Saturday, 27 January 2018 11:35

“መለያየት ሞት ነው” እየተሸጠ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(9 votes)

 የጋዜጠኛና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ “መለያየት ሞት ነው” የተሰኘ ኢ-ልቦለድ መፅሐፍ እየተሸጠ ሲሆን የመጀመርያው 5 ሺህ ኮፒ ዕትም በሳምንት ውስጥ በመገባደዱ፣ሁለተኛው ዕትም ሰሞኑን ለገበያ  ይቀርባል ተብሏል፡፡ መጽሐፉ ፖለቲካ፣ማህበራዊና ጥበብ በሚሉ ሦስት ርዕሶች ተከፋፍሎ ነው የተዘጋጀው፡፡ የመጽሐፉን አብዛኛውን ክፍል የያዘው ፖለቲካ ሲሆን በርካታ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ህጸጾች በድፍረት ተነቅሰዋል፡፡ በ200 ገጾች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ ዋጋው 61 ብር ነው፡፡ አለማየሁ ከዚህ ቀደም፤ “ቅበላ”፣ “የስብሀት ገ/እግአብሔር ህይወትና ክህሎት”፣ “ኢህአዴግን እከስሳለሁ”፣ “የብርሃን ፈለጎች”፣ “ወሪሳ”፣ “አጥቢያ”፣ “ኩርቢት”፣ “መልከአ ስብሃት” እና “በፍቅር ስም” የተሰኙትን ጨምሮ በአጠቃላይ 11 መጻህፍት ለአንባቢያን አድርሷል፡፡  
 “እነ ዲያስፖራ ነውራችሁን ፋቁት!” በሚል ርዕስ ከተከተበው ፖለቲካዊ ሂስ ጥቂት መስመሮች እነሆ፡-”--የዚህ ዘመን ስደት ጭራውን የቋጠረው ከአብዮቱ ጅማሬ ጋር ነው፡፡ የርዕዮተ ዓለም ሽንፈት የአጼ ኃይለሥላሴ ዘመንተኞችን እንዲሰደዱ አስገደደ፡፡ የአብዮት ዘመን ንትርክ በጥይት ምላሽ ማግኘት ሲጀምር፣ እልቂት ያሰጋቸው ስደትን ምርጫ እንዲያደርጉ ግድ አላቸው፡፡ የፖለቲካ መቻቻል ውሃ ሲበላውና አንድ ዓይነት “ዩኒፎርም” መልበስ፣በደርግ ያለአማራጭ ሲቀርብ፣ሁኔታውን መለወጥ የተሳናቸው ስደት ግዴታቸው ሆነ---ዮፍታሄ እንዳለው፤ከእነዚህ ጋር ሁሉ ሀገር ተሰደደች፡፡ እንደ ፋሺስት ኢጣልያ ሁሉ ደርግም፣ ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ እንጂ፣ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ማስወጣት ተስኖት ቆየ፡፡---” (“መለያየት ሞት ነው”፤ ገጽ 82)

Read 7185 times