Monday, 22 January 2018 00:00

የዚምባቡዌ ስደተኞች አዲሱን መሪያቸውን ለማየት 16 ዶላር ክፈሉ ተብለዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በናሚቢያ የሚገኙ ስደተኛ ዚምባቡዌያውያን ከሰሞኑ አገሪቱን የጎበኙትን አዲሱን ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋን በአካል በአይነስጋ ለማየት የሚችሉት 16 ዶላር ከከፈሉ ብቻ እንደሆነ ከኤምባሲያቸው በተላለፈላቸው መመሪያ ክፉኛ መቆጣታቸው ተዘግቧል፡፡
የበጀት እጥረት የገጠመው በናሚቢያ የሚገኘው የዚምባቡዌ ኤምባሲ፣ ሙጋቤን ተክተው ወደ ስልጣን የወጡትን የፕሬዚዳንት ምናንጋግዋን ጉብኝት እንደ አንድ የገቢ ማግኛ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ በናሚቢያ የሚገኙ ዜጎቹንና ድሃ ናሚቢያውያንን ፕሬዚዳንቱን በቅርበት ለማየት 16 ዶላር ክፈሉ ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኤምባሲው በአንድ ሆቴል ውስጥ 300 ሰዎችን የሚይዝ አዳራሽ በመከራየት ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ በቦታው ተገኝተው ከፍለው ለሚገቡ ዚምባቡዌያውያን ንግግር ያደረጉበትን ፕሮግራም ያዘጋጀ ሲሆን፣ ከፍለው የታደሙ የመኖራቸውን ያህል እንዴት መሪያችንን እንደ ቱሪስት መስህብ ከፍለን እናያለን በሚል ቁጣቸውን የገለጹም ነበሩ ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን ደህና ገቢ ያላቸው ስደተኛ ዚምባቡዌያውያን ቀደም ብለው ትኬት ቆርጠው፣ መሪያቸውን ለማየት በሆቴሉ ቢታደሙም፣ ገና አዳራሹ ሳይሞላ የጥበቃ ሰራተኞች ከፍለው ለመግባት የተዘጋጁትንና ከውጭ ቆመው ይቃወሙ የነበሩትን ሰዎች ማባረራቸውንና ይህም ቁጣን መቀስቀሱን ዘገባው አስረድቷል፡፡

Read 2612 times