥላ ውስጥ የቆመውን አቋቋም፣ ከዘመናዊ ሥነ-ጥበብ እና ከዘመንኛ ሥነ-ጥበብ አንፃር እገልፀዋለሁ፡፡ መቼም ብዙ አደከምኳችሁ!
የትርዒቱ ስያሜ ከሆነው ‘ባሩድና ብርጉድ’  እጀምራለሁ፡፡ በዚህ የኩልኮላ ሥራ፣ በፋይበር ግላስ የተሰሩ አምስት ባለ ሦስት አውታረ መጠን ቅርጾች፣ የፌደራል ፖሊስ መለያ አልባሳትና ጫማ የለበሱና በለበሱት ጨርቅ ፊታቸው የተሸፈኑ፣ አቋቋማቸው በተጠንቀቅና ዘብ ላይ ያሉ የሚመስሉ[ግትር ብለው መቆማቸው ለማስፈራራትና ለማናደድ እንደታለመ የሚያሳብቅባቸው]፣ ሌሎች አምስት ባለ ሦስት አውታረ መጠን ቅርጾች ደግሞ የቤተ-ክህነት አልባሳት ለብሰው /አገልግሎት….. በጨርቁ ፊታቸውን ሸፍነው እግራቸው የሆኑ፣ አቋቋማቸው መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰሩ ያሉና በግልጋሎታቸውም ልባቸውና ሁለመናቸው የተዳከመ የሚመስሉ ናቸው፡፡ የባሩድና የዕጣን ብርጉድ ቅልቅል ‹ጭስ› በመሃከላቸው ይጨሳል፡፡ አፍንጫን ከመሰንፈጡ ባሻገር ደስ የማይል ስሜት ይፈጥራል። ሁለቱም በአንድነት መቆማቸውና አኳሃናቸው ሠዓሊው በመደንግጉ፣ በገሃዱ ዓለም ከሁለቱም ፊት ስንቆም ‘ያርዱናል ያንቀጠቅጡናል’ ያለውን ያስተጋባሉ፡፡ ለምን ያርዱናል? ሠዓሊው በመደንግጉ እንደገለፀው፤ ትችትና አቃቂር  ለማውጣት ወይም ለውይይት በር ለመክፈት የታለመ ብቻ ሳይሆን የምናወጣው አቃቂርና ትችት ከምን አይነት የኑሮአችን ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እንደሚዛመድ ራሳችንን እንድንጠይቅ፣ እነሱም በማራድና በማንቀጥቀጥ እንዲቆጣጠሩን ስልጣን የሰጣቸውን አካል፣ ባሕሪና መገለጫን ሞግቶ፣ እንድንሞግት እየጋበዘን ሳለ፣ ‘የማብራራትና የመተረክ ተልዕኮ የላቸውም፤ የትኛውንም አስተያየትና አመለካከት ለመሞገት ወይም ለመስበክ የታለሙም አይደሉም’ በማለት ሠዓሊው በመደንግጉ መግለጹ፣ በሥነ-ጥበብ ስራው በግልጽ የተናገረውን ወይም ያለውን በጽሁፍ መሻሩ፣ ድፍረት ማጣት ወይም አለመፈለግ ሊሆን ይችላል። ወይም ተመልካች የራሱን ልምድ በዕይታው እንዲያክል ለመገፋፋት ይሆናል፡፡ እነዚህን ሁለት “ጨርቆች” የሚለብሱ ግለሰቦች፣መሰረቶች መዋቅሮች ናቸው፡፡ አንደኛው የሃይማኖት ሌላኛው የመንግስት። ሁለቱም በዜጎችና በግለሰቦች ላይ የተለያዩ የበላይነቶችን ይዘው ይገኛሉ፡፡ የበላይ መሆን ብቻ ሳይሆን ማንቀጥቀጥና መቀጥቀጥ፤ ማራድና ማሸበር የተሠጣቸው ፀጋ እስኪመስል በበላይነት ይቆጣጠሩናል። አንደኛው ሌላኛውን ደግፎ ወይም ተደርቦለት ሲተጋገዙ ያየንባቸውና እያየን ያለንባቸው የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታዎች አያሌ ናቸው፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ? በትርዒቱ የቀረቡ ሌሎች ስራዎችንና ለመንደርደሪያነት ያስቀመጥኩትን የዘመናዊነት እሳቤዎችን እያጣቀስኩ እቀጥላለሁ፡፡
ከጥንት ጀምሮ ከኃይማኖት ጋር በእጅጉ የተቆራኘው አኗኗራችንና የተለያዩ ቀደምት መንግስታትን ጨምሮ በአሁኑ ዘመን ሃገሪቱን የሚያስተዳድረው የአገዛዝ ስርዓት በምን መልኩ ነው ሃገሪቷን የዘመናዊ አስተሳሰብና አኗኗር ባለቤት ለማድረግ የሞከሩት? ዜጎችስ ምን አይነት ነጻነትና እኩልነት እንዲኖራቸው አስቻሉ? ሠዓሊው በትርዒቱ የተጠቀመው ጨርቅ፤ የክቡር ዘበኛ አይደለም፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌደራል ፖሊስ መለዮን ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው በቀጥታ ወደ አሁን ዘመንና አስተዳደር ጣቶቹን ይቀስራል። አግባብና ተቀባይነት ባለው ሂደት እየተመራን ነው? ከሆነስ ለምን ከፌደራል ፖሊስ ፊት መራድና መንቀጥቀጥ እጣ ፈንታችን ይሆናል? ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ መንግስታችን ነጻነትን ምሉዕነት በተላበሰ መልኩ ክሱት ማድረግ ባይሆንለት ነፃነት ሊገኝ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች በማመቻቸት ይገለፃልን? መንግስታችን ባሳለፈው የአገዛዝ ሂደት ውስጥ ፖለቲካዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ትውፊታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ …ወዘተ መስተጋብሮቻችን ዜጎችን እኩል ባይሆንም ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ ያደረጋቸው ጥረቶች እንዴት ይገለጻሉ? ያሳካው ወንድማማችነት እንዴት ታይቷል? ሃገራችን እያስተናገደቻቸው ያሉ የሚመስሉ ቀውሶች እየተወሳሰቡ ሊቀለበስ የማይችል አዘቅት ውስጥ እንዳይከቷት አሁን ያለንበት ጊዜ እጅግ ወሳኝ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ትርዒቱ ካቀረባቸው ስራዎች መሃከል ‘ባለ አስራ ሁለቱ ከረሜላ’ የተሰኘው ስራ የሥነ-ጥበብ ለዛ፣ ውበትና ትንኩሽነት ተጣምረው የታዩበትና ሃሳቡ እንደ ከረሜላ እየጣፈጠ፣ በሁለመናችን የሚሟሟና የሚዋኻደን ነው። ከረሜላ ቁርጥ የኮብልስቶን ድንጋይ፣ በቤተ-ክህነት አልባሳትና በፌደራል ፖሊስ መለዮ ጨርቅ እንደ ከረሜላ ተጠቅልለው ቀርበዋል። ሄዳችሁ ቅመሱትማ፤ ሲጣፍጥ!
የምርት ማስፋፊያ ኃይሎችን ማሻሻል የአንድ ሃገር ማህበረሰብ በቀዳሚነት ሊያሳካው የሚገባው ተልዕኮ እንደሆነ ካርል ማርክስ ይተነትናል፡፡ እኛ ከሶስት ሺህ አመታት በላይ በማረሻ አርሰናል፣ እያረስንም ነው፤ እንደ ቸርነቱ፡፡ መቶ ሚሊዮን ነን፤ እንደ ቸርነቱ፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኤኮኖሚ ለመሸጋገር እየሰራንም ነው፤ እንደ ቸርነቱ፡፡ ሠዓሊ በቀለ መኮንን ከአስር አመታት በፊት ማረሻን እንደ እይታዊ ሆሄው ፈልስፎ ተፈላስፎበታል። ያውም ‘አንት ማረሻ፡ ስንቱ በረሃብ እየተረፈረፈ ማነህ እንዲህ በኩራት ሾለህ የምታቅራራው?’ ብሎ እንደ ወንድ ብልት የሾለው ጫፉን ቆልምሞ ነበር፣ አንገቱን ያስደፋው ወይም የተኮላሸ መሆኑን የገለጸው፡፡ በዚህ ትርዒት ዳግም ቀና እንዲል ቢፈቅድለትም ሹል ጫፉን ወደ ላይ ሳይሆን ወደ ጎን አጋድሞ፣ የተጠቀሱትን ጨርቆች እንደ ኮንደም ለጥፎበት፣ ‘ደቦቃ ድርድር’ አጋድሞታል፡፡ ‘ደቦቃ ድርድር’ ምን ይሆን? ሄዳችሁ ተመልከቱ፡፡
‘የዘመን ግርዶሽ በጨርቅ ጭላንጭል’ የተሰኘው ስራ አንድ፣ ሁለት ግድግዳ ብቻ ያለው ቤት ሕይወት ያስቃኘናል፡፡ የቤቱ ሁለቱ ግድግዳዎችና ወለሉ የሚያስቃኘን ቤት ሳይሆኑ የሙዚየሙ ናቸው፡ ምንም አይነት ሥነ-ጥበባዊ ጥረትና ድካም አልፈሰሰባቸውምና። ይህ በመሆኑም የስራውን ደርዝ ቀነስ አድርጎታል። በስተቀር፣ የዘመን ግርዶሽ በበሩና በአንደኛው ግድግዳ ላይ በተሰቀሉት ፎቶዎች፣ ደብዳቤዎች፣ የአበባ ማስቀመጫ በሆነው የመድፍ ቀለሃ፣ በጽዋ፣ ዳንቴል ጣል ባለባት ናሽናል ቴፕና ሌሎች ቁሶች ግርዶሹ አለ፡፡
‘የተዓምራት ዕዳ’ ፖለቲካ ስለሆነ አልነካካውም፤ ሄዳችሁ ተመልከቱት፡፡ አንድ ታዳሚ በመክፈቻው ዕለት፤ “ቶሎ ብለን ፎቶ እናንሳው፤ ፌዴራል መጥቶ በኤግዚቢትነት ሳይወስደው” ያሉት እውነት ከመከሰቱ  በፊት እንድታዩት እመክራችኋለሁ፡፡
ሳጠቃልል፡- ዘመናዊና ዘመንኛ ሥነ-ጥበብን መሰረት በማድረግ በስፋት ወቅታዊ የሃገራችን ጉዳዮችን የሚያሳስቡ ስራዎችን ባቀረበ ትርዒት የሚሞግት ሃሳብ፣ በዘመናዊነት እሳቤ ጥላ ስር ፈልሰስ ብሎ እየታየ፣ ‘የማብራራትና የመተረክ ተልዕኮ የላቸውም፤ የትኛውንም አስተያየትና አመለካከት ለመሞገት ወይም ለመስበክ የታለሙም አይደሉም’ ማለት ‘ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ’ን በስላቅ ያስታውሰኛል፡፡ የሥነ-ጥበብን የማንቃትና የማወያየት ኃይል ይቀንሳል። እሴት ያለው ትርዒትን  ያጫጫል፡፡ በዚህም ረገድ አደባባይ ወጥቶ ጸሃይ እንዲሞቅ የተፈለገው የሥነ-ጥበብ ውጤት የገባው ብቻ እንዲገባው እንጂ ስራው የቀረበበት ሙዚየም፤ ስራውና ማህበረሰቡ እንዲገናኙ መወጣት የሚገባውን ሚና እንደዘነጋ ብቻ ሳይሆን ግድ እንደማይሰጠው  ዳግመኛ ያስመሰከረበት ትርዒት ነው - ‘ባሩድና ብርጉድ’፡፡ ቸር እንሰንብት!

Read 1834 times