Saturday, 27 January 2018 11:47

ዛሬም ብሔራዊ እርቅ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(5 votes)

አንድ ጊዜ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ደራሲያንን ሰብስበው ስለ አብዮቱ እንዲጽፉ ጠየቋቸው ይባላል፡፡ ድርሰት ዝም ብሎ የሚሠራ ሥራ አልነበረምና ሁሉም ግራ ተጋብተው፣ የሊቀ መንበሩን ዐይን ዐይን እያዩ፣ ዝም ብለው ይቀመጣሉ፡፡ በመሃል ዝምታው ያስጨነቃቸው አቶ መንግሥቱ ለማ  ተነስተው፤ ‹‹ጓድ ሊቀ መንበር፤ ምን ብለን ነው የምንጽፍው?››  ብለው ይጠይቃሉ፡፡
‹‹አብዮቱ ወደ ፊት እየተራመደ ነው፤ ስለ አብዮቱ ትግልና ድል ለምን አትጽፉም?›› አሉ ሊቀመንበሩ፡፡
‹‹ጓድ ሊቀ መንበር፤ እሱንማ   ራዲዮውና ጋዜጣው በየዕለቱ ዜና አድርጎ ያቀርበዋል›› ይላሉ - አቶ መንግሥቱ፡፡
‹‹አክብረን ጠራናችሁ እንጂ ቂጣችሁን በሳንጃ እየወጋን ልናሠራችሁ  እንችላለን›› አሉ ሊቀ መንበሩ በቁጣ፡፡
‹‹አሁን እንጽፋለን›› ብለው አቶ መንግሥቱ ከተቀመጡበት ተነስተው ወጡ ይባላል፡፡
ኢሕዴግ ግንቦት 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያን መንግሥት ሥልጣን የያዘው በሕዝብ ምርጫ ሳይሆን በጦርነት አሸንፎ ነው፡፡ የመሠረተውም የአሸናፊነቱን ወታደራዊ መንግሥት ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ  የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥና የወታደራዊው መንግሥት መሪ  ነበሩ፡፡ 75 ከመቶ የሚሆነው የኢሕአዴግ ጦር የሕወሓት ስለነበረም  ፍጹም የበላይነትም  ነበራቸው፡፡
ሰኔ 1983 የተመሠረተው የሽግግር መንግሥት፣ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችን ቢያሳትፍም፣ እንደ ባህል ሚኒስቴር ያሉትን ቦታዎች ለሌሎች ቢሰጥም፣ በተጠና መንገድ የኢሕአዴግን ፈላጭ ቆራጭነት ያስጠበቀ ወታደራዊ አገዛዙን ያስቀጠለ ነበር፡፡ ሕወሓት በነበረው ፍጹም የበላይነት፣ ኢሕዴግን እያፈረሰ ይሠራው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አመራሩም የሚክድ አይመስለኝም፡፡
    የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባርን (ኦነግ) ለማዳከም፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እንደተቋቋመ ሁሉ፣ በአጭር ጊዜ እየጠነከረና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የመጣውን የመላ ዐማራ ሕዝብ ድርጅትን (መዐሕድ)  ለመፈታተን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዲን) ባንድ ሌሊት፣ የአማራ ሕዝብ ተጠሪ ተደርጎ አደረ፡፡ ይህ የሆነው መዕሕድ፤ “አማራው በሽግግሩ መንግሥት አልተወከለም ብሎ ባደባባይ መግለጫ በሰጠ ማግስት እንደነበር መታወቅ አለበት፡፡
    አሁን አሁን እየወጣ ያለው ታሪክ ለእኔ አዲስ ቢሆንም እስከማውቀው ድረስ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ደኢሕዴግ) የተመሠረተው በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው ደቡብ ኅብረት ከተመሠረተ በኋላ ነው፡፡ እድለኛው ደኢሕዴግ፣ እንደ ጉም ተኖ በጠፋው የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ መኮንኖች ንቅናቄ (ኢደመን) ምትክ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት የሆነውም ደቡብ ኅብረትን ከጨዋታው ለማስወጣት በማሰብ እንጂ የግንባሩ አባል ለመሆን የሚያስችል ድርጅታዊ ጥንካሬ ኖሮት አልነበረም፡፡ እነዚህ ድርጊቶች የሚያረጋግጡት እውነት ደግሞ፣   ሕወሓት በዓምሳሉ ከቀረጻቸው ድርጅቶች ውጭ ከማንም  የፖለቲካ ተቋም ጋር ለመሥራት ፈጽሞ ዝግጁ አለመሆኑን ነው፡፡ ይህን ያደረገውም  የበላይነቱን ለማስጠበቅ እንደሆነም  ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ከታች ወደ ላይ ያልመጡት ሶስቱ ድርጅቶች ማለትም፡- ኦሕዴድ፣ ደኢሕዴግ እና ብአዴን ወደ ታች ወርደው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ሕዝባዊ መሠረት ለመጣል በሚፍጨረጨሩበት ጊዜ (ብአዴን ተዋግቶ መምጣቱን መጥቀሱ ባይቀርም፣ እሱን አታብዛው እላለሁ) ሕወሓት በፓርቲ ሥርዓቱ፣ በሕዝብ መሠረቱና በሠራዊት የበላይነቱ ታግዞ ኃያልነቱን እንዳስጠበቀ ቀጠለ፡፡ በቤተ መንግሥቱ አካባቢ መሰማት የማይፈለገው፣ በየጊዜው እየተነሳ ወቅታዊ ሽብር ፈጥሮ ተመልሶ የሚቀዘቅዘው ‹‹የሕወሓት የበላይነት››፤ በሕዝብ እምነት ውስጥ የተተከለው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በሠራዊቱ  ክፍሎች ዘንድ የኃይል መመጣጠን ተደርጓል እየተባለ ቢነገርም፣ ይህን እምነት የሚፋቅ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ይህ የበላይነት ወደ ሕዝቡ ተዛምቶ፣ ንጹሑ የትግራይ ሕዝብ እየተከሰሰበት መሆኑም ድብቅ አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥርዓቱ ተጎጂ ቢሆንም ይህን መቀበል የሚከበዳቸው አያሌ ናቸው፡፡
በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ በወልዲያ የተቀሰቀሰው ግጭት መንስኤ፣ የድርጅት  የበላይነት የፈጠረው “ንቀትና ዘለፋ ደርሶብናል” በማለት መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ ጥር 12 ቀን 2010 የተነሳውና ለሁለት ቀን የቀጠለውን ግጭት፣ የመጀመሪያው ቀጣይ አድርገው የሚያዩትም ወገኖች አሉ፡፡
የከተራንና የጥምቀትን በዓል ወልዲያ ያሳለፈችው በሰላም ነው፡፡ ባካባቢው የሚገኙ ወደ አስር የሚጠጉ ታቦታት በተለመደው መንገድ ወጥተው፣ በመዝሙርና በጭፈራ ተወድሰውና ተከብረው ወደ መቅደሳቸው ተመልሰዋል፡፡ በድንኳኑ ያደረው ጎንደር በር የሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ እሱም ቢሆን በሰላም መግባት ይችል ነበር፡፡ ሁኔታውን የለወጠው ቅዳሜ ጠዋት፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ በስድስት ፒካፕ፣ በአራት ኦራል መኪና መግባቱ ነው፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ የወጣቶች ስሜት እየደፈረሰ መምጣቱ ተነግሮኛል፡፡ ሐሙስና አርብን  ዘፈንና ጭፈራቸው ምንም ዓይነት የፖለቲካ ይዘት ያልነበረው የወልዲያ ወጣቶች፤ ቅዳሜ ዕለት፤
‹‹ምን አለ ጀግናው ምን አለ፣
 አገሬን ለሰው አልሰጥም አለ፡፡
 ይለያል ዘንድሮ
የወያኔ ኑሮ፤›› የሚሉና መሰል ይዘት ያላቸው የማስጨፈሪያ ግጥሞች ማሰማታቸው ታውቋል፡፡ “ሃይማኖታዊውን በዐል ለፖለቲካ ተቃውሞ መጠቀም አልነበረባቸው” ተብሎ ቢታሰብ እንኳ “መንግሥትን በግልጽ መቃወም፣ በሕዝብ ላይ ተኩስ ለመክፈት ምክንያት ይሆናል ወይ?” ብሎ መጠየቅ የግድ ነው፡፡
ገብረመስቀል ጌታቸው የተባለው ግለሰብ በተገደለ ጊዜ አብሮት እንደነበረና እሱም ለትንሽ እንደተረፈ የነገረኝ የመረጃ ምንጬ፤ ታቦቱ ሊገባ እየተቃረበ ባለበት ሰዓት፣ አስለቃሽ ጢስ ባይተኮስ ኖሮ ሁኔታው እንዲያ በቅጽበት ላይለወጥ ይችል እንደነበር ገልጦልኛል፡፡ በዚህ መጥፎ ሰዓት ላይ የተከፈተው ተኩስ ብዙዎች እንዲጎዱ አድርጓል፡፡ የቆሰለው ባይታወቅም  የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ሰባት ሰው መሞቱን ገልጠዋል፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ አስር ይደርሳል፡፡ አንድ ሬሳ  ጎድጓዳ ቦታ ወድቆ መገኘቱም ተነግሮኛል፤  ከሟቾች ውስጥ የዘጠኝ አመት ልጅና አንድ የመከላከያ ሠራዊት አባል ይገኙበታል፡፡
በአምስት ጥይት ገብረ መስቀልን ደብድበው የገደሉ ሰዎችና የመከላከያ ሠራዊት አባሉን ሬሳ ለማቃጠል የተነሱ ወገኖችን አምርሬ አወግዛለሁ፡፡ የማያወቀውን ሰው አስከሬን፣ መንገድ ሽኝቶ ከሚመለስ ማኅበረሰብ ውስጥ የተገኙ ናቸው ለማለትም  ይከብዳል፡፡
የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማው መግባት እንደሆነ ቀደም ሲል ተገልጧል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ወልዲያ ከተማ ለሰበሰቧቸው ወጣቶች፤ መከላከያ እንደገባ አለማወቃቸውን ገልጠዋል፡፡  መከላከያ ከክልል መንግሥታት ዕውቅና ወጪ እየገባ ችግር ሲፈጠር፣ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ነገም ሊቀጥል ይችላል፡፡
‹‹የመከላከያ  ኃይሉን ለግዳጅ ያሰማራሁት እኔ ነኝ፤ በተፈጠረው ችግር አዝናለሁ ››  በማለት ኃላፊነት የሚወስድ አካል እስከ አሁን ብቅ አላለም፡፡ ኤታ ማዦሩም ሆኑ የመከላከያ ሚኒስትሩ አንድም ነገር አልተናገሩም፡፡ መከላከያውን የሚያዝዘው ማን ነው? በየክልሉ የመከለከያ ሠራዊት ሰፍሮ ይገኛል፡፡ “ባቅራቢያው ያለ ሹም ድረስልን” ስላለ መከላከያ እየተወረወረ እየገባ፣ ከሕዝብ ጋር መጋጨት አለበት? የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 51.14 አክባሪና አስከባሪው ማን ነው? ይህን አጥብቄ እጠይቃለሁ፡፡
በወጣቶች መገደል የተበሳጩ ወገኖች፣ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ናቸው ያሏቸውን የትግራይና የአማራ ተወላጆች ንብረትና ድርጅቶች አውድመዋል፡፡ ከተቃጠሉት ቤቶች ውስጥ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት የከተማው ከንቲባ ቤት እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡
መንግሥት እስከ አሁን ከተፈፀመው ምን መማር አለበት?  ሕወሓትስ?
ሕወሓት የፕሮፓጋንዳ ጨዋታውን አቁሞ፣ እስከ አሁን የሔደበትን መንገድ እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ በማልከላዊ መንግሥት ያለውን ድርሻ በሚፈልገው ሳይሆን ከሚገባው ቁመና ጋር ማመጣጠን አለበት፡፡ ‹‹እኔ ከሌለሁ አገር አትኖርም›› የሚለውን እምነቱን ወደ ጎን ገፍቶ፣ ሌሎችም እንደ እሱ እንደሚያስቡ መቀበል ይኖርበታል፡፡
ያለነው ዘረኝነት በተሰበከበት አገር ነው፡፡ እሱ ዋና አቀንቃኝ ሆኖ የሰበከው ዘረኝነት፤ እሱኑ ከመለብለብ አልፎም ለደኃው የትግራይ ሕዝብም እንደተረፈው ሊረዳ ይገባል፡፡
አንድ ግለሰብ ያፈራው ሀብት ለአገር እድገት የሚውለው፣ መንግሥት የሚዘረጋው መሠረተ ልማት ለነገ የሚተርፈው፣የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብት የሥራ እድል መፍጠር የሚችለው አገር ሰላም ስትሆን ነው፡፡ አገርን ሰላም ለማድረግ ደግሞ በአጭር ጊዜ ብሔራዊ እርቅ ማውረድ ያስፈልጋል፡፡
ኢሕአዴግ የተጠናወተውን ማንአለብኝነት ሰብሮ፣ ለእውነተኛ እርቅና ድርድር እራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ ዋናና ወቅታዊው መፍትሔውም ይሄ ብቻ ነው፡፡

Read 2165 times