Saturday, 20 January 2018 12:21

“አንተ ትብስ፣ አንቺ”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሀሳ!
ሰውየው ከአንድ ጓደኛው ጋር እያወራ ነው፡፡
“ስማ፣ አንድ ውለታ እንደትውልልኝ ፈልጌ ነው።”
“ምንም ችግር የለውም፡፡ ምን ላድርግልህ?”
“እባክህ ገንዘቤን አንተ ዘንድ አስቀምጥልኝ፡፡”
“ምን! ለምንድነው ገንዘብህን የማስቀምጥልህ?”
“ትዳር እንደያዝኩ ታውቅ የለ!”
“እኮ! ታዲያ ትዳር ይዘህ ሚስትህ እያለች የአንተን ገንዘብ እኔ ዘንድ የምታስቀመጠው ለምንድነው?”
“ስማ፣ በደንብ የማላውቃት ሴት ቤቴ አስገብቼ ሰላም እንቅልፍ የምተኛ መሰለህ!” አለውና አረፈው።
ሰማችሁት አይደል…በደንብ የማላውቃት ሴት! እናማ… ዘንድሮ ያው እንግዲህ በወሬም፣ በምንም የሰማንያ መፈራረሙን ያህል የሰማንያ መቅደዱም በዝቷል ሲባል እንሰማለን፡፡
ሴትዮዋ ውሻዋን ትእዛዝ እንዲቀበል እያስተማረችው ነው፡፡ በተደጋጋሚ ስትሞክርም አቃታት፡፡ ይሄኔ ባሏ…
“ውዴ፣ ብትረሽው ይሻላል፣ አይሳካልሽም…” ይላታል፡፡ ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“ማሬ፣ አንተም መጀመሪያ ላይ እንዲሁ ነበር ያስቸገርከኝ” አለችውና አረፈችው፡፡ ምንን ከምን እንዳመሳሰለች ልብ በሉልኝማ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ የሰርግ ሰሞንም አይደል…ሁሉንም ጥምረቶች የእድሜ ልክ ያድርጋቸውማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምኞት አንድ ነገር ነው፣ መሬት ላይ ያለው እውነት ደግሞ ሌላ ነው፡፡ “በደንብ የማላውቃት ሴት ቤቴ አስገብቼ” እንዳለው ሰውዬ አይነት የሚያስቡ አይኖሩም አይባልም፡፡ የምር ግን ብዙዎች በሚገባ በጥልቅ ሳይተዋወቁ በተለያዩ ምክንያቶች ቶሎ “ሁለቱም ተለዩ ከእናት ከአባታቸው…” በተባለላቸው መንፈቅ ሳይሞላ እነሱ ተለያይተው ያርፉታል፡፡ (በዛ ሰሞን በሰርጋቸው ማግስት ስለተለያዩ ጥንዶች ስንሰማ ነበር፡፡)
እናላችሁ…በደንብ አለመተዋወቅን የመሰለ ክፉ ነገር የለም፡፡  
“እኔ አኮ ሌሊት እንዲህ እንደሚያንኮራፋ አላውቅም ነበር!”
“አሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል የጀመረች የምታቆመው ሁለት ሰዓት ላይ እኮ ነው!…” አይነት ንጭንጮች የሚበዙት እንደ ‘ፋስት ፉድ’ ትዳሩንም ‘ፋስት’ እያደረጉት ነው ይባላል፡፡
የባህሪይ ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ!
“ምን መሰለሽ፣ አሁን ከተጋባን አይቀር ለወደፊቱ ችግር እንዳይገጥመን ያሉብሽን አንዳንድ የባህሪይ ችግሮች ልንገርሽ” ይላል እሱዬው፡፡
“ተወው አትንገረኝ፡፡”
“ምን መሰለሽ…”
“እባክህ አትልፋ፣ ውዴ፡፡ እነኛ የባህሪይ ጉድለቶች ናቸው ከአንተ የተሻለ ወንድ እንዳላገባ ያደረጉኝ” አለችውና አረፈች አሉ፡፡
እግረ መንገዴን… “ጥር የልጃገረድ ጠር…” ምናምን የሚባለው ተረት ማሻሻያ አልተደረገበትም እንዴ?  አሀ…አሁን ሦስት መቶ ስድሳ አምስቱም ቀናት ‘ጠር’ ሆነዋላ! … በነገራችን ላይ እሱ ነገር ‘ግሬስ’ ጠፋ ማለት ነው! ወይስ ነገርዬው ‘ፕሮፋይሉ’ ዝቅ ብሎ ወደ ‘ኮሞዲቲነት’ መውረዱ ነው! በዛ ሰሞን ‘ጥሪ ዋጋው’ ሀምሳ ሺህ ምናምን ሆኗል ሲባል ሰምተን ነበር፡፡
የምር ግን… እሱን የመሰለ ‘የሰርግ ማግስት አድማቂ’ አልነበረም፡፡ ይሄ በማግስቱ “ምናምን ሰበረልዎ ሸጋው ልጅዎ…” የሚባለው ነገር አይደለም በእውን በድራማ ላይ እንኳ መሰማቱ ቀርቷል፡፡ የእሱን ነገር ሰበራ ‘ጀግንነት’ እኮ ልክ የጦር ሜዳ ጀግንነት እናስመስለው ነበር፡፡
እናላችሁ…በደንብ ሳይተዋወቁ በየራሳቸው ምክንያት ይጣመሩና ባህሪይ ቀስ እያለ ሲወጣ ነገርዬው ሁሉ መላው ይጠፋል፡፡  አሀ…በቋሚነት አብሮ መዋልና ማደር እንትን ፔንሲዮን እንትን ገባ ብሎ ወጣ አይደለማ!
የምግብ ምርጫ ራሱ ቀላል አይደለም፡፡ የምር… የበፊቱ ላዛኛ፣ ሰፔሻል ክትፎ ምናምን ማነጫነጭ ከጀመረው የአልጋ ኪራይ ጋር ታሪክ ሆነው ይቀራሉዋ!
“ምን ይምጣልሽ?”
“እኔ እንጃ፣ ምን ይሻለኛል…”
“ፒፐር ስቴክ ይሁንልሽ?”
“አይ፣ ዛሬ ስጋ መብላት አልፈልግም፡፡”
“ኦኬ፣ ለእሷ ስፓጌቲ አል ዴንቴ፡ ለእኔ ደግሞ የዶሮ አሮስቶ…”
አሪፍ ነው፡ ችግሩ ግን አንድ ጊዜ “ባልንጀሬ ሥሪ ጉልቻ…” ከተባለ በኋላ ‘አሮስቶ’ የሚሆነው ጨጓራ ነው፡፡
“ምንድነው ይሄ?
“ምኑ?”
“በሳምንት ውስጥ አራት ቀን ሹሮ!”
“እና አሮስቶ አማረህ! እ! ጌታው፣ ሹሮውንም ስላገኘን ተመስገን በል፡፡”
“ሹሮ ሠርተሽ ሞተሻል! ወጥ የበላሁ ሳይሆን ዱቄት የቃምኩ ነው የመሰለኝ…” ቂ…ቂ…ቂ...
“ካልፈለግህ አትተወውም ነበር!”
“ሹሮማ እማዬ ትሥራ…”
እናማ እንዲህ፣ እንዲህ እየተባለ በሆነ ባልሆነው
ለምሳሌ እሷ ምንም ነገር ላይ በርበሬ ጠቃ ማድረግ ትወዳለች፡፡ እሱ ደግሞ ባቄላ የምታክል ቃሪያ ሲቀምስ “እሪ!” የሚል አይነት ይሆናል፡፡
“ለምንድነው በርበሬውን እንዲህ የምትሞጅሪው!”
“እና ቀይ ወጥ በቀይ ቀለም ልሠራልህ ነው!” ምናምን አይነት ጭቅጭቅ ይፈጠራል፡፡ አለ አይደል… ከዛ በኋላ ሀይለ ቃል በተነጋገሩ ቁጥር “አንቺ ምን ታደርጊ! ድሮም ይሄን በርበሬ እየቃምሽ ለብልቢኝ እንጂ!” ማለት ይጀመርና በርበሬ ኑሮ ላይ ሚጥሚጣ ይጨመርበታል፡፡
“ቀስ ብለህ ተናገር እንጂ፣ ደንቆሮ ነች አሉህ እንዴ?”
“እና ጆሮሽ ስር መጥቼ ልንሾካሾክልሽ!”
“የእድር ጡሩምባም እንዳንተ አይጮህም፡፡”
“አይ፣ እንግዲህ ደሜን አታፍዪው!”
እሱዬው እኮ “ይዟት በረረ…” ከመባሉ በፊት ሲናገር ከመለስለሱ የተነሳ እንደ አኔስቴዥያም ሊያገለግል የሚችል ይመስል ነበር፡፡ በነገራችን ላይ… “አንቺ ሴትዮ ደሜን አታፍይው!” ምናምን የሚባለው ነገር …የአንዳንዱ ‘ባል’ ደም በግንቦት ሙቀትም፣ በነሀሴ ብርድም የሚፈላው፣ በሶላር ቻርጅ እየተደረገ ነው እንዴ!
“አንቺ ሴትዮ ደሜን አታፍይው!”
“ለእኔ ሲል ለምን አይንተከተክም!”
ጥምረቶችን ‘ደም ከሚያፈላ’ ግንኙነት ይጠብቃቸውማ!
በነገራችን ላይ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘ነገርዬውን’ በተመለከተም የምር የጥንዶች ‘ኮንፍረንስ’ ቢጤ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከትዳር በፊት በሳምንትም በምንም መገናኘትና፣ ሀያ አራት ሰዓት አብሮ ውሎ፣ አብሮ ማደር አንድ አይደለማ፡፡
ቢሮ ቁጭ ብዬ ቅር ቀር ሲለኝ ምንድነው ብዬ ሳስብ፣ ለካስ አሰኝቶኝ ነው…አይነት የጠብ መነሻዎችም አሉ…
“እኔ ለራሴ ደክሞኛል… ዛሬ ምንም ነገር አልፈልግም፡፡”
“እኔ ስፈልግስ!”
ከዚህ ሁሉ በሳምንት በምን ያህል ድግምግሞሽ ‘ጨዋታ’ እንደሚካሄድ፣ በአንድ ‘ጨዋታ’ ከእረፍት በፊት፣ ከእረፍት በኋላ የሚባል ነገር ይኖር እንደሆነ…ደግሞ ጨዋታ እኩል ለእኩል ባይሆንም ተጨማሪ ሰዓት ያስፈልግ እንደሆነ… የመለያ ምት ደረጃ የሚደርስው መቼ እንደሆነ…ስምምነት ቢደረግበትም አሪፍ ነው፡፡
እሷዬዋ…
“ከመጋባታችን በፊት እንደ ንግሥት እንከባከብሻለሁ አላልከኝም ነበር?” ስትለው…
“አንቺን እንደ ንግሥት ለመንከባከብ መጀመሪያ እኔ ንጉሥ መሆን አለብኝ” አለ አሉ፡፡
የሰሞኑን ጥምረቶች እሱና እሷ እንደ ንጉሥና እንደ ንግሥት አንዳቸው ሌላኛቸውን የሚንከባከቡበት፣ “አንተ ትብስ፣ አንቺ” የሚባባሉበት ያድርግላቸውማ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2842 times