Saturday, 20 January 2018 12:28

የሮናልዲንሆ ጎቾ ማስታወሻ Obrigado, Ronaldinho!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

  በሙሉ ስሙ ሮናልዶ ዴ አሲስ ሞሪዬራ ተብሎ ቢጠራም በዓለም ዙርያ ሮናልዲንሆ ጎቾ በሚል ስሙ ይታወቃል፡፡ በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋችነት የመጨረሻ የክለብ ጨዋታውን በብራዚሉ ፍላሚንጎ  ከ2 ዓመታት በፊት ያደረገ ቢሆንም በኦፊሴላዊ ደረጃ ጫማዎቹን በመስቀል ከእግር ኳስ መሰናበቱን በይፋ ያስታወቀው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በ37 ዓመት እድሜው ነው፡፡ ማናጀሩ እና ታላቅ ወንድሙ የሆነው ሮበርቶ አሲስ ባለፈው ማክሰኞ በብራዚሉ ጋዜጣ ኦግሎቦ ባሰፈረው ኦፊሴላዊ መግለጫ ሮናልዲንሆ ጫማዎቹን በመስቀል እግር ኳስን እንደተሰናበተ ያረጋገጠ ሲሆን ራሽያ ከምታስተናግደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ በኋላ  ከረጅም ጊዜ ስፖንሰሩ ናይኪ ጋር በመተባበበር በስሙ መታሰቢያነት ልዩ ዝግጅቶችና ኳስ ጨዋታዎች በብራዚል፤ አውሮፓ እና ኤሽያ በመዘዋወር እንደሚካሄዱም አስታውቋል፡፡
የዓለም እግር ኳስ በየታሪክ ምዕራፉ በርካታ ታላላቅ ተጨዋቾችን አይቷል፡፡ ፔሌ፤ ማራዶና፤ ክሩፍ፤ ፕላቲኒ፤ ሮናልዶ፤ ዚዳን… ከእነ ሜሲ፤ ሮናልዶ እና ኔይማር በፊት ደግሞ ሮናልዲንሆ ነበር፡፡ የእግር ኳሱ ዓለም ሮናልዲንሆን በአዝናኝና አስደሳች ችሎታዎቹ ለይቶ ያስታውሰዋል። ሮናልዲንሆ በክንፍ፤ በአማካይ እና በአጥቂ መስመር መጫወት የሚችል ሁለገብ ኳስ ተጨዋች በመሆኑ እውነተኛ 10 ቁጥር በሚል ተደንቋል፡፡ በቆሙ ኳሶችን አጠቃቀሙ ልዩ ተሰጥኦዎቹን በተደጋጋሚ ያሳየ ሲሆን በተለይ በቅጣትና በኢሊጎሬ ምቶቹ የተካነ ነበር፡፡ በግራም በቀኙም የሚጫወት፤ ምርጥ የቴክኒክና የፈጠራ ችሎታ የታደለ፤ ቅልጥፍና ሚዛን ያለው፤ ኳስ በማንከባለለል እና አብዶ በመስራት የላቀ ነበር፡፡ የሮናልዲንሆ ችሎታ በልጅነቱ ከተጫወታባቸው ጎዳናዎች አንስቶ በትልልቅ ስታድዬሞች፤ በልምምድ ሜዳዎች፤ በፉትሳል ሜዳዎች፤ በባህር ዳርቻ  አሸዋማ ሜዳዎች ላይ ያው ተመሳሳይ  ነው፡፡ በጣም አስደናቂና አስገራሚ ጎሎችን በተደጋጋሚና በብዛት በማስቆጠርም የሚታወስ ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድንና በክለብ ደረጃ ባሳለፈባቸው የተጨዋችነት ዓመታት በመቀስ ምት፤ በቮሊ፤ በተረከዝ ምት፤ ከረጅም ርቀት በተመጠኑ ሹቶች፤ በርካታ ተጨዋቾችን እንዲሁም ግብ ጠባቂን አታልሎ በማለፍ የማይረሱ ጎሎችን በብዛት አስመዝግቧል፡፡ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹን በመጠቀም ኳስን በልዩ ሁኔታ በሚያቀብልበት ተሰጥኦውም ስሙ የሚጠቀስነው፡፡ በጀርባው፤ በትከሻ ምርጥ ኳሶችን ሲያቀበልም አጋጥሟል፡፡  ብራዚላዊው ቶስታኦ ባንድ ወቅት የሮናልዲንሆን ብቃት ሲገልፅ ‹‹የሬቨሊኖ ኳስ የማንከባለል ችሎታ፤ የጌርሰን እይታ፤ የጋሪንቻ የጥንካሬና የደስታ መንፈስ፤ የጀርዚንሆ ፍጥነት፤ የሮናልዶ ተሰጥኦ፤ የዚኮ ቴክኒካል ብቃት እና የሮማሪዮ ፈጣሪነት ያዋሃደ ነው›› ብሏል፡፡
ሮናልዲንሆ በክለብ ደረጃ
የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋችነቱን በ18 ዓመቱ በብራዚሉ ክለብ ግሬሚዮ በ1998 እኤአ ላይ የጀመረ ሲሆን እስከ 2015 እአኤ ድረስ 18 ዓመታት በክለብ ደረጃ ተጫውቷል፡፡ በደቡብ አሜሪካ ብራዚል፤ በአውሮፓ በፈረንሳይ፤ ስፔንና ጣሊያን እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ሜክሲኮ በሚገኙ ክለቦች ነው፡፡
የተጨዋቾች የዝውውር ገበያን በሚያሰላው ትራንስፈርማኬት ድረገፅ እንደተመለከተው በተጨዋችነት ዘመኑ ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ክለብ ባደረጋቸው ዝውውሮች ከ61 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝቷል፡፡ በ2001 እኤአ ላይ ከብራዚሉ ክለብ ግሬምዮ ወደ ፈረንሳዩ ፒ ኤስጂ ሲዛወር በ6 ሚሊዮን ዶላር፤ በ2003 እኤአ ከፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ወደ ስፔኑ ባሴሎና ሲዛወር 40 ሚሊዮን ዶላር፤ በ2008 እኤአ ከስፔኑ ባርሴሎና ወደ ጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ሲዛወር 31 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ ከኤሲ ሚላን ወደ ብራዚሉ ፍላሚንጎ ክለብ ሲዛወር 3.7 ሚሊዮን ዶላር የዝውውር ሂሳብ ተከፍሎበታል፡፡
በክለብ ደረጃ በተጫወተባቸው 18 የውድድር ዘመናት ካገኛቸው ዋንጫዎች መካከል በ2001 እኤአ የአውሮፓ ኢንተርቶቶ ካፕን ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ ጋር ማግኘቱ የመጀመርያ ነው፡፡ ከስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ጋር ሁለት የላሊጋ ዋንጫዎችን በ2004-05 እና በ2005 -06 እኤአ ፤ የስፓኒሽ ሱፕር ካፕ ሁለት ዋንጫዎችን በ2005 እና 2006 እኤአ እንዲሁም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በ2005 -06 እኤአ ላይ በመጎናፀፍ ተሳክቶለታል፡፡  ከጣሊያኑ ክለብ ኤሲ ሚላን ጋር የሴሪኤ ስኩዴቶ ክብርን በ2010 -11 እኤአ የተቀዳጀ ሲሆን፤ ከብራዚሉ ክለብ አትሌቲክ ሚኒዬሮ ጋር በ2013 የኮፓ ሊበርታዶስ እና በ2014 የሪ ኮፓ ሱዳሜሪካና ዋንጫዎችን ለማሸነፍ ችሏል፡፡
በአጠቃላይ ሮናልዲን በክለብ ደረጃ በተጨዋችነት ባሳለፈባቸው 18 የውድድር ዘመናት በ441 ጨዋታዎች ተሰልፎ 280 ጎሎች አስመዝግቧል፡፡ የሚከተሉት በኦፊሴላዊ ደረጃ የተመዘገቡ ናቸው፡፡
በብራዚሉ ክለብ  ግሬሚዮ ከ1998 እስከ 2001 እኤአ በ145 ጨዋታዎች 72 ጎሎች
በፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ከ2001 እስከ 2003 እኤአ በ77 ጨዋታዎች 25 ጎሎች
በስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ከ2003 እስከ 2008 እኤአ በ207 ጨዋታዎች 94 ጎሎች
በጣሊያኑ ክለብ ኤሲ ሚላን ከ2008 እስከ 2011 እኤአ በ95 ጨዋታዎች 26 ጎሎች
በብራዚሉ ክለብ ፍላሚንጎ ከ2011 እስከ 2012 እኤአ በ71  ጨዋታዎች 28 ጎሎች
በብራዚሉ ክለብ አትሌቲኮ ማኒዬሮ ከ2012 እስከ 2014 እኤአ በ80  ጨዋታዎች  28 ጎሎች
በሜክሲኮው ክለብ ኩዌርታሮ ከ2014 እስከ 2015 እኤአ በ29  ጨዋታዎች 8 ጎሎች
ሮናልዲንሆ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ
ሮናልዲንሆ በብራዚል ብሄራዊ ቡድን በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች ለ15 ዓመታት የተጫወተ ሲሆን በ1999 እኤአ ኮፓ አሜሪካን፤ በ2002 እኤአ የዓለም ዋንጫን፤ በ2005 እኤአ የፊፋ ኮንፌደሬሽን ካፕን፤ በ1999 እኤአ አሜሪካን ካፕ እንዲሁም በ1997 በፊፋ ሀ-17 የዓለም ሻምፒዮን ዋንጫን  መጎናፀፍ ችሏል። በዋናው የብራዚል ብሄራዊ ቡድን በ97 ጨዋታዎች ተሰልፎ ያስመዘገባቸው 33 ጎሎችን ናቸው፡፡
ሮናልዲንሆ   በልዩ የክብር ሽልማቶች
ሮናልዲንሆ ከ10 በላይ ትልልቅ የኮከብ ተጨዋች ልዩና የክብር ሽልማቶችን የተሸለመም ነው፡፡ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ለሁለት ጊዜያት በ2004 እና በ2005 እኤአ ላይ፤ በዎርልድ ሶከር መፅሄት የዓመቱ  ኮከብ ተጨዋች በ2004 እና 2005 እኤአ ላይ፤ የፍራንስ ፉት ቦል የወርቅ ኳስ ተሸላሚ በ2005 እኤአ፤ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ፊፍፕሮ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች በ2005 እና 2006 እኤአ ፤ በ1999 እኤአ በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ በኮከብ ግብ አግቢነት የወርቅ ጫማ በኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ፤ የቦላ ዴፓርታ ልዩ ሽልማት በ2000 ፣2011ና 2012 እኤአ ላይ ፤ በላሊጋ ምርጥ የውጭ ተጨዋች በ2004 እና በ2006 እኤአ መሸለሙ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በብራዚል የእግር ኳስ ሙዚዬም፤ በኤሲ ሚላንና የባርሴሎና ክለቦች የዝና መዝገብ ስሙ በወርቃማ ቀለም የሰፈረለት ነው፡፡
ሮናልዲንሆ ደሞዙ፤ የዝውውር ገበያ፤ ንግድና ስፖንሰርሺፕ
በእግር ኳስ ስፖርት በሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጭ  ትርፋማ ከሆኑ ተጨዋቾችም ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው፡፡ በ2017 በእግር ኳስ ያካበተው የሃብት መጠን እስከ 96 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን የተለያዩ መረጃዎች ያወሱ ሲሆን በትልልቆቹ የአውሮፓ ክለቦች ይጫወትባቸው በነበሩት የውድድር ዘመናት ከደሞዝ፤ ከተለያዩ የቦነስ ክፍያዎች፤ ከስፖንሰርሺፕ እና የንግድ ገቢዎች በዓመት እስከ 24 ሚሊዮን ዶላር ይከፈለው ነበር፡፡ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በስፖንሰርሺፕ እና በተለያዩ የንግድ ውሎች በመስራት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ የበቃም ነበር፡፡ በተለይ በ2006 እኤአ ላይ ከፔፕሲ፤ ከኮካኮላ፤ ከኢኤስፖርትስ ከጋቶርዴ እና ዳኖኔ ከተባሉ ኩባንያዎች ጋር በመስራት በአንድ የውድድር ዘመን ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱ የሚጠቀስ ይሆናል። በርካታ የፔፕሲ ኩባንያ ማስታወቂያዎችን ከዴቪድ ቤካም ፤ ቲዬሪ ኦንሪ እና ሊዮኔል ሜሲ ጋርም ሰርቷል፡፡
የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ኦፊሴላዊ አምባሳደር ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ከ2006 እኤአ ወዲህ በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ የህፃናት ፈንድ ኦፊሴላዊ አምባሳደርም ነው፡፡
ሮናልዲንሆ በዩ ቲውብና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች
የአብዶ ችሎታዎቹን፤ ልዩ ልዩ ተሰጥኦዎቹን፤ ምርጥ ጎሎቹን እና በጨዋታ ላይ ያሳያቸውን ተዓምራዊ ቅፅበቶቹን በማህበራዊ ሚዲያዎች ለዓለም ህዝብ በማቅረብም ስሙ የሚነሳ ነው፡፡ ከ2000 እኤአ ወዲህ በዩ ቲውብ ድረገፅ መሰቀል የጀመሩት የሮናልዲንሆ በእግር ኳሱ ዓለም  ፈርቀዳጅ ያደርጉታል፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት ለአሜሪካው የስፖርት ትጥቅ አምራ ኩባንያ ናይኪ ከኮርና የግብ አግዳሚን ለሶስት ጊዜያት አከታትሎ በኳስ እየመታ ያሳየው ትርኢት በዩ ቲውብ ለመጀመርያ ጊዜ  ሲለጠፍ ከ1 ሚሊዮን በላይ እይታ ማስመዝገቡ የሚጠቀስ ነው፡፡ በስፖርቱ ዓለም በማህበራዊ ሚዲያዎች ባለው እውቅና  ከሮናልዶ፤ ሜሲ፤ ቤካም፤ ኔይማርና ካካ ቀጥሎ በ6ኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን  31 ሚሊዮን የፌስቡክ አድናቂዎች አሉት፡፡
ሮናልዲንሆ VS ዚዳን፤ ሜሲና ሮናልዶ
የእግር ኳሱ ዓለም ፔሌን ከሮናልዶ፤ ክሩፍን ከፕላቲኒ እንዲሁም ሜሲ ከሮናልዶ ሲያነፃፅር ይታወቃል፡፡ ሮናልዲንሆ በአቻነት በተደጋጋሚ ይነፃፀር የነበረው ከዚነዲን ዚዳን ጋር ነው፡፡ ሁለቱም በአጥቂ እና አማካይ  መስመር የሚጫወቱ፤ ለየቡድናቸው መነቃቃት በሚፈጥሩበት ስብዕናቸው፤ በግል ጥረታቸው ቡድናቸውን ውጤታማ በማድረጋቸው  በጥሩ የቡድን ስሜት መሪ ሆነው በመስራታቸው ይመሳሰላሉ፡፡
በአጠቃላይ ግን ሮናልዲንሆ ከዚዳን ብበዙ ነገሮች የተሻለ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በሁለቱም የክንፍ መስመሮች ተቀላጥፎ እና ፈጥኖ ስለሚጫወት፤ ተከላካዮችን በሚያምስበት የአብዶ ችሎታው፤ በየጨዋታው በሚፈጥራቸውና በሚቀያይራቸው ኳስ የማታለል ተሰጥኦዎቹ እንዲሁም   ብዙ ጎሎችን በማስቆጠር ማለት ነው፡፡ በጎሎች ብዛት ብቻ ሳይሆን  የማይረሱና ድንቅ ጎሎችን በማግባትም  ዚዳን ቀርቶ ሌላ የሚስተካከለው የለም፡፡ ዚዳን ከሮናልዲንሆ ተሽሎ ሊጠቀስ የሚበቃው ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት ሙያው ገብቶ በአጭር የስራ ዘመናት የላቀ እና ታሪካዊ ስኬቶችን በማስመዝገቡ ይሆናል። የፖርቱጋና የባርሴሎና እውቅ አማካይ የነበረው ዴኮ በአንድ ወቅት ሲናገር‹‹ ሮናልዲንሆ ከሜሲና ከሮናልዶ እጅግ የላቀ ተሰጥኦ አለው፡፡ ችሎታ ተፈጥሯዊ ነበር፡፡ ኳስ አቀብለው በእንቅስቃሴው እና በሚያቆጥረው ጎል ከሌላ ዓለም የመጣ በሚመስል ብቃት ይጠቀምበታል።›› ሲል መስክሮለታል፡፡
የሮናልዲንሆ  ስንብት በታላላቅ እግር ኳስ ተጨዋቾች አንደበት
ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ‹‹ሮናልዲንሆ ኳስ ስትጫወት በመመልከቴ በጣም ብዙ ተደስቻለሁ። ንጉስ ነበርክ፡፡ እወድሃለሁ፡፡››
ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ‹‹ሞክሼ ሆነን በርካታ የታሪክ አጋጣሚዎችን ማሳለፋችን ትልቅ ክብርሬ ነው፡፡ የኳስ ጥበብ እና ደስታን ከአንተ ጋ አሳልፈናል፡፡ አመሰግናለሁ ሮናልዲንሆ››
አንድሬ ፒርሎ ‹‹አመሰግናለሁ ሮኒ፤ ካንተ ጋር ተጫውቶ ማሳለፍ ትልቅ ፀጋ ነበር፡፡››
ሪካርዶ ካካ ‹‹የአንተን ጨዋታ መመልከት ፀጋ ነው። ከጎንህ ተሰልፌ በመጫወቴ እና ዋንጫዎችን በማሸነፌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል፡፡ በቀጣይ የህይወት ምዕራፍህ ስኬት ንእመኝልሃለሁ፡፡ የህይወት ዘመን አጋሬ፤ ጎውቺንሆ››
ካርሎስ ፒዮል ‹‹በጋራ መጫወታችን ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ አንተ ደስታን ሰጥተሀናል፡፡ በስኬት የተሞላ ምዕራፍ ፈጥረህልናል፡፡ ሁሌ ትዝ የሚለኝ ወደ ሜዳ ስንገባ  ‹‹አንተ ተከላከል እኔ አጠቃለሁ›› የምትለኝ ነው፡፡ አመሰግናለሁ ጓዴ››
ሊዮኔል ሜሲ ‹‹ሁሌም እንደምናገረው ከጎንህ ሆኜ ብዙ ተምሬብሃለሁ፡፡ ዕድለኛ ሆኜ ጋር ብዙ ታሪኮችን አብሬህ በማሳለፌ እጅግ በጣም የምደሰትበት ልምድ ነው፡፡ ከኳስ ጋር ባለህ ተሰጥኦ ብቻ ሳይሆን በታላቅ ስብዕናህ አከብርሃለሁ፡፡ እግር ኳስን ብትሰናበትም ማንም ፈገግታህን ሊረሳው አይችልም፡፡ ሁሉም ምርጥ ይሁንልህ ሮኒ››፡፡
ኔይማር ‹‹ካንተ ጋር የተጋራኋቸው ታሪኮች ስለነበሩኝ እጅግ ክብርና ደስታ ይሰማኛል፡፡ የእግር ኳስ ጥበብ ላይየሰራሀውን ሁሉ ማንም አይስተካከለውም፡፡ ለስፖርቱ አፍቃሪዎች ላበረከትከው ሁሉ ምስጋና ይገባሃል፡፡››

Read 4740 times