Sunday, 28 January 2018 00:00

ዘርዓያዕቆብ - የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ጠንሳሽ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(7 votes)

  ክፍል ፪ - ዓለማዊነት፣ የግለሰብ ነፃነትና የሐሳብ ብዝሃነት በዘርዓያዕቆብ ውስጥ
                   (ይህ ፅሁፍ በምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን አዘጋጅነት “ዋኖቻችንን እናስብ” በሚል ዓላማ ጥር 1፣ 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብን ለመዘከር በተዘጋጀው መድረክ ላይ የቀረበ ፅሁፍ ነው)

    17ኛው ክ/ዘ ላይ በዘርዓያዕቆብ የተጀመረው የኢትዮጵያ ፍልስፍና እርስበርስ የተቆላለፉ ሁለት ዓላማዎች ነበሩት፡፡ አንደኛው ለዕድገት እንቅፋት የሆኑ ባህሎችን፣ ልማዶችንና አስተሳሰቦችን መተቸት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያን የማዘመን ሐሳብ ነው፡፡ ምንም እንኳ የዘመናዊነት ሐሳብ የተጀመረው በአውሮፓ ቢሆንም፣ ዘመናዊነትን ከአውሮፓዊነት ጋር ብቻ ማስተካከል ግን ስህተት ነው፡፡ “ምክንያቱም፣ የሥልጣኔ መንፈስ የሰው ልጅ ብልሃትና ዕውቀት ወዳለበት ይነፍሳል። የሥልጣኔ ሐብታት ከሰው የህሊና ጥረት የሚገኙ ስለሆኑ በየትም ቢወለዱ ዘመዳሞች ናቸውና” (ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ 2003፣ ገፅ 78)፡፡
ለመሆኑ ዘመናዊነት ምንድን ነው?
በአሁኑ ወቅት በጣም በአስገራሚ ሁኔታ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህራንና ተማሪዎች ውስጥ ዋነኛ የመወያያና የጥናትና ምርምር አጀንዳ ሆኖ እየወጣ ያለው ሐሳብ “የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት” ጉዳይ ነው፡፡ ይሄም የሆነበት ምክንያት የተማሪዎች ንቅናቄ የመጨረሻ ዙር የሆነው ኢህአዴግ ያመጣው የህዳሴና የዘመናዊነት ፕሮጀክት ባለመሳካቱና፣ የድህረ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ከወዲሁ ህዝቦቿን ወደፊት የምታራምድበት አዲስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት የፍለጋ መንፈስ ላይ በመሆኗ ነው፡፡ ምናልባት ይህ መንፈስ የፍልስፍና መምህራኖችና ተማሪዎች ላይ ሳይወርድ አይቀርም፡፡ (ተጨማሪ ሐሳብ በክፍል ፩ ፅሁፌ ላይ ያገኛሉ፡፡)
ዘመናዊነት ከድሮው (ከመካከለኛው ዘመን) ልማድና አስተሳሰብ መነጠል ነው፤ ተነጥሎም ህይወትን በዕውቀትና በአመክንዮ መዘወር ነው። ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ “ከአህያና ከበቅሎ ፍጥነት ሳንወጣ ምን ያህል ዘመናት አለፈን?”  እያሉ የተቆጩትም ሆነ፣ ወልደ ሕይወት “ሥራን ትግል አታድርገው፤ ይልቅስ አዳዲስ ፈጠራዎችን እየጨመርክበት ድካምህን ቀንስ! ትርፋማነትህንም አሳድግ!” እያለ የፃፈው የድሮውን ኋላ ቀር አሰራር መተው እንዳለብን ለማመላከት ነው፡፡
“ዘመናዊነት ከድሮው አሰራር፣ ልማድና አስተሳሰብ መነጠል ነው” በሚለው ትርጉም ከሄድን፣ የዘመናዊነት ፅንሰ ሐሳብ የተጀመረው አዳም ዕፀ በለሷን ከበላበት ወቅት ጀምሮ ነው ልንል እንችላለን፡፡ “ምክንያቱም…” ይላሉ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር እጓለ፣
“ምክንያቱም ይሄንን ሐሳብ በነፃ ህሊና ለመረዳት ከሞከርን፣ ሰው በስጦታ ወይም በችሮታ በሚገኘው ድሎት የማይደሰት መሆኑንና ከገነት ለመውጣት የደፈረውም ከራሱ ዕውቀት በሚገኘው ጉልበት ራሱን ለማስተዳደር ነው” (ገፅ 35)፡፡
አዳም ዕፀ በለሷን በመብላቱ ከበፊቱ ልማድና አስተሳሰብ ለመነጠል መወሰኑን ያስገነዝበናል። ሆኖም ግን አዳም ህይወቱን ከራሱ ጥረት በሚያመነጨው ብልሃትና ነፃ ፈቃድ ለመምራት የሚያስችል የንቃተ ህሊና ከፍታ ላይ ገና ስላልደረሰ ደፍሮ በአመፁ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ በመሆኑም ወዲያው አመፁን በፀፀት ሻረው፤ ያን ጊዜ የአዳም የዘመናዊነት ፍላጎት ተቀለበሰ፡፡
ሆኖም ግን ከአዳም አመፅ የምንረዳው ነገር ቢኖር የሰው ልጅ በራሱ ጥረት በሚያመነጨው እውቀትና ነፃ ፈቃድ ብቻ ህይወቱን የመምራት ተፈጥሯዊ ፍላጎት እንዳለው ነው፡፡ ይሄም ፍላጎት የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሆነ ዘመንና ቦታ ላይ መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ዘመን አውሮፓ ላይ 15ኛው ክ/ዘ ላይ ሲከሰት፣ ኢትዮጵያ ላይ ደግሞ (ሰፊ መሰረት ባይኖረውም) በ17ኛው ክ/ዘ ላይ ተከስቷል - በዘርዓያዕቆብ፡፡
የምዕራባውያኑ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ከአመፅ (በድሮው ላይ ከማመፅ) ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይሄም የሆነበት ምክንያት የመካከለኛው ዘመን ላይ (እነሱ “የጨለማው ዘመን” ይሉታል) የተንሰራፋው እምነቶቻቸውና ልማዶቻቸው የሰውን ልጅ ውስጣዊ ኃይልና ችሎታ በማኮሰስ አጠቃላይ ህይወቱ በውጫዊ ኃይሎች (በእግዚአብሔርና በተፈጥሮ) ችሮታ ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን ስላደረገው ነው። ይሄ አገላለፅ እኛ ኢትዮጵያውያንንም ይመለከታል፡፡
በመሆኑም፣ ዘመናዊነት በምዕራቡ ዓለም፣ በድሮው ላይ ማመፅ፣ ከድሮው ልማድ፣ አሰራርና አስተሳሰብ መነጠል ነው፡፡ የምስራቁ ዓለም ዘመናዊነት ግን ምናልባት ከምዕራቡ የተለየ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም፣ የምስራቁ ዓለም ፍልስፍናና መንፈሳዊ አስተምህሮ ከሰው ልጅ ውስጣዊ ኃይልና ፀጥታ ጋር የተገናኘ ስለሆነ፣ ለምሳሌ ስለ ጥሞና (Meditation) እና ስለ ሰው ልጅ ስቃይ ያላቸው አረዳድ ከውጫዊ ኃይሎች ጋር የተገናኘ ስላልሆነ፣ የእነሱ ዘመናዊነት ከአመፅ ጋር የተገኛኘ ላይሆን ይችላል፡፡
ምንም እንኳ፣ የምዕራቡ ዓለም ዘመናዊነት በዋነኛነት ከድሮው ልማድና አስተሳሰብ መነጠል ነው ብንልም፣ ከድሮው ወደ አሁኑ የሚተላለፉ አስተሳሰቦችና እሴቶች በጭራሽ የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ የ20ኛው ክ/ዘ ፈረንሳዊው ፈላስፋና ሶሲዮሎጂስት Emile Durkheim “false beliefs cannot survive” ይላል - ሐሰትና ድንቁርና የሐሳብ ዝግመተ ለውጥንና ዘመናትን ሊሻገሩ እንደማይችሉ ሲያመላክት፡፡ ይሄም ማለት ከድሮው ወደ አሁኑ ዘመን የሚተላለፉት እውነት ላይ የተመሰረቱ አስተሳሰቦችና እምነቶች ብቻ ናቸው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ በዘመናዊነት ውስጥ ከድሮው የሚነጠለው እውነትነት ከሌላቸው ልማዶቹና አስተሳሰቦቹ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ዘመናዊነት የእውነትነት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው ዘርዓያዐዕቆብ እውነትን ከሐሰተኛ ልማዶችና አስተሳሰቦች አንጥሮ ለማውጣት ያደረገው ጥረት በኢትዮጵያ ውስጥ የዘመናዊነት ጠንሳሽ ያስብለዋል።
ሆኖም ግን፣ ዘመናዊነት የእውነትነት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ይልቅስ ከኃይል ጋራም የተሳሰረ ነገር አለው እንጂ፡፡ ምክንያቱም፣ ዘመናዊነት እውነትን ከሐሰተኛ ልማዶችና እምነቶች ነጥሎ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ የሰውን ልጅ ከውጫዊ ኃይሎች ቀንበር ነፃ ማውጣት ጭምር ነውና። የሰው ልጅ ይሄንን ማድረግ የሚችለው ደግሞ ህይወቱን ከውስጡ በሚወጣ ችሎታና ነፃ ፈቃድ ለመምራት የሚያስችል የንቃተ ህሊና ከፍታ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት፤ ግለሰብን የመጨረሻው የእውቀትና የእውነት ዳኛ በማድረግ፣ የሰው ልጅ ኑሮውን በውስጣዊ ኃይሉ ላይ እንዲያደርግ ወትውተዋል፡፡
በመሆኑም፣ ዘመናዊነት - የሰውን ልጅ በህይወቱና በአካባቢው ላይ ባለ ሙሉ ሥልጣን ሆኖ የሚከሰትበት ዘመን ነው፡፡ አዳም ያንን ሙከራውን በፀፀት ቀለበሰው፡፡ የሰው ልጅ በአመፁ ዳግም ላይፀፀት ከድሮው ልማድና አስተሳሰብ መነጠል የጀመረው በ15ኛው ክ/ዘ የህዳሴ ዘመን ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያም፣ የሀገራችንን ማህበረሰብ ለዕድገት አላላውስ ያለው ልማድና አስተሳሰብ ላይ የመጀመሪያውን አመፅ ያካሄደው ዘርዓያዕቆብ ነው።
የሰው ልጅ በኑሮውና በአካባቢው ላይ ባለ ሙሉ ሥልጣን ሲሆን ደግሞ መጀመሪያ የሚያደርገው ነገር በስጋውና በነፍሱ፣ በመንፈሳዊና በዓለማዊ ህይወቱ መካከል ያለውን ቅራኔ መፍታት ነው፡፡ ለዚህም ነው ከዘመናዊነት መርሆዎች ውስጥ ዋነኛው ዓለማዊነት (Secular life) የሆነው፡፡ Leo Strauss የተባለ የፖለቲካ ፈላስፋ ዘመናዊነትን ሲተረጉም Modernity is the secularization of faith ይለዋል - የሃይማኖትን ዓለማዊ ይዘቱን መጨመር ወይም መንፈሳዊና ዓለማዊ ህይወትን ማስታረቅ እንደ ማለት ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብም ለኢትዮጵያ ህዝብ ይዞት የመጣው አዲስ ፕሮጀክት ነፍስና ስጋ፣ መንፈሳዊና ዓለማዊ ህይወት፣ አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት የሚታረቁበት ኦሪጅናል ፕሮጀክት ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በምንኩስና ባህል የተነሳ ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ከስጋውና ከዓለም ተጣልቶ እንዲኖር ተደርጓልና፡፡ ወልደ ሕይወትም ሥጋችንን በአመጋገብ፣ በአለባበስ፣ የሚያምር መጠለያ በመስጠትና የወሲብ ፍትወቱንም በማርካት ልንንከባከበው እንደሚገባን በግልፅ ፅፏል፡፡
በርካታ ፈላስፎችና የስነ ሰብዕ ምሁራን የተስማሙበት ነገር ቢኖር፣ ዘመናዊነት ሦስት መርሆዎች እንዳሉት ነው  - ዓለማዊነት፣ የግለሰብ ነፃነትና የሐሳብ ብዝሃነት፡፡ እነዚህን ሦስት የዘመናዊነት መርሆዎች የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና ውስጥ ስለምናገኛቸው ነው የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ፅንሰት ከዘርዓያዕቆብ ጋር የምናስተሳስረው፡፡ ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ ግን ይሄንን ፅንሰት ከዘርዓያዕቆብም አርቀው ወደ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን (15ኛው ክ/ዘ) ይወስዱታል፡፡ ሆኖም ግን ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን በመንፈሳዊና በዓለማዊ ህይወት መካከል ያለው ተቃርኖ ይበልጥ እንዲካረር የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ እነሱን የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት መነሻ ማድረግ ስህተት ነው፡፡
የሐሳብ ብዝሃነት
“ዓለማዊነትና የግለሰብ ነፃነት” ከሚለው መርህ አንፃር እንዴት ዘርዓያዕቆብ የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት መነሻ ሊሆን እንደሚችል ከላይ ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ “የሐሳብ ብዝሃነት” ከሚለው ሦስተኛው የዘመናዊነት መርህ አንፃር ዘርዓያዕቆብንና ወልደ ሕይወትን እንመልከታቸው።
ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ “The Challenges of the New Millennium: Renaissance or Reappraisal?” በሚለው መጣጥፋቸው ላይ ሁለቱን ዘርዓያዕቆቦች ያነፃፅሯቸዋል - ንጉሱንና ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብን፡፡ ፕ/ሩ ሁለቱን ዘርዓያዕቆቦች የመረጡበት ምክንያት የሐሳብ ልዩነትን በተመለከተ በኢትዮጵያ የምሁራን ታሪክ ውስጥ ያለውን ተቃርኖ ፅንፍ የሚወክሉ በመሆናቸው ነው፡፡
በዚህም፣ ንጉሱ ዘርዓያዕቆብ በጣም ሊቅ፣ ሀገር አቅኝና አዋኻጅ ቢሆንም ሃይማኖትን በተመለከተ ግን ልዩነትን (ብዝሃነትን) የማይፈቅድ፣ የማይታገስና እጅግ ጭካኔ የተሞላባቸውን እርምጃዎች የወሰደ ንጉስ ነው፡፡ በአንፃሩ፣ ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ምሁራዊ ሰብዕናው የሃይማኖትና የአስተሳሰብ ልዩነትን እስከማበረታታት ድረስ የሚሄድ ነው፡፡ የዘርዓያዕቆብ ተማሪ ወልደ ሕይወት በሐተታው ምዕራፍ ስድስት ላይ በግልፅ፤“ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል መብት አለው” በማለት ከዘመናዊነት መርሆዎች ውስጥ አንደኛው የሆነውን “የሐሳብ ብዝሃነት” ደግፎ ፅፏል፡፡
ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት በዚህ መልኩ ስለ ሐሳብ ብዝሃነት ቢከራከሩም፣ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ በ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ እስኪመጣ ድረስ ግን ይሄንን የፈላስፎቻችንን ሐሳብ ያስተጋባ አንድም ምሁር አላገኘንም፡፡
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት የተፀነሰው በ17ኛው ክ/ዘ ላይ በዘርዓያዕቆብና በወልደ ሕይወት ቢሆንም፣ ዋነኛ መገለጫው ግን “ተቆራራጭነቱ” (Discontinuity) ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት በ17ኛው ክ/ዘ ያነሷቸው የዘመናዊነት ሐሳቦች ለ250 ዓመታት ደብዛቸው ከጠፋ በኋላ በድጋሚ የተነሱት በ20ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ እንደነ ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/እየሱስ፣ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝና በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ተ/ማርያም ባሉ ምሁራን ነው፡፡
ሆኖም ግን የሐሳብ ብዝሃነት የሚለው የዘመናዊነት መርህ ላይ ስላልሰራን፣ በአፄ ዮሐንስ ዘመን ብዙ ሰብዓዊ ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ በ1966ቱ አብዮት ማግስት ደግሞ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር በሚል ጎራ አንድ ሙሉ ትውልድ አጥተናል፡፡ ይህ መርህ አሁን ድረስ ሊዋኻደን ስላልቻለ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማፍረስ፣ እንዲሁም ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የማሰሩንና የማስፈራራቱን መንገድ አጠናክረን ይዘነዋል፡፡ ወልደ ሕይወት ፊውዳላዊውን የገባር ሥርዓት “በሰው ላብ ላይ የተንጠለጠለ ሌባና ቀማኛ” በማለት የተቸበት መንገድ ወዲያው ተቀባይ ምሁራንን ቢያገኝ ኖሮ፣ የ1966ቱን የመሬት ላራሹ አብዮት ማስቀረት ይቻል ነበር፡፡
ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ፤ “የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ያዋለደው የ1966ቱ የተማሪዎች ንቅናቄ ነው” ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና የዶክትሬት ተማሪ የሆነው አቶ አሞን በቀለ ግን በዚህ የፕ/ር አንድርያስ ሐሳብ አይስማማም፡፡ እንደ አቶ አሞን አመለካከት፤እንዲያውም የተማሪዎች ንቅናቄ የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት የተከዳበትና የተጨናገፈበት ወቅት ነው፡፡ የተማሪዎቹን ንቅናቄ ተከትሎ፣ በሀገሪቱ ምሁራን ላይ የተንሰራፋውን የታሪክና የብሄር ጭቅጭቅ እንዲሁም የአንፃራዊነት ሐሳብ ገዥ ሆኖ መውጣት ስንመለከት፣ በ17ኛው ክ/ዘ ላይ የተጀመረው የዘመናዊነት ፕሮጀክታችን ሳይጠናቀቅ፣ የተማሪዎች ንቅናቄ ኢትዮጵያን ወደ ድህረ ዘመናዊነት (Postmodernism) ንትርክ እንድትገባ አድርጓታል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የተማሪዎች ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ያዋለደ ነው ከሚለው ሐሳብ ይልቅ ያጨናገፈ ነው የሚለው ሐሳብ ሚዛን ይደፋል፡፡
ባጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት በተቆራራጭነቱ የተነሳ የአፄ ቴዎድሮስ ርዕይ እንዳይሳካ፣ የኢትዮጵያውያን ኑሮም እንዳይሻሻልና በስተመጨረሻም በአብዮት ምስቅልቅላችን እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- (ጸሃፊው፤በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ነው፡፡)


Read 1184 times