Print this page
Monday, 29 January 2018 00:00

የ2018 ኦስካር ዕጩዎች ይፋ ተደርገዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ለ90ኛ ጊዜ የሚካሄደው የ2018 የኦስካር ሽልማት ዕጩዎች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ 13 ጊዜ ለሽልማት የታጨው ዘ ሼፕ ኦፍ ዋተር፣ በአመቱ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን የያዘ ፊልም ሆኗል፡፡
የሮማንቲክ ሳይንስ ፊክሽን ዘውግ ያለው ዘ ሼፕ ኦፍ ዋተር፣ በዘንድሮው የኦስካር ሽልማት በብዛት በመታጨት ታሪክ ቢሰራም፣ በኦስካር ታሪክ 14 ጊዜ በመታጨት ክብረወሰኑን ከያዙት ታይታኒክ፣ ኦል አባውት ኢቭ እና ላላ ላንድ ተርታ በመሰለፍ ሌላ ታሪክ መስራቱ ለጥቂት ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
በ24 የተለያዩ ዘርፎች ዕጩዎች በቀረቡበት በዘንድሮው ኦስካር፣ በብዛት በመታጨት የሚመራው በስምንት ዘርፎች የታጨው ዳንኪርክ ሲሆን፣ ስሪ ቢልቦርድስ አውትሳይድ ኢቢንግ ሚሱሪ በ7፣ ፋንተም ትሬድ በ6 ይከተላሉ፡፡ የ22 አመቱ የፊልም ተዋናይ ቲሞቲ ቻላሜት፣ በኦስካር ታሪክ በለጋ እድሜው ለምርጥ ወንድ ተዋናይነት በመታጨት የሶስተኛነት ደረጃን መያዙን ያስታወቀው ተቋሙ፣ ሁለቱን ደረጃዎች የያዙት ጃኪ ኩፐር የተባለው የ9 አመት ታዳጊና ሚኪ ሩኒ የተባለው የ19 ወጣት መሆናቸውን አስታውሷል፡፡
ኦል ዘ መኒ ኢን ዘወርልድ በሚለው ፊልሙ በምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፍ ለሽልማት የታጨው የ88 አመቱ የፊልም ተዋናይ ክሪስቶፈር ፕላመር፣ ረጅም እድሜ የገፋ የኦስካር ዕጩ በመሆን በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
በብዛት በታጨው ዘ ሼፕ ኦፍ ዋተር ላይ የምትተውነው ኦክታቪያ ስፔንሰር፣ ለሶስት ጊዜ ለኦስካር ሽልማት በመታጨት ቀዳሚዋ ጥቁር ሴት ተዋናይት የሚለውን ማዕረግ ከቪዮላ ዳቪስ ጋር ተጋርታለች፡፡ ዴንዘል ዋሽንግተን በበኩሉ፤ ስምንት ጊዜ በመታጨት ቀዳሚው ጥቁር የፊልም ተዋናይ በመሆን ታሪክ ሰርቷል፡፡ ሁለቱም ጥቁር ተዋንያን በብዛት በመታጨት ብቻ ሳይሆን፣ በተከታታይ አመታት ለዕጩነት በመቅረብም ታሪክ መስረታቸው ተነግሯል፡፡የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት አሸናፊዎች የሽልማት አሰጣጥ ስነ-ስርዓት፣ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ በደማቅ ሁኔታ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 2235 times
Administrator

Latest from Administrator