Print this page
Saturday, 20 January 2018 11:56

አቶ ልደቱ አያሌው በፓርቲያቸው ጉዳይ ፓርላማው ጣልቃ እንዲገባ ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ምርጫ ቦርድ ከ4 የቀድሞ አመራሮች ጋር “መርህ አልባ” ግንኙነት ፈጥሯል ብለዋል

    በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የለውም የተባለው የእነ ልደቱ አያሌው የኢዴፓ አመራር ቡድን፣ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ ፓርላማው ጣልቃ እንዲገባ ጠየቀ፡፡
አመራሩ እንዴት ወደ ፓርቲ ስልጣን እንደመጣ የፓርቲውን ህገ ደንቦች አጣቅሶና ከምርጫ ቦርድ ጋር የተካሄደውን የደብዳቤ ልውውጥ በዝርዝር አስፍሮ፣ ለፓርላማው ጽ/ቤት በላከው የአቤቱታ ደብዳቤ፤ ምርጫ ቦርድ ከዶ/ር ጫኔ ከበደ አመራር ጋር “መርህ አልባ ግንኙነት ፈጥሯል” ሲል ቡድኑ አማሯል፡፡
ታዋቂውን ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት፣ በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል የተባሉት አቶ አዳነ ታደሰ የተካተቱበትን የ18 ሰዎች ስም ዝርዝር የያዘው ደብዳቤ ላይ እንደተመለከተው፤ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ህገ ደንብ አንብቦ ለመረዳት ምንም አይነት ሙከራ ሳያደርግ፣ ከእነ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ጋር በፈጠረው “መርህ አልባ” ግንኙነት የተነሳ፣ ከእንግዲህ ምንም አይነት ደብዳቤ ከእናንተ አልቀበልም ብሎናል ይላል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለፓርቲያችን ብሄራዊ ም/ቤት፣ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ለኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ፣ ለፕሬዚዳንቱና ለዋና ጸሐፊው በጭፍን እውቅና በመንፈግ፣ በህግ ከተቋቋመለት ዓላማ በተቃራኒ፣ ፓርቲ የማፍረስ ተልዕኮ እየተወጣ መሆኑን በአቤቱታ ደብዳቤያቸው የጠቀሱት እነ አቶ ልደቱ፤ “የብዙ ሺዎች ፓርቲ የሆነው ኢዴፓን ወደ ግለሰብ/ሳምሶናይት/ ፓርቲነት እየቀየረው ይገኛል” ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ምርጫ ቦርድ ለዶ/ር ጫኔ ከበደ የእውቅና ደብዳቤ በመስጠቱም ማህተምና ቢሮ አስረክቡን የሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው እነ አቶ ልደቱ ጠቁመው፣ ምርጫ ቦርድ ከ4 የፓርቲው የቀድሞ አመራሮች ጋር “መርህ አልባ ግንኙነት” በመፍጠር ፓርቲያችንን እያፈረሰብን ነው ብለዋል፡፡
የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ይህ ድርጊት በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ሂደት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመገንዘብም፣ በሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ በማጣራት፣ መፍትሄ እንዲሰጣቸው  እነ አቶ ልደቱ ጠይቀዋል፡፡   

Read 5784 times