Saturday, 13 January 2018 15:51

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(5 votes)

    “ጊዜው አሁን ነው፤ እውነቱን የምንነጋገርበት”
             
   ጊዜ አይከሰስ፣
ጊዜ አይገረሰስ፣
ጊዜ ጥርሱን ሲነክስ፣
አይጣል ነው! አያድርስ!!
ጊዜ የሰጠው ቅል
ድንጋይ ሲፈረክስ፣
ጊዜ የሰጣት አይጥ
ዝሆን ስትገነድስ፣
አይጣል ነው! አያድርስ!!
ጊዜ ጊዜን ወልዶ፣
ጊዜ ጊዜን ሽሮ፣
እንደ ወራጅ ውሃ፣
እንደ ሴት ሸረሪት፣
ራሱን በራሱ ተክቶ እስከሚፈስ፣
ራሱን በራሱ በልቶ እስከሚጨርስ፣
አይጣል ነው! አያድርስ!!
ውጣ ውረድ በበዛበት፤ በሾሃማው የህይወት መንገድ ተጉዘን ከግባችን የምንደርሰው፣ ዱላና ስቃይን የምንቋቋምበት፣ አቅም ስናዳብር ነው፡፡ (Any man who wants to go far along life’s tough road must set himself to develop his power of resistance to blown and pressures) የሚለን ኸርበርት ኤን ካርሲኦን ሲሆን ሚካኤል ፕሮስትም፤ “ከመከራና ስቃይ የምንገላገለው፣ መከራና ስቃይን በደንብ ስንለማመደው ነው።” (we are healed of a suffering only by expreiencing it) በማለት ከላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ እውነትነት ያረጋግጥልናል፡፡
“ጊዜው አሁን ነው!! እውነቱን የምንነጋገርበት፤ እስከ ዛሬ ድረስ ችለነው፤ ደብቀነው፣ ሸሽገነው ያኖርነውን ምሬት አደባባይ የምናወጣበት!! … ‹በቃ!› የምንልበት ጊዜ አሁን ነው!!” በማለት የተናገረችው ኦፕራ ዊንፍሬይ፤ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር፡፡ ኦፕራ ለዚህ ታላቅ ሽልማት የበቃች የመጀመሪያዋ አፍሪካን አሜሪካን ሴት ናት። የዚሁ ሽልማት አሸናፊ የነበረው የመጀመሪያው ጥቁር ደግሞ “To Sir with love, Guess who is coming to dinner” እና ሌሎች ብዙ ታዋቂ ፊልሞችን በመሪ ተዋናይነት የተጫወተው ሲድኒ ፖይተ ነበር፡፡
ሲድኒ ፖይተ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፣ ከንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ጋር በመሆን ከሰራቸው ፊልሞች ውስጥ አንደኛውን በአምባሳደር ሲኒማ ቤት ታድመዋል ተብሎ ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ ይህን ጉዳይ ፖይተ በፃፈው የህይወት ታሪኩ መጽሐፍ ውስጥ ግን አልጠቀሰውም፡፡
“ጊዜው አሁን ነው!! … ጊዜ ለጨቋኞች በሚያደላበት ቦታ ፍትህ ማግኘት አይቻልም፡፡ … ፍትህ ትሞታለች” ያለችው ኦፕራ፤ ከብዙ ዓመታት በፊት በስድስት ወሮበሎች ጥቃት የደረሰባት፣ በጊዜ አድልዎ ምክንያት ፍትህ የተጓደሉባት ስትሆን፣ ከአስር ቀናት በፊት በሞት ስለተለየችው ምስኪን ሴትም አንጀት የሚበላ ታሪክ ነግራናለች፡፡
በዚሁ የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ዛሬ ትልቅ ቦታ የደረሱ ሴት ተዋንያንና ሌሎች ታድመዋል። አሁን ለደረሱበት ዝና ባመጣቸው የስኬት መንገድ ላይ ለመግባት የከፈሉትን ‹የመስዋዕትነት ጉቦ› በማስታወስ “Me too!” እና “Time is up!” በሚሉ መፈክሮች በታጀቡ ኡኡታዎች ያለውን ጊዜ ኢ-ፍትሃዊነት አጋልጠዋል፡፡ ኦፕራ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ አገራችን በመምጣት ለፌስቱላ ሆስፒታልና በህመሙ ለተጠቁ ወገኖቻችን ትልቅ መፅናኛና ድጋፍ አድርጋለች፡፡
ወዳጄ ጊዜ ደፋሩን ፈሪ፣ ፈሪውን ደፋር፣ ጠንካራውን አሽመድምዶ፣ ሸመድማዳውን ጠንካራ የማድረግ ዐቅም አለው!! … ጊዜ .. አዋቂውን እንዳላዋቂ፣ ደንቆሮውን እንደ ሊቅ ማስመሰል ይችላል!! … ጊዜ .. ብረት የማጉበጥ፣ ትውልድ የመስበር ኃይል አለው!! .. ጊዜ ከምንም አንስቶ ሊያነግስህ ወይ የተቀመጥክበትን ዙፋን በጠረባ የመዘረር ስልጣን አለው!! … ጊዜ ለወንድምህ ገነት፣ ላንተ ሲዖል ሊሆን ይችላል!!
አንዳንድ ሊቃውንት .. “ጊዜ የምንለው ነገር የሚኖረው የሆነ ወይ የተደረገ፣ በመሆን ወይ በመደረግ ላይ ያለ ነገር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ወደፊት ሊኖር ወይ ሊደረግ የሚችል ነገር ውስጥ ሃሳብ እንጂ ጊዜ የለም” … ይላሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ቡና ወይም ሌላ ነገር ቢተክልና ከሶስት ወይ ከአራት ዓመት በኋላ ያፈራልኛል ብሎ ቢያስብ፣ ወይ ከአምስት ዓመት በኋላ ዕድሜዬ አርባ ወይም ሃምሳ ይሞላል ብሎ ቢናገር፣ ነገሩ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ ስለዚህ ጊዜ ‹ጊዜ› የሚሆነው አንድ ነገር በተጨባጭ ሲከሰት ወይም ሲኖር (emprical) በመሆኑ፣ የሰዎቹ ሃሳብ ‹ሃሳብ ብቻ› ሆኖ ይቀራል ለማለት ነው፡፡ የምንኖርባትም ሆነ ሌሎች ዓለማት ከመፈጠራቸው በፊት ጊዜን ማሰብ አይቻልም፡፡ … እንደ ማለት ይመስላል፡፡
“እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር በጊዜ ውስጥ ሳይሆን ከጊዜ ጋር ነው፡፡ ፍጥረትና ጊዜ የማይቀዳደሙና የማይነጣጠሉ ኩነቶች ናቸው፡፡” (Non intempore, sed cum tempore fin xit Deus mundum) በማለት ሊቁ አውግስጢኖስ የፃፈው ከላይ ለተመለከትነው ሃሳብ እንደማረጋገጫ ይጠቀሳል፡፡
ወዳጄ … እስኪ አንድ ነገር ልብ በል፡፡ … የበቁ፣ የነቁና ያወቁ ሰዎች አሉ ይባላል፡፡ ህመምን ያሸነፉ፣ ምኞትና ፍላጎታቸውን (desire) ገርተው ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲታዘዝላቸው ማድረግ የሚችሉ፣ (Nirvana, Mukti, the highest level of consciousness, life of contemplation እንደሚባለው) … የአእምሮአቸውን የማሰብ ዓቅም `average man` ከሚባለው ሰው እጅግ በላቀ መጠን ያዳበሩ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ጊዜን ማቆም ወይም ጊዜ እነሱ እንደሚፈልጉት እንዲሆንላቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሰብዕና የሚገነባው ያለ መታከት ከማንበብና ዕውቀትን ከመሻት ነው ይላሉ፡፡
አንተስ ወዳጄ የማሰብ አቅምህ እንዲጎለብት፣ ሩቅ ተጓዥ እንድትሆን፣ የውስጥህ ብርሃን እንዲንቦገቦግ የምትተጋበት ጊዜ መቼ ነው? “የአንድ ሺህ ማይል ርቀት ከአንድ እርምጃ ይጀምራል።” (Ajourney of one thousand miles starts from a pace) ይባላልና …“ጊዜው አሁን ነው!!` ብለህ ብትጀምር ብልህነት አይመስልህም?
ወዳጄ ልቤ፤ ዞሮ ዞሮ ጨዋታችን በጊዜ ዙርያ የሚሽከረክር ይመስላል፡፡ ወይስ ጊዜ ጨዋታችንን እያሽከረከረው ይሆን?... ጊዜና ሰው፣ ሰውና ኑሮው፣ ኑሮና ምሬት፣ ምሬትና ቀልድ መቼም የተሳሰሩ ናቸው…
ሰውየው ባጋጣሚ ከእግዜር ጋር ተገናኘ አሉ፡፡ በጨዋታቸው መሃል፡-
“ለጊዜው ያለህ ትርጉም እንዴት ነው?” በማለት ሰውየው እግዜርን ጠየቀው፡፡...
እግዜርም..
“ለኔ አንድ ቢሊዮን ዓመት ማለት አንዲት ሰከንድ ማለት ናት” ሲል መለሰለት፡፡
“ገንዘብ ላይስ?”
“እሱም እንደዛው ነው፡፡… አንድ ቢሊዮን ዶላር፣ ለኔ አንዲት ሳንቲም ማለት ናት”
ሰውየው በእግዜር ፀጋ እየተደነቀ፣ ሲፈራ ሲቸር…
“ታዲያ ምናለ አንዲት ሳንቲም ጠብ ብታደርግልኝ?” አለው በአይኑ እየተለማመጠው።
እግዜርም… “ችግር የለም! አንዲት ሰከንድ ብቻ ጠብቀኝ”… አለው፡፡
ሰውዬው እስካሁን እየጠበቀ ነው። ወደ መነሻችን ስንመለስ፣ አንተስ ወዳጄ አፍነህ፣ ችለህ የያዝከው ብሶት የለህም?... እነ ኦፕራ እንዳደረጉት? … ጊ”ዜው አሁን ነው!!” የምትልበት?
እኔ ሞልቶኛል!!
ሠላም!!

Read 4177 times