Saturday, 20 January 2018 12:52

ነገ በባህርዳር የሚካሄደው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ዝግጅት እየተጧጧፈ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 · ሳውንድ ኢንጅነሩ የዴሜይን ማርሌይ ሳውንድ ኢንጅነር ነው
          · የላይት ኢፌክት ባለሙያዎች ከደቡብ አፍሪካና ከእስራኤል መጥተዋል
          · ትኬቶቹ በህብረት ባንኮችና በንግድ ባንክ እየተሸጡ መሆኑ ታውቋል
          · የመደበኛ ትኬት ዋጋ 350 ብር፣ የቪአይፒ 1ሺ ብር ነው
            
   ነገ በባህርዳር እንደሚካሄድ በጉጉት የሚጠበቀው “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” የተሰኘው የዝነኛው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ኮንሰርት ዝግጅት እየተጧጧፈ  መሆኑን የአዘጋጁ ጆይ ፕላስ ኤቨንትስ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ  ቴዎድሮስ ክፍሌ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ የኮንርሰቱ ሳውንድ ኢንጅነር የቦብ ማርሌይ ልጅ የዴሜይን ማርሌይ ሳውንድ ኢንጂነር የሆነውና ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተቀዳጀው ኬት ግራምፕ ሲሆን ላይት ኢፌክቱን የሚሰሩት ባለሙያዎች ከደቡብ አፍሪካና ከእስራኤል መምጣታቸውን አቶ ቴዎድሮስ  ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“በተፈጠረው የጊዜ እጥረት እንጂ መድረኩን በተለየ መልኩ ለመስራት አቅደን ነበር” ያሉት የጆይ ፕላስ ኤቨንትስ ሥራ አስኪያጅ፤እንዲያም ሆኖ በተቻለ መጠን መድረኩን ለየት ለማድረግ የቴክኒክ እቃዎች ከውጭ መግባታቸውንና ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ ስታዲየሙን ተረክበው በ“ሚኪዛየን ኢንተርቴይመንት” አማካኝነት ግንባታ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡   
የኮንሰርት መግቢያ ትኬቶቹ በአዲስ አበባ በተመረጡ የህብረት ባንክ ቅርንጫፎች ማለትም፡- በጣይቱ ሆቴል ቅርንጫፍ፣ በመርካቶ ጣና የገበያ አዳራሽ ቅርንጫፍ፣ በሂልተን ሆቴል ቅርንጫፍ፣ ወሎ ሰፈር በርታ ተባበር ቅርንጫፍና ኤድናሞል አጠገብ በሚገኘው ቦሌ መድሀኒያለም ቅርንጫፍ በኤፕላስ ኤቨንትስ ወኪልነት እየተሸጡ ሲሆን በባህርዳርም በህብረት ባንኮች በጥሩ ሁኔታ እየተሸጡ መሆኑንና ከረቡዕ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በንግድ ባንክ መሸጥ መጀመሩም ታውቋል፡፡
አጠቃላይ የማስተባበሩ ሥራ ለባህርዳር ወጣቶች መሰጠቱንና የመጨናነቅና ሌሎች ችግሮች እንዳይፈጠሩ ወጣቶቹ ጠንክረው ለመስራት መስማማታቸውን አቶ ቴዎድሮስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ለሽያጭ ምን ያህል ትኬቶች ተዘጋጅተዋል በሚል ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ለጊዜው ቁጥሩን ለመግለፅ እቸገራለሁ” በማለት የትኬቱን ብዛት ከመግለፅ የተቆጠቡት አቶ ቴዎድሮስ፤መደበኛ ትኬቶች በ350 ብር፣ ቪአይፒው በ1 ሺ ብር በጥሩ ሁኔታ በመሸጥ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በነገው ዕለት ከአቡጊዳ ባንዱ ጋር ተቀናጅቶ፣ የተሳካና አድናቂዎቹ የሚደሰቱበት ታሪካዊ ስራ እንደሚሰራ የጆይ ፕላስ ኤቨንት ሥራ አስኪያጅ ጽኑ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡  

Read 1288 times