Saturday, 20 January 2018 12:43

“አባታችን ማይምነት የተዋጉ ትልቅ አርበኛ ናቸው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

     • የተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ “የፊደል ገበታ” 100ኛ ዓመት ይከበራል
          • የነጠረ እውቀት ያለው ትወልድ ያጣነው፣ ቄስ ት/ቤት ስለቀረ ነው
          • ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ በስማቸው ቤተ መፃህፍት ሰይሟል
          • ህብረት ባንክም አንዱን ቅርንጫፉን በስማቸው ሊሰይም ነው

     በ1895 ዓ.ም ታህሳስ ወር ነው በቡልጋ የተወለዱት፡፡ ከዚያም በታዳጊነት እድሜያቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው የፊደል ገበታን ፈለሰፉ፡፡ “ለመላው ዓለም ምዕመናን የህይወት ምግብ አዘጋጅና አከፋፋይ” የሚል ማዕረግ የተቀዳጁት ተስፋ ገ/ሥላሴ ዘብሄረ ቡልጋ፤ ከ300 በላይ መፅሐፍትን በአማርኛና በግዕዝ ያዘጋጁ ትልቅ የሀገር ባለውለታ ናቸው። በ1992 ዓ.ም በ97 ዓመት ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ  በትጋትና በጥንካሬ ሲሰሩም ቆይተዋል፡፡ እነሆ በካርቶን ላይ በመቅረፅ የጀመሩት የፊደል ገበታም መቶኛ ዓመት በዓል  ሚያዚያ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ታውቋል፡፡ በዓሉ በምን ዝግጅቶች ሊከበር ታስቧል? የቄስ ት/ቤት በመቅረቱ ትውልዱ ምን ያጣው ነገር አለ? የተስፋ ገ/ሥላሴን ሥራዎች ለማስቀጠል ምን ታቅዷል?  
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ አባታቸው ከሞቱበት ጊዜ አንስቶ ለ17 ዓመታት የተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ማተሚያ ቤትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ከመሩት አምስተኛ ልጃቸው አቶ እንዳልካቸው ተስፋ ጋር በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-

   እስቲ ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ፣ እንዴትና ለምን ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ይንገሩን?
አባታችን በተወለዱበትና ባደጉበት ቀዬ አክርሚት፣ የሚካኤል ታቦትን በድቁና እያገለገለ ነው ያደገው፡፡ ከዚያ አዲስ አበባ ሄጄ ሥራ እሰራለሁ ብሎ፣ በባዶ እግሩ አምስት ቀን ተጉዞ፣ አዲስ አበባ ገባ፡፡ እዚህ በመጣ በዓመቱ፣ በ1910 ዓ.ም የፊደል ገበታን ፈለሰፈ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰራውን ተዓምር የምታውቁት ነው፡፡
ከእነማን ጋር ነበር የመጡት? መጥተውስ የት አረፉ? ፊደል ከመፈልሰፋቸው በፊትስ የነበረውን አንድ ዓመት እንዴት አሳለፉት?
እንግዲህ በ1909 ዓ.ም ጠቅልሎ ወደ አዲስ አበባ  ከመምጣቱ በፊት ቀደም ብሎ መጥቶ ነበር። በዛን ወቅት የዚያ አገር ነጋዴ፣ ግብር የሚከፍለው አዲስ አበባ እየመጣ ነበር፡፡ ግብር መክፈያ ወቅቱ ሲደርስና ነጋዴዎቹ እንደሚመጡ ሲያውቅ፣ ነጋዴዎቹን ከኋላ ከኋላ እየተከተለ፣ እነሱ ሳያዩት ሞጆ ይደርሳሉ፡፡ ሞጆ ሲደርሱ አዩት፡፡ ወደ ኋላ እንዳይመልሱት እንዴት ያድርጉ፣ ብቻውን ሊሆን ነው፡፡ ከዚያ ይዘውት አዲስ አበባ መጡ፡፡ አምስት ቀን ተጉዘው፣ ከነሱ ጋር አዲስ አበባ ገባ፡፡ ከዚያ በዛን ወቅት ቤተ መንግስት ውስጥ ጥሩ ሥራ የነበረው ታላቅ ወንድሙ ብርሃኔ ገ/ስላሴ ዘንድ ነው የመጣው፡፡ ታላቅ ወንድሙ ሲያየው፣ “እንዴት መጣህ? ለመሆኑስ እናትና አባታችን ሰምተዋል?” ብሎ በጥያቄ ያጣድፈዋል፡፡ “አልተናገርኩም” ይላል። “በል አሁን ገብተህ እረፍና አብረውህ ከመጡት ጋር ትመለሳለህ” ብሎ ያስገባዋል። ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ አገሩ ይመልሰዋል፡፡ በወቅቱ ልቡም አይኑም ወደ ኋላ እያየ፣ “እዚህማ ተመልሼ እመጣለሁ፣ የሚከለክለኝን አያለሁ” እያለ እየዛተ ነበር የተመለሰው፡፡ እንደዛተውም በ1909 ዓ.ም ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡
ከዚያስ---ታላቅ ወንድማቸው ምን አሉ?
ከዚያማ ታላቅ ወንድሙ፤ “በል እንግዲህ ልብህ አላረፈም፤ መልሼም አልሰድህም፡፡ አንድ ክፍል ቤት አለችኝ፤ እዛ እረፍና የምትፈልገውን ትሰራለህ” አለው፡፡ ከዚያ ሰው ላለማስቸገርና ራሱን ለመቻል ሲል ሱቅ በደረቴ ሆኖ ስራ ጀመረ፡፡
ሱቅ በደረቴ ሆነው ምን ነበር የሚሸጡት?
በወቅቱ ኩክ ማውጫ፣ መርፌ ቁልፍ፣ ምላጭ፣ መፋቂያና የመሳሰሉትን እያዞረ ይሸጥ ነበር፡፡ ከዚያም ወንድሙን ብድር ጠየቀ፡፡ በወቅቱ ከባድ ብድር ነበር የጠየቀው፡፡
 ከባድ ሲባል---- ምን ያህል?
75 ሳንቲም (በጣም ሳቅኩኝ) አትሳቂ! በወቅቱ ይሄ ገንዘብ ከባድ ሥራ ነበር የሚሰራው፡፡ ብድሩን የጠየቀው ንግድ ለመጀመር ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ ሳንቲም እንኳን አንድ ቤሳ ትባል ነበር፡፡ ብዙ ቁምነገር ነበራት፡፡ በዚያች 75 ሳንቲም በወቅቱ ታዋቂ የነበረ “ባለሁለት ወፍ” ሽቶ ይሸጥ ነበር፡፡ ይህ ሽቶ ከፈረንሳይ በጅቡቲ አድርጎ ነበር የሚመጣው። ወደ እዚህ አገር የሚያስመጡ ነጋዴዎችም ነበሩ። አባታችን ሽቶውን በ75 ሳንቲም ይገዛና፣ እሪ በከንቱ በዛን ጊዜ እንደ ደጃች ውቤ ቅልጥ ያለ ሰፈር ስለነበር፣ እዚያ ያሉ ሴቶች ጋር ይሄድና፣ “ሽቶ የሚገዛ አለ ሽቶ” ሲል፣ አንዷ ትወጣና እስኪ አምጣ ብላ ስታሸትተው ትወደዋለች፡፡ “ለመሆኑ ስንት ነው?” ስትለው፣ “አንድ ብር ከሃምሳ” ይላል፤ ትገዛዋለች፡፡ ይህንን ያዩ ሌሎች የሰፈሩ ሴቶች፤ “ለእኛም አምጣ” ሲሉት፣ በብር ከሀምሳው ሁለት ገዝቶ አምጥቶ፣ እንደገና ሶስት ብር ይሸጣል፤ እንደገና አራት ይገዛና ሸጦ፣ ያችን ገንዘብ ይይዝና መፅሐፍ ገዝቶ መሸጥ ይጀምራል፡፡ ያን ጊዜ ግዕዝም ሆነ አማርኛ ማንበብ መፃፍ፣ በቤተክህነትና በቤተ መንግስት የተገደበ እንጂ ሰፊው ህዝብ ጋር አልተዳረሰም ነበር፡፡ ስለዚህ ለሰዎች መፅሐፍ ቅዱስ በግዕዝም በአማርኛም ያነብላቸውና፣ “በሉ ግዙ፤ ይጠቅማችኋል” ሲላቸው፣ “አንተን አብረን ካልገዛን ማን ያነብልናል፤ ልጆቻችን አያውቁ እኛ አናነብ” ይሉት ነበር፡፡ ይህን ጊዜ ነው “እንዲህ ሰርቼ፣ እንዲህ ቢማሩ፣ በኋላ የተለያዩ መፅሀፎችን እያዘጋጀሁ እሸጣለሁ፤ እኔም እጠቀማለሁ፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ምንም ጥቅም አላገኝም” ብሎ እሩቅ አስቦ እነ ሀሁን፣ አቡጊዳን፣ መልዕክተ ዮሐንስን…በአጠቃላይ ከ300 በላይ የሀይማኖት መፅሐፍትን ለማዘጋጀትና ለማሳተም የበቃው፡፡
ማተሚያ ቤቱ የተቋቋመው መቼ ነበር?
በ1921 ዓ.ም ነው ማተሚያ ቤቱ የተቋቋመው፡፡ ከዚያ ጣሊያን ወሰደበት፤ እንደገና ጣሊያን ከወጣ በኋላ ማተሚያ ቤቱን ተረክቦ አጠናከረና ቀጠለ፡፡ እንግዲህ ከገጠር እንደመጣ፣ ወንድሙ ቤት አሁን ባዕለወልድ ያለበት ነበር፤ እዛው አረፈ፡፡ ከዚያ ስላሴ ይሰራል ለልማት ነው ተባለና ወደ ላይ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሄደ፡፡ እንደገና ቦታው ለልማት ተፈለገና፣ በመጨረሻ አሁን መሀል አራት ኪሎ ማተሚያ ቤቱ ያለበት ቦታ ላይ 7 ሺህ ካ.ሜ ቦታ ነበረው፡፡ ከዚያ ልማት ተብሎ የቤተሰባችን ቤት ሁሉ ፈርሶ፣ ስንት ነገር ተወጥቶ ተወርዶ፣ ማተሚያ ቤቱ ቅርስ ነው ተብሎ፣ የእኔ ቤትና ማተሚያ ቤቱ አሁን 2500 ካ.ሜ ቦታ ነው ያለው፡፡
አባትዎ ከሞቱ በኋላ ለ17 ዓመታት ማተሚያ ቤቱን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ በኋላ ግን ከአመራርነቱ ለቀቁ፡፡ በምን ምክንያት ነው የለቀቁት?
አባታችን ሀላፊነት አስረክቦኝ ነው ያለፈው። በዚያ መሰረት ስመራ ቆይቼ ከእህት ወንድሞቼ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ጉዳዩ እስከ ፍርድ ቤት ሄዶ፣ ተረታሁና ሃላፊነቴን አስረከብኩኝ። አሁን የሚመራው ታላቅ ወንድሜ ጋሽ ጥበቡ ተስፋ ገ/ስላሴ ነው፡፡ እኔም የአባቴ አደራ ተጠብቆ በመቀጠሉ ላይ ጥርጣሬ ስላለኝ፣ “የተስፋ ልጅ አታሚ አሳታሚ” የሚል የራሴን ከፍቼ፣ ሁሉም አይነት መፅሐፍት ይዘታቸውን ሳይለቁ፣ ጥራታቸው ተጠብቆ፣ በኦንላይን በውጭና በአገር ውስጥ ለማከፋፈል ህትመት ጀምሬያለሁ፡፡ በቀጣዩ ዓመትም በሙሉ አቅም በብዛት ወደ ህትመት እገባለሁ፡፡ የፈጣሪ ፈቃድ ይሁን፡፡
የፊደል ገበታ 100ኛ ዓመት በዓል አከባበር ምን ምን ዝግጅቶችን ያካትታል?
እንግዲህ አባታችን ማይምነትን የተዋጋ ትልቅ አርበኛ ነው፡፡ እስካሁን በስሙ ት/ቤት፣ አደባባይም ሆነ መንገድ አልተሰየመለትም፡፡ ለምን የሚለውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን፣ ትምህርት ሚኒስቴርን፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን፣ ቅርስ ጥናትና ባለስልጣንን… ጋብዘን እንጠይቃለን፡፡ እስከ ዛሬ በእሱ ዙሪያ ብዙ ዶክመንተሪዎች ተሰርተዋል። ሲኤንኤን ሳይቀር መጥቶ ሰርቷል፡፡ በርካታ ገጣሚያን ግጥሞች ገጥመውለታል፡፡ ወሰን ደበበ የተሰኘ ደራሲ “ዘመን ተሻጋሪ ባለውለታ” የተሰኘ መፅሐፍ ፅፎለታል፡፡ ድምፃዊ ፀሀዬ ዮሐንስ፣ ስሙን ባይጠቅስም ሥራውን አስመልክቶ ዘፍኖለታል፡፡
ተስፋ ገብረሥላሴ የ2008 ዓ.ም “የበጎ ሰው ሽልማት” አሸናፊ በነበሩ ጊዜ፣ እርስዎ በውክልና ሽልማቱን ሊወስዱ ወደ መድረክ ሲወጡ፣ ፀሀዬ ዮሐንስ “ማንበብና መፃፍ ዋናው ቁም ነገሩ” የሚለውን ዘፈን ድንገት ማቀንቀን ሲጀምር ምን አይነት ስሜት ነበር የተሰማዎት?
አዎ አስታወስሽኝ… በጣም ደስ የሚል ነበር። እሱና ቴዲ አፍሮ ትልልቅ የአገር ባለውለታዎችን አወዳሽ እንደመሆናቸው፣ ለአባታችን መታሰቢያ የሚሆን ሥራ እንዲሰሩ ለመጠየቅ አቅደናል፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ብዬ እንዳልኩት፤ ብዙ ዘጋቢ ፊልሞች የተሰሩለት ቢሆንም ከልጅነት እስከ ህልፈቱ ያሳለፈውን የሚያሳይ ፊቸር ፊልም የሚሰራ ሰው ብናገኝም ብለን አስበናል፡፡ ብዙ ያልተነገረለት ትልቅ አርበኛ ነውና፣ የሚመለከታቸው አካላት አንድ አደባባይ ወይ ሃውልት እንዲሰራለት እንዲያደርጉ በበዓሉ ወቅት  ለመመካከር አቅደናል፡፡ እርግጥ ነው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አዲስ የከፈተውን ቤተ-መፃህፍት  በአባታችን ስም ሰይሟል፤ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ህብረት ባንክም በ2009ኙ “የበጎ ሰው ሽልማት” ላይ በአምስት የአገር ባለውለታዎች ስም ቅርንጫፍ ይሰየማል ብሎ ቃል ከገባላቸው መካከል ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ይገኙበታል፡፡ ቃላቸውን ይጠብቃሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ፣ ምን ያህል ልጆችን አፍርተዋል?
13 ልጆችን ወልዷል፡፡ ሦስቱ በህይወት የሉም፤ አስራችን አለን፡፡ በህይወት እስከነበረበት ጊዜ ድረስ 42 የልጅ ልጆች አይቷል፡፡ አሁን ይሄ ቁጥር ጨምሯል፡፡ እኔ እንኳን እሱ ከሞተ በኋላ ሁለት ልጆች ወልጃለሁ፡፡ የልጅ ልጅ ልጅ ከ18 በላይ ናቸው፡፡ አሁን ቅምቅም አያት ሊሆን ነው፡፡
እናታችሁን ባለፈው ዓመት በ99 ዓመት እድሜያቸው እርስዎ ቤት አይቻቸው ነበር፡፡ አሁን እንዴት ናቸው?
በጣም ደህና ናት፡፡ አሁን 100 አመት ከ3 ወር ሆኗታል፤ ራሷን ችላ ትንቀሳቀሳለች፡፡ በእርግጥ እርዳታ ያስፈልጋታል፤ እየተቀያየሩ የሚያግዟትና የሚጠብቋት ሁለት ነርሶች አሏት፡፡ በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡
እርሳቸው እንግዲህ የፊደል ገበታን ሰርተው ብዙ ኢትዮጵያውያን ተምረውበታል፡፡ አሁን ይሄ የቄስ ትምህርት እየቀረ ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት እየተላኩ ነው፡፡ ቄስ ት/ቤት እየቀረ በመምጣቱ ትውልዱ ቀረበት የሚሉት ነገር አለ?
በጣም ወሳኙን ጥያቄ አንስተሻል፡፡ በእውነት እኛ ሁላችን 13ቱም ልጆች፣ እድሜያችን አራት አመት ከአራት ወር ከአራት ቀን ሲሞላ፣ ወደ ቄስ ት/ቤት ተልከናል፡፡ ዘመናዊ ት/ቤት ከአምስት ዓመት በኋላ ነበር የምንገባው፡፡ በወቅቱ ዘመናዊ ት/ቤት ግማሽ ቀን ስለነበር፣ ስንመለስ ቄስ ት/ቤት እንቀጥል ነበር። ከላይ ያነሳሽው ወሳኝ ጥያቄ፣ የቄስ ት/ቤት ጥቅም ምን ነበር? አሁን እየጠፋስ መምጣቱ ከትውልዱ ምን አጎደለ ነው አይደለም?
ትክክል!
እንግዲህ ይሄ ጎደሎ ሳይታለም የተፈታ ነው። የበፊት የመንግስት ሀላፊዎችና ባለስልጣናት እንዲሁም ሊቃውንት የምንላቸው መሰረታቸው ቄስ ት/ቤት ነው፡፡ ቄስ ት/ቤት ተምረው ወደ ዘመናዊ ት/ቤት የሚገቡ ልጆች በጣም ብሩህ ናቸው፡፡ አሁን የነጠረ እውቀት ያለው ትወልድ ያጣነው፣ ቄስ ት/ቤት ስለቀረ ነው፤ ይሄንን በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡ አሁን አባባና የኔታ በፋዘር ተቀይሯል፡፡ በየከተማው ያሉትን ሆቴሎች ስም ተመልከቺ፡፡ ጠቅላላ የፈረንጅ ነው፤ እከሌ እከሌ ማለት አያስፈልግም፡፡ አማርኛችንን በአጭሩ የትም ጥለነዋል፡፡ በመቶኛው አመት ክብረ በዓሉ ላይ በአፅንኦት የምናገርበት ዋናው ርዕስም ይሄው ጉዳይ ነው፡፡
የቄስ ት/ቤት መቀጠል አለበት ብለው የሚያምኑ ከሆነ፣ በበኩልዎ ምን ለማድረግ አስበዋል?
በጣም መቀጠል አለበት፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ አለ፤ ግን በጣም ተዳክሟል፡፡ እኔ እንደውም በስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካትቶ፣ ለሁሉም እንዲዳረስ ነው ህልሜ፡፡ ይህንን ለሚመለከተው ሁሉ እያነሳሁ አሳስባለሁ፡፡ በግሌ የአባቴ ስራዎችና መፅሀፎች፣ 300ውም እንዲቀጥሉ፣ አሁን ከድርሳነ ሚካኤል አንስቶ ማሳተም ጀምሬያለሁ፡፡ በዚሁ እቀጥላለሁ፡፡
ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ዘመናዊ ትምህርት ተምረዋል?
በፍፁም! አልተማረም፡፡ በራሱ ትግል ABCDን እየተንገዳገደ ነው የለመደው፡፡ ቋንቋም ቢሆን ከግዕዝና ከአማርኛ ውጭ አያውቅም፤ የተፈጥሮ ጂኒየስ ነው፡፡
ከአባትዎ የሚያስደምምዎት  ነገር ምንድን ነው?
አባቴ ለልጆቹ እንደ አባትም እንደ ወንድምም እንደ ጓደኛም ሆኖ መቅረብ መቻሉ ያስደምመኛል። ከዚያ ደግሞ ለስራው ያለው ፍቅርና ትጋት የሚገርም ነው፡፡ አብሬው በምሆንበትና አብረን በምንጓዝበት ጊዜ የሚመክረኝና የሚያስረዳኝ ሁሉ፣ አሁን የህይወት ስንቅ እንደሆነኝ  ገብቶኛል። ስለዚህ የእሱ ልጅ መሆን ያኮራል ያስደስታል፡፡ በ1986 ዓ.ም ጉብኝት ይዤው ልሄድ ትኬት ገዛሁ። ከዚያ አልሄድም አለኝ፡፡ እንዴት ለጉዞው ትኬት ቆርጬ፣ ኪሰራ ላይ ትጥለኛለህ ስለው፣ ደንገጥ አለና እንግዲያውስ እንሂድ አለኝ፡፡
የት የት ጎበኛችሁ?
ጉብኝቱ ከባህርዳርና ከጣና ገዳማት ተጀምሮ፣ ወደ ጎንደር ላሊበላና አክሱም የሚዘልቅ ነበር። ከዚያ ዘጌ ገዳማት፣ ውራ ኪዳነ ምህረት ገባን፡፡ “በሉ ክፈሉ” ብለው ቄሶቹ አስቸገሩ፡፡ “እንከፍላለን ምን ያስቸኩላል” አለና ገፋ አድርጓቸው ገባ። አንድ አብሮን የነበረ ሰው፤ “መፅሀፍ አላችሁ?” ብሎ ቄሶቹን ሲጠይቅ፣ “አዎ ይሄ ይሄ አለን” አሉ። “እስኪ አምጡት” አለ፤ አመጡ፡፡ ከዚያ ፎቶውን አዩና በጣም ደነገጡ፤ “እሳቸው ራሳቸው ናቸው” አሉ፡፡ ትከሻውን ሳሙት፡፡ ከዚያማ መስተንግዶው ቀለጠ፤ ስጋጃው ተነጠፈ፣ የአፄዎች እቃ ተደረደረ፤ ገለፃ ተደረገልን፡፡ ካሰብነው በላይ እዛ ቆይተን ብዙዎቹን ሳንጎበኝ ቀረን፤ ይሄን አልረሳውም፡፡ እኔ ገዳማቱን ብዙ ጊዜ ጉብኝቻቸዋለሁ፡፡ ዝም ብዬ ተጋፍቼ ጎብኝቼ፣ በአንዳንድ ቄሶችም እየተበሳጨሁ እመለስ ነበር፤ ከዚችኛይቱ ጉዞ በኋላ የአባቴ ገናናነት ታወቀኝ፡፡ ከዚህ ጉዞ በኋላ ታዲያ ከሰው ጋር ስተዋወቅ፤ እንዳልካቸው ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ብዬ ነው፤ ጥቅሙ ገብቶኛል እልሻለሁ፡፡

Read 2779 times