Saturday, 20 January 2018 11:40

የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ይከበራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ (ከጎንደር)
Rate this item
(1 Vote)

· ለዝግጅቱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰሩ ጥናቶች ተመርጠዋል
           · ቴዲ አፍሮ በፕሮግራሙ ላይ እንዲያቀነቅን ይጋበዛል ተብሏል
           · በስማቸው ፋውንዴሽን ወይም ቋሚ ሙዚየም ለመገንባት ታቅዷል
                 
    የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በተባባሪ አካላት ትብብር በተለያዩ ዝግጅቶች ከሚያዝያ 2 - 6 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚከበር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከትላንት በስቲያ ጎንደር በሚገኘው ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም፣ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳውና ሌሎችም የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አፄ ቴዎድሮስ በዘመናቸው ዘመናዊ አስተዳደርን በመመስረት፣ ዝቅተኛውን የማህበረሰብ ክፍል በማገዝ፣ በወቅቱ የነበረውን የባሪያ ንግድ በይፋ በመቃወም፣ በአፍሪካ የመጀመሪያውን  የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ በማቋቋም ያደረጉትን አስተዋፅዖ አውስቶ፤ በንጉሡ ስኬት ድክመት ላይ የተመሰረቱ በርካታ ጥናታዊ ፅሑፎች ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች ተቋማት ቀርበው ለመታሰቢያ በዓሉ የሚሆኑት መመረጣቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ተናግረዋል፡፡
አፄ ቴዎድሮስ የኖሩበት፣ ንግሥና ተቀብለው የተቀቡበት፣ ቴክኖሎጂ የቆረቆሩበት፣ ጦርነት ያካሄዱበትና ከንጉሡ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቦታዎች (እንደ ደረስጌ ማርያም፣ ቋራ፣ መቅደላ፣ ዳፋትና ሌሎችም) ለበዓሉ በተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ላይ ተካትተዋል ተብሏል፡፡  በመታሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ  የፓናል ውይይት የሚካሄድ ሲሆን በመቅደላ ጦርነት ወቅት ተሰርቀው የተወሰዱና በእንግሊዝ የሚገኙ ቅርሶችን የማስመለስ ስራ ላይ፣ በዓሉን አክብሮ ከማለፍ በዘለለ በስማቸው ቋሚ ሙዚየም ወይም ፋውንዴሽን ይቋቋም በሚለው ዙሪያና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት እንደሚካሄድም ዶ/ር ደሳለኝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡  በዚህ የመታሰቢያ ፕሮግራም ላይ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ አርቲስቶች፣ ትልልቅ የትምህርት ተቋማት፣ ታዋቂ ሰዎችና ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ቲያትር፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ አፄ ቴዎድሮስን የሚዘክሩ መጽሐፍቶችና ለዲፕሎማሲያዊ ሥራ ይለዋወጡዋቸው የነበሩ ደብዳቤዎች በአውደርዕይ መልክ እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡
የአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ በዋናነት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሀሳብ አመንጪነት ቢዘጋጅም የክልሉን 7 ዩኒቨርሲቲዎች ጨምሮ በርካታ ተቋማት የሚሳተፉበት ሲሆን በጎንደር፣ በደብረ ታቦርና በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲዎች የመታሰቢያው አካል የሆኑ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ዶ/ር ደሳለኝ አክለው ገልፀዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም በበኩላቸው፤ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጀመረው ፕሮግራም ለመልካም ስራ የሚያነሳሳና የሚቆሰቁስ መሆኑን ገልፀው “ያለፉ ጀግኖችን መዘከርና እውቅና መስጠት አሁን ላለንበት ኩራትና ወደፊት ለምናልመው ራዕይ መሰረት ነው” ያሉ ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤታቸው ዝግጅቱን በየትኛውም መልኩ ለመደገፍ ከዩኒቨርሲቲው ጎን እንደሚቆም ቃል ገብተዋል፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳው  ባደረጉት ንግግርም፤ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር የተያያዙ ታሪክ ያላቸው ቦታዎች፣ የቱሪስት መዳረሻና የሀብት ማመንጫ እንዲሆኑ ክልሉ በተቻለው መጠን መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያ” በሚለው አልበሙ አፄ ቴዎድሮስንና ጎንደርን ያወደሰው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በፕሮግራሙ ላይ እንዲያቀነቅን እንደሚጋበዝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3717 times