Sunday, 28 January 2018 00:00

የጄፍ ቤዞስ ሃብት በ1 ቀን በ2.8 ቢ. ዶላር ጨምሯል፤ የአለማችን ከፍተኛው ሃብት ባለቤት ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   የተጣራ ሃብታቸው 113.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል
   የታዋቂው አማዞን ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ሃብት፣ ባለፈው ማክሰኞ ብቻ በ2.8 ቢሊዮን ዶላር መጨመሩን ተከትሎ፣ ግለሰቡ በአለማችን ታሪክ እጅግ ከፍተኛውን የሃብት መጠን ያካበቱ ቁጥር አንድ ባለጸጋ መሆናቸውን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
ጄፍ ቤዞስ፤ አማዞን ጎ የተባለውን አዲስ ቅርንጫፍ በሲያትል ባለፈው ማክሰኞ መክፈታቸውን ተከትሎ፣ የኩባንያቸው የአክስዮን ድርሻ መጠን በ2.5 በመቶ ማደጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህም የግለሰቡ የሃብት መጠን በ2.8 ቢሊዮን ዶላር በመጨመር 113.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቷል፡፡
ከአማዞን በተጨማሪ የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ባለቤት የሆኑት ባለሃብቱ፤ በአሁኑ ሰዓት ያካበቱት የ113.5 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት መጠን በታሪክ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን የጠቆመው ዘገባው፣ ቢል ጌትስ በ92.5 ቢሊዮን ዶላር፣ ዋረን በፌት በ92.3 ቢሊዮን ዶላር የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘው እንደሚከተሉ ገልጧል፡፡
ከኩባዊ ስደተኛ አባትና ከአሜሪካዊት እናት የተወለዱት ጄፍ ቤዞስ፣ በርካታ ኩባንያዎችን በመክፈት ትርፋማ ቢዝነስ ላይ መሰማራታቸውንና ከአጠቃላዩ ሃብታቸው 16 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው በቴክኖሎጂ የታገዘ የሽያጭ ስራ በሚያከናውነው አማዞን ኩባንያ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለሃብቱ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ በስፋት እንደተሰማሩና በቅርቡም ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መርጃ የሚውል የ33 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ልገሳ ማድረጋቸውን አስታውሷል፡፡


Read 2402 times