Sunday, 28 January 2018 00:00

አገሬን እንደምወዳት የማውቀው፤ ስትሳሳት ደፍሬ መናገር በመቻሌ ነው

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

     በርዕሱ የተነሳውን ሐሳብ ሙሉ የሚያደርግ ሌላ ሐሳብ መጨመር ይኖርብኛል፡፡ ‹‹አገሬን እንደምወዳት የማውቀው፤ ስትሳሳት ደፍሬ መናገር በመቻሌ ነው›› ብያለሁ፡፡ እርሷ ደግሞ እኔን እንደምትወደኝ የማውቀው፤ ስህተት የመሰለኝን ነገር በድፍረት የመናገር መብቴን ስታከብርልኝ ነው፡፡ እንደምትወደኝ የማውቀው፤ ሐሳቤን አክብራ - ዘክራ፣ በአንክሮ አዳምጣ መልስ ስትሰጠኝ ነው፡፡ ሐሳቤን በትዕግስት የማስተናገድ ደግነት ስታሳየኝ ነው፡፡ ሐሳቤን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ስታከብርልኝ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ሐገሬ ትወደኛለች እላለሁ፡፡ ሆኖም እርሷ ባትወደኝም እኔ መውደዴን እቀጥላለሁ፡፡ ሐገሬን በእውነት እወዳታለሁ፡፡
ፍቅር፤ የስሜት ዕዳ ስለሆነ እኔ መውደዴን እቀጥላለሁ፡፡ እርሷ ባትወደኝ እንኳን፤ እኔ ሐገሬን እወዳታለሁ፡፡ በአባት - በእናቶቼ፤ በእልፍ አእላፍ ሰማዕታት ወገኖቼ ደም፣ በነጻነት ጸንታና ታፍራ የኖረችው ሐገሬ ብትጠላኝ እንኳን፤ እኔ እወዳታለሁ፡፡ እርሷ ባትወደኝ እንኳን፤ እምነቷን በጥርሴ አንጠልጥዬ ይዤ፤ ፍቅሬን በጉያዬ ሸሽጌ፤ በ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት›› ዜማ ሙሾ አውርጄ፤ እንባዬን ከጉንጮቼ አብሼ፤ ስለፍቅሯ እኖራለሁ እንጂ ስለጠላችኝ አልጠላትም፡፡
ተከብረሽ የኖርሽው፣ በአባቶቻችን ደም፤ (2)
እናት ኢትዮጵያ፣ የደፈረሽ ይውደም (2) እያልኩ፤ ቀን ቀርቶ ሌት ዘብ እቆምላታለሁ፤ እንቅርቴ እስኪፈርጥ - ወገቤ እስኪጎብጥ ስለ ደህንነቷ እሰራለሁ፡፡ ልፋቴን ከውለታ ሳልቆጥር፤ ቀለብ ሥፈሪልኝ፤ ደመወዝ ቁረጭልኝ ሳልል አገለግላታለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ከራሴ አብልጬ እወዳታለሁ፡፡ እኔ ሐገሬን በጣም እንደምወዳት የማውቀው፤ እርሷ እየጠላችኝ እኔ ስወዳት ነው፡፡ ሐገሬ ስትሳሳት ደፍሬ ስህተቷን በመናገሬ ነው፡፡  
እስኪ ወገኖቼ፤ አንድ ጊዜ ዝም በሉ!
የሐገር ጥፋት ቅመም ሲወቀጥ ትሰማላችሁ፡፡ ምርኳችሁን የሚቀማ አውሬ ሲያገሳና መሬቱን ሲጎደፍር ትመለከታላችሁ፡፡ አንዴ ዝም ካላችሁ፤ የሞት ደጆች ሲከፈቱ ትሰማላችሁ፡፡ ሐገርን የሚያፈርስ፣ እናቶችን ከል የሚያለብስ፣ አባቶችን የሚያስለቅስ፤ የጥፋት አውሬ ሲያደባ ታያላችሁ፡፡ የህጻናትን የጨዋታ ድምጽ፣ የልጆችን ድሱት ዜማ የሚያፍን፤ የሰላምን ርግቦችን ከቀዬ የሚያሰድድ፤ የፍቅር ጎጆአችንን አመድ የሚያደርግ እና ግር ብሎ የሚነድድ እሣት ሲጫርና ሲንቀለቀል ታያላችሁ፡፡ ዕድር፣ ዕቁብ፣ ደቦ፣ ጅጌ፣ ወንፈሉን የሚያፈራርስ፤ እንደ ደራሽ ጎርፍ እየጋለበ ህብረትን ጠራርጎ የሚወስድ፤ ሐገር አውዳሚ ክፉ አውሬ እመር ሲል - ሲምዘገዘግ ታስተውላላችሁ፡፡ ጥንብ አንሣው በሰማይ ሲያንዣብብና ሲያኮበኩብ፤ መንቆሩን አሹሎ፤ ሰላማችንን ሊዘርፍ ቁልቁል ሲወረወር በዓይነ ህሊናችሁ ታያላችሁ፡፡
እስኪ አንደዜ ዝም በሉ!
ዝም በሉ፡፡ ጸጥ በሉ፡፡ ልብ በሉ፡፡ ልብ ብላችሁ አስተውሉ፡፡ ብዙ የተሳሳቱ ነገሮች አሉ፡፡ ይህች ሐገር ወዴት እየሄደች ነው? በዚህ ጽሑፍ ሐገሬ የተሳሳተችውን ነገር ደፍሬ እነግራታለሁ፡፡ እንዲህ እንደ አሁኑ በድፍን ሐገሩ ስሜት ቁጣ ሲነግስ፤ ህሊና ለመሆን የሚሞክር ሰው ቃል፣ ኮሶ ነው፤ አይወደድም፡፡ ደጋግመን በታሪክ እንዳየነው፤ ስሜትናቦታ ሲይዙ፤ የማስተዋል ልሳን ይሸበባል፡፡ የእውነት አንደበት ይዘጋል፡፡
ሐገሬ፤ ብሶት በወለደው ስሜት ታፍናለች፡፡ አሁን ህሊና የሚሆናት ሰው ትፈልጋለች፡፡ እንዲህ ባለው የጨነቀ ጊዜ ሽማግሌ አጥታ ስትቸገር፤ እርሷ ከሽማግሌ ባትጥፈኝም - አባት አድርጋ ባትቆጥረኝም፤ የአባት እና የሽማግሌ ድምጽ ሆኜ፤ ስህተቷን በመናገር ልጋፈጣት እፈልጋለሁ፡፡
እስኪ አንደዜ ዝም በሉ!
የምናገረውን ነገር አትደግፉትም ይሆናል፡፡ ግን ሐገሬን ወደ ውድቀት ሲገፉ ከማያቸው በርካታ ስህተቶች መካከል አደገኛ ውጤት ያላቸውን ሁለቱ ስህተቶችን ብቻ እጠቅሳለሁ፡፡ ደፍሬ እናገራለሁ፡፡ እንደ ዳኛ ከስሜቴ ይልቅ ለአዕምሮዬ በማድላት እናገራለሁ፡፡ ሁለት ስህተቶችን አነሳለሁ፡፡ እነዚህን ሁለት ስህተቶች ለመግለጽ በመሞከሬ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች ቅርይላቸው ይሆናል፡፡ ሆኖም ሐገሬ ስትሳሳት እያየሁ ዝም በማለት ከማገኘው ጊዜአዊ ሰላም ይልቅ፤ በመናገሬ የሚመጣውን ነቀፌታ መቀበል እመርጣለሁ፡፡ ‹‹አገሬን እንደምወዳት የማውቀው፤ ስትሳሳት ደፍሬ መናገር በመቻሌ ነው›› ያልኩት ለዚህ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በመልካም አስተዳደር ችግር፤ በብልሹ መንግስታዊ አገልግሎትና በጸረ ዴሞክራሲያዊ አያያዝ በደል እንደ ደረሰበት አውቃለሁ፡፡ እንደተበደለ እና እንደተማረረም እገነዘባለሁ፡፡ በዚህ ከጎኑ እቆማለሁ፡፡ ሆኖም በደሉ እና ምሬቱ በሚፈጥርበት ቁጣ ተነሳስቶ፣ የተሳሳተ መንገድ ሲከተል መሳሳቱን ደፍሬ እናገራለሁ፡፡
በመጀመሪያ፤ ‹‹በዚህ ስርዓት የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ ሆኗል፤ የትግራይ ህዝብ የበላይነት ሰፍኗል›› ብሎ የሚያስብ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ መኖሩ ይሰማኛል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊትን ህዝባዊነት የመጠራጠር እና ‹‹አግአዚ›› በሚል የሚጠራ የሠራዊቱ ክፍል (በእውነት ይኑር አይኑር እርግጠኛ አይደለሁም) ህዝብን ለይቶ ለማጥቃትና ለመግደል የተሠለፈ ኃይል አድርጎ የማቅረብ ዝንባሌ መኖሩን አያለሁ፡፡ ስለሆነም ህዝብን ከህዝብ የመነጠልና በአጠቃላይ የሠራዊቱን መልክ የሚያጠፋ አስተሳሰብ እየተጠናከረ መሆኑን የሚያመለክቱ ነገሮች ተበራክተዋል፡፡ ሁለቱም አስተሳሰቦች የተሳሳቱና በጣም አደገኛ ውጤት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ አንደኛው የማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ይከተናል፡፡ ሁለተኛው፤ የሠራዊታችንን የህዝብ ድጋፍና ተቀባይነት በመሸርሸር ለቀውስ ያጋልጠናል፡፡ ሁለቱም አንድ ላይ ተደምረው ለውጭ ኃይል ተጋላጭ ያደርጉናል፡፡ በዙሪያችን በአንድ ጀንበር ጠፍተን ብናድር የሚመኙ ብቻ ሳይሆን፤ ጎርፍ ቢወስደን ምራቃቸውን እንትፍ ብለው መጨመር የሚፈልጉ፤ ጥፋታችንን ለማጣደፍ እንቅልፍ አጥተው ሲሰሩ የሚያድሩ ወገኖች አሉ፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ቀውስና ግጭት ርቆት በማያውቀው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ  ተቀጣጣይ የሆኑ ኩነቶች እየተከማቹበት፣ በቋፍ ያለ እና በእሣት አጠገብ የተከመረ ጭድ ሆኖ የቆመ ክፍለ አህጉር ሆኗል፡፡ ይህ ክፍለ አህጉር ይበልጡን በእኛ በኢትዮጵያውያን የሰላም ዋልታነት ተደግፎ የቆመ እንጂ በራሱ ያለ ቀጣና አይደለም፡፡ የተከበብነው እንደ መንግስት የመቆም አቅም አጥተው በሚቸገሩ ሐገራት ነው፡፡ በምሥራቅ፤ ለሃያ ዓመታት ከወደቀችበት መነሳት ያቃታትና በየዕለቱ በአሸባሪዎች ቦምብ እየተቃጠለች የምታጣጥረው ሶማሊያ ናት፡፡ በደቡብ ምዕራብ ለአስርት ዓመታት እንደኛው በእርስ በእርስ ጦርነት ስትጠበስ ከርማ በመጨረሻ ነጻነት አግኝታ መንግስት መመስረት ብትችልም፤ ሁለት ዓመታት እንኳን ፋታ ሳታገኝ፤ መልሳ አውዳሚ ከሆነ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የተዘፈቀችው ደቡብ ሱዳን ናት፡፡ በሰሜን ተስፋ የራቃትና በሻዕቢያ ተቀስፋ በሞት እና በህይወት መካከል የቆመችው ኤርትራ ናት፡፡ በደቡብ ሁሌም በጎሣ ግጭትና ብልጭ ድርግም በሚል የፖለቲካ ቀውስ የምታቃስተው ኬንያ ናት፡፡
በአጭሩ፤ በዚህ የፈራረሰና የበርካታ ኃይሎች መራኮቻ በሆነ አካባቢ፤ በትርምስ ውቂያኖስ ውስጥ የምትገኝ የሰላም ደሴት መስላ የምትታየው፤ በሁሉም አቅጣጫ በስደት ለሚመጡ የጎረቤት ሐገራት ህዝቦች መጠጊያ የሆነችው የእኛ ሐገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህች ተስፋ እና ሥጋት የሚያንገላቷት ሐገራችን እንዲህ ከውስጥ በሚነሳ ቀውስ እየተናጠች ብዙ መዝለቅ አትችልም፡፡ ስለዚህ ከገጠመን ችግር ለመውጣት የምናደርገው ትግል በዚህ አውድ የሚከናወን መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ የሐገራችን የመከላከያ ሠራዊት እንደ ተቋም ያለውን መልካም ስም በሚጎዳ፣ የህዝቡንም አመኔታ በሚንድ፣ በዚህም ጥንካሬውን በሚሸረሽር አስተያየት ጉዳት እንዳናደርስበት መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ይህም ሁኔታ ቀደም ሲል ካነሳሁት አካባቢያዊና ሐገራዊ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡
ይህን አስተያየት ስሰጥ የወገኖቼ ሞት ሳያሳዝነኝ ቀርቶ አይደለም፡፡ ይልቅስ ሐገርን ከሞት ለመጠበቅ እንጂ፡፡ በመሆኑም፤ በኃይል አጠቃቀም ረገድ የተፈጠረ ችግር ካለ፣ በአግባቡ መታየት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ፖለቲከኞቹ ሥራቸውን በአግባቡ ባለመሥራታቸው በየጊዜው የሚቀሰቀስ የህዝብ አመጽና ሁከት ጋር የመጋፈጥ ዕዳ እየተሸከመ፣ በየአካባቢው የሚሰማራውንና በተልዕኮው ባህርይ ወይም ከሥልጠናው ይዘት ጋር በተገናኘ የፖሊስ ኃይል የሚያገኘውን አድማን ወይም አመጽን የመቆጣጠር ልዩ ሥልጠና ሳይኖረው ግዳጅ የሚሠጠውን የመከላከያ ሠራዊታችንን ‹‹አግአዚ›› የሚል የተዛባ አመለካከትን ሊፈጥር የሚችል ቅጽል እየተጠቀምን የጥንካሬው መሠረት የሆነውን የህዝብ አመኔታ አሳጥተን፣ ሐገርን የሚጎዳ ችግር እንዳንፈጥር ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ አሁን ወደ ሁለተኛው ነጥብ ልለፍ፡፡             
ሁለተኛው ነጥብ፤ ‹‹በዚህ ስርዓት የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ ሆኗል፤ የትግራይ ህዝብ የበላይነት ሰፍኗል›› የሚለው ሐሳብ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ ከሰሞኑ በተከሰቱ ግጭቶች መነሻነት ‹‹የትግራይ ተወላጆች ቤት እና ንብረት ተለይቶ መቃጠሉ ለምንድነው?›› በሚል ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ አንድ ሰው፤ ‹‹የትግራይ ተወላጆች በሚደርስብን በደል ከኛ ጎን ተሰልፈው አይቃወሙም፡፡ ህወሓትን ያመልካሉ›› የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡ ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ገዢውን ፓርቲ የማይቃወሙ ተደርገው ይታያሉ፡፡ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች ክልሎች ያልተናነሰ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች (በግለሰብ እና በፖለቲካ ድርጅት ደረጃ) ተቃውሞ የሚያነሱ አሉ፡፡
ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው፤ ገና ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ህወሐትን በመቃወም የተነሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡ በ1975 ዓ.ም አካባቢ ዶ/ር ኃይሌ በተባሉ ሰው ይመራ ከነበረው ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃነት›› ከተባለ የፖለቲካ ድርጅት ጀምሮ በትግራይ ተወላጆች የተመሰረተ የተቃውሞ ኃይል ነበር፡፡ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ከድርጅቱ የተሰናበቱና የተለያየ ቅሬታ የነበራቸው የትግራይ ተወላጆች፤ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝብ ትግራይ›› (TPDM ወይም ድምሒት) የሚል ድርጅት በማቋቋም የትጥቅ ትግል እንደሚያካሂዱ ይታወቃል፡፡ የህወሓት መሥራች የነበሩ እና ለረጅም ጊዜ በድርጅቱ ታቅፈው ሲታገሉ የቆዩ ሰዎችን በአባልነት የያዘ፤ እንዲሁም በአሜሪካ እና በአውሮፓ በስደት የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ያቋቋሙት ‹‹ዴሞክራሲያዊ ምትህብባር ትግራይ›› -Tigray Alliance For National Democracy - (TAND ወይም ዴ.ም.ት) በ1987 ዓ.ም ተቋቁሟል፡፡ ሁላችንም የምናውቀውና በሰላማዊ መንገድ ትግል እያደረገ ያለ ‹‹ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት›› የተሰኘ ድርጅትም አለ፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ‹‹የትግራይ ተወላጆች ገዢውን ፓርቲ አይቃወሙም›› በሚል ጥቃት መፈጸም ግን በፍጹም ተገቢ አይደለም፡፡ የአንድ ብሔር ወይም ድርጅት የበላይነት የሚንጸባረቅበት አስተዳደር አለ የሚለውን ጉዳይም ሳይንሳዊ ጎዳና መመርመር እንችላለን፡፡ ሳይንስ አንድን ጉዳይ ሲያጠና፤ የሚጠናውን ነገር ወደ መጨረሻው ዝቅተኛ ክፍልፋይ አውርዶ፣ የነገሩን መሠረታዊ ውቅር በመለየት ነው፡፡ ስለዚህ አንድን ነገር በሳይንሳዊ መንገድ ለመረዳት የሚሞክር ማናቸውም አጥኚ፤ የነገሩን ዝቅተኛ አዋቃሪ ክፍል ለማግኘት ይሞክራል፡፡ ትልቁን ነገር ሸንሽኖ መሠረታዊ አዋቃሪ ክፍሉን ይመረምራል፡፡ በተፈጥሮም ሆነ በማህበራዊ ሳይንስ የጥናት ዘርፎች እንዲሁ ይደረጋል፡፡
አሁን የምንነጋገረው ስለ ማህበረሰብ ነው፡፡ ሳይንሳዊ የጥናት ዘዴን በተከተለ አካሄድ ማህበረሰብን ስንመረምረው፤ የአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመጨረሻ አዋቃሪ ቅንጣት ሴት እና ወንዶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ በሌሉበት ማህበረሰብ አይኖርም፡፡ ስለ ማህበረሰብ መነጋገር አይቻልም፡፡ ከነዚህ ከሁለቱ (አንድ ሴት እና አንድ ወንድ) ማህበራዊ ትስስር ቤተሰብ ይገኛል፡፡ ቤተሰብ በመንደር ይኖራል፡፡ መንደር የዝቅተኛው ማህበረሰብ ጡብ ይሆናል፡፡ ብዙ መንደሮች ቀበሌ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ - እንዲህ እያልን ሐገረ - መንግስት ከሚባል ሁሉን አካታች ማህበረሰብ እንደርሳለን፡፡
ታዲያ በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ የአንድ ግለሰብ፣ ቤተሰብ ወይም ቡድን የበላይነት ሲንጸባረቅ፤ የማህበረሰቡ ህይወት የተባላሸ ይሆናል፡፡ አንድ የመንደር አለቃ፣ የቀበሌ ሹም ሆነ የሐገር አስተዳዳሪ ሥልጣኑ በህዝብ ፈቃድ ያልተባረከ ሲሆን ወይም የሁሉንም አባላቱን የጋራ ጥቅም በእኩልነት ለማስከበር በሚያስችል መርህ ተወስኖ ለማስተዳደር ካልቻለ፤ ችግር ይፈጠራል፡፡ በመሆኑም፤ የብዙሃኑን ፍላጎት በማክበር፤ የመላውን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብር ዓላማ ይዞ ያልተነሳ መንግስት ጸንቶ ሊቆም አይችልም፡፡ የአንድን ብሔር የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት አፍራሽ ነው፡፡ ግን እንዲህ ዓይነት ጥረት የሚደረገው የህዝብን  ሳይሆን የቡድኖችን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚኖር ፍላጎት ነው፡፡
አንድን ህዝብ ከሌላው ለይቶ ለመጥቀም የሚሞክር መንግስት፤ በተጨባጭ በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ከመጥቀም አልፎ፤ እወክለዋለሁ ብሎ የሚያስበውን ህዝብ ጥቅም ሊያስጠብቅ አይችልም፡፡ ሁለት ህዝቦችን እኩል ለማየት የማይችል አንድ የፖለተካ ኃይል ወይም የክልል መንግስት፤ በራሱ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ዞኖችን፣ ወረዳዎችን፤ ክፍለ ከተሞችን፣ መንደሮችን፣ ቡድኖችን፣ ቤተሰቦችን እና ግለሰቦችን እኩል ለማየት አይችልም፡፡ ይህ መንግስት በፍትሕ እና በእኩልነት መርህ ላይ የቆመ ባለመሆኑ፤ እወክለዋለሁ ወይም እጠቅመዋለሁ እያለ ስሙን የሚጠራውን ህዝብ መነገጃ ያደርገው ይሆናል እንጂ የማህበረሰቡ አባላትን ጥቅም ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ ዛሬ ባይሆን ነገ፤ እዚህ ባይሆን እዚያ፤ ውሎ አድሮ እወክለዋለሁ የሚለው ህዝብ ተጻራሪ ኃይል መሆኑ አይቀርም፡፡
በሌላ በኩል፤ ሁሉንም ማህበረሰብ በፍትሕ እና በእኩልነት መርህ ለመምራት የሚጣጣር መንግስት ከሆነ፤ ይህ መንግስት በቋንቋም ሆነ በባህል ለማይመስሉት፤ በአጭሩ ለሰው ልጆች ሁሉ ሊጠቅም የሚችል መንግስት ይሆናል፡፡ በመሆኑም፤ የራሱን ብሔር ወይም ቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚችል መንግስት፤ የሰው ልጆችን ሁሉ ጥቅም ለማስከበር በሚችል መርህ የሚመራ መንግስት ነው፡፡ ዣን ፖል ሳርትር፤ ‹‹አንድ ሰው ለራሱ ሲመርጥ፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ይመርጣል›› ይላል፡፡ እውነቱን ነው፡፡
የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት የማይከተልና በዴሞክራሲያዊ መርሆች የማይመራ መንግስት፤ ውሎ አድሮ በስሙ በሚነግድበት ህዝብ መካከል በሚኖሩ ልዩነቶች እየተሳበ፣ ሚዛን የሚስትና ከአንዱ ወይም ከሌላኛው ንዑስ ቡድን ጋር በመወገን፤ በመደብ፣ በቋንቋ፣ በብሔር ወይም በሌሎች ልዩነቶች ተጠልፎ፣ የአንድ ቡድን አገልጋይ መሆኑ አይቀርም፡፡ ራሱን ከዚህ አይነት መሰናክል ለማዳን የሚያስችል የስነ ልቦና ወይም የመርህ ገደብ ሊኖረው ስለማይችል ሁሌም ሲሳሳት ይገኛል፡፡
ስለዚህ አንድ መንግስት እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ጭምር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊያገለግል የሚችለው፤ ሁሉንም በእኩልነት ለማገልገል የሚያስችል ወይም የሰው ልጆችን በመላ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መርህ የሚከተል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በዚህ እይታ አንድን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚችል መንግስት፤ ሁሉንም የሰው ልጆች ሁሉ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚችል መንግስት ነው፡፡ አንድን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል መንግስት፤ በመርህ የሚመራ እንጂ በአድሎ የሚሰራ መንግስት አይደለም፡፡ ለአንድ ቡድን ጠቃሚ ሆኖ የተገኘ ቡድን፤ ሁሉንም የፖለቲካ ማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚ የሚያደርግ መንግስት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም፤ ሁሉንም የፖለቲካ ማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚ በሚያደርግ መርህ የሚመራ መንግስት፤ የአንድ የተወሰነ ህዝብ አገልጋይ ለመሆን አይችልም፡፡
ሆኖም ብዙነትን ለማክበር ታስቦ የተገነባው የፌደራል ስርዓት ወቅታዊ ተግዳሮት ‹‹የአንድ ብሔር የበላይነት አለ›› የሚል አስተያየት ነው፡፡ በዚህ መደናገር ውስጥ እርግጠኛ መሆን ይገባናል፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው፤ ‹‹የራሱን ብሔር ወይም ቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚችል መንግስት፤ የሰው ልጆችን ሁሉ ጥቅም ለማስከበር በሚችል መርህ የሚመራ መንግስት ነው፡፡›› ስለዚህ የአንድ ብሔር ወይም ቡድን ጥቅምን ለማስከበር የሚፈልግ ማናቸውም የፖለቲካዊ ኃይል፤ የሰው ልጆችን ሁሉ ጥቅም ለማስከበር በሚያስችል መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ መርህ ያፈነገጠ ኃይል፤ የተወሰኑ ሰዎችን ቡድናዊ ጥቅም ከማስከበር ተሻግሮ፤ ቆሜለታለሁ የሚለውን ህዝብ ጥቅም ሊያስከብር አይችልም፡፡ የህወሓትን የበላይነት በማረጋገጥ፣ የትግራይ ህዝብን ጥቅም ማስከበር አይቻልም፡፡ ስለሆነም ‹‹የህወሓት የበላይነት›› ቢኖር እንኳን፤ የተወሰኑ ሰዎች ጥቅም ሊከበር ካልሆነ፤ የትግራይ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም፡፡
ስለዚህ ‹‹የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ ነው›› የሚለው የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ በርግጥ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች፤ የመንግስት ሥልጣን ከያዙ ሌቦች ጋር በመተባበር ዘረፋ እንደሚያካሂዱ ሁሉ የህወሓትን ስም እየጠሩ ያልተገባ ጥቅም የሚያግበሰብሱ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ የሌቦችን ዘረፋ እንጂ  ‹‹የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ ነው›› የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ሆኖም በተፈጠረ የተዛባ አመለካከት ሳቢያ በተለያዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች በላብ እና በወዛቸው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለጭንቀትና ለሥጋት የተዳረጉበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አልፎ አልፎም አካላዊ ጥቃት፣ ሞትና የንብረት ውድመት ተከስቷል፡፡ ይህ የሐገሪቱን አንድነትና የህዝቦችን ተከባብሮ የመኖር ነባር ባህል የሚሸረሽር አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ በከተማ ውር ውር የሚሉ ሌቦች፣ በትስስር ለመጠቃቀም የሚሯሯጡና የመንግስትን ሐብት ለመዝረፍ የሚሞክሩ የተለያዩ ብሔር - ብሔረሰቦች አባላት አሉ፡፡ እነዚህ ሌቦች አማራውን፣ ኦሮሞውን፣ ጉራጌውን፣ ወላይታውን እንደማይወክሉ ሁሉ የትግራይ ህዝብንም አይወክሉም፡፡ በዚህ ረገድ ያለው የተዛባ አመለካከት በቶሎ መስተካከል ይገባዋል፡፡ በረጅም ዘመናት ሂደት የተገነባውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከጥቃት መጠበቅ ይገባናል፡፡ ሐገሬን እንደምወዳት የማውቀው ስትሳሳት ደፍሬ መናገር በመቻሌ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ በዴሞክራሲያዊት እና ፌደራላዊት ኢትዮጵያ አንዳች ትርፍ ያላገኘ፤ ለሃያ ዓመታት በቤት ኪራይ እየተንከራተተ በሚኖር፤ እንደ ጋሪዮሹ ስርዓት በፍሬ ለቀማ የሚተዳደር እና ‹‹ከሰንሰለቱ በቀር ሌላ የሚያጣው ሐብት በሌለው›› ሰው የተጻፈ ነው፡፡ ግን የሐገሩ ሰላም እና የህዝቡ አንድነት ያሳስበዋል፡፡ ይህም ሐገሩን እና ህዝቦችዋን ከልብ እንደሚወዳቸው ይመሰክራል፡፡        

Read 2605 times