Saturday, 20 January 2018 12:23

“ሀ ያሉ ጦም አደሩ!” (ወግ)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን! ማግኘት ምንድን ነው? ምስጋና የሚሰጠውስ ለየትኛዉ ዓይነት ማግኘት ነው? መልሱ ምንም ሆነ ምን እኔና ቤቴ ግን ተርፎን ስለምንረጨዉ ንዋይ ሳይሆን፤ ያዘነልን ስለሚወረውርልን፤ የራራ ስለሚያበድረን ወር መፍጃ እናመሰግናለን፡፡
አንዳንዴ ትካዜዬ ሌላ ትካዜን ይወልድና በሣሣዉ ኑሮዬ ላይ ተንጠላጥዬ፣ የወሩ አራት ሳምንታት በሠሩት መስኮት አጨነቁራለሁ። መስቀልያ ሠርቶ በጊዜ አናት ላይ በቆመው ወር ላይ እኔን የመሰለ አንድ የመንግስት ድርጅት ተቀጣሪ፣ በአራት ሚስማሮች ተቸንክሮ ይታየኛል። ሚስማሮቹ የወሩን አራቱን ሳምንታት ይወክላሉ፡፡ ይህን ተቀጣሪ ስለማቀው መልስ፤ በጥያቄ ወጥሬ እይዘዋለሁ፡፡ ያለመሰልቸት የማውቀዉን መልስ ይመልስልኛል፡፡ ገነት እንደገባው ወንበዴ ንጹሕ ልብ አለው፡፡ ደጋግሞ እንደሚናገረው፤ ተቀጣሪው በመማሬና ሥራ በመያዜ አተረፍኩ የሚለው ወር ሲደርስ ማግኘት፣ ወሩ ከደረሰ በኋላ ማጣትና ወሩ እስኪደርስ መበደርን ነው፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ ትካዜዬ ሌላ ትካዜን ወልዶ፣ የወሩ አራት ሳምንታት በሠሩት መስኮት ሳጮልቅ፤ እኔን የሚመስለው ተቀጣሪ በመስቀሉ ላይ እንዳለ፣ እንደ ንፋስ የቀለለ እንጀራ እየቆረሰ፤ ልጅ እያለ ለእንቁጣጣሽ አበባ ይስልበት ከነበረዉ የአስር ሳንቲም ቀለም በቀጠነ ወጥ እያጠቀሰ፤ ባልጠረቃው ሆዱ ዉስጥ እንዲህ ያስባል፡-
‹‹የተማረና ሥራ ያለው ሰውን ከሌላው (ከሌለው) የሚለየው ምንድነው? እውነት የሚኖረዉ የተደላደለ ህይወት ወይስ እንደ መስቀል ከጫንቃው የተሸከመው መከራ? እውነት ይህን ኑሮ፤ ኑሮ ካሉት መቃብር ይደላል፡፡ የተማረና ሥራ ያገኘ ሰው የሚያመሰግነዉ ስለሚኖረዉ መልካም ህይወት ሳይሆን፣ አምኖ የሚያበድረው በማግኘቱ ነዉ፡፡ በዚህ ዘመን ገንዘብ የሚሰጥ አበዳሪ ማግኘት፤ ንስሃ የሚሰጥ አባት ከማግኘት የተሻለ ጥሩ ስሜትን ይፈጥራል፡፡›› እንዲህ እንዲህ እያለ በሚጎርሰው የሣሣ እንጀራ ልክ፤ የሣሣ ቅኔ ይቀኛል፡፡
የቸገረዉ ተኝቶም አያርፍም፡፡ እኔም ተምሬ ሥራ ከያዝኩ ጀምሮ አርፌ አላውቅም፡፡ ከቸገረው መሀል የደላዉ በቁሙ እከክ ወርሶ እንዳይጨርሰው ቅቤ ሲጋት ያድራል፡፡ የፈረደበት ወተቱን ቅቤ ሊያደርግ ሲንጥ ያድራል፡፡ በጣም የፈረደበት ደግሞ ወተት ሊያመርት በሬ ሲያልብ ያነጋል፡፡ በድቅድቁ ጨለማ መስቀልያ ሠርቶ በጊዜ አናት ላይ በቆመው ወር ላይ በአራት ሚስማር ተቸንክሮ የተሰቀለው ተቀጣሪ ደጋግሞ ሲጮህ ይሰማኛል፡-
‹‹አቤቱ የምሠራውን አላውቀውምና ይቅር በለኝ››፡፡
ተቀጣሪውን ከመስቀሉ ጋር አብረው የሠፉት አራቱን ሳምንታት የሚወክሉ አራቱ ሚስማሮች ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ኒቆዲሞስ እና ሆሳህና ይባላሉ። የጊዜ ዉጤቶች በመሆናቸው፣ ሳምንታቱ ተራ በተራ ወቅታቸውን ጠብቀው ይስሙታል ወይ ይሰሙታል፡፡
አራት ሳምንታት - ከጊዜ ምንጭ እየወረዱ ሰባት፣ ሰባት ቀናትን በእንስራቸው  እየጨለፉ ተሸክመው የሚመጡ-የማይደክማቸው፣ የማይሰለቻቸው ወረተኞች (ደከመው፣ አልደከመው ጊዜ እንደው ወረተኛ ነዉ)፡፡ አራት ሳምንታት-እንደ መድኃኒተኛ ደስታንና ሀዘንን ሲያሻቸው ለየቅል፣ ካልመሰላቸውም በርዘው መፍጠር የሚችሉ። አራት ሳምንታት-በጭፍግና በኢ-ጭፍጋቸዉ የፊት ገጽታን የሚቆጣጠሩ፤ የፊት ቆዳን ወደ ጎን በመለጠጥ አልያም ወደ ላይ በመቆልመም የተካኑ፡፡ አራት ሳምንታት- አራት የእርግዝና ሳምንታት፡፡ እልፍ ምኞት ተረግዞ፤ እልፍ ደስታና ሀዘን የሚወለድባቸዉ፡፡ የተረገዙት ጨንግፈው፤ የተወለዱት የማይበረክቱባቸው፡፡
እነዚህ አራት ሳምንታት ባላሰበበት እየዋለ፤ ባልዋለበት እያደረ የሚኖረዉ አዲሳባዊ መንግሥት መሥርያ ቤት ተቀጣሪ ኑሮ፤ ፈትሎ የሚያዉለበልባቸዉ ወርሃዊ ሰንደቅ-ዓልማዎች ናቸዉ፡፡ ከአራቱ አቅጣጫ የሚፈልቁት ነፋሳት የሰንደቅ-ዓልማዉ አጫፋሪዎች እና አስጨፋሪዎች ናቸዉ፡፡ እነዚህ አራት ሳምንታት ከቀኝ ከግራ፤ ከፊት ከኋላ ተደግነዉ ተቀጣሪዉ እንደፈረስ ሠርክ ዳንግላሳ እንዲጫወታቸዉ የሚጋርዱ ድግምቶች ናቸዉ፡፡ ግን እነዚህን ድግምት ማነው ያሠራቸው?...ማነዉ የሠራቸው? ...ማነዉ ያሠራብን? ...ለምን ጉዳይ? ...ቀጣሪ እንጂ ተቀጣሪ እንዳያልፍለት ነው? ሚስማራቱስ ስለ ምን አራት ሆኑ? ትርጉማቸውስ?

ዘወረደ
የመጀመርያዉ ሚስማር፡፡ ከደሞዝ በፊት ያለ ሳምንት፡፡ ጨለማዉ ሲጠልቅ ጎህ ሲቀድ ታየ፡፡ ‹ፔይ ሮል› ከአካውንታንቶች ወደ አጽዳቂዎች ወረደ፡፡ ገንዘብ ከከፋዮች አካውንት ወደ ተከፋዮች አካውንት ተወረወረ፡፡ የተቀጣሪዎች ኪስ ገንዘብ ሊጠነሰስበት ይሟሽ፣ ይታጠን ጀመረ፡፡ ደሞዝ መድረሱን የተረዱና ደህንነት የተሰማቸው አበዳሪዎች እጃቸዉ ይፈታ ጀመር፡፡ ደሞዝ ቀድመው የተቀበሉ የሌላ ድርጅት ተቀጣሪዎች /ከአበዳሪዎች የአንበሳዉን ድርሻ የሚይዙት/ እየጋበዙ ያበድሩ ገቡ፡፡ ችግሩ ብድሩ እንደሚከፈላቸው እያወቁ እንኳን ማስጠንቀቅ ያበዛሉ፡፡ በዚህ ሳምንት ተቀጣሪ የደረሰ ደሞዙን ተማምኖ በወሩ ከተበደረው ገንዘብ ድምር የሚልቅ ገንዘብ ይበደራል፡፡
በዘወረደ ቀጣሪዎችና በድርጅቶችና በተቋማት ‹ፒቲ ካሽ› ቀናቸውን የሚገፉ አካዉንታንት፣ ሌላዉ ተቀጣሪ ደሞዝ በወቅቱ እንዳይከፈለው የሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት እልባት አግኝቶ ደሞዝ ወደ ባንክ ይወርዳል፡፡ የብር መቁጠርያ ጣት ማራሻ ስፖንጆች በውሃ ይርሳሉ፡፡ መስቀልያ ሠርቶ በጊዜ አናት ላይ በቆመዉ ወር ላይ በአራት ሚስማር ተቸንክሮ ያለው ተቀጣሪ ግን አሁንም ደጋግሞ ይጮሀል፡-
‹‹አቤቱ የምሠራውን አላውቀውምና ይቅር በለኝ››፡፡  
ቅድስት
ሁለተኛው ሚስማር፡፡ የመልካሞች መልካም! በመንግሥት መሥርያ ቤቶች ከልደታ እስከ ባዕታ የሚባለው በሌሎች ደግሞ ከደሞዝ በኋላ ያለው ሳምንት ነው፡፡ ደሞዝ ከባንክ አካውንት ገባ፡፡ የባንክ የገንዘብ ማውጫዎች ሥራ እንደያዘ ልጅ፣ ከገንዘብ ማስገቢያዎች የበለጠ ተፈላጊነታቸው ጨመረ፡፡ ኪስ በገንዘብ ሞላ፡፡ የተወሰነ ዕዳም ተከፍሎ-የቀረዉ ለሚቀጥለው ወር ተዛወረ፡፡ ሆድም አዲስ ነገር አየ፡፡ በሰሞነ ህማማት የተገባዉ ቃል ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ባለፈዉ ወር ተገዝቶ ሣይሰራ የተቀመጠው አስቤዛ ላይ ጭማሪ አስቤዛ ተገዛ፡፡ እቤት አብስለን እንብላ የሚል ቢጠፋም፤ ወዳጅ ዘመድም በዛ፡፡ መለኪያ ተሞላ፡፡ ብሉልኝ ጠጡልኝ ተባለ፡፡ በስንት ልመናና እግዝዮታ አልታረቅም ብላ ያኮረፈች የሴት ጓደኛም ሆድዋ ተፈቶ፣ ቅያሜዋ ጠፍቶ እራሷ ደውላ መጣች፡፡ ሳምንትዋም የተቀደሰች-ቅድስት ሆነች!፡፡ መስቀልያ ሠርቶ በጊዜ አናት ላይ በቆመዉ ወር ላይ ያለው ተቀጣሪ ግን አሁንም ደጋግሞ ይጮሀል
‹‹አቤቱ የምሠራውን አላውቀውምና ይቅር በለኝ››፡፡  

ኒቆዲሞስ
ሦስተኛዉ ሳምንት፡፡ የሞላዉ ጎደለ፡፡ ከአፋፍ ቆሞ ‹‹ኪሱን ጉደል ብለዉ አለኝ በኒቆዲሞስ›› እያለ ዋሽንት ይጫወት የነበረው ችግርም በተሸረሸረው ላይ ተረማምዶ ከእነ ችግሩ ወደ ጓዳ ዘለቀ፡፡ ወዳጅ ዘመድም እራቀ፡፡ ቶሎ ቶሎ የሚከፋት የሴት ጓደኛም ያለውን ከፍለዉ እንደሸጧት ከመጨረሻው ወጪ ጋር ከቤት እንደወጣች ቀረች፡፡ በየወሩ እየተጨመረ ከጓዳ ዲብ የሠራውን አስቤዛ ወደ ምግብነት የመቀየር ጥረት ተጀመረ፡፡ አብስሎ ከመብላቱ ሽንኩርት እየላጡ ማልቀሱ ባሰ! እንባው የሽንኩርቱ ብቻ አይደለም፡፡ ከማጣት በላይ ምን የሚያስለቀስ አለ? (ሐዘን ላይ ማልቀስ-የሚወዱትን ማጣት፡፡ ታሞ ማልቀስ-ጤና ማጣት፡፡ ቤት ዘግቶ ማልቀስ-እሷን ወይ እሱን ማጣት፡፡ ሽንኩርት እየላጡ ማልቀስ-የበሰለ ነገር ወይ ምታበስል ማጣት።) ደግሞስ ሽንኩርት እያላጡ ካለቀሱ፤ ሲከትፉ ምን ሊሆን ነዉ? እሱም ብርቅ ሆነና ከሁለት ቀናት በኋላ ግን ማብሰያው ከየት ይምጣ? ኒቆዲሞስነት ብቻ ቀረ፡፡ ሲገድ ደመወዛቸውን እንደ ደምና ወዛቸው ከሚቆጥቡት ጋር ተመሳስሎ ሥቆ፤ እጥፍ እያሉ በለጋሾችና አበዳሪዎችን ዙርያ ጭራ መቁላት ተጀመረ፡፡  የባሰ አታምጣ አሉ!  መስቀልያ ሠርቶ በጊዜ አናት ላይ በቆመው ወር ላይ ያለው ተቀጣሪ ግን አሁንም ደጋግሞ ይጮሀል፡-
‹‹አቤቱ የምሠራዉን አላውቀውምና ይቅር በለኝ››፡፡   
ሆሳዕና
ለወሩ መዳረሻ የሚሆን ገንዘብ ከኪሱ የተረፈዉ እርሱ የተመሰገነ ነዉ፡፡ ሆሳዕና-የህማማት መባቻ፡፡ መጨረሻው፤ የማይታወቀው አምሳለ ሲኦል፡፡ ወደ ስቅለት መንደርደርያ፡፡ ካለፉት ሦስት ሳምንታት ቀናት ድምር የሚበልጡ እረጅምና የማያልቁ ቀናት፡፡ ከችጋር በቀር ሁሉም የሚርቅበትና ጀርባቸውን የሚሰጡበት፡፡ ቀናቶቹም ይከፋፈላሉ። የመጀመርያው ቀን አባካኝነት የተረገመበት ቀን፡፡ ሁለተኛው ቀን፣ የጥያቄ ቀን፡፡ ለምን?...እንዴት?...በምን ሀጥያቴ? የሚባልበት ምሬት የበዛበት ቀን። ቀጣዩ ቀን የምክር ቀን፡፡ እንዴት ላድርግ? ምን ይሻለኛል? የሚባልበት ቀን፡፡ ከሱ ቀጥሎ ያለው ቀን ጸሎተ ሐሙስ፡፡ ተሸናፊነት ታውጆ አጽናኝ፣ አበርታኝ የሚባልበት፤ እርዳታ የሚጠየቅበት። ተከታዩ ቀን ስቅለት የሚጀምርበት!፡፡ ስቅለት የሚጸናበት! አባት ሆይ፤ ለምን ተውከኝ የሚደገምበት፡፡ ክፋቱ ሰቃዮቹ ኪስን በጦር ቢወጉት ጠብ የሚል ነገር የለም! ከንፈር በችጋር እንዲያ ተሰነጣጥቆ እያዩ እንኳን ሀሞትና ከርቤ በሰፍነግ ሞልተው፣ በሁሶፕም አድርገው ወደ አፍ ለመስደድ ይስገበገባሉ፡፡ ብቻ የማዘጋጀት ቀንን አልፎ ዘወረደ እየመጣ ነዉ፡፡  መስቀልያ ሠርቶ በጊዜ አናት ላይ በቆመው ወር ላይ ያለው ተቀጣሪ ግን አሁንም ደጋግሞ ይጮሀል፡-
‹‹አቤቱ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!››     

Read 4707 times