Saturday, 20 January 2018 12:28

‹‹…እናት ጤና…ሁሉም ጤና…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(0 votes)

  • ለጤናማ እናትነት ……. ይብቃ ማርገዝ ……...በአፍላ ወጣትነት
      • እድሜያቸው ል ጅ የ ሆነ … ማለትም እ ስከ 1 8/አመት ድረስ የሆኑ ሴቶች ለፊስቱላ መጋለጥ ብቻ ሳይሆን          ከእርግዝና ጋር ለተያያዘ ሌሎች ተያያዥ ችግሮችም ይጋለጣሉ፡፡

    በኢትዮጵያ Safe motherhood የእናቶች ደህንነት በየአመቱ ከጥር 1-30/ሲከበር እነሆ 12/አመት ሆነው፡፡የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህንን በአል በየአመቱ ሲያከብር በጉዳዩ ላይ በቂ እውቀት እንዲኖር እና ንቃተ ህሊናንም ከማዳበር አንጻር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ነው፡፡ ይህንን የእናቶችን ደህንነት ለማጠናከር የሚረዳውን  ተግባር ዘንድሮም ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የዘንድሮውም Safe motherhood የእናቶች ደህንነት ፕሮግራም አከባበር ያተኮረው የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የእናቶችንና ጨቅላዎችን ጤንነት በመጠበቅ ረገድ የጠራ እና ተደራሽነት ያለው የተጠናከረ የጤና አገልግሎት አሰራርን እንዲያደረጁ እና ለህብረተሰቡም መስጠት እንዲችሉ እንዲሁም ከአሁን ቀደም የነበራቸውን ኃላፊንትና ድርሻ እንዲያጎለብቱ ማድረግ ነው፡፡ ህብረተሰቡም ተገቢ የሆነውን አገልግሎት እንዲሻ እና እንዲጠቀም ማስቻልም የዚህ በየአመቱ ለአንድ ወር የሚከበረው Safe motherhood የእናቶች ደህንነት ፕሮግራም አላማ ነው፡፡   
ባለፈው ሳምንት ህትመት የጀመርነው የፊስቱላ ሕመም እና ሕክምናው ጉዳይ ዛሬም ቀጣዩን ለንባብ ብለናል፡፡ እናቶች ጤናቸው በእጅጉ ከሚቃወስባቸው ምክንያቶች አንዱ የፊስቱላ ሕመም ነው፡፡ በተለ ይም ሴቶች አካላቸው ሳይዳብር እድሜያቸው ከታዳጊነት ሳያልፍ እርጉዝ መሆናቸው በምጥ ሰአት ለሚፈጠሩ የአካላቶቻቸው መቀደድ እንዲዳረጉ ያደርጋቸዋል ፡፡ በውስጥ አካሎቻቸው ላይ አላስፈላጊ ቀዳዳ ሲፈጠሩ ሽንትና ሰገራን መቆጣጠር ያቅታቸዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ትዳራቸው ይናጋል፡፡ ቤተሰቦቻቸ ውም ከእግዚሐር የተላከ ቁጣ ነው ብለው ስለሚያምኑ ብዙዎች ለሕክምና ሳይበቁ በእንግልት የሚኖ ሩባቸው አጋጣሚዎች ተስተውለዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን በአብዛኛው ስፍራ ይህ ሕመም በምጥ መራዘም እና በአካሎቻቸው መሳሳት ምክንያት የሚከሰት እንጂ በእግዜር ቁጣ የመጣ እንዳልሆነ እና በዚህም ምክንያት ሴቶች እድሜ ልክ ለሚቀጥል ስቃይ መዳረግ የለባቸውም በሚል ወደሕክምና ተቋም መሔድ ከተጀመረ አመታትን አስቆጥሮአል፡፡ በተለይም ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከተቋቋመ ወዲህ በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን በየክልል መስተዳድሩ ከሚገኙ ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር የፊስቱላ መታከሚያ ክፍል በተለይ በመክፈት ሴቶች በአቅራቢያቸው እየተገኙ እንዲታከሙ በመደረግ ላይ ነው፡፡ የዚህ አምድ አዘጋጅም ከአሁን ቀደም በተለያዩ መስተዳድሮች (አዲስ አበባ… ጎንደር…መቀሌ…ባህርዳር …ወዘተ) በመገኘት ዘገባውን ለአንባቢ ያደረሰች ሲሆን አሁንም በአሰላ ሆስፒታልና በአዲስአበባ ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በመገኘት ታካሚዎችን እና ሐኪሞችን የማነጋገር እድል አግኝታለች፡፡
‹‹…እኔ የመጣሁት ከደብረሲና ነው፡፡ የዛሬ 11/አመት የመጀመሪያ ልጄን ስገላገል 5/ቀን ያህል ምጥ ቆይቶብኝ ነበር። ያን ጊዜ የተዳርኩት በ16/አመቴ ነበር፡፡ እናም በአመቱ ልጅ ተረገዘና በቀላሉ መገላገል ግን አልቻልኩም፡፡ ከዚያ ወዲያ ወደሆስፒታል ቢወስዱኝም ልጅ በሆዴ ጠፍቶ ኖሮ ብዙ ተሰቃየሁ፡፡ በሁዋላም የሞተውን ልጅ አዋልደውኝ ወደቤቴ ስመለስ ሌላ ችግር ተፈጠረ፡፡ እኔ ሳልሰማው ሽንቴ ይፈስ ጀመር፡፡ እኔም ውሀ መጠጣት አቆምኩ፡፡ ጠዋት ሰው ሳይነሳ ተነስቼ የሽንት ጨርቄን አጥቤ እዚያው ከደጅ ከድንጋይ ላይ ተቀምጬ እውላለሁ፡፡ የምበላውን እዚያው ይሰጡኛል። የባለቤቴ እናትም ለባለቤቴ ‹…ልጅቱን ወስደህ ለእናቷ ስጥ አሉት፡፡ እሱም ለምን? ብሎ ቢጠይቃቸው‹…እንደዚህ ያለ መርገምት ያለባት ልጅ እኛ ምን እናደርጋታለን…አሉት፡፡ እሱም …መርገምት ከሆነም በጸበል ሕመምም ከሆነ በሐኪም ትፈወሳለች እንጂ…ስትታመም አውጥቼ እጥላለሁ? ብሎ መለሰላቸው፡፡ ሐምሊን ሆስፒታል ታክሜ ድኜ…ወደሀገሬ ስመለስ…ሐኪሞቹ እንዲህ አሉኝ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ስታረግዢ በቅርብ ወደሚገኘው ጤና ጣቢያ እየሄድሽ በደንብ ተከታተዪ። ከዚያም መውለጃሽ ገና ሲቃረብ ወደ እኛ ጋ ነይ አሉኝ፡፡ እኔም እንደነገሩኝ እያደረግሁ…. አሁን ሶስተኛ ልጄን ልወልድ መጣሁ፡፡
ለጤናማ እናትነት ……. ይብቃ ማርገዝ ……...በአፍላ ወጣትነት
የእናቶች ደህንነት ሲባል የእኔ ድርሻ አይደለም የማይባል የሁሉም ተግባር ነው ፡፡ዶ/ር ፈቃደ አየናቸው ከሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ስለልጅነት እርግዝና የሚከተለውን ብለዋል፡፡
‹‹…በልጅነት እድሜ የሚፈ ጠረው እርግዝና ለፊስቱላ ብቻ ሳይሆን ከእርግዝና ጋር ተያያዥ ለሆኑት ሌሎ ችግሮች የበለጠ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡እነዚህን ችግሮች በመጠኑ ብንመለከታቸው ለምሳሌ… እንደደም ግፊት ፣ደም ማነስ፣ አለግዜ መውለድ፣ በምጥ ጊዜ መራዘም ጋር ለተያያዙ ችግሮች የበለጠ ይዳርጋቸዋል፡፡ ስለዚህም ከመውለድ ጋር ለተያያዘ ሞት እና ሌሎች የአካል ጉዳቶች ይዳርጋቸዋል፡፡ በውጭው አቆጣጠር በ1990/ዎቹ አካባቢ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወደ /70-80/በመቶ የሚሆኑት ለሕክምና ወደ ሆስ ፒታል የሚመጡት እናቶች አማካይ እድሜያቸው ወደ /17-18/አመት የሚደርስና የመጀመሪያ ልጃቸውን ሲወልዱ ችግር የገጠማቸው ነበሩ፡፡ አሁን ግን ሁኔታው ተሸሽሎ ወደ 1/3ኛ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ የመጀ መሪያ ልጃቸውን ሲወልዱ ችግር የሚገጥማቸውና ፊስቱላ የሚኖራቸው ሆነዋል፡፡ ተጎድተው የሚመጡ እናቶች አማካይ እድሜም ወደ 23/አመት ተራዝሞአል፡፡ ይሁን እንጂ የጉዳታቸው መጠን፣ ከሕክምና በሁዋላ ሽንት የመቆጣጠር ሁኔታ፣ ከታከሙ በሁዋላ የማርገዝ እድላቸው የመሳሰሉት ሁሉ እድሜያ ቸው በ17/ ወይም 18/ - 20/ ድረስ ባሉት ላይ የከፋ ሆኖ ይታያል፡፡ ስለዚህም እነዚህ ሴት ልጆች  ለፊስቱላ ብቻ ሳይሆን ከመውለድ ጋር በተያያዘ ለሌሎች ችግሮችም ይዳረጋሉ፡፡ ከታመ ሙም በሁዋላ ከበሽታው የመዳን እድላቸው ከሌሎች ሴቶች ይልቅ ዝቅ ያለ ነው፡፡
ዶ/ር ዋሲሁን አለማየሁ የማህጸንና ጽንስ እስፔሻሊስት ሐኪም እና በአሰላ ሆስፒታል የፊስቱላ ክሊኒክ ኃላፊ እንደገለጹት በፊስቱላ ሕመም ምክንያት ወደሆስፒታላቸው የሚመጡት ሴቶች ከሕመሙ ጋር በርካታ አመታትን ያስቆጠሩ እና ሲሰቃዩ የኖሩም ጭምር ናቸው፡፡ በሕመሙ 30/እና ከሰላሳ አመት በላይም የታመሙ ሴቶች ለሕክምናው የሚመጡ ሲሆን አንዳንዶቹ ለመዳን ከማይችሉበት ደረጃ ሕመም ይገጥማቸዋል፡፡ ለዚህም ሕክምናው በሚደረግ ጊዜ የመቃወም ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ሁለተኛ ወይንም ሶስተኛ ደረጃ ለሚባሉት የፊስቱላ ደረጃዎች የሚሰጠው ሕክምና በሆድ በኩል ሽንት እንዲወጣ የማድረግ ስራ ሲሆን በአብዛኛው በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የማይኖረው ሽንትን በማስወገጃ ወይንም በአይን በሚታይ ሁኔታ በቱቦ የማስተላለፍ የመሳሰሉትን መርጃ መሳሪያዎች ለመቀበል መቸገር ነው፡፡ ይህንን የህክምና ዘዴ ከመቀበል ይልቅ ከነችግሩ ብኖር ይሻለኛል የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡
በከባድ ሁኔታ የተጎዱ ሴቶች የሚደረግላቸውን የቀዶ ሕክምና እና ተጨማሪ መርጃ መሳሪያ የማይቀበሉ ከሆነ ሌላ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በምን መንገድ ከችግሩ ጋር መኖር እንዳለባቸው እና በምን ያህል የጊዜ ልዩነት ወደሕክምናው መቅረብ እንደሚገባቸው በተቻለ መጠን ይነገራቸዋል፡፡ የሽንት መቀበያ ዲያፐር እንዲኖራቸው፣ የኩላሊትና የሽንት ቧንቧ ውስጥ ጠጠር እንዳይኖር ውሀ በደንብ እንዲጠጡ ይመከራሉ፡፡ ውሀ በደንብ የሚጠጡ ከሆነ የሽንት ሽታውም ስለሚቀንስ ከሰው ጋር አብሮ የመኖር እድላቸውንም ሊያሰፋው ይችላላ፡፡
ዶ/ር ዋሲሁን በተጨማሪም እንዳብራሩት የፊስቱላ ችግር ማለት የሁለት አካላት በቀዳዳ መገናኘት ስለሆነ በማኝኛውም ሰአት ማለትም ሲተኙም ፣ሲቀመጡም ፣ሲራመዱም ሽንት ይፈሳል፡፡ ስለዚህም የሚመጣው የጤና ችግር የተለያየ ነው፡፡
አካላዊ ችግር(የተፈጠረው የአካል ቀዳዳ እራሱ)
የተራዘመ ምጥ የነበረ ስለሆነ በነርቮቻቸው እንዲሁም በእግር ላይ የጤና ችግር ያስከትላል፡፡
ችግሩ እንደተፈጠረ በተለይም ለሁለት አመታት ያህል እግራቸው ላይጉዋዝ ነርቫቸው ላይታዘዝ ይችላል፡፡
ማህጸን ቢድን እንኩዋን ጠባሳ ሊኖረው ስለሚችል የግብረስጋ ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ ከፍተኛ ሕመም ሊሰማቸው ይችላል፡፡
የመውለድ እድል ያለመኖር፣
በተራዘመው ምጥ ምክንያት ማህጸን ሊወጣ ስለሚችል የወር አበባ አለማየት ሊከሰት ይችላል፡፡
ሽንት ሁልጊዜ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ ስለሚፈሳቸው በውስጥ እግራቸው እንዲሁም ሽንቱ ተደጋግሞ በሚፈስበት አካባቢ አካላዊ ቁስለት ይኖራቸዋል፡፡
ማህበራዊ ችግር ያስከትላል፡፡ (የትዳር መፍረስ፣ የቤተሰብ ማግለል፣ በአካባቢያቸው ያለውን ማህበራዊ ኑሮ መቀላቀል አለመቻል፣ በእምነት ተቋማት መገኘት አለመቻል…) ወዘተ፡፡
ፊስቱላ ከሌሎች በሽታዎች የበለጠ የስነልቡና ችግር ያስከትላል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎችም እርግማን ነው በሚል ከመኖሪያ ቤት እንዲወጡና ፈንጠር ብሎ ወደተሰራ ጎጆ ለብቻቸው እንዲኖሩ የሚደረጉበት ሁኔታም አለ፡፡ ስለዚህም ተስፋ መቁረጥ፣ ድብርት፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ከመኖር አለመኖር ይሻለኛል በማለት እራሳቸውን እስከማጥፋት ሊደርሱ ይችላሉ፡፡
ፊስቱላ ጥንቃቄ ከተደረገ ሊደርስ የማይችል ሕመም ነው፡፡ ማንኛዋም ሴት እርግዝና ሲኖራት አስቀድማ የህክምና ክትትል ብታደርግና በመውለጃዋም ወቅት ወደሕክምና ተቋም በመሄድ በሰለጠነ ሰው እንድትወልድ ቢደረግ የተራዘመ ምጥ ስለማይኖር ፊስቱላ አይከሰትም፡፡
ለጤናማ እናትነት ……. ይብቃ ማርገዝ ……...በአፍላ ወጣትነት

Read 2041 times