Print this page
Saturday, 20 January 2018 12:54

የከተራ ምሽት - (ምናባዊ ወግ)

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

     ከጥምቀተ ባህር ከተመለስኩ በኋላ ቀልቤ ብዙም አልተሰበሰበም፡፡ የጎረቤታችን የአቶ መኮንን ድምፅ ውስጤ እያስተጋባ፣ ድምፃቸው ነፍሴን እያመሳቀላት አምሽቼ፣ እራቴን በላሁና ተኛሁ። አቶ መኮንን እስክስታቸው ሁሌም ይገርመኛል፤ ትከሻቸው ንቅል ብሎ የሚሄድ ነው የሚመስለው። በያመቱ ጥምቀት ሲመጣ ከጎረቤት ቀበሌዎች ሳይቀር ብዙዎች፣ የእርሳቸውን ዘፈን ለመስማትና በእስክስታቸው ለመደመም ይመጣሉ፡፡ እርሳቸው የሌሉበት ጥምቀት አይደምቅም፡፡
ዛሬም እንደዚያው ነበር፡፡ ትንሽ ሀዘን ቢጤ ቢታይባቸውም እንደ ወትሮው ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ባለቤታቸውም በእልልታቸው ለበዓሉ ጣዕምና ድምቀት በመስጠት ይታወቃሉ፡፡
መንደራችን ክብ ሰርተው በተቀለሱ ጎጆዎች የደመቀች ናት፡፡ ደመራ የምናበራው፣ ችቦ የምንለኩሰው እዚያች ክብ መስክ ላይ ነው፡፡ ቀን ቀን፣ ዳር ዳሩ እንቦሳዎች ይታሰራሉ፡፡ አንዳንዴም ላሞች ይሰማራሉ፡፡  ብዙ ጊዜ ግን እንደ ሸንጎም፣ እንደ መናፈሻም ያገለግለናል፡፡
እንቅልፍ አልወስድ ብሎ አስቸግሮኛል፡፡ በእዝነ ልቡናዬ የጥምቀቱ ዜማ እየፈሰሰ፣ የሚሰማኝን ስሜት ቀይሮታል፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ ቡሬዋ ላማችንና ወይፈኑ ልጅዋ ሲያመነዥጉ ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ ይላል፡፡ ቤቱ ቀዝቅዟል፡፡ እናቴና ታላቅ ወንድሜ ያንኳራፋሉ፡፡ ወንድሜ ሁሌ እንደተኛ ነው፡፡ በላ ጠጣ፣መተኛት ነው፡፡ ህይወቱ ከዚህች ቀለበት አታልፍም፡፡ ጥያቄ የለው ..ህልም የለው… መኝታ ብቻ!
እናቴ ባልዋን ሆስፒታል አስተኝታ፣ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ውስጥ ናት፡፡ የእንጀራ አባታችን ሁካታና ቁንጥጫ በመታመሙ ሳቢያ ጋብ ባይል ኖሮ፣ መከራችን ሳይብስ አይቀርም ነበር፡፡ ሆኖም  ወንድሜ ታፈሰ ደንታ የለውም፡፡ እንጀራ አባታችን አድርግ ያለውን ሁሉ ያደርጋል፤ ይበላል፣ ይጠጣል። በቃ! የህይወት ድንበሩ እዚያ ድረስ ነው ለእሱ! … ለእርሱ አምላኩ እግዜርም ሰይጣንም አይደሉም፤ ሆዱ ነው!
አልጋዬ ላይ ተገላበጥኩ፤እንቅልፍ የለም፡፡ በራችን ድንገት ተንኳኳ፡፡ ያ ጠማማ ጓደኛዬ መሆን አለበት፡፡ አሸብር! እንደ ጅብ ሲሄድ የሚያድርበት ቀን አለ፡፡ በተለይ የፋሲካ ምሽትና ጥምቀት ሌሊቱን ሙሉ አይተኛም፡፡ ለነገሩ እኔስ መች ተኛሁ፡፡
በራችን በድጋሚ  ተንኳኳ!
“እናንት እንቅልፋሞች! … እስከመቼ ትተኛላችሁ? … አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሳ!” ብሏል ወንጌሉ፡፡
አሸብር እንዳልሆነ ወዲያው ገባኝ፡፡ እሱማ የወንጌል ቃል ከየት አባቱ አምጥቶ?!  
አቶ መኮንን የላኩት ሰው መሆን አለበት፡፡ ምሳሌያዊ ንግግር የሚችሉት እርሳቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡  ግን እሳቸው ደግሞ እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ? ሰካራም ነው እንዳልል አንደበቱ ጥርት ያለና የሰከነ  ነው፡፡ “ታቦቱ ውጭ እያደረ … እናንተ ትተኛላችሁ?” ያለኝ መሰለኝ፤ ልቤ፡፡ ኦርዮንን ለማስገደል፣ ንጉስ ዳዊት ያሴረውን ሴራ ያከሸፈው በዚህ ቃል ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ታቦት ውጭ እያደረ፣ እኔ ቤት ገብቼ ከሚስቴ ጋር አልተኛም ብሎ፡፡ ወቀሳ ቢመስለኝም ችላ አልኩት፡፡  
እናቴ ቅዠት ውስጥ ነበረች፡፡ ስለ ባልዋ መሰለኝ የምትቃዠው፡፡ ፍታኝ … ፍታኝ አልፈልግም በቃኝ! … የኔና ያንተ ነገር ይበቃል፡፡ አትለወጥም፣ ዞሮ ያው ነህ! …
“እንዴነሽ ገዳዎ … አሃሃይ ገዳዎ!” ሌላ የጠጣ ሰው ድምጽ ነው፡፡ ጥምቀት ስለሆነ የተለመደ ነው ብዬ ዝም አልኩ፡፡
“ሀገሯ ያ- ው- ና! ይታያልና!”
“ሀገሯ ምንጃር - የጤፍ ሀገር!”
አሁንም የቅድሙ ድምፅ በድጋሚ ወደ ጆሮዬ መጣ፤ “ታቦታችሁን ትነጠቃላችሁ! …ዋ! … እንቅልፋሞች…”
ይህ ድምፅ በየቤቱ ደጋግሞ ተዳረሰ፡፡ ወጥቼ ማየት ፈልጌ ነበር፤ግን  ፈራሁ፡፡ ጥምቀት በኛ ሰፈር ጦሰኛ በዓል ነው፡፡ ደም ይበዛዋል፤ አመፅ አያጣውም፡፡ ነፍሴን ሰሰትኳት፡፡ ሰማያት ብትቃትትም፣ “እረፊ፣ ፈሪ ለእናቱ” ብዬ ጆሮዋን መዘለኩት፤ በሃሳቤ፡፡ ሳቀች፡፡ “ቂል! ዝም ብለህ ተኛ! .. ዋጋህን ታገኛለህ!” ያለችኝ መሰለኝ፡፡
የጎረቤቶቻችን ፍየሎች በያቅጣጫው ይጮሃሉ። ምን አይነት ግራ የሚያጋባ ጥምቀት ነው? … እንዴት ያለ ጥምቀት ነው? … ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ፣ በመጥምቁ ዮሐንስ ሲጠመቅ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደበት እንጂ መዓት አልወረደበት፡፡ … እኛ ጋ ነገሩ እንዴት ነው፡፡ ጎረቤቱ ሁሉ ጫጫታ! እናቴ ባልዋን ሆስፒታል አስተኝታ ትቃዣለች! እግዚዮ መሃረነ ክርስቶስ!
የቀኑን የልጃገረዶች ድምፅ፣ በእልልታ አጀብ ላዳምጥ ሞከርኩ፡፡
አለው አለው ብር ዋንጫ፣ አለው ብር ዋንጫ
የመድህኔ መጠጫ አለው ብር ዋንጫ!
በእልልታ ሲታጀብ ይጥማል፡፡ የወንዶች ጎርናና ድምፅ! ---እንዴ ነው ገዳዎ፣ አሃሃይ ገዳዎ! ላባቸው ጠብ ጠብ ሲል ታየኝና ተገላበጥኩ፡፡ በዚህ መሀል እናቴ እንደ መባነን አለችና ኩራዟን ለኮሰች። ግድግዳው ቀይ፣ ላሚቷ ቀይ፤ ወይፈኑ ቀይ፣ ጣሪያው ሁሉ ቀይ ሆኗል፡፡ የንጋት ጎህ መስሎ፣ ያጓጓል፡፡ በቀዳዳ ተመለከትኳት፡፡
እኔ ከተሜ ነኝ፡፡ በኮረንቲ  ከተቀጠለችው ሀዋሳ ከተማ ነው የሄድኩት፡፡ ወንድሜ ደግሞ ዝዋይ ነው። እናቴ እዚያው ገጠሯ፣ የገበሬዎች መንደር ነዋሪ ናት፡፡
የተኩስ ድምፅ ሰማሁ፡፡ እናቴ ግን መልሳ ተኝታለች፡፡
የረሳሁት ድምፅ የበለጠ አስበረገገኝ፡፡ ከከብቶቹ ግርግም ግንዱ ላይ ከሰፈሩት ዶሮዎች አንዱ ጮኸ። እንደ አዲስ አስደነገጠኝ፡፡ ሀገር ሁሉ ተኝቶ እኔ እንዳፈጠጥኩ ሊነጋ ነው፡፡ ነግቶ ከሰዎች ጋር ለመቀላቀል ቸኩዬአለሁ፡፡ እስከዚያው ግን ለብቻ መቃተት፣ ለብቻ ማልቀስ! …. ገጣሚው እንዳለው፤ “ካ’ለም ተለይቶ መተኛት”---  ወይ መቃተት!
የአቶ መኮንን ድምፅ አንዳንዴ በምሽት ላይ ይሰማ ነበር፡፡ ዛሬ ግን የለም፡፡ የተኮሱት እርሳቸው ይሆኑ? … ጥሎባቸው ጠመንጃ ይወዳሉ፡፡ ዘፈን ይወዳሉ፡፡ ጠጅም ይወድዳሉ፡፡ ጢማቸውን አስረዝመው እየፈተሉ፣ የሚያወሩት ታሪክ ልብ ያፈስሳል፡፡
እናቴና ወንድሜ ያንኳርፋሉ፡፡
አሁን ተኩሱ ቀለጠ፡፡ ጩኸቱም ቀለጠ፡፡ … የአቶ መኮንን ድምጽ ተሰማ፤”… የታባቱ! ተኩላ .. የተኩላ ልጅ! …ሟርተኛ!”
“ምንድነው? … ምንድነው?” ጎረቤቱ ሁሉ ይንጫጫል፡፡ እናቴ ባልዋን ሆስፒታል አስተኝታ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ እንቅልፏን ትለጥጣለች። ልቀሰቅሳት ሞከርኩ፡፡ ግን መች ትሰማለች! … ሲቀሰቅሷት መልሳ በመተኛት የታወቀች ናት። ጎረቤቱ ሁሉ እናቴን “ገፊ!” እያለ ያሳቅቃታል፡፡ ባልዎችዋን የገፋች፣ ልጆችዋን የቀበረች ይሏታል፡፡ እኛ ግን ይህንን ሁሉ ረስተናል፡፡ ወንድሜ ታፈሰም  ለሆዱ፣ እኔም ለነገ እንኖራለን፡፡
ጩኸቱ በረድ ሲል፤ “…ይህ ሁሉ ጩኸት ታቦታችንን ለመንጠቅ ነው፡፡” አሉ አቶ መኮንን፡፡ ይህን አባባል ከየት እንዳመጡት፣ ለምን እንደሚሉት አይገባኝም ግን ያዘወትሩታል፡፡
በአባ ነፍሶ ባልቻ መንደር እሳቸው የንጉስ ያህል ክብር አላቸው፡፡ በላንፍሮ፣ ታሪክ፣ ስማቸው በተንጣለለው ሃይቅ ውሃ፣ እንደ ቀለም ቢፃፍ የሚከፋው የለም፡፡ የእናቴ ባል፣ የእንጀራ አባቴ ብቻ ነው፣ ይህን የማይወደው፡፡ ታሪክ ሲባል፣ ያመዋል፡፡ እስካሁን እናታችን ካገባቻቸው ባሎች እንደዚህኛው ዱላ የሚወድ፣ ሳቅ የሚጠላ የለም፡፡ አቶ መኮንንና መሰሎቻቸውንም አይወዳቸውም፡፡
ሲነጋ የዕድሩ ጥሩንባ ነፊ፣ ሀገሩን ነቀነቀው፡፡ አሳዛኝ ጥምቀት ሆነ አልኩ በልቤ፡፡ በተኩሱ የሞተ ሰው አለ ማለት ነው? ማን ሊሆን ይችላል? ….
የላንፍሮ ቀበሌ ነዋሪዎች ሁሉ፤ ዛሬ ምሽት በተከሰተው ያልታሰበ ችግር ላይ ለመነጋገር ሁላችሁም በክብዋ መስክ እንድትገኙ፡፡ ከካህናት ዲያቆናት በቀር ሁሉም ሰው ተገናኝቶ እንዲነጋገር ተብሏል፡፡----
“አደጋ ቢፈጠርም፣ ሰው አልሞተም!” ብዬ አሰብኩ፡፡ አሁን እናቴም ዐይኗን ጠራረገች፤ ወንድሜም ተነሳ፡፡ እኔም ልብሴን ለባብሼ ጓደኛዬን ፍለጋ ወጣሁ፡፡ ታደሰ ዐይኖቹ የድልህ ኳስ መስለዋል፡፡ ፊቱ ተዘበራርቋል፡፡ ከወሊሶ የመጣው ከኔ ቀደም ብሎ ነበር፡፡ ሁለተኛ ደረጃ አብረን ተምረናል፡፡
“ምን ሆነሃል?” አልኩት፡፡
“ዝም ብዬ ነው፡፡”
“የማታው ስድብ ምንድነው?”
“እንቅልፍ የከለከለኝ እርሱ ነው፡፡ ማን እንደተሳደበ ታውቋል፡፡ አቶ መኮንን አሳድደው ተኩሰውበት ነበር፡፡ ግን አልተመታም፡፡ እንዲያውም ካህናቱንና ምዕመኑን አስደንግጠዋል፣ ተብለው ተወቅሰዋል፡፡”
ነገሩ እንዳልገባኝ ነገርኩት፡፡
“ያንን ሁሉ በየሰው በር አንገትዋን አሰግጋ ያወራችው ቀበሮ ናት፡፡”
“አሁንም አልገባኝም---” አልኩት፡፡
“ቀበሮ  አታውቅም፤ በጎችን አድና የምትበላው ቀበሮ! እርሷ ናት የተሳደበችው፡፡ እናንተ በጎቻችሁን በሙሉ አርዳችሁ የጨረሳችሁ አረመኔዎች! … ለሰው ሞት አነሰው! … ነበር ያለችው፡፡”
ባይገባኝም ዝም ብዬ አደመጥኩት፡፡ “ለመሆኑ ቀበሮ ከመቼ ወዲህ ነው ለበግ ተከራካሪ የሆነው?”
“እንግዲህ እርሱ ነው ምስጢሩ! … አሳዛኙ ነገር ግን፣ በዚህ ጥምቀት አቶ መኮንን አለፉ!”
ክው ልኩ፡፡ “ቀበሮዋን ሲያባርሩ ከኋላ ተተኮሰባቸው፡፡ … ቀበሮ ሲባል ግን ቀበሮ ስጋ የለበሰው እንዳይመስልህ፤ እዚህ አካባቢ እንደ ዓምላክ የሚቆጠረው መንፈስ ማለቴ ነው፡፡”
ጥሩንባ ነፊው፣ አሁንም ጥሩንባ ነፋ፡፡
አሁን ሁሉም ሰው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ሄዶ፣ ታቦቱን ማጀብ ይኖርበታል፡፡
ልጃገረዶች፤ “አለው አለው ብር ዋንጫ--” ማለት ጀመሩ፡፡ የብዙ ሰው ስሜት ግን ቀዝቅዟል። ቀበሮ የሰደበው ህዝብ! ….

Read 1272 times