Saturday, 20 January 2018 12:02

የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ዕጣ ፈንታ ቤተ ክርስቲያኒቱን አሳስቧል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 · ታሪካዊነቱን ለማጣት ተቃርቧል፤” ተብሏል
              · “የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የመጨረሻ ዝግጅት ተጠናቋል”

    የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ አስፈላጊ መረጃዎችን በሙሉ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ማስረከቧን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገለፀች ሲሆን፤ በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባ በዓሉ በዋናነት የሚከበርበት የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ዕጣ ፈንታ እንደሚያሳስባት  አስታውቃለች፡፡
የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ባለፈው ዓመት እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስታወሱት የቤተ ክርስቲያኒቱ የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዘክር ዋና ሓላፊ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፤ የጥምቀት በዓል አከባበር ታሪካዊ አመጣጥን፣ በየዘመናቱ ያሳለፈውን ሂደትና ለሃገር ያበረከተውን አስተዋፅኦ ያካተተ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተፃፈ ሙሉ ሰነድ ቤተ ክርስቲያኒቱ አዘጋጅታ ሰሞኑን ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ማስረከቧን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የበዓሉን አከባበር ገፅታ የሚያሳዩ የምስል ወድምፅ ትዕይንትም ከአክሱም፣ ከጎንደር፣ ከላሊበላና ከጃንሜዳ ተሰብስበው ለሚመለከተው አካል መቅረባቸውን የጠቆሙት ቀሲስ ሰሎሞን፤ በተጨማሪም ከተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች የተሰባሰበ የ300 ሰዎች ፊርማ መቅረቡንም አውስተዋል፡፡ ሰነዶቹን፣ በመጪው መጋቢት ወር ዩኔስኮ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ጉዳዩ የሚመለከተው የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዋና ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ከተመዘገ ዓለምአቀፍ ጥበቃ ይኖረዋል፤የቱሪስት ፍሰቱም ስለሚጨምር  ለሃገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል፤ ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል፣ የጥምቀት በዓል የሚከበርባቸው ታሪካዊ ቦታዎችንም እኩል ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ የጠቆሙት ቀሲስ ሰሎሞን፤ አንዳንድ አህጉረ ስብከት ቦታውን ባለበት ለማቆየት፣ በይዞታው ላይ ቤተ ክርስቲያን መገንባት መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ በአገር አቀፍ  ደረጃ በዓሉ በዋናነት የሚከበርበት የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ጉዳይ ግን አሳሳቢ መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡
“ጃንሜዳ ታሪካዊነቱን በሚያሳዝን መልኩ እያጣ ነው፤” ያሉት ቀሲስ ሰሎሞን፤ “ከንጉሰ ነገስቱ ዘመን ጀምሮ የከተራ እና የጥምቀት በዓል አከባበርን ጨምሮ በየመንግሥታቱ በርካታ ታሪካዊ ክንውኖችን ማሳለፉን አስታውሰው፣ቦታው በራሱ በቅርስነት ሊያዝ ሲገባው፣ተቆነጣጥሮ ሜዳነቱን አጥቷል፤” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጃንሜዳ በኮንስትራክሽኖች ሳቢያ እየጠበበ መምጣቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እጅግ እንደሚያሳስባት የጠቆሙት ሓላፊው፤ ቅዱስ ሲኖዶስም ከሁኔታው አሳሳቢነት የተነሳ  የጃንሜዳን ጉዳይ በቋሚነት የሚከታተል ኮሚቴ አቋቁሟል፤ ብለዋል፡፡     “ጃንሜዳ የአዲስ አበባ ብሎም የሀገሪቱ ታሪካዊ ቅርስ ነው፤” ያሉት ቀሲስ ሰሎሞን፤ በግንባታዎች ሳቢያ እየተሸራረፈ ማነሱ በበዓል አከባበሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ መሆኑን በመጠቆም፣ መንግስት በጉዳዩ ላይ በፅኑ ሊያስብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Read 8334 times