Print this page
Saturday, 20 January 2018 12:07

የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፤ የዱር አራዊት ስለ እድራቸው ለመወያየት እንደተሰበሰቡ፤ የአንበሳ ድምፅ ከወደ ጫካው ይሰማል፡፡ ስብሰባቸውን አቋርጠው፤
“ኧረ ንጉሥ አንበሳ ይጮሃል፡፡ ምን ሆኖ ይሆን?” አለ አንደኛው፡፡
“ሲያገሣ ይሆናል ባንጨነቅ ይሻላል” አለ ሌላው፡፡
“ኧረ ግዴላችሁም፤ ጩኸቱን እየሰማችሁ ለምን ዝም አላችሁ፤ ብሎ ይጨርሰናል፡፡ ኧረ እንሂድና ምን ሆነሃል እንበለው” አለ ሶስተኛው፡፡
ጥቂት እንደተከራከሩ፣ ጦጢት፤
“አንሂድ፡፡ ለምን እንደጮኸ ሳናውቅ ምን አስኬደን?” አለች፡፡
“ምንም ይሁን ምን፤ ንጉሣችን ነው፡፡ ንጉሥን መፍራት ያስፈልጋል” አለ፤ አንድ ትጉ አውሬ፡፡ እንሂድና እንየው የሚለው ሀሳብ አሸናፊ ሆነና ሁሉም ወደ አያ አንበሶ ሄዱ፡፡
አያ አንበሶ ታሞ የመጨረሻው ሰዓት ላይ ደርሶ ኖሯል የሚጮኸው፡፡ አውሬዎቹ ሌላ ውይይት ጀመሩ፡-
“ማነው አያ አንበሶን ተክቶ የሚወርሰው?” አለ አንደኛው
“ነብር” አለ ሁለተኛው
“ነብር በጣም ይሞነጭራል”
“ዝሆን!”
“ዝሆን ቀርፋፋ ነው አይመራንም”
“ጎሽ”
“ጎሽ አይሆንም፡፡ ለልጁ ሲል ማንንም ይወጋል- በማንም ይወጋል”
“ታዲያ ማን ወራሽ መሪ ይሁን?”
ጦጢት ጣልቃ ገብታ፤
“እስቲ አያ አንበሶ መጀመሪያ በወጉ ይሙት? እስቲ ጥቂት ጊዜ እንጠብቅ”
“አንቺ ደግሞ ጊዜ ጊዜ ጊዜ ትያለሽ፡፡ ከሞተ በኋላ ከምንጨቃጨቅ አሁኑኑ ብናስብበት አይሻልም” አለ ነብሮ፡፡
“እኔ‘ኮ ከትላንት ወዲያ ነው ስለ ወንበሩ እንነጋገር ያልኩት፡፡ ያኔ እሺ ብላችሁኝ ቢሆን ይሄ ሁሉ መደናበር ባልኖረም ነበር- አሁንም የአያ አንበሳን የመጨረሻውን ቃል እንስማ!”
አያ አንበሶ እያቃሰተ የመጨረሻውን ኑዛዜውን ተነፈሰ፡-
“ዙፋኔን የሚወርሰው ልጄ ደቦል ነው!” አለ፡፡
“በቃ ተገላገልን፡፡ ወራሽ ገዢያችንን አወቅን!” አለ አንዱ፡፡
“አልጋ ወራሽ መኖሩ ታላቅ ዜና ነው”
ይሄኔ ጦጢት፤
“ደቦል የታለ?”
“አያ አንበሶ ልጅ ሳይኖረው ወራሼ አይልም፡፡ አንቺ ደግሞ ጭቅጭቅ ትወጃለሽ፡፡”
“ምናለበት ይምጣና እንየው፡፡ መሪያችን ከሆነ በሜዳ ስሙ ሳይሆን ይምጣና ራሱን ያስተዋውቀን!”
“ሰባት ዓመት አፅሙ የገዛን ንጉሥ በነበረበት ዓለም ደቦል ታየ አልታየ ምን ያነታርከና?”
“ዕውነቱን ነው! ዕውነቱን ነው! ዕውነቱን ነው!” ሁሉም ጮኹ፡፡
በማህል አያ አንበሶ፤
“አቅም እየተሰማኝ፣ ነፍስ እየዘራሁ ነኝ! እንኳን ደስ አላችሁ!”
ሁሉም በየሆዱ፤
“ይሄም አለ እንዴ?!”
ጦጢት ብቻ ሳቋን ለቀቀችው!
*    *    *
የጊዜ ግምት የሁልጊዜ ችግራችን ነው፡፡ አለማሰብ የሁልጊዜ ችግራችን ነው፡፡ የተንገዳገደውን ወደቀ ማለት የሁልጊዜ ችግራችን ነው፡፡ በስሜት መነዳት እጅግ የጠና ችግራችን ነው፡፡ በራስ መተማመን ትተን በሌሎች ድክመት፣ መሰነጣጠቅና ገባ - ወጣ ላይ ተንተርሰን ዕጣችንን መወሰን ኋላ አባዜው ብዙ ነው! ምክንያቱም ዕድሜ ልካችንን በሰው እጅ የመጎሳቀልን ዕድል ለሌሎች አሳልፈን ሰጥተናል! የሚገርመው ቀጣይ ገዢ ፍለጋ በየማዕዱ መጨቃጨቃችን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ብለነዋል፤ ሰሚ ከጠፋ ዛሬም እንደግመዋለን፡-
“… አሁን የት ይገኛል፣ ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ፣ የባሰ ደንቆሮ!”
አሁንም የህዝቡን የልብ - ትርታ እናዳምጥ!
“በጠበቧ ቢሮዋችን ተቀምጠን የሰፊውን ህዝብ የልብ ትርታ እናዳምጣለን” ያለው ደርግ፤ “ካላዳመጥከን ወዮልህ!” ወደ ሚል ቅኝት መለወጡን ከእነ ሙሉ ቃሉና ደሙ እናስታውሰዋለን!
“እንደሙሴ ታቦት፣ ዘውዱን ካናታችሁ
አሁንም ጭናችሁ፤
እናንተ ገዢዎች
እናንተ ደርጋሞች
ምነዋ አፌዛችሁ
ምነዋ ቀልዳችሁ!”
እስከማለት ተናግረን ነበር!
የኃይለ ሥላሴም መንግስት ቢሆን ከተረቶች ሁሉ የሚያደንቀው፤ “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ”ን ነበር! 3ኛ ክፍለ ጦር አመፀ - ምላሹ ዝም! የአርሲ፣ የባሌ፣ የጎጃም አርሶ አደር አመፀ - ጭጭ ማለት ወይም ጭጭ ማድረግ! ተማሪው ተነሳ - ተዉት የትም አይደርስም!
በመጨረሻ “ወሎ ተራበ፣ ተሰደደ‘ኮ” ሲባሉ “ወሎ መሰደድ ልማዱ ነው - ተዉት” አሉ አሉ፡፡
የወሎው ባለስልጣን ለገሠ በዙ!
ይሄ ሁሉ ማትጊያ ደወል (Death-bed) የንጉሡን መንግስት መንበሩን አልነቀነቀውም! የአንድ ቀን ቤንዚን ዋጋ መቀጠል (የዛሬውን አስባችሁ “እግዚኦ!” እንዳትሉ አደራ!) አየር እየበዛበት የተነፋፋውን የፖለቲካ ባሉን (ፊኛ) ጠቅ ሲያደርገው አብዮት ፈነዳ (Tipping point እንዲሉ) ያቺ ጠቅታ የብሶት፣ የምሬት፣ ክፉ ጥርቅም ውጤት ናት! በደርግ ጊዜ የዚሁ ብልልት ውጤት ነው የታየው! ዛሬም ያው ነው - ግን anachronistically (ጊዜና ቦታውን ያልጠበቀ ድምዳሜ) ሳናስበው፤ መከራን እንደማወዳደር ሳይሆን እንደጊዜው ባኮ (current package) እናስበው!
“ያለው መንግስት ይውደቅ” ስንል የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር እንዳሉት፤ ሟርት ባይሆንስ? የተቃዋሚ “አማራጭ አልባ” ትግል ባይሆንስ? የህዝብ መንፈስ ቢሆንስ? እና ቢሳካለ ማንን እንተካለን? መልሱን ከማንም አንጠብቅ - ከራሳችን እንጂ! ሮበርት ብራውን፤
“ደሞም ማወቅ ማለት …
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ!”
(ትርጉም ገ/ክርስቶስ ደስታ)
የሀገራችን ግራ መጋባት የሚጀምረው “የአብዬን እከክ ወደእምዬ ልክክ” ስንል ነው፡፡ ለማንም ላይጠቅም ሀገርና ህዝብን የመበደል ጥፋት ነው! ካለፈ በኋላ የሚቆጭ፤ ሳንማማር የመጨረሻችንን ጥርጊያ ጎዳና የሚያመቻች፣ ጥሬዎቹን የማያበስል፣ የበሰሉትን የሚያራግፍ የቤት ጣጣ! ሀገራችን ራዕይ የቅዠት ኑዛዜ የሆነባት የዕርግማን ቋት ናት! የሚበጇትን እየገፋች የሚንቋትን እያቀፈች፤ በራሷ ዛቢያ ላይ የምትሽከረከር ናት! ገና ረዥም መንገድ አለባት! የሚገርመው ሳይደራጁ እግርና እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ለማን ይበጃል፡፡ ለመደራጀት የጋራ አመለካከት እንጂ አንድ ዓይነት መፍትሄ አይጠበቅብንም!   
ነገር ሁሉ እንደፈለግነው ቢሆን እንኳ እንዴት እንመራዋለን እንበል፡፡ የሌሎችን መውደቅ ስንመኝ፤ የእኛ መነሳትም ገና ዝግጅት እንደሚፈልግ፣ የአለመደራጀት ጣጣ መልሶ ለተደራጀ ወገን አሳልፎ እንደሚሰጠን አንርሳ! የ1966 ዓ.ም አብዮት ያንን ካላስተማረን፣ ያ ሁሉ የተከፈለው ደም ምንም ፍሬ አልነበረውም ማለት ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ያሉትን አንዘንጋ፡-
“ያልተደራጀ ኃይል፤ ኃይል አይደለም!”
ለማንኛውም ቆም ብሎ ማሰብ፣ ረጋ ብሎ መወያየት፣ ካበደ ጋር አለማበድ ወደ መፍትሔ ያመራን ይሆናል፡፡ “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል!”

Read 5113 times
Administrator

Latest from Administrator