Saturday, 20 January 2018 12:45

የደበበ ሰይፉ የግጥም ቅፆች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(39 votes)

 ጥበብ ያጋተ ልብ ሲታለብ፤ የትውልድ መልክ፤ የዘመን ቁመናና ሚዛን፣ የሣቅና የለቅሶ ቀለም ይወጣዋል፡፡… የሀሣብ ጥንስሱ መነሻ የጉዞው ዐላማና ግብ ካርታ፣ የአስተሳሰቡና ፍልስፍናው ስሌት ከቁናው ላይ ይዘገናል፡፡
የብያኔው የራሱ ሰብዕና፣ ፍልስፍናና አተያይ፣ ከማህበረሰቡ ማንነት ቀለም ጋር ሲዋሃድ የሚፈጥረው ውበት፣ በየሰው አቅምና ልክ እየተጨለፈ ሲቀመስ እማኝነቱና ወሰኑ ይገመታል። ብዙ ጊዜ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍ፣ ብያኔውንና ተበያኒውን ይነካል፡፡ ያንዱን ህመም፤ ወዳንደኛው ያሥተጋባል፡፡ ያንዱን መዝሙር በሌላኛው አድማሥ ይቀበላል፡፡ የህይወት ጣዕምን ያመጣል፤ የህይወትን ትግል ያበርረዋል፡፡
ዛሬ ቀልቤ ያረፈባቸውን የታላቁ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ የግጥም ጥራዞችም ለዚህ ዐይነት ማንፀሪያ ይሆኑኝ ዘንድ በጥቂቱ ልናያቸው ወድጄአለሁ፡፡
የደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር” ቅፅ አንድ፣ ከ”የብርሃን ፍቅር ቅጽ 2 (ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ)” ጋር የሚገናኙበትም የሚለያዩበትም መንገድ፣ ግጥም የሚያፈቅርን፣ ሀሳብ የሚጎነጉንን ሰው ቀልብ ይነጥቁታል፡፡ ምናልባትም እንደ የልካቸው ይደመሙበታል፡፡ ሲጀመር ግጥም ወዳድነት መነሻው ጥልቀት ፈላጊነትና ሀሳብ አሣዳጅነት ይመሥለኛል፡፡ በዚህ መነሻነት ያየሁት የደበበ ሰይፉ የብርሃን ፍቅር ቅጽ አንድ፤ ከሁለተኛው የሚለይበት፤ የቅርጽና ይዘት፤ ልዩነቶች አሉት፡፡
ለምሣሌ ቅጽ አንድን ብናይ፣ በርካታ ተራኪ ግጥሞች አሉት፡፡ በዚህ ዘውግ ደግሞ የቋንቋ አጠቃቀሙ ያን ያህል ልቀት እንዲኖረው አይጠበቅም፤ ቀለል ባሉ ቃላት መተረክ ይቻላል። ይህን ዓይነት መልክ እንዲኖረው ያደረገው ደግሞ፤ ዘውጉ ተከታታይ ሁነቶችን መያዙ ሲሆን በታሪኩም ውስጥ ገፀ-ባህርያትና መቼት መኖራቸውም  ነው። ስለዚህ ባብዛኛው ታሪኩን ጠብቆ መሄዱ ላይ ያተኩራል፡፡
እስቲ ለማሣያ አንድ ግጥም እንመልከት፡-
ብርማይቱ ጨረቃ
የብርሃን ጠበል አፍልቃ
ተፈጥሮን ስትጠምቃት
እንደገና ስትወልዳት
ነፋሱ በቀስታ
በበረዶ እጁ ሲማታ፤
አዴ ላንቃም
ጦሩን ከጎኑ አጋድሞ
ያስተውላል እንደነገሩ
አሽቆልቁሎ ከስሩ
እንደዘበት
አፈርሳታ የቆመበቱን
የእንሰት
ጭስ ይጨሳል ዐልፎ ዐልፎ
ለአዴ ላንቃም
እየተዳፈነ ነው ቀቄሎ፤
በቅቤ የጠገበውን
ቡልኮውን
ገለጥ እንደማድረግ ብሎ
ሆዱን ሲያሻሸው
እንዲርበው
መልሶ ተወው
ብርድ ነከስ ቢያደርገው፡፡
ይህ ግጥም “አዴ ላንቃም” በሚል ርዕስ ከተጻፈ ላይ የተቀነጨበ ተራኪ ግጥም ነው፡፡ የሚያሣየንም አንድ የሲዳማ አባ ወራን ህይወት አካል ነው፡፡ ስለ ጎጆዎቹ፣ ስለ ሚስቶቹ፣ ሚስቶቹ ስለሚያዘጋጁለት ከቆጮ የሚሠራ ምግብ (ቀቄሎ) ነው የሚተርከው። ይህ ግጥም በጥቅሉ፤ የሲዳማን አባ ወራ አለባበስ፤ ምግብ አሠራር፤ መልከዐ ምድር፣ የአየር ንብረት ሁሉ ያሣያል፡፡ የሚተርከውም ስለ ሰውየው ወይም ስለ አካባቢው፣ አካላዊ ገፅታና ሕይወት ነው፡፡
በገጣሚው የዕድሜ እርከን ሥናየውም በወጣትነትና ጎልማሳነት አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ ቀልቡ ያረፈው በስነ-ሰብዐዊ፣ ማህበራዊና ሥነ-ተፈጥሯዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡
ከዚሁ ግጥም ጋር በቅርጽ ተመሳሳይ ከሆኑት ግጥሞች አንዱን ልጨምር፡- “እቴቴ” የሚለውን፡፡
ድሮ ነው ፊት
በልጅነቴ ሰዐት
ፍራፍሬ ከማወርድበት ቦታ
    መጥታ
ትጠራኝ ነበር ያች እቴቴ
    የጎረቤቴ፤
“ቡጠና፣ ወንዝ እንውረድ
ሸንኮራ ቆርጨልህ እንደትጎምድ…”
“እሺ እቴትዬ” ብዬ
ጣሳውን ከእጅዎ ተቀብዬ
እከተላታለሁ ወንዝ እቴቴን
እቴቴን- የጎረቤቴን፡፡
ውሃውን
ፀሐይዋ ስታፀኸየው
በወርቅ መርገፏ ስታጌጠው
እቴቴም
ጨርቋን ስታንጠፈጭፈው
ስታሽ ስትጠመዝዘው
ስትዘረጋ ስትቀለብሰው፤
ደሞም ስትዘፋፍነው
“የኔ ቤት እቆላ ያንተ ቤት አፋፍ
ልቤን አመጡልህ እየደጋገፉ”
ስትለው…ስትለው
ትንሹን ልቤን እንዴት ነበር ደስ የሚለው
ደስ የሚለው?
ግጥሙ ይቀጥላል፡፡ ገጸ ሰቡ “እቴቴ” የሚላት ሴት፤ ወንዝ ልብስ ልታጥብ ሄዳ፣ ሰውነቷን ስትታጠብ፣ ቡጡ (ገፀባህሪው) ሰው ሲመጣ እንዲያይላት ስታስጠብቀው፣ የሚሰማውን ስሜት ሁሉ ነው የሚነግረን፡፡ ስለ መቸቱ ለማወቅ ዝርዝር እንኳ ሳንፈልግ ሸንኮራውና ፍራፍሬ ማራገፉ፣ ወንዝ አጠባ መሄዱና “ቡጡ” የሚለው ስያሜ፣ ከገጣሚው ሌሎች ግጥሞች ጋር በማዛመድ ይርጋለም አካባቢ ወይም ሲዳማ ውስጥ መሆኑን እንረዳለን፡፡
ከላይ ከጠቀስኳቸው ሁለት ተራኪ ግጥሞች በተጨማሪ “ዳኢቴ”፣ “ያቺ ቆንጅት” እና ሌሎችም አሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ ግጥሞች ተራኪና የሰውን ልጅ ውጫዊ ማንነት የሚያሣዩ ናቸው፡፡ “ልጅቷ የዘመነችቱ” የሚለውም ግጥም ስለ አንዲት ዘመናዊ-ነኝ ባይ ሴት የሚያሣይ ይሁን እንጂ ዋናው ጉዳዩ ልብሷና ገላዋ ላይ ነው፡፡
ደበበ ሠይፉ በቅፅ አንድ ግጥሞቹ ትኩረቱ በወፍ በረር ይህን ይመሥላል፡፡ በኔ ፍተሻና ምልከታ የብርሃን ፍቅር ቅጽ 2 (ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ) ግን ከቅጽ አንድ በእጅጉ ይለያል፡፡ ቅፅ አንድ በቅርጹ ይለያል፡፡ ምክንያቱም በርከት ያሉ ግጥሞቹ በቅርጻዊ ፍረጃ ሲፈረጁ፣ ሌሪከ ወደሚባለው ዘውግ ያደሉ ናቸው፡፡ “ሌሪከ” ደግሞ በእጅጉ ውስጣዊ ሙዚቃ ነው፡፡ በርግጥም ሌሪከ ግጥም አጠር የሚል ሙዚቃ ላንቃውን የተነካው፤ ከመዝሙርና ከእንጉርጉሮ ጋር ዝምድና ያለው ነው፡፡ አጭር ስንል ግን እንደ ፈረንጆቹ “ሶኔት” በስንኞቹ ድንበር የተሰጠው አይደለም፡፡ በአብዛኛው ግን በፈጣን ስሜት የተወነጨፈ አጭር ነው፡፡ ባብዛኛው ግላዊም ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ታዲያ ደበበ ሰይፉ እኒህን ግጥሞች በሚፅፍበት ጊዜ በበሰለ የህይወት ድባብ ውስጥ ዘልቋል፡፡ ይሁንና ለጥበብ ሰው ብስለት ማለት ጥልቀት ነው። መሥረግ ነው፡፡ ባህር ላይ ከሚንሣፈፍ መርከብ ይልቅ ወደ ውስጥ የሚዘልቅ ሶቶማሪና አይነት ሆኗል፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ ግጥሞች የህይወትን- ውስጥ የሚፈትሹና ከተጨባጭ ሀሳብ ወደ ረቂቅ-ጉዳዮች የተሻገረበት ነው ማለት ያሥችላል፡፡ እጅጉን ሥነ-ልቡናዊነት ይንፀባረቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ … “ጠብቄሽ ነበረ” የሚለውን ግጥሙን እንይ፡-
መንፈሴን አጽድቼ
    ገላዬን አጥርቼ
አበባ አሳብቤ
    አዱኛ ሰብስቤ
    ጠብቄሽ ነበረ፤
ብትቀሪ ጊዜ፤
መንፈሴን አሳደፍኩ
ገላዬን አጎደፍኩ
አበባው ደረቀ
አዱኛው አለቀ፤
ስትቀሪ ጊዜ
የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞኝ ጠፋ፡፡
የተስፋ አበባ-የተስፋ ጥውላጌ-ጥፋት፡፡ ግጥሙ ለተቃራኒ ፆታ የተጻፈ ቢመስልም ማረጋገጫ የለውም፡፡ ምናልባት በእንስት ፆታ የምትጠራው “ኪነት”ም ልትሆን ትችላለች፡፡ ሕይወት ራሷም ብትሆን ማንም አይከለክላት! ግን- ደግሞ ተስፋ ውስጣዊ ነው፤ ስነ ልቡናዊ ነው፤ ረቂቅ ነው፡፡ አበባ የተስፋ ትዕምርት ነው፡፡ የተስፋ ተምሳሌት ነው፡፡ አዱኛ መኖሪያ ነው፡፡ መንፈስም ረቂቅ ነው፤ ንፁህ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግጥሙ ወደ ውስጥ የሚያይ ነው፡፡ ስለ መልክዐ ምድር፣ ስለ አካላዊ ውበት፣ የሚታይ ጥበብ አይደለም፡፡ በቅርጹም- ሌሪካዊ - ነው፡፡ በአሠኛኘትም በእጅጉ ጥንቃቄ የተሞላበት፤ የአርኬዎቹ ስደራም፤ የሀሳብ መሻገሪያ፤ የትንፋሽ መመለሻ እንዲኖረው ጥንቃቄ የተደረገለት ነው። ከአንዱ አርኬ ወደ ቀጣዩ መሸጋገሪያ ላይ የተተወው ቦታ፣ እንደ ዐውዱ ጊዜን አመላካች ሊሆን እንደሚችል አንባቢው ማስተዋል አለበት፡፡
 እስቲ ሌላ አጠር ያለች ግጥም ደግሞ እንመልከት፡፡ “ተይው እንተወው” የሚለውን፡-
ተይው እንተወው…
የዘመን ቃፊሩን ማለፍ አልቻልንም
ይህ ዓለም ጥበቱ አልመጠነንና፤
ተይው እንተወው፤…
ውጥኑ ግብ ይሁን
ጅማሬው ፍጻሜ፤
ቅጽበቷ ሙሉ ዕድሜሽ
ወቅቷ ዘላለሜ፡፡
በዚህ ግጥም ውስጥ ያለው ገፀባህሪ፣ የጊዜን ቀለበትና ተስፋ፤ በቅጽበት ውስጥ እንጠቅልለው የሚል ይመስላል፡፡ ዘመን በሚባለው ሰፊ ቅጥር ውስጥ መሠናከል የሆነ፤ ቃፊር የቆመ ነገር ክልከላ፣ በእንስት የምትጠራውን ሀሳብ ተቀባይ አላፈናፍን ብሏል፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ወገኖች ችግሩን በገቢር ሳይሆን በፍልስፍና ለሚጥፍ፣ በትርጉም ዝላይ ድል ሊነሱት ቋምጠዋል፡፡ ውጥኑን እንደ ግብ፤ ጅማሬውን እንደ ፍፃሜ፣ ጠባብዋን ቅፅበት፣ እንደ ዘመን-ውቅያኖስ ሊያደርጉት፤ እንጀራቸው ላይ ያፈሰሱትን ወጥ፤ በዘላለም መስክ ሊተረጉሙት ተሠልፈዋል፡፡
የደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር ቅጽ ሁለት” በነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ ጥልቅ ሀሳቦች፤ ረቂቅ ጉዳዮች፤ ሥነ-ልቡናዊ ደውሎች ተሞልተዋል፡፡ በግርድፉ እንዳየነው የደበበ ሰይፉ ሁለት የግጥም ጥራዞች፤ የአስተሳሰብ፣ የዕውቀትና የአተያይ ለውጥና ልቀት አምጥተዋል፡፡ ደበበ ሰይፉ ጊዜ በጨመረ ቁጥር፣ በንባብ በገፋው ልክ ከውጭ ወደ ውስጥ ማየት ጀምሯል፡፡ የሰውን ውጫዊ ማንነትና ገቢር ሳይሆን ውስጣዊ ጥዝጣዜና ህመም ለማዳመጥ የልቡ ጆሮዎች ተከፍተዋል፡፡ ምናልባትም ብዙ ቢጠኑ፣ ብዙ ምስጢርና ፍልስፍና የሚነበብባቸው፤… የስነ ግጥም ልቃቂቶች ናቸው፤ ቢባል አልተጋነነም፡፡

Read 21905 times