Saturday, 21 April 2012 16:50

ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

ከቅርብ አመታት ወዲህ በአገሪቱ እየተበራከቱ ከመጡ የንግድ ዘዴዎች መካከል የአክስዮን ማህበራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአክስዮን ማህበራት እየተደራጁ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች እንቅስቃሴ በማድረግ የተሻሉ ሥራዎችን እየሰሩ የአክስዮኑን አባላት፣ አገራቸውንና ዜጐቻቸውን እየጠቀሙ ያሉና ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገቡ ማህበራት እንዳሉ ሁሉ የአክስዮን ሽያጫቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዱካቸውን ያጠፉ፣ ከሥራቸው ይልቅ ማስታወቂያቸውና ወሬአቸው የቀደመ፣ ሊታዩና ሊጠኑ የሚገባቸው ማህበራትም እየተበራከቱ ነው፡፡ ሰሞኑን ለመጐብኘት እድሉ ከገጠመኝ አንድ አክስዮን ማህበር የታዘብኩትም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡

ጃካራንዳ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ በሚል ስያሜ ይታወቃል አክስዮኑ፡፡ በግብርናና የኢንዱስትሪ ግብአቶች ላይ የሚሰራው ይኸው ድርጅት ከተቋቋመ 3 አመታትን አስቆጥሯል፡፡ በከብት ማድለብ፣ በአሣ እርባታ፣ በንብ ማነብና አትክልትና ፍራፍሬዎችን ማምረትና ወደ ውጪ አገር መላክ ሥራ ላይ እንደተሰማራ የሚናገረው ይኸው ድርጅት ከ2000 በላይ አባላት አሉት፡፡ ማህበሩ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ቴፒ ወረዳ ውስጥ ከመንግስት የተረከበውንና በትራክተር አሳርሶ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያመረተ ወደ ውጪ አገር የሚልክበትን የእርሻ ማሣ እንድንጐበኝ ጥሪ ከተደረገላቸው ስድስት የቲቪ፣ የሬዲዮና የህትመት ጋዜጠኞች አንዷ ሆኜ ባለፈው ማክሰኞ ወደሥፍራው ተጓዝኩ፡፡

ጉዞአችን የተጀመረው ማለዳ ላይ ቢሆንም 16 ሰዎችን የጫነችውና በኪራይ የተገኘች ሚኒባስ መኪና ረፍት የለሹንና አድካሚውን ጉዞ አጠናቃ ከታለመላት ሥፍራ የደረሰችው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ ነው፡፡ ረሃብና ውሃ ጥሙ ያሰቃየው ጋዜጠኛ ከእርሻው ማሣ ደርሶ የተዘናፈለውን የአትክልትና ፍራፍሬ እስከ ሚያይና ከበሰለው ፍሬ እስከሚቀምስ ቸኩሏል፡፡

በትራክተር የታረሰ የተንጣለለ ሜዳ ላይ ስንደርስ ሥፍራው መድረሳችን ተነገረንና ወረድን፡፡ ሁሉም ጋዜጠኛ ግራ መጋባቱ ከፊቱ ላይ ይነበባል፡፡ ጭው ያለውና የተንጣለለው የእርሻ ማሣ ዘር ናፍቆታል፡፡ በትራክተር እየተገመሰ ታርሶ የዘር የለህ በሚለው እርሻ ላይ ተጉዘን የችግኝ ማፍያና ማባዣ ቦታ ነው ወደተባለው ሥፍራ ደረስን፡፡ከሃያ በላይ ዝርያ ያላቸው የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ዓይነቶች በዚህ ሥፍራ እየተፈሉ ወደሌላ ቦታ እንደሚዛወሩ ቢነገረንም በሥፍራው ያየናቸው የቲማቲም፣ የሰላጣ፣ የቃሪያ፣ የቆስጣ፣ የጐመንና የፎሶሊያ ችግኞችን ብቻ ነው፡፡ በመደብ በመደብ እየተከፈሉ እንዲፈሉ የተደረጉት ችግኞች በማህበር በተደራጀ መልኩ የተሰሩ ናቸው ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና አዲስ አበባ ከተማ እንዲህ ግቢ አልባ ከመሆኗ በፊት በግለሰብ ቤቶች ጓሮ የሚተከሉት የጓሮ አትክልቶች በብዛትም በዓይነትም የተሻሉ ነበሩ፡፡ በአረምና ኩትኳቶ ሥራ ላይ ተሠማርተዋል ተብለው በዕለቱ በሥፍራው ከነበሩ ሴት ሠራተኞች መካከል አንዷን ክንድናና ግር መርጠው ሰጡን፡፡ በዚህ መንገድ ከሚመረጡ ሰዎች ጥሩ መረጃ ማግኘት እንደማይቻል በልምድ የምናውቀው ጉዳይ ነውና እሷን ከሌሎች ትተን የራሳችንን ምርጫ አደረግን በድርጅቱ መሥራት ከጀመረች 12 ቀናት እንደሆናት፣ በቀን የሚከፈላት 20 ብር መሆኑን፣ መኖሪያዋ ከእርሻ ሥፍራው እጅግ የራቀ እንደሆነ ከነገረችን ወጣት ጋር ጥቂት ቆይታ አደረግን፡፡

ከተመደቡልን ሰዎች ውጪ ማነጋገራችን እምብዛም ያልተመቻቸው የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ጉብኝቱ እንዲቀጥል ጠየቁ፡፡ የሚጐበኘው ነገር ግራ የገባው ጋዜጠኛ ሥራ አስኪያጁን ነገር ግራ የገባው ጋዜጠኛ ሥራ አስኪያጁን ተከትሎ ጉዞ ጀመረ፡፡ ቢሄዱት ቢሄዱት የማያልቀው የታረሰ መሬት ያታክታል፡፡ አንድ ቦታ ቆም ብለን ሥራ አስኪያጁ ኢንተርቪው እንዲሰጡን ጠየቅናቸው ይህ ጥያቄያችን ሁለት አላማዎችን ያነገበ ነበር፡፡ አንድም ተሠራ ስለሚሉትና በዓይናችን ልናየው ስላልቻልነው ነገር የሚነግሩን ካለ እንዲነግሩን ሲሆን ሌላው ከያዘን ድካም ጥቂት አረፍ ለማለት እንድንችል ነበር፡፡

አክስዮን ማህበሩ 2000 አባላት እንዳሉት በከብት ማድለብ ሥራው ለዘጠኝ ዙሮች ወደተለያዩ አገራት የቁም ከብቶችን መላካቸውን፣ በዚህ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትም ከ3 ወራት በኋላ መላክ እንደሚጀምሩ ገለፁልን፡፡ እንዴ ምኑ ነው የሚላከው? ሁላችንም ጠየቅን፡፡ ችግሮቹ ከሶስት ወራት በኋላ ምርት እንደሚሰጡና ይህም ወደውጪ እንደሚላክ አስረግጠው ነገሩን፡፡ አነጋገራቸው ዝም ብላችሁ የተነገራችሁን ፃፉ የምን ጥያቄ ነው ይመስላል፡፡ ለእርሻ መሬቱ አዋሣኝ ከሆነውና በሕንድ ባለሃብቶች ከተያዘው ቦታ ጋር አለመግባባት መኖሩን፣ ከቦታው ላይ ከተነሱት አርሶ አደሮች ጋር ውዝግብ እንደነበረና ይህ ከምን እንደደረሰ ከጋዜጠኞሀት የቀረበላቸውን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑት አቶ ደመላሽ ጉብኝቱን መቀጠሉ እንደሚሻል ነገሩንና የተቋረጠው ጉዞ ተጀመረ፡፡ የተንጣለለ የእርሻ መሬት ማየት የታከተው ጋዜጠኛ ማጉረምረም ጀምሯል፡፡ እንዴ እኛ የመጣነው ወሰን ልንለካ ነው እንዴ? ሁሉም ያጉረመርማል፡፡ ቀስ በቀስ ትዕግስቱ እየተሟጠጠ የመጣው ጋዜጠኛ መሀል የእርሻ ማሳው ላይ ተሰብስቦ ከአንድ ውሣኔ ላይ ደረሰ፡፡ ወደ ኋላ መመለስ፡፡ ይህ ውሣኔ ሥራ አስኪያጁን አላስደሰታቸውም፡፡ ጉብኝቱን እንድንቀጥል ማግባባቱን ተያያዙት፡፡ አልተሣካላቸውም፡፡ ልመናና ማግባባቱ ብቻ በቂ አለመሆኑ የገባቸው ሥራ አስኪያጁ የቲቪ ኦሮሚያ ጋዜጠኞችን ይዘው መጐተት ጀመሩ፡፡ ና ሂድ አልሄድም፡፡ ምንም የሚታይና በካሜራ የሚቀረፅ ነገር በሌለበት ሁኔታ ከዚህ በላይ ለመሄድ አንፈልግም፡፡ ለደቂቃዎች ሙግቱ ቀጠለ፡፡ የቲቪ ካሜራ ማኑ ፊቱን መልሶ ወደመጣበት ጉዞ ሲጀምር ተስፋ ቆረጡ፡፡ መኪናዋ ወደቆመችበት ከ2 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘን ብንደርስም በውሣኔያችን የተከፉት አቶ ደመላሽ ከቆሙበት አልተነቃነቁም፡፡ በአቅራቢያው ካለ ወራጅ ወንዝ በውሃ ፓምፕ እየተሣበ ወጥቶ የፈሉትን ችግኞችና ጥቂት ፈንጠርጠር ብለው የተተከሉትን የቃሪያ፣ የቲማቲምና የጐመን ተክሎችን የሚያጠጣ የመስኖ ውሃ አለ፡፡ ከአንድ ብርቱ የከተማም ሆነ የገጠር ነዋሪ የጓሮ አትክልት ያልተሻለውንና የሚያኰራ ሥራ ያልተሠራበትን ሥራ ያልተሠራበትን ይህን የእርሻ ሥፍራ እንድንጐበኝ መጠራታችን ለሁላችንም ግራ ሆኖብናል፡፡ ከ3 ወራት በኋላ መላክ ይጀምራል የተባለው አትክልትና ፍራፍሬ ከየት እየመጣ እንደሚላክ የሁሉም ጥያቄ ነበር ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችን እንደያዝን ለሰዓታት አቶ ደመላሽን መኪናው ሥር ተቀምጠን መጠበቅ ግዴታችን ሆነ፡፡ እስቲ መኪናውን ነድታችሁ ትሄዱ እንደሆነ አያለሁ ያሉት የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ንዴታቸውን የሚወጡበት አጋጣሚ በማግኘታቸው ደስ ያላቸው ይመስላል፡፡ ከ290 ኪሎ ሜትር በላይ ከፊታችን እንደሚጠብቀን በማወቃችን ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ ሥጋታችንም በዛው መጠን ጨመረ፡፡ ከብዙ እልህ አስጨራሽ ጥበቃ በኋላ መጡና የመልሶ ጉዞአችን ተጀመረ፡፡ 45 ኪሎ ሜትር ፒስታ መንገዱን ጨርሰን ጌዶ ስንደርስ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አልፏል፡፡ በመንገዱ ላይ የነበሩትን ጉዳዮች መዘርዘሩ አንባቢውን ላይ የነበሩትን ጉዳዮች መዘርዘሩ አንባቢን ከማሰልቸት ውጪ የሚፈይደው ነገር ባለመኖሩ ባልፈውም ድካም ረሃብና ውሃ ጥም፣ እንዲሁም እንቅልፍ ያደከመው ጋዜጠኛ ድካሙን ለመርሣት ሲያሰማ የነበረውን ህብረ ዝማሬ የድርጅቱ ሠራተኛ የሆነ ወጣት ኃይለ ቃል በተሞላበት ሁኔታ ማስቆሙን ሣይገልፁ ማለፉ ተገቢ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አዲስ አበባ በመድረስ የተጠናቀቀው ጉዞ ያስገኘውን ውጤት ረጋ ብዬ ለማሰብ ሞከርኩ፡፡ ምንም አጣሁበት፡፡ ማስታወቂያቸው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ በስፋት የሚነገርላቸው የአክስዮን ማህበራት ውስጣቸው በእጅጉ አሣሰበኝ፡፡ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ እንዲሉ፡፡

 

 

Read 2931 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:53