Print this page
Saturday, 20 January 2018 12:26

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(29 votes)

 አንድ የአሜሪካን ባህር ኃይል አባል ታሪክ ትውስ አለው፡፡ አንድ ጦር መርከብ ከአንድ ወደብ ተነስቶ ወደ ሌላ ግዳጅ በሚሰማራበት ወቅት የእያንዳንዱ ክፍል ኃላፊ ያለውን የሰው ኃይልና የተመደበበትን ክፍል ምን ያህል ዝግጁ ሆኖ እንደሚሰለፍ ለካፒቴኑ እየመጣ ተራ በተራ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ በአንደኛው ግዳጅ ላይ ቀዘፋው ተጀምሮ አንዱ መርከበኛ የደረሰበት ጠፋ፡፡ የመርከቧ ጓዳ ጎድጓዳ ሁሉ ተፈለገ፡፡ አልተገኘም፡፡ ይህንን አሳዛኝ ዜና ለባህር ኃይል መደብ ሪፖርት አድርገው ወደ ፊት ቀዘፋቸውን አቀኑ፡፡
ይህ ልጅ በጠፋበት አካባቢ አንድ ሰማያዊ ዓሣ ነባሪ በዓሣ አጥማጆች ተሰገረ፡፡ ዓሣ ነባሪውን ያሰገረችው መርከብ፣ የራሷ ቄራ ነበራትና ዓሣ ነባሪውን ጎትታ ወደ ቄራው እገባችው፡፡ በላቾቹ በፍጥነት የዓሣ ነባሪውን ሆድቃ አንዳች በሚያክለው ቢላቸው ሲበረግዱ፤ አንዱ ጥግ ላይ ያ ከመርከብ ላይ ጠፋ የተባለ መርበኛ እጥፍጥፍ ብሎ እንቅልፉን እየለጠጠ ነበር፡፡ በላቾቹ ተደናግጠው ሲቀሰቅሱት፤ “ምነው የዘብ ሰዓት ደረሰ እንዴ?” ብሎ መጠየቁ ይወራለታል፡፡
ይህ መርከበኛ ከመርከቧ ላይ እንደወደቀ ዓሣ ነባሪው ዋጥ አድርጎታል፤ ሳያውቀው ወደ ሞቱ እያዘገመ ነበር፡፡ ዛሬ ዕድሜ ለዓሣ አስጋሪዎች በሕይወት ተረፈ፡፡ ይሁን እንጂ ሕይወቱን በሙሉ ለምጣም ሆኖ ኖረ፡፡
“የእኛስ ምን ይሆን ዕጣችን?...” አውጠነጠነ፡፡ ምላሽ የለውም፡፡ መፍጠን አለበት፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሻርክ ራት ሆነው የቀሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አሜሪካውያን፣ ጀርመናውያንና እንግሊዛውያን መርከበኞች ታሰቡትና አሁን ሲሆን ያየ ይመስል ዘግንኖት አይኖቹን ጨፈነ። ደገመና “የእኛስ መጨረሻ ምን ይሆን?” ሲል በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ዓለም ውስጥ ሲኖር መግቢያው ብቻ ሳይሆን መውጫውንም ማውጠንጠን የግድ ነው፡፡
ጀርባዋ ላይ በእርዳታ የታደለ ቦክራ የዱቄት ወተት አለ፡፡ ብዙዎቹ መርከበኞች በጥብጦ የመጠጣት ልምድ የላቸውም፡፡ ያሬድ ሐጎስ ባህር ኃይል በልክ ሰፍሮ የሚሰጠው ምግብ ከአንጀቱ ጠብ ስለማይል ቦክራውን በጥብጦ በመጠጣት የምግብ ፍላጎቱን ያሟላል፡፡ ከተማ ወጥቶ ተዝናንቶ እስኪመለስ የበጠበጠውን የቦክራ ወተት ፍሪጅ ውስጥ አስቀምጦ ይሄዳል። ምሽቱ ሲጋመስ በደንብ ቀዝቅዞ ስለሚጠብቀው አንጀት አርስ እንደሚሆንለት ዕምነቱ ነው፡፡ ይህንን አልሞ በጥብጦ የማስቀመጥ ባህሉን ቢያዳብርም፣ በቅርቡ ግን ማንነቱን ያላወቀው መርከበኛ እየሰረቀ ጠጥቶበት በተደጋጋሚ ባዶ ጆግ ፍሪጅ ውስጥ አጋጥሞታል፡፡ ይህን ቀበኛውን ለማጥመድ ዛሬ ቦክራው ውስጥ “ፈንጂ” አጥምዶበት ነው ፍሪጁ ውስጥ ያኖረው፡፡
(ከደራሲ ዘነበ ወላ “መልህቅ”
የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ላይ የተቀነጨበ)

Read 7866 times
Administrator

Latest from Administrator